በየ ጊዜው አጀንዳ እየተሰጠን እኛ የነሱ ገበያ መሆናችን ሁሌም ግርም ይለኛል፡፡ መሠረታዊ ነገር እንዳናስብ በወሮበሎች አስተሳሰብ ተጠምደን ባዝነን አያለሁ፡፡ ሰሞኑን የጀዋርና ልደቱ ሌላ የጥፋት ሴራ ድንፋታ በየማህበራዊ ድረ-ገጹ ተጥለቅልቆ አየሁ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ላሉ ግለሰቦች እድል እየተሰጠ አገርና ሕዝብ መቼም ቢሆን ከችግር ይወጣሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔን ግን አሁንም የምጠይቀው ነገር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች በወሳኝነት ቦታ ሳይቀር እንዳሉ ይነገራል፡፡ ሌሎች ደግሞ ዜጎች ያላገኙትን መብት ተሰጥቷቸው እንደውም በልዩ ሁኔታ ከለላ እየተደረገላቸው እንደፈለጋቸው እየፈነጩ እናያለን፡፡ ከእነዚህ አንዱ ጀዋር መሀመድ የተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ይሄ ግለሰብ የአሜሪካ ዜግነት የነበረው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ አሁን ዜግነቱ ቀይሯል የተባለበት አግባብም ግልጽ አደለም፡፡በመጀመሪያ ይሄ ግለሰብ ለብዙ ለጠፉ ጥፋቶች በወንጀል ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡ ከዛ ግን አልፎ ይሄው የፓርቲ አባል ሆኛለሁ ብሎ አሁንም በኢትዮጵያ እየደነፋ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ብዙ ሌሎች ግለሰቦች በተለያየ መልኩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ሆነው ተሳፍረዋል፡፡
የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ልደቱና የተለመደው የሽብር ቀስቃሽ ግለሰብ አንዳነዶች እንደሚሉት የግሪሳ (የመንጋ) አስተሳሰብ አራማጁ በዛው በተለመደው የሽበር ማሰራጫ ሚዲያ ኦኤም ኤን ቀርበው ለአዲስ ሽብር ሲያሟርቱ ሰምተናል፡፡ ልደቱ የተባለው ግለሰብ ቀደም ብሎ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ ስለማይቻል ይራዘም ሲል ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከመስከረም 30 በኋላ ይለያል አይነት ፉከራ ሲደነፋ ሰምተንዋል፡፡ ጀዋር የተባለውም ግለሰብ ከመስከረም 30 በኋላ መከላከያው አይታዘዝም፣ ፖሊስ አይታዘዝም እያለ ሲደነፋ ሰምተናል፡፡
ልብ በሉ ቢያድለን መከላከያና ፖሊስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ዛሬ ይሄን ግለሰብ በሽብር ወንጀል ሊጠይቀው በተገባ፡፡ ሲጀምር የአንድ አገር መከላከያም በሉት ፖሊስ ወይም የፍትህ ሥርዓት የፓርቲ ሎሌ ሳይሆን የአገርና ሕዝብ ነው፡፡ የእነጀዋር አይነት የወሮበላ አስተሳሰብ እንዲህ ቦታ እንዲኖረው ያደረገው በአለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ፈርሶ ወያኔ የራሱ ጠባቂ ሎሌ መዋቅር በመፍጠሩና አሁንም የዛው አስተሳሰብ ተገዥ የሆነ መከላከያ መቀጠሉ ነው፡፡ ፓርላማ በሉት ሌላ የፖለቲካ ተቋም ኖሮ አልኖሩ መንግስታዊና አገራዊ ተቋሞች በተለመደው ሁኔታ ሥራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ መንግስት ማለት ፓርቲ አደለም፡፡ በርካታ አገራት ያለ ፓርላማ ወኪሎች ለወራት በሠላምና ሥርዓት ተጠብቆ ቀጥለዋል፡፡ በተለይ የአገር ደህንነትና ፍትህ ጋር የተያያዙ ተቋማት ፓርላማ ቢኖር እንኳን የሚታዘዙት በየጊዜው በሚለዋወጡ የፓርቲ አስተሳሰብ ሳይሆን መሠረታዊ በሆኑ የአገርና ሕዝብ ወካይ አስተሳሰቦች (ሕገመንግስት) ስለሚሆን ማንም እንደፈለገ የሚዘውረው አካሄድ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ያን መሠል አስተሳሰብ ስለጠፋና መከላከያውም ሆነ ፍትሁ የኢህአዴግ ስልጣን ጠባቂ በመሆኑ የኢህአዴግ ፓርላማ ካልቀጠለ አይታዘዝም ወይም የሌላ ደጋፊ በመሆን ከሌላ ጋር ይወግናል ነው የዛሬው የጀዋር አስተሳሰብ፡፡ ለዚህ ደግሞ የእኔ አድናቂ የሆኑ ወታደሮች ብጥብጥ ይፈጥሩልኛል በሚል በተስፋ የሚጠብቃትን መስከረም 30ን እየናፈቀ መሆኑን ነው፡፡
አዝናለሁ የኢትዮጵያ መንግስት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተያዘው የፓርቲ እንጂ ምንም አይነት የመንግስታዊና አገራዊ ሥርዓት በማይገባቸው በመሆኑ ለዘመናት እኛ ከሌለን አገር የለም በሚል ለሌሎችም ይሄኑን በደንብ አሳምነዋል፡፡ ልደቱ አያሌው ያኔ ጋባዥና ተጋባዥ የለም እያለ ሲፎክር የምንሰማው ከዚሁ የአስተሳሰብ ነው፡፡ ለመሆኑ ዛሬስ ጋባዡና ተጋባዡ ማን ነው? መንግስት ወይ ፓርቲ? እንግዲህ ፓርቲዎች ወደምርጫ እየገቡ ያሉት በዚህ ስነልቦና ከሆነ ነገ ደግሞ እነሱ ሲመረጡ እንዲሁ የለመዱትን ማስቀጠላቸው አይቀሬ ለመሆኑ ይሄ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ለዘመናት በፖለቲካ (ቁማርም ቢሆን) የኖረው ልደቱ የሚያስበው እንዲህ አሁን እንደሰማንው ነው፡፡ እንደወጉ የምርጫ ማስፈፀም ሀላፊነት ለምርጫ ቦርድ ተሰጠ የተባለው የጋባዥና ተጋባዥን ቁማር ለማስቀረት ተብሎ መስሎን፡፡ ሁሉም ፓርቲ እኩል መብትም ግዴታም አላቸው፡፡ ትክክለኛ መንግስት ቢኖር፡፡ ነገሮችን ማመቻቸትና ማዘጋጀት የመንግስት ኃላፊነት ነው፡፡ እስኪ የሌሎችን አገርት አሰራር አስተውሉ በፓርላማም በፕሬዚደንትም የሚወከሉ አገራትን፡፡ ምርጫቸውን እንዴት ነው የሚያከናውኑት? እንግዲህ ተለውጫለሁ የሚለው አካል ሊለካበት ያለው አንዱ ይሄ ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው እስካሁንም ተለክቶ በብዙ ነገሮች ወድቋል፡፡ አገራዊና መንግስታዊ ሥርዓቶችን ከማስፈን ይግለሰቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይቀር የመንግስትን መዋቅር ሲጠቀምበትና ሕዝብን ለከፋ አደጋ ሲያጋልጥ አይተናል፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ጥፋቶች የዜጎች ሕወታቸውን ሳይቀር እነ ጀዋር ባስነሷቸው ሁከቶች ተከስተው አይተናል፡፡በሌላ መልኩ አይናቸው ያልወደደውን ሰው አድነው ሲያጠፉ አይተናል፡፡ የመንግስት መዋቅር አገርንና ሕዝብን ለማስተዳደርና ለመጠበቅ ሳይሆን የወሮበሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሲሆን አይተናል፡፡ ይህን የለመዱ ግለሰቦች ይሄው ዛሬም ሊያውም በወረርሽኝ ምክነያት አገር ተዘግታ ባለችበትና ሁሉም ስለወረርሽኙ እያሰበ ባለበት በዚህ ወቅት እነሱ የዚህ ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳለቀ ወደ ለመዱት ብጥብጥ የሚገቡበትን ዘዴ ከወዲሁ አቅደው እየነገሩን ነው፡፡ መንግስት ነኝ የሚለው በተለይ መከላከያው፣ ፖሊስና ፍትህ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማን እንደሆነ ሊታይ ነው፡፡ ለመንግስት አይታዘዙም የተባሉት ፖሊስና መከላከያ ከእኔ ወገን ይሆናሉ በሚል ነው ዛሬ ይሄ ግለሰብ እየደነፋ ያለው፡፡
ከወዲሁ ምን አልባት ለበርካታ አመታት ይሄው የመንግስት መዋቅር ተወሮ በወሮበሎች ስለዋለ መንግስት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የጠፋብን መሠለኝ፡፡ ኃይለስላሴ ከስልጣን ሲወርዱ መከላክያው ቀጠለ፡፡ ምክነያቱም ያ መከላከያ የኢትዮጵያ እንጂ የኃይለሥላሴ ስላልነበር፡፡ ሊያውም በዛ ቀውጢ ሁኔታ፡፡ እንደዛ ያለ መከላከያ ዛሬ ኢትዮጵያ የላትም፡፡ በቅርቡ በጎረቤት ሱዳን አልበሽር ከዘመናት በኋላ ከስልጣን ሲነሱ መከላከያውና ወሳኝ መንግስታዊ መዋቅሮች አገርን አስቀጥለዋል፡፡ መሪ ፓርቲ እስከሚወክል አገርን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በሌሎች አገራት ከእነጭርሱ የፓርቲ ውክልና ያስፈልጋል ወይ እስከሚባል ድረስ ሁሉም ነገር ያለ ፓርላማና መሪ ፓርቲ ቀጥሏል፡፡ ለምሳሌ በጀርመን ለወራት፣ በስፔን ወደ 10 ወር የተጠጋ፣ በኒዘር ላንደ በተደጋጋሚ ግን በአንድ ወቅት ወደ 8 ወር የተጠጋ፣ በቤልጂየም ከዓመት በላይ እንዲሁ በሌሎችም ይኖራል፡፡ በእነዚህ ወቅቶች በእነዚህ አገራት አንድም የተጓደለ ነገር አልነበረም ምን ዓልበት አዲስ ውል ከአገራት ጋር መዋዋል አልተቻለ ከሆነ እንጂ፡፡ የሚገርመው እንደነቤልጂየም ያሉ ከዓመት በላይ የዘለቀው መሪ ዓልባ መንግስታዊ መዋቅር ዓመታዊ በጀት እንዴት እንደጸደቀ አላውቅም፡፡ ሆኖም እስከዚህ ድረስ በኃላፊነት አገርንና ሕዝብን ደህንነት ጠብቀው የአገሪቱን መንግስታዊ አሰራሮች የሚያስቀጥሎ ለሕዝብና ለአገር ብቻ የተወከሉ ተቋማት እንደሆኑ እናያለን፡፡ በእርግጥም መንግስት ፓርቲ አደለም፡፡
ወደ እኛው አገር ስንመጣ ይሄ አይታሰብም፡፡ እንደሱዳን እንኳን በሀገርና ሕዝብ ላይ መሠረቱን ያደረገ መከላከያ ተቋም የለንም፡፡ መከላከያው ከተፈጠረ ጀምሮ የኢሕአዴግ የተባለ ቡድን የግል ተቋም ሆኖ በመኖሩ ነገ ሌላ ፓርቲ ቢመጣ አብሮ ለመቀጠሉ አጠያያቂ ነው፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ነው ችግሩ፡፡ በተመሳሳይ ግብጽ ሞባረክ ከስልጣን ሲወርዱ የመከላከያውን ሚናና አሰላለፍ ተመልክተናል፡፡ መንግስታዊ መዋቅር በተለይም ደግሞ መከላከያ በየትም አገር ያለው ባሕሪ ይሄ ነው፡፡ መጀመሪያ በአስተሳሰብ ድኩማን የሆኑ ግለሰቦች በፓሪተ ውስጥ ዋና ሆነው ተሰልፈዋል፡፡ በአገራችን እኩል ኃላፊነትና መብት አለን ብለው ሳይሆን በሚጣልላቸው ዳረጎት እንደምንም በግላቸው ፓርላማ ለመግባት ከዛም ስልጣን ለመያዝ የሚያስቡ እንጂ መንግስትና ሕዝብ አገር ማለትን የሚረዱ አደሉም፡፡ በመሆኑም እላለሁ አሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መከላከያ፣ ፖሊስና ፍትህ ላይ እየሰራችሁ ያላችሁ ሰዎች አስቡበት፡፡ ለዘመናት ከአእምሮአችን ስለጠፋ ማስታወስ ያስቸግራል፡፡ ሕዝብ ደግሞ መንግስት ማለት በደንብ ይረዳ፡፡ ዛሬ ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ከሌሎች በተለየ የምነግስትና ሕዝብ ሀብት ለምርጫም ሆነ ለሌላ የመጠቀም መብት የለውም፡፡ የመንግስት ሚዲያዎችም ከዚህ ራሳቸውን ነጻ ያውጡ፡፡ የመንግስትን ፖሊሲና እቅድ ማቅረብ እንጂ የፓርቲ ፕሮፓጋንዳ መንዣ ባይሆኖ መልካም ነበር፡፡ ይሄ አሁን ባለው ሁኔታ አይታሰብም፡፡ መዋቅሮች በሕግና ሥርዓት ሳይሆን በፖለቲካዊ ውሳኔና በባለስልጣናት የምን አለብኝነት ትዕዛዛት ስለሚመሩ፡፡
ምርጫው ድሮውንም ታስቦበት በነበረበት ወቅት ለመካሄድ እንደማይቻል የዛሬው ከመስከረም በኋላ እንተያያለን የሚለውን ልደቱን ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎች ሲናገሩ ነበር፡፡ መስከረም 30ም በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ሕገመንግስት እየተባለ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥፋት የሚጠቀሰው ሕግ የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይወክል በመሆኑ በእሱ ተቀመጠም አልተቀመጠም መደበኛ የሕግ አሰራር እንጂ ሕገመንግስት በሚባለው ውስጥ የተሰነጉ ሴራዎች ተግባራዊ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ ሲጀምር ሕገ መንግስት የመንግስታዊ አደረጃጀት ሥርዓት እንጂ ሕግና ሥርዓትን ለማስጠበቅ መደበኛው ሕግ ነው የሚወስነው ብዬ አስባለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!
ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ! ማስተዋልን ይስጠን!አሜን!
ሰርፀ ደስታ