ዋዜማ- በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን፣ የጥቅምት ወር ደምወዝ አልተከፈለንም ያሉ መምህራን፣ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ስር ባሉ በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጥቅምምት ወር ደምወዝ አልተከፈለንም ያሉ መምህራን ሥራ ማቆማቸውንና ተማሪዎቻቸውን መበተናቸውን ዋዜማ ሰምታለች።
ለአብነትም በወረዳው መንደፈራ፣ ዞብል፣ አረቋቲ፣ አዲስ ቅኝ፣ ቀዩ ዳሪያና ጎለሻን በመሳሰሉ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ መምህራን የጥቅምት ወር ደምወዝ እንዳልተከፈላቸው ዋዜማ ተረድታለች።
ከከተማ ራቅ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር ትምህርት ካቆሙ ቆይተዋል ሲሉ መምህራኑ አስረድተዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው መምህራን እንዳሉት ከአንድ ወር በፊት በወረዳው ቀዩ ዳሪያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙንና ትምህርት ቤቱ መውደሙን አስታውሰዋል።
በዚሁ ምክንያት የድሮን ጥቃቱ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እያሉ ዳግም ቢፈጸም ኃላፊነት የሚወስድ አካል የለም በሚል ስጋት መምህራን ተማሪዎቻቸውን መበተናቸው የተነገረ ሲሆን፣ መንግሥት በበኩሉ ትምህርት እስካልጀመራችሁ ድረስ ደምወዝ አልከፍልም ማለቱን መምህራኑ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት መምህራኑ ወደ ትምህርት ቤት ሄደው እንዳያስተምሩ የተለያዩ ዛቻና ማስፈራሪያዎችን እንደሚያደርሱባቸው ያስረዱ ሲሆን በመንግሥት በኩል ደግሞ ወደ ሥራ እንድንገባ ከፍተኛ ጫና ይደረግብናል ብለዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ ያሉ መምህራን የጥቅምት ወር ደምወዝ እንዳልተከፈላቸው ያስረዱ ሲሆን፣ ደምወዝ ይከፈለን ብለው የጠየቁ በርካታ ርዕሳነ መምህራንና መምህራን ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ጊምቢቹ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ መምህራንም በተመሳሳይ የጥቅምት ወር ደመወዝ እስካሁን እንዳልተከፈላቸው በዚህም ምክንያት ማስተማር ማቆማቸውንና ተማሪዎቻቸውን መበተናቸውን አስረድተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከፋ ዞን ጎባ ወረዳ እንዲሁ መምህራን ለልማት በሚል ሰበብ በየጊዜው የወር ደመወዛቸው እየተቆረጠባቸው በመሆኑ በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ለዋዜማ የተናገሩ ሲሆን፣ ሆኖም ምንም መፍትሄ አለማግኘታቸውን አንስተዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት ወቅቱን የሚመጥን ደመወዝ ለመምህራን እንዲከፈል እና መንግሥት በደመወዛቸው ላይ የጣለውን ከፍተኛ የሥራ ግብር እንዲቀነስ አጠንክረው ለመጠየቅ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም መምህራኑ ለዋዜማ ተናግረዋል።