የክብርት ፕሬዚዴንት ወይዘሮ ሣህለ ወርቅ ነገር – ጌታቸው ኃይሌ

ጌታቸው ኃይሌ

የክብርት ፕሬዚዴንት ወይዘሮ ሣህለ ወርቅን ስም መረዳት አቅቶኝ ሳለ የሞያቸው ማንነት ግልጽ አለመሆን ተጨመረበት። “ሣህለ ወርቅ” ግዕዝ ነው። ወደ አማርኛ ሲተረጐም “የወርቅ ምሕረት” ይሆናል። ምን ዓይነቱ ምሕረት ነው “ከምሕረቶች ሁሉ ተለይቶ ወርቅ ምሕረት ይህ ነው” የሚባለውና ተጠሪውን የሚገልጸው? “ዘነበ ወርቅ”፥ “የሻሽ ወርቅ ”፥ “ፈትለ ወርቅ”  ሲባል የሰሙ ወላጆች ሳያስቡበት ያወጡት ስም ይሆን? ግልጽ ስላልሆነልኝ የፖለቲካ ማንነታቸው ጥያቄዎች ከማንሣቴ በፊት መጀመሪያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ስላደረጉት ንግግር የተሰማኝን ልተንፍስ።

ክብርት ወይዘሮ ሣህለ ወርቅ በዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ያደረጉት ንግግር በብሔራዊ ቋንቋ መሆኑ በዓለሙ ውስጥ የኢትዮጵያ ቦታ የት እንደሆነ ያሳያል። በብሔራዊ ቋንቋ መናገራቸው የሚገርመው ካለ፥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ሌሎቹ የጥንትና ነፃነታቸውን ጠብቀው የኖሩ ሀገሮች በማን ቋንቋ እንደሚናገሩ ልብ ይበል።

መልእክተኞቹ አይገረሙም፤ የሚገረሙ ካሉ፥ ለታሪክ እንግዳ የሆኑ ናቸው። ለምሳሌ፥ በዓሥራ ሰባተኛው ምእት ዓመት የዛሬውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመስል ማኅበር ለመፍጠር ሐሳብ ቀርቦ እንደነበረ እናስታውሳለን። ከሐሳቡ ጋር ከተነሡት ጉዳዮች አንዱ ማእከሉ ለኢትዮጵያ ከማይርቅ ሀገር መሆን አለበት የሚል ነበር። ኢትዮጵያ በጀኔቫው የሕዝቦች ጉባኤ (League of Nations) እና በኒው ዮርኩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (United Nations) አባል የሆነችው ከብዙ ሀገሮች ቀድማ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ በብሔራዊ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩት ሌላ ቋንቋ ስለማያውቁ አልነበረም። ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ያውቁ ነበረ። “ሐዊሳ”፥ “አሻም”፥ “ብራቮ” ዶክተር ዐቢይ፤ “ሐዊሳ”፥ “አሻም”፥ “ብራቮ” ወይዘሮ ሣህለ ወርቅ።

ወይዘሮ ሣህለ ወርቅ ሴት መሆናቸውን ለጉባኤው መናገራቸው ግን አስፈላጊ አልነበረም። በመድረኩ ላይ ከእሳቸው በፊት ብዙ የብዙ ሀገር ሴቶች ወጥተውበታል። አንዳቸውም ሴት መሆናቸውን በገጻቸው እንጂ በቃላቸው አላስታወቁም። በታሪክም ቢሆን የሳቸው ሴትነት ከሌሎቹ ሴትነት አይለይም። ሴቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ቀኖናና ከተፈጥሮ አቅማቸው ሌላ በዓለማዊ ሕይወትና በመንግሥት አገልግሎት  ከወንዶች የሚያሳንሳቸው ምንም ነገር የለም። በውርስ ከወንድ እኩል ናቸው፤ መንግሥት የመሩ ሴቶችም ነበሩን። ጉዲት ታሪኳን ሁላችንም ባናደንቀውም መሪ ነበረች። ሞተለሚን የምናውቀው በናቱ በእስላንተኔ ጀግንነት ነበር። ሴቶች ከጥንት ጀምሮ ሐስጓ (የጠቅላይ ግዛት ገዢ) ይሆኑ ነበር። ለምሳሌ፥ በንጉሥ ዘርአ ያዕቆብ በዘመን ሲሕ መንገሣ ሐስጓ እንደነበረችና ንጉሡ ፈጸጋርን “ምድረ ሲመታ” (የግዛቷ ምድር) እንዳለው ተመዝግቧል። የአፄ ገላውዴዎስ እናት (የአፄ ልብነ ድንግል መፃምርት) እቴጌ ሰብለ ወንጌል፥ የራስ ዓሊ አሉላ እናት እቴጌ መነን፥ የአፄ ምኒልክ መፃምርት እቴጌ ጣይቱ፥ ፋሺስት ጣልያንን የተቋቋሙ አርበኛ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ ከየትኛውም የወንድ ጀግና እኩል የጀገኑ ሴቶች ነበሩ። ክብርት ፕሬዚዴንቷ ከነዚህ ጀግኖቻቸው ማህል ስለ ስንቱ ያውቃሉ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኔና ስርጉተ--  አልተግባብቶም        ይገረም አለሙ

ወይዘሮ ሣህለ ወርቅ፥ ከስማቸው ይልቅ፥ በኢፌዲሪ ምክር ቤት ላይ ተገኝተው የኢሕአዴግን  ራእይ የሚመለከት ንግግር ማድረጋቸው ብዙ ጥያቄዎች እንድናነሣ ያደርገናል። እመቤቲቱ ከኢሕአዴግ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምንድነው? የኢሕአዴግ ምልምል እንደሆኑ እናውቃለን። ግን የተመለመሉት እንደ ባንዲራ፥ እንደ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ አንድነት ምልክት (አርማ) እንዲሆኑ ነው ወይስ የመልማሊዎቻቸው መሪ እንዲሆኑ?

በአሁኑ ሰዓት ብዙ ፓርቲዎች ተወዳድረው ሥልጣን ለመያዝ እየተሰበሰቡ ድል የሚያገኙበትን ዘዴ ሲተልሙ እናያለን። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ኢሕአዴግ ሆኖ ሳለ፥ ከሌሎቹ ስብሰባ ላይ ሳይገኙ በምን ምክንያት ነው በኢፌዲሪ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የኢሕአዴግ ልሳን የሆኑት? ኢሕአዴግ ከሌሎች ፓርቲዎች (ከኢዜማ፥ ከመኢአድ፥ ወዘተ.)  ጋራ ተወዳድሮ በሥልጣን ለመቆየት እየተዘጋጀ ያለ ፓርቲ ነው። ወይዘሮ ሣህለ ወርቅ የሀገር ምልክት ከሆኑ፥ ከምልክትነታቸው አልፈው የኢሕአዴግ ፓርቲ ፕሮግራምን ወደማብራራት ምን ወሰዳቸው? ምክር ቤቱን መክፈታቸው ተገቢ ነው፤ ግን የሀገሪቱ መሪ እንደመሆናቸው ለሀገሪቱ ያላቸውን የራሳቸውን ራእይ አካፍሎ ከመሄድ አልፎ ለጎሳ ፓርቲዎች ማቀንቀን አድላዊነትና እንደነሱ ጎሰኛ መሆን ነው።

ክብርት ፕሬዚዴንት ለፕሬዚዳንትነት በኢሕአዴግ ከመመረጣቸው በፊት እንደ ኢሕአዴግ ጎሰኛ ነበሩ ወይስ ውለታ ለመመለስ እንደ ኢሕአዴግ  ጎሰኛ ሆኑ?  ጽኑ ሰው ውለታውን ለመመለስ ሲል እምነቱን ወይም ሃይማኖቱን አይለውጥም። የሀገር መሪ ሆኖ እንደ ኢሕአዴጎች የኢትዮጵያን ታሪክ  ሲያጠለሹት መስማት እንደ ተወረወረ ጦር ያማል። አኵሪ ታሪካችንን ምነው ባላወቅሁ ያሰኛል። የተቻለውን ያህል በሕግ ይተዳደር የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት “ፍርድ ያጓድል ነበር፤ ሕዝብ ይጨቁን ነበር” ማለት የራስን ታሪክ  ማጠልሸት ነው። የሀገርን ክብር መጠበቂያ ወምበር ላይ በአደራ ተቀምጣችሁ የልጆች ፍልስፍና ማስተጋባት የሚያሳስር ክሕደት ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያህል ትልቅ መሥዋዕት የተሠዋለት አምላክ ስሙ ማን ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ትግሉ ኑረምበርግ ደርሷል"

ደርግና ተማሪዎች እስከነገሡበት ዘመን ድረስ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝቡን ያስተዳደረው ረቂቅ በሆነ ሕግ እንደ ነበረ ብዙ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል። ሌላው ቢቀር በዚህ ዓመት ለማሳተም ከማዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ለምሳሌ ያህል አንድ የግዕዝ ጥቅስ ወደ አማርኛ ተርጕሜ ደግሜ ላሳይ፤

“ግራና ቀኝ ወምበሮች ለዳኝነት በሰቀላ (= በፍርድ ቤት) ሲቀመጡ፥ ከያሬድ ቃል በዜማ  እንዲህ እያሉ በመጸለይ ይጀምራሉ “ሃሌ፡ ሉያ፥ አመ፡ ዕለተ፡ ፍዳ፡ ወአመ፡ ዕለተ፡ ደይን፡ አመ፡ ዕለተ፡ እግዚአብሔር፡ ምንተ፡ ንብላ፡ ለነፍስ፡” እስከ፡ ፍጻሜሁ። (ሃሌ፡ ሉያ፥ ዕዳ  በሚከፈልበት ዕለት፥ የፍርድ ዕለት፥ የእግዚአብሔር ዕለት ለነፍሳችን ምን እንላታለን? ወዘተ.)  ይህንን ሦስት ጊዜ ካሉ በኋላ ትርጓሜውን ከጽራግ ማሰሬና ከሊቀ ማእምራን ይሰማሉ። ከዚያ በኋላ ለዳኝነት በንጉሡ ሰቀላ በቀኝና በግራ ይቀመጣሉ። ከበሽተኞች፥ ከሴቶች፥ ከመምህራን (= ከገዳም አበምኔቶች) በቀር ማንም፥ ትልቅ ሆነ ትንሽ፥ ሹም (ሀገረ ገዢም) ሆነ ወይም ቢትወደድ፥ ወይም ደጃዝማች በሰቀላ ውስጥ በዳኞቹ ፊት ቁጭ ብሎ አይፋረድም። ስለሹመቱ ክብር ተቀምጦ የሚፋረድ የአክሱም ነብርድ (ብቻ) ነው።

ክብርት ፕሬዚዴንቷ  ስለዚህ ሕግና ሥነ ሥርዓት አንብበዋል ወይ? ከአነጋገር ስለሚፈረድ፥ እንኳን ሊያነቡት መኖሩንም የሰሙ አይመስሉም። ፍትሐ ነገሥቱ በግዕዝ ቢጻፍም ወደ አማርኛና ወደ እንግሊዝኛ ተተርጕሟ። ክብርት ፕሬዚዴንቷ አንብበውታል?  አሁን ሥራ ፈት ስለሆኑ ለማንበብ ጊዜ አላቸው። ፍርደ ገምድል ዳኛ ሊኖር ይችላል። ግን እኩይ ዳኛ የሌለበት ሀገር ካለ፥ ልናውቀው እንፈልጋለን።

በሀገራችን ስለነበረውና ኢሕአዴግ ስላስወገደው የጎሳዎች ጭቆና “ሕዝቦች” እያሉ በሙሉ እምነት ተናገሩ። ግን አንድ ሕዝብ ተለይቶ እንደተጨቆነ ምሳሌ አልሰጡም። እርግጥ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከመንግሥቱ ቋንቋ በቀር ሌሎቹ ቋንቋዎች የጽሑፍ ቋንቋ እንዳይሆኑ ተደርጎ ነበር–ለአጭር ጌዜ። እንዲህ ያለ ሕግ ከዚያ ዘመን በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልነበረም። ጸሐፊ ያገኙ ቋንቋዎች ሁሉ ይጻፍባቸው ነበር። የኢትዮጵያን ሥልጣኔና ኢኮኖሚዋን ወደ ኋላ የጎተቱን ታላላቅ ጥፋቶች እየደበቁ ይኸንን የአጪር ዘመን ስሕተት ሲያመሰኩ መኖር የሀገር መሪ ሥራ አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የነዳንኤል ክብረትና የኔ - ሁለት አቢይ አህመዶች! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ዛሬ የባለዘመኖች ወንጀለኛ ነፍጠኛው ነው። እማን ላይ ቆመሽ እግዚአብሔርን ታሚያለሽ ያለውን ያስታውሱናል። ቡና የምታመርቱባት፥ ከብታችሁን የምታግዱባት ኢትዮጵያ የነፍጠኛው ስጦታ ነች። ወራሪ ቱርክን ከሰሜን ኢትዮጵያ ያባረረ ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? አድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ የመታው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? የግራኝና የኦሮሞዎች ወረራ ያንኮታኮታትን ኢትዮጵያ የጠገናት ማነው? ነፍጠኛው አይደለም?  ኤርትራ እንዳትገነጠል ደሙን ያፈሰሰው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? የሱማሌን ወረራ የመከተ ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? ፋሺስትንና ናዚስትን ድል የነሣው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? ለዓለም ሰላም ኮርያ ላይ አጥንቱን የከሰከሰው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? እኩይን ድል የነሣን የሚኰንን እኩይ ብቻ ነው። ከተሞች ባሉበት ሁሉ ከማህል አደባባይ ላይ ላልታወቀው ነፍጠኛ ሐውልት ማቆም አለብን።

ይቺን ድርሰት ጽፌ ስጨርስ ክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኖብል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ሰማሁ። ስንቶች የተመኟትን እኛ ስላገኘናት ደስታው የሁላችንም ነው። ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ጸጋ ለመሆኗ የሽልማቱ አሸናፊ መሆን አንዱ ማስረጃ ነው። ሆሞም፥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሽልማቱ ጋራ የመጣውን ማሳሰቢያ እንዳላጤኑት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ በመከልከል አሳይተዋል።

ድል ለሰላም፥ ድል ለሰው ልጅ መብት ተሟጋቾች፥ ድል ለዲሞክራሲ።

 

5 Comments

  1. Prof we are in debt for you, please make avialable a site where we can see all your work (articles). Long live and good health you are an icon of Ethiopia no doubt for that, your analysis, your judgment, your knowledge all combined will make you a school of thought. Great respect

  2. የፕሮፌሰር ጌታቸውን ጽሑፍ ለማንበብ ከሚሽቀዳደሙ መሓል ነኝ። የሚያሳፍረው ግን ፕሮፌሰሩ እንደ አዛውንትና ምሑር ሳይሆኑ ሲቀር ማየቴ ነው። ሁሌ የወረደ አሳብ ሳይለውሱበት አያሳርጉም። 1/ አገራችን ሴቶች መሪዎችን አፍርታለች ለማለት ጉዲትን ከታሪክ ያጣቅሱና፣ ቀጥሎ ከሺህ ዓመት በኋላ እነ ጣይቱን ይጨምራሉ። 2/ ኢሕአዴግን እነ መለስ ሦስት ተለጣፊ ድርጅቶችን ጨምረው በ1983 እንደመሠረቱና እስካሁንም አገሪቱን የሚገዛው ፓርቲ መሆኑን ዘንግተው ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን አሁንም እዛው ነህ እንዴ ብለው ይወቅሳሉ። ህወሓት 27 ዓመት የገመደውን በሁለት ዓመት ይፈታ ምን ዓይነት ዳኝነት ነው ወይስ እውርነት? 3/ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅን ስለ ተባበሩት መንግሥታት ፕሮቶኮልና ንግግር ሊያስረዱ ይሞክራሉ፤ ምጥ ለናትዋ አስተማረች ይመስላል። 4/ የሴቶች መብት በኢትዮጵያ እንደ ተከበረ ያክል ከታሪክ ሁለት ሦስት ጠቅሰው ሲናገሩ ምን ያህል ኋላ ቀር እንደሆኑ እንደሚመሰክርባቸው ዘንግተው ነው! 5/ ወደ ተለመደው እንደ አማራ ቸርና አዋቂ የለም ቀረርቶአቸው ይዛመታሉ፦ “እማን ላይ ቆመሽ እግዚአብሔርን ታሚያለሽ ያለውን ያስታውሱናል። ቡና የምታመርቱባት፥ ከብታችሁን የምታግዱባት ኢትዮጵያ የነፍጠኛው ስጦታ ነች። አድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ የመታው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? የግራኝና የኦሮሞዎች ወረራ ያንኮታኮታትን ኢትዮጵያ የጠገናት ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? ኤርትራ እንዳትገነጠል ደሙን ያፈሰሰው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? የሱማሌን ወረራ የመከተ ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? ፋሺስትንና ናዚስትን ድል የነሣው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? ለዓለም ሰላም ኮርያ ላይ አጥንቱን የከሰከሰው ማነው? ነፍጠኛው አይደለም? እኩይን ድል የነሣን የሚኰንን እኩይ ብቻ ነው። ከተሞች ባሉበት ሁሉ ከማህል አደባባይ ላይ ላልታወቀው ነፍጠኛ ሐውልት ማቆም አለብን።” ይኸ ወራዳ ንግግር ነው፤ ታሪክ አውቃለሁ ብለው ያቦካሉ፤ አማራ ብቻ ነው ኢትዮጵያዊ፤ ሌላው ሁሉ መጤ ነው እያሉን ነው። 6/ መደምደሚያ ላይ ለእስክንድር ወሮበላነት ድጋፋቸውን ለማሰማት “የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ በመከልከል አሳይተዋል።”ይሉናል! ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እስክንድር፣ ጀዋርና ልደቱ ዓይነቶች አያስፈልጉንም! ፕሮፌሰር ጌታቸውም በጀመሩት በጥንታዊት ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ቢቀጥሉበት ይሻላል።

    • ቤዛዊት ወይስ ሸዊት መቼም ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ባንች ደረጃ ይወርዳሉ ብዬ አላስብም። ለመሆኑ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ የሚጽፉት በወጉ ይገባሻል ወይስ በሳቸዉ ስም የሚጻፈዉን ትተሺ አእምሮሺ ዉስጥ ያለዉን ነዉ የምታነቢዉ? ብዙ እህተ ማርያምም በሳይበሩ ተበትነዋል ለካ? አይ ትንታኔ አይ ግንዛቤ አይ ታሪክ አዋቂ። ፕሮፌሰር ጌታቸዉ አዋቂ ብቻ ሳይሆኑ የአዋቂ መለኪያ ናቸዉ “ቤንች ማርክ” እንደሚሉት።

      ዘመድ ካለሺ ትኩስ የፈለቀ ጠበል ይዞሺ ይሂድ ለጻፍሺዉ ጽሁፍ ግን ምክንያታዊ ዉይይት ማድረግ የሚሆን ነገር አይደለም። ፈረንጆቹ “ሚስ ማች” እንደሚሉት ማለት ነዉ። የድር ባለቤቶችስ እንዲህ ያለ እንጭጭ ሀሳብ በትልቅ ምርምር ከተጻፈዉ ከፕሮፌሰር ጌታቸዉ ጽሁፍ ጋር አዳምረዉ መላካቸዉ ምን ይባላል? መቼ ነዉ ለጀግኖቻችንን ሺፋን የምንሰጠዉ የምንቆምላቸዉ? እንዲህ ያለ ጽሁፍ ለሚመጥነዉ ለትግራይ ኦን ላየን ወይም ደግሞ ለኦፌኮ/ኦነግ ጽ/ቤት እንጂ እዚህ ምን ይሰራል? እዚሁ ቤታችን መጥተዉ ተሳድበዉ እንዲሄዱ ከተፈቀደ በጣም ያሳዝናል እንዲህ ከሆነማ የድር ገጹም እኛም ቆሻሻ መጣያ መሆናችን ነዉ።

      • Semere,
        I think you have a serious problem. I read Bezawit’s comments but you failed to respond to any of her critique of Prof. Getachew’s article. Instead you went into diatribe. May be you have to read it again or ask somebody else to explain it to you. Ciao.

  3. ዘረ-ያዕቖብ/Tewoflos/Bezait to begin with you are not Ethiopians, it is not hard for us to identify your identity from your writtings. I have never been in tegreas or shabiyans rooms, I wonder what are you doing here dont you feel ashamed to find yourself in Ethiopians room? Is there pride and integrity in your vocabulary? any how it is not profitable argument to deal with people like you. We are Ethiopians there is unparalel differences betwen you and us, keep your distances please.

    You have never lived as a free country Ottomans/Egypts/Italiyans/British/Arabs were your masters and I dont think you will get use to live in a free society, that is why you are comfortable with Afeworki. when I get time I will write detailed articles your activity in Ethiopia.
    Good for you.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share