ግንቦት 16፣ 2012 የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ‘በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የአስቸኳይ አዋጁን በሚያስፈጽመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ‘ በሚል ባወጣው አስደማሚ ጽሁፍ የሚከተለውን አስነብቦናል:: “ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን እንዲከታተል ያቋቋመው መርማሪ ቦርድ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ የሆነውን የሚኒስትሮች ኮሚቴ የአንድ ወር የሥራ አፈጻጸም ገምግሞ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራት ከሞላ ጎደል አወድሶ ነበር። ቦርዱ ባካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ሊታረሙ ይገባቸዋል ተብለው ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚያወጣቸው መግለጫዎችና ምክረ ሃሳቦች ሰፊ ትኩረት የተሰጣቸው ነበሩ። ”
ላለፉት 29 አመታት ከኢህአዴግ ስብሰባ የተማርነው ነገር ቢኖር፣ ግምገማ በሚል ሲቀመጡ እራሳቸውንና ተግባራዊ አደረግነው የሚሉትን ጉዳይ አወድሰው ፣ ጥፋት አለ ብለው ነቅሰው ካወጡ ደግሞ፣ ሃላፊነቱን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠትን ነው:: በዚህም ስብሰባ የሆነው ከዚህ የተለየ አልነበረም::
እርግጥ ነው የህወሃትን የበላይነት ከርክሞ የበላይነትን ተቆጣጥሮ የነበረው ኦህዴድ (አሁን እንኳን የአብይ መንግስት ማለት ሳይቀል አይቀርም) ሰብዓዊ መብትንና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ፣ የተለየ መንገድ እንደሚከተልና ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሻጋግራችዋለሁ በሚል ቃል ገብቶ፣ቁርጠኝነቱንም ለማሳየት በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል:: ከነዚህ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱና ምስጉን የሆነበትም፣ ለአመታት በግፍ አስሮ የፈታውንና ፣ከሀገሩ ተሰዶ በውጭ ሃገር በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ትልቅ ሃላፊነት ይዞ ይሰራ የነበረውን ዶክተር ዳንኤልን ወደ ሃገሩ ተመልሶ ፣ ‘ያለምንም የመንግስት ጣልቃ ገብነት’ ብሎ ቃል በመግባት ፣የ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ መቻሉ ነበር::
እርግጥ በመጀመሪያው ሰሞን ቃል የተገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ፣ በሂደት ቃል በተገባው መሰረት መሄድ ሲገባቸው ዳተኝነት መታየቱ፣ አንዳንዴም መታጠፋቸው ወይንም በቀድሞው አስከፊ መንገድ ሲካሄዱ ማየቱ፣ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍል አባላት ላይ ጥያቄዎች አጭሮ፣ ነገሮች ተለወጡ በተባለ ቁጥር እንደቀድሞው ያው መሆናቸው አይቀርም እንደሚለው ብሂል አየሆነ ነው በሚል ተስፋቸውን አጨልሞባቸዋል::
ሆኖም ሀገራችን ለዓመታት ገብታበት ከነበረው አስቸጋሪ አጣብቂኝ ትንሽ ፋታ ማግኘቷና የተስፋ ጭላንጭሉ አሁንም መኖሩ፣ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል አባላት የተገባው ቃል፣ የህበረተሰቡ ንቁ ተሳትፎና ግፊት ከተጨመረበት፣ ቃሉ፣ በከፊልም ቢሆን መሬት ላይ እንዲያርፍ የማድረግ ዕድል አለ፣ይሄም ዴሞክራሲን ለማስፈን ለሚያስፈልገው ረጅም ጉዞ እገዛ ያደርጋል ብሎ የሚያምን ይመስለኛል::
ለዚህም ነው እንዲህ ያለ ያልተገባ ንጭንጭና ማስፈራሪያ የመሰለ ነገር በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተድርገዋል የሚለውን ጽሁፍ ሳነብ፣ አሁን በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር ከሙገሳ በቀር ለዘብተኛም ቢሆን ፣ለወቀሳና ስህተቱን እንዲያርም ሲመከር በቅንነት የመቀበል ትከሻ አለው ወይንስ የለውም የሚል ጥያቄ እንድጠይቅ እገደዳለሁ::
በዚህ ለራስ ውዳሴ ተጠርቶ በነበረ ስብሰባ በ ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ቆስቋሽነት ፣ ከምክትል ጠቅላይ ምኒስትሩ ደመቀ እስከ ሰላም ምኒስትሯ ሙፈሪያትና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጓ ወ/ሮ አዳነች፣ ዶክተር ዳንኤል የሚመራው ተቋም ያቀረባቸውን አስተያየቶችና ምክረ ሃሳቦች አስመልክቶ ተገቢ ያልሆኑ ወቀሳዎችና ማስፈራሪያ የመሰሉ ሃሳቦች እንደተሰነዘሩ ሪፖርተር ዘግቧል::
የሚገርመው ይሄው አቶ ተስፋዬ ዳባ ከአንድ ወር በፊት አንዲት ሩት የተባለች ወጣት በመሃል አዲስ አበባ ከትንንሽ እህቶቿ ጋር የፋሲካ ዕለት በመንገድ ሲሄዱ ‘ተራርቃችሁ አትሄዱም’! በሚል ከመኪና ዘለው ወርደው ያለ ርህራሄ በቆመጥ ደብደበዋቸው የሄዱ ወታደሮች ያደረሱባትን ግፍ፣ ሃላፊነት እንዳለበት በመገንዘብ ደውላ አቤት ብላ ብትነግረው ‘የማውቅልሽ የለም’ ብሎ ጆሮዋ ላይ ስልክ የዘጋ፣ ትንሽም ሃላፊነት የማይሰማው፣ ለስፍራው የማይመጥን ሹም መሆኑ ነው::
እነ ደመቀም ቢሆን ወደ ትናንትና ጠባያቸው ተመልሰው፣ ለጆሮአቸው የማይጥም አስተያየትም ሆነ ምክረ ሃሳብ የሚያቀርቡ ሰዎችንና ተቋሞችን ለማስፈራራት መሞከር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ተገንዝበው ወደ ቀልባቸው ቢመለሱ ለአስተዳደራቸውም ሆነ ለሀገር ይበጃል :: የሹም ዶሮ ነን አትንኩን የሚለው ፈሊጥ ጊዜው ካለፈበት ትንሽ ቆየ!!
ደግነቱ፣ ዶክተር ዳንኤል ስራውን ጠንቅቆ በማወቁና ያለምንም ጣልቃ ገብነት ለመስራት በተስማማው መሰረት ፣ በድርጊቱ ምንም ሳይሸበር የሚመራው ተቋም መንግሥትንና ሹማምንቶቹን አስመልክቶ ያቀረቡት ወቀሳ ስህተት እንደሆነና ፣ በቀጣይም “መስማት የሚፈልጉትን ሳይሆን መስማት የሚገባቸውን እናስረዳቸዋለን” በሚል የሰጠው መግለጫ የሚበረታታና ድጋፍም የሚያስፈለገው ነው:: ሁሉም ተቋሞችና አመራሮቻቸውም ከ ዶክተር ዳንኤልና ከሚመራው ተቋም በመማር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መንግስትናና ባለሥልጣናቱን ተጠያቂ በማድረግና በመሞገት ለሕዝብ የሰጡትን ቃል ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ መታገል ይጠበቅባቸዋል ::