የሱዳንና የኢትዮጵያ ግንኙነት የአሜሪካንንና የካናዳን ግንኙነት መምሰል አለበት። ለዚህም በቂ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ የሥጋ ዘመዳሞች ነን። መርዌዎችን በመልክ ከኢትዮጵያውያን መለየት አይቻልም። ዝርዝሩ ውስጥ ባልገባም ሁለቱ ሕዝቦች የሰላም መልክተኞች ይለዋወጡ ነበር።
ሁለተኛም፥ አንዱ በሱዳን አስተዳደር የሚኖር ጎሳ ከሱዳን አስተዳደር ወጥቶ ወደኢትዮጵያ የመጣው በበጎ ፈቃዱ ነው። መርዌዎች ጳጳስ ከግብጽ እንድናስመጣላቸው እርዳታ ለመጠየቅ ጊዮርጊስ የሚባለው ንጉሣቸው መልክተኛ ልኮ የነበረው ወዳጆች ስለሆንን ነው። “ሱዳን” በዐረቢኛ፥ “ኢትዮጵያ” በግሪክኛ ይሁን እንጂ ትርጉሙ አንድ ነው። “ጥቍሮች”፥ “ጠይሞች”፥ “ኩሻውያን” ማለት ነው።
ከሁሉም ይበልጥ ይልቅ፥ ሱዳን ችግር ሲገጥመን የምንሸሽባት አገር ነች። ፋሺስት ኢጣልያ በ1928 ዓ. ም. ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን በመሸሽ ሕይወታቸውን አድነዋል። እንግሊዝ ኢጣልያን ለመውጋት በኢትዮጵያ ደቡብ በኩል ስትዘምት ብዙ ወታደር የመለመለችው ሱዳን ውስጥ በጥገኝነት ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ነው። ባጭሩ “ከሩቅ ዘመዴ የቅርብ ጎረቤቴ” የሚለውን አነጋገር የሱዳን ጉርብትና አስመስክሯል። ያንን ወዳጅነት ተንከባክበን መያዝ አለብን።
በቅርቡ እንደሚሰማው ኢትዮጵያም ሱዳንም ምድሬ ነው የሚሉትን በኢትዮጵያውያን እጅ ያለውን መሬት ሱዳን ወርራለች። ይኼ ድርጊት መልካም ጉርብትናን ከማጉደፍ አልፎ ጦርነት የሚያስነሣ ድፍረት ነው። ከሕዳሴ ግድባችን ጋር የተያያዘ አደፋፋሪ እንዳለ ግልጽ ነው። ሆኖም ድፍረቱ ሕይወቷ የኢትዮጵያ ውሐ የሆነውን ሱዳንን አርቆ አስተዋይ የሌለባት ሀገር አድርጓታል። ምክንያቱም፥ ማንም መንግሥት ለማስተዳደር የተሾመበትን ወይም ራሱን የሾመበትን ሀገር ሌላ ሀገር ሲዳፈር ምን እንደሚያደርግ ግልጽ ነው። ያላንዳች ጥያቄ ጦርነት ያስነሣል።
ይህ ሱዳን የወረረችው መሬት ባለቤቱ ማን እንደሆነ ኢትዮጵያን አጼ ምኒልክ፥ ሱዳንን እንግሊዝ ከሚያስተዳድሩበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱን የጎረቤት አገሮች ሲያጨቃጭቅ እስከዛሬ የቆየ ነው። የሱዳኖች መከራከሪያ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሆኑ እንግሊዞች ያሠመሩት የድምበር ምልክት ሲሆን፥ የኢትዮጵያውያን መከራከሪያ የሕዝቡ ሰፈራ ነው። መሬቱ ላይ የሰፈሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው። የሰፈረን ሕዝብ “የያዝከውን መሬት ልቀቅ” አይባልም። ልቀቅ ካልተባለ ሱዳን “መሬቱ የኔ ነው” ስትል፥ የሰፈሩበትን ኢትዮጵያውያን ሱዳኖች ሁኑ ለማለት ይሆን? ለማንኛውም መሬቱ ለበልግ በሚዘጋጅበት ጊዜ ወርራለች፤ ይህ ድርጊት ከድፍረት አልፎ ሰውን ለረኀብ የሚዳርግ ወንጀልም ነው። ወረራው ወንጀልም ሰይፍ የሚያማዝዝም ሆኖ ሳለ፥ ኢትዮጵያ ያለፈውን ታሪክ በማስታወስ፥ የወደፊቱን የጋራ ጥቅም በማሰብ ትዕግሥት ማሳየቷ የሚያስመሰግናት ነው።
ገለልተኛ ታዛቢም ሆነ ገላጋይ መሬቱ የማን እንደሆነ የሚያውቅበት መንገድ የለውም። የእንግሊዙ ደምባሪ የደነበረውን ለመቃወምም ሆነ ለማጽደቅ ኢትዮጵያ ድምበሩን ሄዳ አላየችም። እንግዲህ፥ ለነዚህ ሁለት ዘመዳሞችና መልካም ጎረቤት ሀገሮች የሚያዋጣው የተጀመረውን የውሳኔ ውይይት ከመጨረሻው ማድረስ ነው። ያ ካልሆነ፥ ጉዳዩን ሁለቱ ሀገሮች ለሚመርጣቸው ገለልተኛ አስታራቂዎች ይስጡት። ፍርዳቸው በምንም ዓይነት ሁለቱንም ሀገሮች እኩል አያስደስትም። ሁሉም የሚደሰተው ምድሩ ያንተ ነው ቢባሉ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ አይቻልም። የድምበሩ ታሪክ ይኸን ዕድል ዝግ ያደርገዋል። ስለዚህ የአስታራቂዎቹ ፍርድ ከሁለቱ ሀገሮች አንዱን ወይም ሁለቱንም እንደሚጎዳ ሁለቱም ሀገሮች አስቀድመው አውቀውትና “ተጎዳሁ” የሚለውም ሀገር ውጤቱን እንደሚቀበል አስቀድሞ ቃል መግባት አለባቸው። ውሳኔው መሬቱን ወይ ለኢትዮጵያ ወይ ለሱዳን መስጠት ወይም እንዲካፈሉት መጠየቅ ይሆናል። አለዚያም (ለዘረከቦ ይርከቦ፥ “ለደረሰው ይድረሰው”) ብላችሁ ዕጣ ተጣጣሉበት የሚል ይሆናል። አስታራቂው ኮሚቴ የወሰነውን ውሳኔ ሁሉም መቀበል አለባቸው፤ ስንት የሚፈጽሙት የጋራ ጉዳይ እያላቸው መጨረሻ በሌለው ንትርክ ሲነታረኩ አይኑሩ። ሕዝባቸውንም ውጤቱን እንዲቀበል ቀደም ብለው ያዘጋጁት። የሁለቱም ሀገር ሕዝቦች በሀገር ፍቅር፥ “ሀገር አናስደፍርም” ይላሉ። ሲሉ “እዚያም ቤት እሳት” አለ የሚለውን ምክር በጥሞና ማስተዋል ይኖርባቸዋል።