በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ድሮ! ድሮ! ጥንት! ገና በጥኋት! እንግሊዝ፣ፈረንሳይና ጀርመን አገር ተመሆናቸው እጅግ እሩቅ ጊዜ በፊት! ነጋዴው ኮሎምበስም ወርቁን ሊያግበሰብስ ፓስፊክ ውቂያኖስን አቋርጦ “አሜሪካን አገኘሁ” ተማለቱ ረጅም ጊዜ በፊት በሰው መፈጠሪያዋ ኢትዮጵያ ሊቃውንት በሰምና ወርቅ በተዋበ ተረትና ምሳሌ እንዲህ እያሉ ትውልድን ያስተምሩ ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንድ የጅብ ልጅ ሞተና ሰማዩ ገና የአህያ ሆድ ሳይመስል አህያ መርዶውን ተረዳች፡፡ የራሷ ልጆች ሲሞቱ አፏን ተእንክርዳድ ተክላ ድምጥ የማታሰማዋ አህያ፤ ድፍን አህዮች ያለድብዳብ ቅርቀብ እየተጫኑ ጀርባቸው ምልጥልጥ ሲል “እኔ ተሞትኩ ሰርዶ አይብቀል”ን እየተረተች መስኳን “ቡርፍ ቡርፍ” እያደረገች ስትግጥ የኖረች አህያ፤ የራሷን ታፋ ጅብ እንደ ቡሄ ዳቦ እየከፈለ ሲገምጠው እንኳ ድምጥ የማታሰማ አህያ የጅብ ውርንጭላ ሞተ ስትባል ቀበሌው እስቲናጋና አገር ድብልቅልቁ እስቲወጣ “ኡ ኡ ኡኡ!” የሚል ጩኸቷን ለቀቀች፡፡ ይኸንን ጩኸት የሰሙ የሰፈሩ አህዮች “ምን ጉድ መጣ” እያሉ ተምትጮኽበት መስክ እንደደረሱ “ለቅሶ መድረስ የምትፈልጉ ተከተሉኝ!” ብላ ጋማዋን እንደ ነጠላ ዘቅዝቃና ፊቷን በወፍጥ ድንጋይ ነጭታ ልታስቀብር ወደ ጅቦች መንደር ነጎደች፡፡
አህዮ ተጅቦች መንደር ስትደርስና የጅብ ሐዘንተኞች የቆዳ በርኖሳቸውን ለብሰው ምድሩን አጣበውት ስታይ የሐዘን ሲቃ መንፈሷን በረዘውና ዛር እንደሚያስጎራው ተላይ ዘላ እየወደቀች መንከባለል ጀመረች፡፡ ይኸንን ያዩ ሐዘንተኛ ጅቦች ልቅሷቸውን አቋረጠው በአግራሞት ሲመለከቷት ጭራሽ ባሰባትና ጅቦችን ለመምሰል “አው እውውይ! አውውይይ!” እያለች ልቅሶዋን ለቀቀች፡፡
ስትመኘው የነበረውን ትኩረት ተጅቦች ያገኘችው አህያ፣ ለአህዮች ደንታ ሳይኖራት ለሌሎች እንሰሳት ወንፊት ልትጥድ የምትደርሰዋ አለማቀፋዊቱ አህያ የበለጠ የሐዘን ሲቃ ገፋፋትና እንዲህ ስትል የለቅሶ ሚሾዋን አወረደች፡፡
“ምን እሩቅ ቢጮኹ ቅርብ ነው ድምጥዎ፣
ምን ጥቁር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ፣
አሁን የእርስዎን ልጅ ምን አገኘብዎ፡፡”
ይኸንን ሚሾዋን ስታወርድ ተከትለዋት የሄዱት አህዮችም እየዘለሉና እየነጠሩ አዳመቁ፡፡ የጅብ አዘንተኞች ግን አይናቸውን እንደ ጉርጥ ማጉረጥረጥ ጀመሩ፡፡ አይናቸውን አጉረጥርጠው ይመለከቱ ከነበሩት ጠብል ጅቦች አንዱ በምራቁ ላንቃውን ወለወለና “አሁን እንዲህ ብለሽ ይኸን የተረትሽ፤ የጅብ ሐዘንተኛ ምን ይብላ ብለሽ” ብሎ የመልስ ምቱን ሳይጨርስ የግድድሞሽ ንግግሩ ለአህያዋ ገባትና “አህያም ይሩጥ ጅብም ይዘርጥ!” ብላ የምታመልጠበትን መንገድ ማሰላሰል ጀመረች፡፡ ዳሩ ግን አህያዋ የምትወጣበትን መንገድ ስታሰላስልና ስታመነታ ከመቅጽበት በጅቦች የሰላ አቀንጣጤ ታርዳ ለጅብ ሐዘንተኛ ንፍሮ ተቀቀለች፡፡
ህሊና፣ ማተብና ሃይማኖት ለሌለው ጅብ የሚያሸረግድ መጨረሻው የዚች አለሁ ባይ አህያ እጣ ፈንታ ነው፡፡ ከማይታወቅበት አገር ሄዶ “ቆርበት አንጥፉልኝ” ተሚል ጅብ፤ ሽምግልናን፣ ፍርድን፣ ኑዛዜን፣ ንስሀንና ሱባኤን ተማያውቅ ጅብ ስምምነንት፣ እርቅና ወዳጅነት ለማፍራት የሚንፈራገጥ መጨረሻው የዚች አህያ እጣ ፈንታ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ ሰባት ዓ.ም.