የሕገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ አስተያዬት – ኢሳያስ ሃይለማሪያም

ጭብጦች 

(1) በኢትዮጵያ፣ “የቅድመ ምርጫ ዝግቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈፃሚው አካል የስራ ዘመን ምን ይሆናል?”

(2) “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በሗላ [ምርጫውስ] በምን ያክል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?”

. •— መግቢያ —•

የህግ ትርጉም አስፈላጊ የሚሆነው አወዛጋቢ ክርክሮች (cases and controversies) ሲኖሩ፣ ወይም አንድን ነገር ማድረግ (action) ወይም አለማድረግ (omission) ከህጎች ተቃርኗል ተብሎ ሲገመት ነው። ግልፅ የሆኑ የሕገ-መንግስት አንቀፆች ያለተጨማሪ ማብራሪያና ትርጉም በቀጥታ የሚፈፀሙ ድንጋጌዎች (self-executing provisions) በመሆናቸው በአብዛኛው ትርጉም አያስፈልጋቸውም። ለትርጉም ተጋላጭ የህግ ድንጋጌዎች ቅድመ ሁኔታን የሚያስቀምጡ: “በግልፅ ካልተደነገገ በስተቀር” (unless provided by law)፣ ወይም “ዝርዝር ጉዳዮ በሌላ ህግ ይወሰናል” (particulars shall be determined by law) የመሳሰሉ ዐረፍተ-ነገሮችን ያዘለ ሊሆን ይችላል³። ሕግን የመተርጎም ዋናው አላማ የህጉን መንፈስ ለመረዳትና ለማብራራት እንጂ ክፍተት ተጠቅሞ አዲስ ህግ ለመፍጠር መሆን የለበትም።

የፌደሬሽን ምክር ቤት የተረጎማቸው አብዛኞቹ የህገ-መንግስት ጉዳዮች ከመደበኛ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት የተመሩ ሲሆን፣ አሁን አስፈፃሚው ያቀረበው ህገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ግን ከዚህ በፊት ፍርድ ቤት አይቶት ስለማያውቅ ጉዳዩ የሚታየው በተሻሻለው አዋጅ 789/2005 መሰረት አንቀፅ 5 “ከፍርድ ቤት ውጭ ስለሚቀርብ የትርጉም ጥያቄ” ስር ስለሆነ፣ በሌላ መልኩ፣ የቀረበውን የሕገ-መንግስት ጥያቄ በተመለከተ መሰረት የጣሉ ተመሳሳይ የፍርድ ቤትም ይሁን የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎች (precedents) ካለመኖር አኳያ፣ በአለም ተቀባይነት ያላቸውን የህገ-መንግስት አተረጓጎም መርሆዎች (principles of interpretation)፣ እና ያንዳንድ ሃገራት የፍርድ ውሳኔዎችን ከኢትዮጵያ ስርዐተ-ህግ፣ የመንግስት አወቃቀር፣ ፖሊቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብር አኳያ መቃኘት ተገቢ ነው።

ከላይ የተገለፀውን ሃሳብ ለማጠናክር የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ 789/2005 እንደሚጠቁመው: “ምክር ቤቱ የሚቀርቡለትን ሕገ-መንግስ ጉዳዮች መርምሮ ለመወሰን ጠቃሚ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸውን የህገመንግስት አተረጓጐም መርሆዎች መለየትና በስራ ላይ” በማዋል፣…ለምክር ቤቱ የቀረበው ጥያቄ በሕገ-መንግስቱ የሰፈሩትን መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች የሚመለከት ሲሆን ትርጉሙ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን አለማቀፍ ሰብአዊ ህግጋት ከአለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግ ጋት፣ አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና የአለማቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ” እንደሚተረጎም አቅጣጫ ይሰጣል።

(1) በኢትዮጵያ፣ “የቅድመ ምርጫ ዝግቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈፃሚው አካል የስራ ዘመን ምን ይሆናል?”

አስፈፃሚው ካነሳው የሕ-ገመንግስት ትርጉም ጥያቄ በተገናኘ ሊነሱ የሚችሉ አንዳንድ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ-ገመንግስት ድንጋጌዎች ከተለያዩ የአተረጓጐም ስልቶች አኳያ:

(ሀ) ቀጥተኛ ወይም ሌጣ ትርጉም/Textualism/: መጀመሪያ ህጉን ያወጡት ሰዎች ቃል በቃል፣ በቀጥታ “ምን ቃል ነበር የተጠቀሙት?” ብሎ በመጠየቅ የህጉን ሌጣ ትርጉም (plain meaning) መመልከትና በቀጥታ ጥቅም ላይ ማዋል (direct application) ነው።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 58 (1): “የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ [በመሆኑ]..”

ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ/መ አንቀጽ 60 (1): “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት… ምክር ቤ[ቱን መበተን ስላለበት…]፣

ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ/መ አንቀጽ 60 (3): ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት ምክር ቤቱን ከበተነ “ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ” ስለሚጠበቅበት” (የበተነው አዲስ ምርጫ ለማድረግ ከሆነ)፣ በሌላ መልኩ፣ ከላይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ/መ አንቀጽ 58 (1) የምክር ቤቱ አምስት አመት የሥራ ዘመን በግልፅ ስለተወሰነና በአንቀጽ 58 (3) የፓርላማው አምስት አመት እድሜ ሰኞ፣ ሰኔ ሰላሳ መሆኑ በግልፅ በመገደቡና ከዛ በላይ ሊራዘም ስለሚችልበት ድንጋጌ በየትኛውም የህገመንግስቱ ክፍል ስላልተገለፀ፣

ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ/መ አንቀጽ 54 (1): “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤… በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ” ስለሚመረጡ፤ በሌላ መልኩ፣ በ አንቀጽ 60 (3): ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት ምክር ቤቱን በአንቀጽ 58 (1) እንደተገለፀው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ከመድረሱ በፊት መበተን ስላለበት፣

በአንቀጽ 58 (3) መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት [ስለሆነና]፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ [ተካሂዶ ስለሚጠናቅርቅ]፤ በመጨረሻም፣

በ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ/መ አንቀጽ 106 መሰረት የ ሕገ-መንግሥቱ “የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻው ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ” ስለሆነ በአማርኛ ቛንቛ ደግሞ፣ “ሰኞ፣ ሰኔ ሰላሳ” በ ሰኔ 29 እና ሃምሌ 1 መካከል የሚገኝ ቀን ከመሆን ውጭ ሌላ ተለዋጭ ትርጉም ስለሌለው፣ በቀጥተኛ አተረጓጎም (textually)፣ ሰኞ፣ ሰኔ ሰላሳ የምክር ቤቱና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዘመን ያበቃል ማለት ነው።

(ለ) የህጉ የመጀመሪያው ቅጂ ትርጉም/Original Meaning/: አንዳንድ የህገ-መንግስት ሊቃውንት የመጀመሪያ ቅጂ/የኦሪጂናላዊ (originalist/nontexological) ያተረጓጐም መርህን ከቀጥተኛ አተረጓጐም መንገድ (textualism) ጋር ሲያቀላቅሉት ቢታይም ነገር ግን የተለያዩ ናቸው። ኦሪጂናላዊ ትርጓሜ ህጉን ቃል በቃል በመተርጎም ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ህጉ በፀደቀ ዚጌ የነበሩት ሰዎች ሊረዱት ከሚችለው እይታ (perspective) እና አገባብ (context) በመነሳት የህጉን መንፈስ ለመረዳት መሞከር ነው።

የዛሬ 25 አመት የተፃፈው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገመንግስት ረቂቅ (draft)105 አንቀፆች ነበሩት:: አሁን በስራ ላይ ያለው፣ የፀደቀው ደግሞ 106 አንቀፆች አሉት:: ከአስፈፃሚና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን ጋር በተያያዘ በሁለቱ ሰነዶች መካከል መሰረታዊ የፍሬ ነገር (substantive) ልዩነት የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለሳኡዲው ባለሃብት ሼክ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ “ዝምታን” ለምን መረጡ?

ለምሳሌ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን ጋር በተያያዘ የሁለቱን ቅጂዎች አንቀፆች እናነፃፅር።
● በስራ ላይ ያለው የ ኢ.ፌዴ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 58 (3): “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል” ሲል፣

● ረቂቁ የ ኢ.ፌዴ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 58 (3) ደግሞ : “…የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ መደረግ አለበት::” ይላል።

የመጀመሪያው ጠበቅ ያለ (conservative) ቢመስልም፣ የሁለቱም ሰነዶች መንፈስ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመኑ ከማለቁ አንድ ወር ቀደም ብሎ ብሄራዊ ምርጫ በማካሄድ ቀጣዩን ምክር ቤት መተካት እንዳለበት አፅንኦት ለመስጠት ነው።
● የ ኢ.ፌዴ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 72 (3) ክፍተት ይኖረው ይሆን?
ህግ አውጪው በወቅቱ ያልታዘባቸው ወይም ያልገመታቸው ሁኔታዎች ዛሬ ላይ ጥያቄ ሲያስነሱ፣ ተቀባይነት ያላቸውን መርሆዎች በመከተል ሕጉን መተርጎም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

አንቀጽ 72 (3): “በዚህ ሕገ-መንግሥት መሰረት በሌላ አኳሗን ካልተወሰነ በስተቀር የጠቅላይሚኒስትሩ የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ነው” የሚለውን ገልብጠን ስናነበው፣ በሌላ አኳሓን ከተገለፀ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዘመን ምክር ቤቱ ከተበተነም በሗላ ሊቀጥል ይችል ይሆናል ለማለት ይሆን? የአርቃቂዎቹ ሃሳብ (legislators’ intent) ጥያቄ ውስጥ የሚገባው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው::

ህጉን ባረቀቁት ሰዎች ሃሳብ (intent)፣ “የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስልጣን ዘመን ከምክር ቤቱ የስልጣን ዘመን ትንሽ ረዘም ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመክፈት አስበው ወይም ሕገ-መንግስታዊ ቅርቃር (gridlock) ሲከሰት የአስፈፃሚው የስራ ዘመን እንደ አስፈላጊነቱ ከመደበኛው የስራ ዘመን ትንሽ ረዘም እንዲል አስበው ይሆን?” ብለን ለመጠየቅ፣ በመጀመሪያ፣ በሌላ አኳሗን የ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ስለሚራዘምበት አጋጣሚ የሚገልፅ (በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ) ድንጋጌ መኖር አለበት።

ለምሳሌ፣ በማይናማር (Maynamar) ሕገ- መንግስት፣ የኢትዮጵያ አይነት ሁኔታ ሲከሰት፣ መንግስት ከተፈቀደለት የስራ ዘመን ለተጨማሪ ጊዜ መቆየት እንደሚችል ይገልፃል። ድንጋጌው ስላለ፣ ክርክር ቢነሳ ተርጓሚው አካል ጉዳዩን ሊመለከተው ይችላል።

በኢትዮጵያ ህግ ግን ከዚህ ጋር የሚቀራረብ ድንጋጌ የለም፣ የሕጉ አርቃቂዎች ሃሳብም ይህን በሚመለከት የሚጠቁመው ፍንጭ ወይም ለትርጉም ተጋላጭ ድንጋጌ የለም። ባጭሩ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተጠቅሞ ህዝባዊ ምርጫን ማራዘም ስለሚቻልበት ሁኔታና አጋጣሚ የሚገልፅ የህገ-መንግስቱ ድንጋጌ የሕጉ አርቃቂዎች ሃሳብም የለም።

● አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የምርጫ ሰሌዳ:
“የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ…” እንደሚያውጅ ተመልክቷል። በዚህ አዋጅ፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል፣ ዴሞክራሲያዊ መቶችም ሳይቀሩ ሊገደቡ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ይገልፃል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ገደብ መጣል ማለት ግን፣ በህገመንግስቱ የተወሰነውን የምርጫ ቀን እስከማስቀየር ይደርሳል ማለት አይደለም። የኢ.ፌዴ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 93 ከ 72 እና 58 በጣምራ ሲነበቡ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሂደት ላይ እያለ የስራ ዘመኑ የሚያልቅበት አስፈፃሚ፣ በቀጣይ ሊተካው ለሚችለዉ አዲስ አስፈፃሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስተላልፎ ከማለፍ ውጭ፣ በሕገ-መንግስቱ ከተፈቀደለት የስራ ዘመኑ ተሻግሮ በሃገሪቱ መፃኤ የፖለቲካና ማህበራዊ ሁኔታዎች ዛሬ ላይ ከስራ ዘመኑ ባሻጋር መወሰን የሕገ-መንግስቱን የበላይነት የሚፃረር ብቻ ሳይሆን፣ የመንግስት የስልጣን ክፍፍል መርሆን (principle of separation of power) በመቃረን ሌሎቹን የመንግስት አካላት የሚገዳደር ይሆናል:: የአስፈፃሚ የማስፈፀም ስልጣን ከስልጣን ዘመን ማብቃት ጋር አብሮ ያከትማል (የ ኢ.ፌዴ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 72 [3])

(ሐ) መሠረት የጣሉ የፍርድ ውሳኔዎች (Stare Decisis or Judicial Precedents): የኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት በይበልጥ በተፃፉ ህጎች (codified laws) መሰረት በመሆኑና፣ ይህን አወዛጋቢ የህግ ክርክር በሚመለከት ከዚህ በፊት ለትርጉም ቀርቦ የሚያውቅ ጉዳይ ወይም ተቀራራቢ ውሳኔ ባለመኖሩ፣ በሌላ መልኩ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከዚህ በፊት ትርጉም የሰጠባቸው ክርክሮችም ቢሆኑ ለጉዳዩ በቀጥታ መልስ የሚሰጡ ስላልሆኑ፣ የዚህ አይነት የአተረጓጎም ዘዬ ለጊዜው ብዙም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል።

(መ) አወንታዊ ምልከታ /Pragmatism/: የዚህ አተረጓጎም ዋና ትኩረት፣ የሚተረጎመዉ ጉዳይ (ቢተረጎም) የሀገሪቱ ቋሚ ህግ ስለሚሆን፣ ውሳኔው ከሌሎች ህጎች ጋር የሚኖረውን ተቃርኖ በማጤን፣ የህዝብ አቋም መመሪያ (public policy) አንፃር በሀገሪቱ፣ በህዝቧና የፖሊቲካ ስርአቱ ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ጫናን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ህገ-መንግስት ከህግነቱ በተጨማሪ የፖለቲካ ሰነድም ስለሆነ፣ “ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ” ከሚል እሳቤ በመነሳት ህጉን ከነባራዊ ሁኔታ በማጣጣም ለመተርጎም መሞከር ነው። ችግሩ፣ አስፈፃሚው ይሄን ያተረጓጎም ዘዬ በመጠቀም በ “ፐብሊክ ፖሊሲ እና የህዝብ ጥቅም” ሰበብ አይነኬ (nonderogatory) የህገመንግስት ድንጋጌዎችን ሳይቀር ለመሸራረፍና የግል የፖለቲካ አጀንዳዎችን ለመሰንቀር እድል መክፈቱ ነው።

አሁን ካለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ አስፈፃሚው “ለህዝብ ጤና” በሚል የምርጫ ሰሌዳን የመቀየር እርምጃው፣ ያንን ተከትሎ ያቀረበው “የሕገ-መንግስት ይተርጎምልኝ” ጥያቄ ወደዚህ ያተረጓጎም ስልት ያደላ የትርጉም ፍላጎት እንዳለው ይጠቁማል። የ አስፈፃሚው አካል የምርጫ ማራዘም ውሳኔና ያንን ተከትሎ የሚፈጠረው የስልጣን ክፍተት (power vacuum) ለበጎ ነው ብለው ውሳኔውን የሚደግፉት እንዳሉ ሁሉ፣ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ሃገራዊ ውዝግብ በማስከተሉ፣ ብሎም በቀጣይ የምርጫ ሂደት ተአማኒነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳድር፣ የ አገር አለመረጋጋትና የዴሞክራሲ ተቋማት መናጋትን ግምት ውስጥ ያስገባ ገንቢ የትርጉም አቀራረብ መከተል ጠቃሚ ነው። መሠረታዊ የህገ-መንግስት ጥያቄ በይበልጥ ከህግ አንፃር በመመልከት፣ በቀጣይ ጠንካራ ሕብረብሄራዊ ሕገ-መንግስታዊነትን (multinational constitutionalim) ለማጠናከር ይረዳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብአዴናዊነት (ከበሃይሉ ምኒልክ)

(ሠ) የመንግስት አወቃቀርና ግንኙነት/Structuralism/: በመሰረቱ፣ የዚህ አይነቱ የህገመንግስት አተረጓጎም የህገመንግስቱን ስሪት፣ በፌደራል እና የክልል መንግስታት መካከል (ፌሰራሊዝም) እና በሶስቱ የመንግስት አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት (የስልጣን ክፍፍል)፣ ብሎም በመንግስትና በዜጎች መካከል የሚኖረውን መስተጋብር ግምት ውስጥ ያስገባ አተረጓጎም ስልት ነው። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርዐት በክልልሎችና የፌደራል መንግስቱ በጥምር ሉአላዊነት (dual sovereignty) የሚገለፅ በመሆኑ፣ የፌደራል አስፈፃሚው አካል ርምጃዎችና ውሳኔዎች የክልሎችን ሉአላዊነት ከተጋፋ የህገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆዎች ተጣሱ ማለት ነው።

(ረ) ታሪካዊ ልምዶች/Historical Practices/: የኢትዮጵያ፣ ሕገመንግስቱ ከመፅደቁ ጥቂት አመታት ቀደም ብሎ ለመበታተን ጫፍ ላይ ደርሳ የነበረች ሃገር መሆኗ ሲታሰብ፣ የሕጉ አርቃቂዎች ሃሳብ (legislative intent) ሕብረብሄራዊ ሕገ-መንግስታዊነትን መመስረት እንደነበር መገመት አያዳግትም። በመሆኑም፣ ይህ የአተረጓጎም መርሆ ከላይ የተጠቀሱትን የጋራ እሴቶች ከማስጠበቅ አኳያ ነው ሕገ-መንግስታዊነትን የሚመዝነው። የኢትዮጵያ ያለፈ ታሪክ በተጨባጭ የሚያሳየው፣ ሕገመንግስት መብቶችን ለማስጠበቅ የተቀረፀ ሰነድ በመሆኑ፣ ከሕዝቦች ሉአላዊት በሚቃረን መልኩ የሚወሰዱ ማናቸውም የፌደራል አስፈፃሚ ውሳኔዎች ህገመንግስታዊ መሰረት አይኖራቸው።

ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኋያ የህገ-መንግስት ተርጓሚ አካል የላይኛው ምክር ቤት ወይም የፌደሬሽን ምክር ቤት ቢሆንም፣ ምንም እንኳ የአሜሪካ የፍትህ ስርዐት፣ የፌደራሊዝም ስሪት እና ተጨባጭ ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ ቢለይም፣ የ ሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው የአሜሪካን ህገ-መንግስት ሳይንስ ፍልስፍና (constitutional jurisprudence) ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በማጣጣም የህገ-መንግስት ክለሳ ስራ ቢተገብር ጠቃሚ ጎኖች አሉት። በ ኢትዮጵያ የፍትህ ስርዐት የፍርድ ክለሳ (judicial review) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ቢኖረውም፣ ህገመንግስቱን የመተርጎም የወል ስልጣን ግን የለውም::

የፍርድ ውሳኔዎችን ህገመንግስታዊነት የመከለስ ደረጃዎች በኢትዮጵያ (Standards of Judicial Review):
የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ 789/2005 አንቀፅ 7 (1): “ለአጣሪ ጉባኤው የሚቀርብ የሕገመንግስት ትርጉም ጥያቄ አቀራረብ በአዋጁ በሚወጣ መመሪያ መሰረት ይሆናል” ይላል። የህገ-መንግስት ማጣራት ሂደቱ የሚከተላቸውን የህገመንግስት መርሆዎችን (standards of review) ቢገልፅ መልካም ነው።

የአሜሪካ የፍርድ መከለስ ሂደት (judicial review process) ህጎች ወይም ድርጊቶች ከሕገ-መንግስቱ መቃረናቸውን ለመገምገም በሶስት የተለያዩ መሰረታዊ ደረጃዎች ይመረምራል:

● “Rational Basis” (ምክንያታዊ/ቀላል)- ለምሳሌ፥ የግለሰብ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብትን የሚገድብ ህገመንግስታዊ ድንጋጌን ጥያቄ ዉቅስጥ ሲገባ፤

● “Intermediate Basis” (መካከለኛ)- ፍርድ ቤቶች ሕገመንግስታዊነቱን የሚመረምሩት ህግ ወሳኝ የመንግስት ጥቅምን የሚያራምድ መሆኑን በማየት መመርመር ፤

● “Strict Scrutiny” (በጥልቀት መፈተሽ መመርመር)-የአንድን ቡድን፣ ብሄር፣ ዘር፣ ወይምግለሰብ መብትን ለመገደብ አስፈፃሚው አካል በፍርድ ክርክር ወቅት የማስረዳት ሸክሙ (burden of proof) እጅግ ከፍ ያለ ነው፣ ምክንያቱም የግለሠብም ሆነ የቡድን ነፃነትን ለመገደብ መንግስት እጅግ አሳማኝ ምክኒያት ሊኖረው ስለሚገባ፣ በሌላ መልኩ መንግስት የዜጎችን ነፃነትና ሉአላዊነት አደጋ ውስጥ እንዳይከት ከለላ ለመስጠት፣ የሕጎችና ድርጊቶችን የሚመረምረው ፍርድ ቤት በአስፈፃሚው አካል የሚወሰድ እርምጃን ህገመንግስታዊነትን ጠበቅ ባለ መስፈርት ይገመግማል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ፣ የምርጫ መራዘም፣ የክልሎች ሉአላዊነትና ሕብረብሄራዊ ፌደራሊዝም:
የስልጣን ምንጭ ሕዝብ በመሆኑና ለህዝብ ቅርበት ያላቸው ደግሞ የአካባቢ መስተዳድሮች (local governments) ስለሆኑ፣ ከፌደራል መንግስት ይልቅ ክልሎች በይበልጥ የሉአላዊነት መገለጫ ናቸው። የክልሎች ስብስብ የፌደራል መንግስት ስለሚፈጥር፣ የፌደራል መንግስት የክልሎች ፖለቲካዊ ፍጥረት ነው ማለት ይቻላል። የክልሎችን ሕገ-መንግስታዊ ሉአላዊነት በሚጋፋና፣ የጥምር ሉዐላዊነትን መርሆን ግምት ውስጥ ሳያስገባ የምርጫ ማራዘም ውሳኔ የፌደራል አስፈፃሚው መወሰኑ መሰረታዊ የሉአላዊነት መርሆን ስለሚፃረር፣ ጉባኤው የትርጉም ጥያቄውን የሚመረምረው ከላይ በአሜሪካ ስርዐት (struct scrutiny) በመሰለ ጥብቅ ምርመራ መሆን አለበት፣ በሌላ መልኩ ጥያቄውን ያቀረበው አስፈፃሚ ከፍ ያለ የማስረዳት ሸክም (burden of proof) አለበት።

ለምሳሌ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የፌደራሉን ሕገ-መንግስት ተንተርሶ ባፀደቀው ህገመንግስትናየክልሉን ህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባከቤትነት ለማረጋገጥ፣ የመንግስት አስተዳደርን ለማስቀጠል፣ የነዋሪዎቹን ጤና አደጋ በማይጥል መልኩ ምርጫ ለማድረግ ወስኛለሁ ይላል። በሌላ መልኩ፣ የፌደራሉ አስፈፃሚ ከዚህ የተለዬ አቛም አለው። የ ፌደራሉ አስፈፃሚ አካል የምርጫ ማራዘም ውሳኔ በፌደራሉንም ሆነ የክልል ሕገ-መንግስታት፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የሕጓ አካል ያደረገቻቸውን አለማቀፍ ስምምነቶች በመጣስ፣ የክልሎችን ሉዐላዊነት በመጋፋት የሕገመንግስቱን ሉአላዊነት ይገዳደራል።

የመምረጥና መመረጥ መብት ወሳኝ ዴሞክራሲያዊ መብት መሆኑ ግልፅ ነው። በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 38 (1) መሰረት “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣…ልዩነት ሳይደረግበት… በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ መብት” እንዳለው ይገልፃል። በትግራይ ክልል ህገ- መንግስት መሰረት ደግሞ፣ የክልሉ ህዝብ በክልሉ ጉዳይ ላይ የሉአላዊነት ባለቤት እንደሆነ፣ በአንቀፅ 8 ( 9) ሉአላዊነቱ የሚገለፀው የክልሉ ነዋሪዎች በቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ሂደት በመረጧቸው ተወካዮቻቸው እንደሆነ፣ አንቀፅ 9 (1) ይህ መብት በምንም መልኩ ሊገደብ እንደማይችል ያስረግጣል።

በተመሳሳይ፣ በአማራ ክልል ህገ-መንግስት ምእራፍ ሁለት፣ አንቀፅ 8 ንኡስ አንቀፅ 2 መሰረት፣ የክልሉ ህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት እንደሆነና፣ ይህ ሉአላዊነት የሚገለፀው ደግሞ፣ በሚመርጧቸው ተወካዮች እና ራሳቸው በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እንደሆነ ይገልፃል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ ማናቸውም የአስፈፃሚ አካል ፖሊቲካዊ እርምጃዎች “ለዜጎች ጥቅም” በሚል የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን (በተለይም የመምረጥና መመረጥ መብትን) ሊገድብ እንደማይገባ፣ የኢትዮጵያ ህገ- መንግስት ምንጭ፣ በሗላም አካል በሆነው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለማቀፍ ሰብአብዊና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) ላይ በግልፅ ተቀምጧል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለዜጎች ደህንነትና ጤና ሲባል መፈፀሙ አስፈላጊነቱ ባያከራክርም፣ ራሱ ሕገ-መንግስቱ ከለላ የሰጣቸውን መሰረታዊ በራስ ጉዳይ የመወሰን መብቶች፣ የክልሎችን ሉዐላዊነት በመጋፋት፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ የሚወሰድ የአስፈፃሚ ርምጃ ኢ-ህገመንግስታዊ ይሆናል። ግልፅ የጥቁር ቀለም የሕገ-መንግስት ድንጋጌዎች ሲጣሱ የህገመንግስት ትርጓሚ የሚያስፈልግበት አገባብ የለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደወል 2 ዘኢትዮጵያ ደወል 2፡ ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት ለኢትዮጵያ - ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

የአንድን ቡድን፣ ብሄር፣ ዘር፣ ወይም መሰረታዊ የመንቀሳቀስ መብትን ለመገደብ ህጉን ያወጣው መንግስት በፍርድ ክርክር ወቅት የማስረዳት ሸክሙ እጅግ ከፍ ያለ ነው፤ ምክን ያቱም፣ የግለሠብም ሆነ የቡድን ነፃነትን ለመገደብ መንግስት እጅግ አሳማኝ ምክኒያት ሊኖረው ስለሚገባና ህዝብ ሉአላዊነቱን አሳልፎ የሚሰጥበት ሕገ-መንግስታው መሰረት ስለሌለ።

ጉዳዩ ያገባኛል ስለማለት (Locus Standi) እና የአንድ ወገን አቤቱታ (One-sided Petition):

ህገ መንግስቱን የሚቃረን ውሳኔ ሲከሰት የትርጉም ጥያቄውን ለምክር ቤት ማቅረብ ያለበት በውሳኔው ያልተስማማ ሌላ ሶስተኛ ወገን ነው ወይስ ከ ህገ-መንግስቱ የሚቃረን ውሳኔ ወስኛለሁ ብሎ የሚያምነዉ ራሱ አስፈፃሚው አካል?

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው መሰረት በሆነው የ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕ/መ 84 (2) መሰረት: “በፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጐች ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳና ጉዳዩም በሚመለከተው ፍርድ ቤት ወይም በባለ ጉዳዩ ሲቀርብለት መርምሮ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ያቀርባል” በማለት የጉባኤውን ተግባርና አላማ ያብራራል።

የሕገ-መንግስቱን ድንጋጌ አንቀፅ 84ን ለማሟላት በወጣው በተሻሻለው አዋጅ 789/2005 መሰረት: “በማንኛውም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን የመጨረሻ ውሳኔ … መብቴና ነፃነቴ ተጥሷል የሚል ማንኛውም ሰው… ለ ጉባኤው…ማቅረብ ይችላል” ይላል። በ በርካታ ሃገራት ህጎች “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም አርቲፊሻል ሰው ሊሆን ይችላል። አስፈፃሚውን እንደ ተቋም (juridical person) እንውሰድና፣ ራሱ የምርጫ ማራዘም ሃሳብ ለምርጫ ቦርድ አቅርቦ፣ የራሱ ውሳኔ ከህግ ጋር ስለተጋጨበት እንዲተረጎምለት ጥያቄ የሚያቀበው ራሱ አስፈፃሚው ይሆናል ማለት ነው። እንግዲህ፣ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የሚያቀርበው ያንድ ወገን አቤቱታ አቅራቢ (lone petitioner) ሌላ ወገን ተቃራኒ ሃሳብ ማቅረብ በማይችልበት ሁኔታ፣ የአጣሪ ጉኤው፣ ከዛም አለፍ ብሎ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩ ከቀረበ፣ ምክር ቤቱ፣ የሁለት ወገን ሃሳብ እንዳያይ የ “ይተርጎምልኝ” ጥያቄው አቀራረብ ጉዳዩን አስቸጋሪ ያደርገዋል።

አስፈፃሚው “የራሴ ውሳኔ ከገ ሕገ-መንግስቱ ጋር ተቃርኖብኛል” ብሎ የፌደሬሽን ምክር ቤትን “ተርጉምልኝ” ማለቱ፣ ከመጀመሪያውኑ የምርጫ ማራዘም ውሳኔው ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ስለሌለው አከራካሪ እንደሆነና፣ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም ሊሄድ እንደሚችል አስፈፃሚው ተስፋ በማድረግ ቀድሞ እያወቀ የወሰደው እርምጃ ነበር ማለት ነው። ያለበለዚያ፣ “ጉዳዩ የህግ ትርጉም ያስፈገዋል” ወይም “ሕገ-መንግስቱን ተቃርኗል” የሚለው ጥያቄ ይመጣ የነበረው፣ በአስፈፃሚው የምርጫ ማራዘም ውሳኔ ቅር በተሰኝ ሌላ ሶስተኛ ወገን ይሆን ነበር። አጣሪ ጉባኤው፣ “አስፈፃሚው የሕገመንግስት ትርጉም ጥያቄ ለማቅረብ የሚገባው ወገን (real party in interest) መሆኑንም መጠየቅ ይኖርበታል።

(2) “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በሗላ [ምርጫውስ] በምን ያክል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?”

ሁተኛው ፍሬነገር ከህግ ትምህርት ቤት የመላምት ጉዳይ (hypothetical case) ጋር ይመሳሰላል። ገና የመጀመሪያው፣ ዋናው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ (አስፈፃሚው መቼ፣ ምን እንደሚያደርግ ሳይታወቅ)፣ በፖለቲካ ውሳኔ ባንዣበበበት ሁኔታ) የህግ አስተያየት መሰንዘር ብዙም ጠቃሚ ባይሆንም፣ በሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ አንቀጽ 54 (1) ምርጫ በየአምስት አመቱ መደረግ ስላለበት እንዲሁም 58 (3): “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት…፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ስለሚጠናቀቅና አስፈፃሚው እንደሚለው ምርጫውን ማድረግ ስላልተቻለ፣ የኮሮናቫይረስ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርጪት መጠን ተገምግሞ፣ ከአስፈላጊ ጥንቃቄ ጋር በተቻለ ፍጥነት ምርጫ ቢደረግ፣ ዜጎች በፈቀዱትን መንግስት የመተዳደር ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን በተቻለ ፍጥነት እንዲጎናፀፉ ያግዛል።

ማጠቃለያ፥
ሕገ-መንግስት የህግና የፖለቲካ ስነድ ከመሆኑ አኳያ የፖለቲካ ውሳኔዎችም ችግር ፈቺ ሊሆኑ ቢችሉም፣ ግልፅ የሆኑ፣ ራሳቸው በራሳቸው የሚፈፀሙ (self-executing) የጥቁር ቀለም ሕጎችን ለማስተርጎም መሞከር ግን አዲስ ህግ ለመፍጠር ከመሞከር አይለይም።

አማራጭ አንድ: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጪት ተገምግሞ፣ ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር በተቻለ ፍጥነት ምርጫ በማድረግ ቅቡል የመንግስት አስተዳደር ማስቀጠል፤

አማራጭ ሁለት:በአግባቡ በተጠና በቂ መረጃ መሰረት የቫይረሱ ስርጭት ምርጫ ለማድረግ እንደማያስችል ሃገራቀፍ መግባባት ከተደረሰና ሰኔ ሰላሳ ካለፈ፣ ህብረብሄራዊ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ የአደራ መንግስት (caretaker government) በማቛቛም፣ የአደራ አተዳደሩ ምርጫ በማካሄድ ስልጣን ለሚመረጥ ፓርቲ ወይም የፖርቲዎች ጥምረት ማስተላለፍ፤

አማራጭ ሶስት:
ሁለተኛው ካልተቻለ፣ የሃገሪቱ ርእሰ ብሄር (ፕሬዝደትን) ብሄራዊ ምርጫ ተካሂዶ ሌላ መንግስት እስኪተካ ሃገሪቱን በአደራ መንግስትነት ቢያስተዳድሩ (የርእሰ ብሄር የስራ ዘመን ከጠቅላይ ሚኒስቴር በአንድ አመት በመብለጡ የሚፈጠረውን የስልጣን ክፍተት (power vacuum) በመሸፈን የሽግግር ሂደቱን ሊመሩ ይችላል።

ESAYAS HAILEMARIAM:
HARAMAYA UNIVERSITY, COLLEGE OF THE LAW;
UNIVERSITY OF CALIFORNIA, BERKELEY SCHOOL OF LAW.
(አንዳንዶቻችሁ እንደምታውቁት፣ የመወያያ ጭብጦቹን የወሰነው የሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው ነው)።

1 Comment

  1. This current constitution in question has never been drafted and had never been implemented to benefit all Ethiopians , it only was put in place to benefit EPRDF’s interests. The new Sidama drafted Ethiopian Constitution should be given a chance to be presented .

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share