ከአልማዝ አሸናፊ
Imzzassefa5@gmail.com
Wyoming, USA
ሕይወት በሦስት የጊዜ ክፍሎች ትከፈላለች: ያለፈው፣ ያለውና (የአሁንና) የሚሆነው (የወደፊቱ/መጭው) ናቸው። ካለፈው ድርጊቶችና ሁኔታዎች በመማር በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ድርጊት በማድረግ ጥሩ ሁኔታዎችን ለማግኘት : ካለው ወይም ከአሁኑ ደግሞ ተምረን የወደፊቱና ወይም መጭው እጅግ ያማረና ያመረቀነ ኑሮ ለመኖር እንዲቻል ነው::
ሆኖም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ዕጣ በደመናው ውስጥ ትንሽ የብርሃን ጨረር ይታያቸውና የተሻለ ቀን ይመጣል ሲባል ደመናው ጉም እየሆነ የበለጠ እየጨለመና ተስፋ ሚያስቆርጥ ጊዜ እየሆነባቸው መጥቷል:: የዛሬዎቹ ካለፉት ስህተቶች ተምረው ዛሬን የተሻለ በማድረግ ለመጪው ጊዜ አምራቂ ሁኔታዎችን ያወርሳሉ ተብለው ሲጠበቁ : እንዳለፉት በስህተት ውስጥ እየወደቁ በመንከባለል የኢትዮጵያ ፖለቲካ አመድ ከመልበስ ሊጠራ አልቻለም::
የፖለቲካው ቲያትር አርእስትና ጭብጥ መልእክቱ በጊዜ ተገድቦ ተመርምሮ ተፈትሾ ተፈትኖ ያለፈው ተገምግሞ የሚያስተምረው ውጤቱ ታይቶ የሚተረክ ሳይሆን የፖለቲካው ቲያትር ተጫዋቾችና ደጋፊ ተዋናዮች መቀያየር ነው:: ሰፊው ሕዝብም እነዚህ የፖለቲካ ተጫዋቾችና ደጋፊ ተዋናዮች ያቀረቡትን ቲያትር በፍርሃት መመልከት እንጂ ቲያትሩ አልጣመኝም ብሎ የመተቸት መብቱ መገፈፉን ጥንቅቅ አድርጎ ስላወቀ የቀረበለትን ቲያትር በትዝብት ማየት ግድ ይለዋል:;
መረሳት የሌለበት ቲያትር አዘጋጅዎቾና ተዋናዮች የራሳቸው ቲያትር ተራኪዎችና ተችዎች መሆን አይችሉም:: ልታረምና ሊሆኑ ይችላሉ:: ይህም የሚሆነው ለሰው ልጅ ሃሳቢነት : ሰብአዊነት : ለእውነት መቆምና መልካምነትን በልባቸውና በሂሊናቸው የተጎናፀፉ ከሆኑ ነው:: እውነተኛና የተሻለ ቲያትር ደራሲ አቀነባባሪና ተዋናይ መሆን የሚፈልግ በቅድሚያ ተመልካቾች የሚፈልጉትና የሚጥማቸው ምንድነው ብሎ ማሰብና መገናዘብ ይኖርበታል:: የትያትሩን ማራኪነት ጥሩነት ወይም ተቃራኒ መሆኑን የሚገመግሙትና የሚዳኙት የቲያትሩ ተመልካች ሰፊው ሕዝብ መሆኑን ውጤታማ መሆን የሚፈልግ ቲያትረኛ መረዳት ይችላል:: በዚያ መሰረት ቲያትሩን ያዘጋጃል:: ትያትሩ አልጣመኝም ብሎ ሰፊው ሕዝብ ሲያጉረመርም የቲያትሩ ደራሲዎች አቀነባባሪዎችና ተዋናዮች ተመልካቾችን በግድ ቲያትራችንን ማየት አለብህ ብሎ ማስፈራራትና ማስገደድ ለቲያትሩም ሆነ ለደራሲዎቹ አቀነባሪዎቹና ተዋናዮቹ ዘለቄታ አይፈጥርም::
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቲያትር ባለፈውም ሆነ በአሁን ጊዜ የሚፃፈው የሚቀነባበረውና የሚተወነው ሰፊውን ሕዝብ ተመልካች ግንዛቤ ውስጥ በመክተት ሳይሆን በፖለቲካው ቲያትር ሠራተኞች ፍላጎትና እሽት ላይ የተመሠረተ ብቻ ነው:: ሰፊውን ተመልካች ሕዝብ ፍላጎትና ስሜት የማይካትት የፖለቲካ ቲያትር ጨዋታ የቲያትሩን ደራሲዎች እቀነባባሪዎችና ተዋናዮች ለጊዜው ያኖራል ያስደስታል እንጂ እነሱንም እንዲሻሻሉና ጥልቀት ያለው እድገት አያመጣላቸውም:: ስራቸውም ተቀባይነት ኖሮት የወደፊት የስራቸው ወራሾችን አይፈጥርም:: አያዳብርም:: ያለፉትን እነሱ አንኳሰው ሂስና ትችት እንዳቀረቡባቸውና የተሻለ ቲያትር እነሰራለን ብለው ተመልካች ሰፊ ሕዝብ እንዳጡ : በዚያው ሁኔታ ያሁኑ ቲያትራቸው እንዳለ ከቀጠለ መጭው ቲያትረኛም በተረኝነት ስሜት ውስጥ የሚዘፈቅ እኔ አውቅልሃለሁና የማቀርብልህን ቲያትር ሳታጉረመርም ዝም ብለህ ተመልከት የሚል ተረኛ እንጂ የቲያትሩ አስቀጣይ ወራሽ እንዳልሆነ መገመት አያቅትም::
ያለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ያሳየን የፖለቲካ ቲያትር በዋሻ ውስጥ እንዳለ ብርሃን ነው:: በዋሻው ውስጥ የምናየው ብርሃን (LIGHT IN THE TUNNEL) በዋሻው መውጫ በር የገባ ሳይሆን ከዋሻው አናት ባለች ትንሽ ጉድጏድ ፀሃይ ቀጥታ በጉድጏዱትክክል ስታልፍ ብልጭ ያለች ጮራ ነች:: ምክንያቱም ዋሻው መውጫ በሩ ተደፍኖ የሚጠበቀው ብርሃን ድምድም ብሎ ጠፍቷል:: የቋጠርነውም ተስፋም በተቀደደ ከረጢት ውስጥ ነው:: ቲያትሩም የሚታየውና የሚጨበጨብለት የቲያትሩ ቤት ጠባቂዎችን ቁጣና ግልምጫ በመፍራት እንጂ ሰፊው ተመልካች ቲያትሩ ጥሞትና አስደስቶት እንዳልሆነ ባለቲያትሮቹም ይገነዘቡታል::
አሁን ያሉት የፓለቲካው ቲያትር ደራሲዎችና : መሪ ተወናዋዮች : ያለፉትን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቲያትር ደራሲዎችንና መሪ ተዋናዮችን : ጥሩ ቲያትሮች አልፃፉም ትወናቸውም የማይጥሙ ናቸው ብለው እንደወነጀሏቸው እነሱም እንዳይወነጀሉ : ፈጣሪ ልቦና ሰጥቷቸው ለሰፊው ተመልካች ሕዝብ እስካሁን የሚያቀርቧቸው ቲያትር ድርሰቶች ካለፉት የተሻሉ ካለመሆናቸውም ሌላ : አስከፊ መሆናቸውን ተረድተው ለሰፊው ተመልካች ሕዝብ የተሻለ የሚጠቅምና የሚያስደስት ቲያትር አዘጋጅተው ቢያቀርቡ ሕዝቡም የተሻሻለውን ቲያትርና ትወና በድጋፍ ጭብጨባ ይቀበለዋል የሚል ግምት ይኖራል:: ቲያትር ያለሰፊ ሕዝብ ተመልካችና ተቀባይነት አያምርም:: ሰፊውን ሕዝብ የሚያስደስትና ደጋግሞ ለማየት የሚፈልገውን ቲያትር ማዘጋጀትና ማቀነባበር ለቲያትር ቤቱም ሞቅታና ለቲያትረኞቹ ዘለቄታ ያመጣል::
ትያትሩ በሕዝብ ተቀባይነቱና እሰየው የሚያሰኘው : ድርሰቱ በአገር ደረጃ ካየነው የሰፊው ሕዝብን : በቲያትር ተመልካችነት ክተረጎምነው : የታዳሚውን ፍላጎትና ስሜት አቃፊ ነው ወይ ብለን በመጠየቅ : የምናገኝው ምላሽ ነው:: ደራሲው (በአገር ደረጃ : የአገር መሪ) የሚፅፈው ቲያትር (አገር አስተዳደር) : የሚፃፈው ለታዳሚዎች (ለሕዝብ) እንጂ ለተዋናኞች (ለመንግስት ባለስልጣናትና ከበድን ላልተሻሉ የፓርላማ አሻንጉሊቶች) ከሆነ : ደራሲውና ቲያትሩ በታዳሚዎች (በአገር ደረጃ በሕዝቡ) ተቀባይነት አይኖራቸውም::
ይህንን ሃቅ መገንዘብ የማይችል ቲያትር ደራሲና (በአገር ደረጃ የአገር መሪ) ድርሰቱ (በአገር ደረጃ የመንግስት አመራር) በታዳሚዎች (በአገር ደረጃ በሕዝብ) ተቀባይነት ካላገኘ ውድቀቱን ገምቶ እንዴት ልሻሻል ማለት ይገባዋል:: ግን ተስፋ የተጣለበት የአቢይ አህመድ መንግስት : ከመንግስቱ ኃይለማሪያም የደርግ አስተዳደርና የጎሳ ፖለቲካን ለ27 ዓመታት ዘርግቶ የ3000 ዓመት የነፃነት ታሪኳን ገፎ ዛሬ ኢትዮጵያን ለደረሰችበት የማንነት ጥያቄ ላይ የጣላትን የወያኔን ጎሰኛ አመራር የተካው የአብይ አህመድ አጭበርባሪ መንግስት : ከሱ አመራር በፊት የነበሩትን የደርግና የወያኔን መንግስታት : እንዴት የተሻሉ እንደነበሩ ዛሬ አብይ የሚመራት ኢትዮጵያ ትመሰክራለች:: ኢትዮጵያ ለ3000 ዓመታት ለቆየችበት ዘመናት ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ድርሻቸውን አበርክተዋል:: ግን ዛሬ ኢትዮጵያን እንመራለን የሚለው በኦሮሞ ስም የሚነግደው የአብይ አህመድ ስግብግብና ጎሰኛ መንግስት ኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን ከተቀረው ኢትዮጵያውያን ከማለያየት በስተቀር : ለኦሮሞ ተወላጅ የሚያመጣው ጥቅም የለም:: ይህ መንግስት እስካለ ኢትዮጵያ በፊት የነበራትን ክብርና ሞገስ እንደማይኖራት የተረጋግጠ መሆኑን አብይ አህመድ ለመረዳት የአስተሳሰብ አቅም እንደሌለው በየዕለቱ እያስመስከረ ነው:: የኦሮሞን ጎሳኝነት የበላይ አድርጎ ከ82 ጎሳዎች በላይ ያላትን አገር አስተዳድራለሁ ብሎ ማሰብ “ላም አለኝ በሰማይ: ወተቷንም አላይ::” የሚለውን ተረት ከማሰማት በስተቀር : ኢትዮጵያን ያንድ ጎሳ የበላይነት የማድረግ ችሎታ ማንም የቲያትር ደራሲ አይኖረውም:: ምክንያቱም እንደዚያ ዓይነት በጠባብ ጎሰኝነት ላይ የተመሰረተ ቲያትር : ተመልካችና አዳማጭ እንደሌለው : ለቲያትር ደራሲው (አብይ አህመድ) እና ለተወናዋዮቹ (ለአብይ እህመድ መንግስት ተወካዮች) እንደማይሰራ እንዲገነዘቡ ማድረግ እስፈላጊ ነው::
አብይ አህመድ በ2018 የደረሰውና ያቀነባበረው ቲያትር በእሱ መሪ ተወናዋይነትና ከየጎሳዎች የተመለመሉ ረዳት ተወናዋዮች ድጋፍ የተሰራው ትያትር : ካለፉት ቲያትሮች ለየት ባለ ስለተጫወቱት : ለመጀመሪያ ጊዜ በተመልካቾች ተቀባይነትን አግኝቶ አድናቆትን አትርፎ ነበር:: ብዙም ሳይቆዩ : ተመልካቾች የአጨዋወት ስልቱ ከበፊቶች ስልቶች ይለያል: ይሻሻላል ብሎ እየጠበቀ ሳለ : መሪ ተወናዋዩና ረዳቶቹ ያለፈውን ቲያትሮች አስመስለው ሲያቀርቡ : ተመልካቾቹም ቲያትሩን ማየትና ማድነቅ ቀርቶ ተወናዋዮቹን ለማየትም አሻፈረኝ እያለ ይገኛል:: ይህንን ቲያትር ለማየት እንቢ እያሉ ያሉትን የቲያትሩን ተመልካቾችን : ደራሲውም : አቀነባሪውም ሆነ ተወናዋዮቹ ፍፁም ሊረዱ አልቻሉም:: የማይረባና የረከሰ ትወናቸውን : ውደዱልን : ተቀበሉት : አጩብጭቡለት : ጥሩ ነው በሉ በማለት ተመልካቾቹን እያስጨነቁት ይገኛሉ:: ተመልካቾቹም ግፊቱ ስለመረራቸው : ይህንን አስከፊና አስቀያሚ ጎሳ ላይ የተመሰረተውን ቲያትር አናይልህም:: አናጨበጭብልህም:: እስቲ የምትሆነውን እናያለን በማለት ቲያትሩን ላለማየትና መሪ ተወናዋዩንም ሆነ ረዳት ተወናዋዮቹን ከቲያትሩ ለማስወጣት ተፋጧል:: ቲያትር መድረስ : ማቀነባበርና መተወን ይቻላል:: ተመልካችና ተቀባይ የሌለው ቲያትር : ቲያትር ሊመስል አይችልም:: ቲያትር ተመልካቾቹን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው:: ምክንያቱም ትክክለኛ ሰዎችን ዒላማ ለማድረግ : ፍላጎቶቻቸውን የሚያውቅና ፍላጎቶቻቸውን የሚናገር ይዘት ለመፍጠርና የቲያትሩን መልእክት ከተመልካቾች ጋር የሚስማማ መሆኑን ያረጋግጣል።
የዘመኑ የአብይ አህመድ ቲያትር ሲጀምር ታዳሚዎቹን አውቆ ነበር:: የታዳሚዎችን ፍላጎቶች ከማወቅ በተጨማሪ የቲያትሩ ይዘት ፍላጎታቸውን መናገር ጀምሮ ነበር::vመልእክቱም ተስማሚ መስሎ ነበር:: ግን ከቲያትሩ መግቢያ በስተቀር : የአብይ አህመድ ቲያትር ፍሬ ነገሩ ለታዳሚዎች የማይስማማ : ፍላጎታቸውን የናቀና መደምደሚያው የትያትሩን ውድቀት የሚያመጣ መሆኑን እያሳየን ነው:: ስለዚህ ጥሩ ቲያትር ፀሐፊ የተመልካቾቹን ፍላጎት የሚያውቅና የሚናገር በመሆን ለተመልካቾች የሚስማማ መልእክት ማቅረብ ይገባዋል:: ያማረና ያስደስታል ተብሎ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የአብይ አህመድ ቲያትር ተመልካቾችን እጅግ ተስፋ ከማስቆረጡም ሌላ ቲያትረኛውንና ቲያትሩን ላለማየትና ላለመስማት የሚያስወግዱበትን መንገድ እየፈለጉ ይገኛሉ::
አብይ አህመድም ቲያትሬንና ትወናዬን በግድ ካላያችሁ በማለት ከተመልካቾቹ ጋር ግብግብ ተያይዟል:: ለጊዜው ጠንካራ መስሎ ቢታይም : ከእሱ በፊት እንደነበሩት ቲያትር ደሪሲዎች : መሪ ተወናዋዮች : እቀነባባሪዎችና ረዳት ቲያትረኞች በቲያትራቸውና በትወናቸው ያልተማረኩ ተመልካቾች እንቅረው እንደተፏቸው ያለመገንዘቡ : አብይ አህመድ ምን ያህል በተሳተተ እምነት ውስጥ እየዋዠቀ እንዳለ ሊረዳ አልቻለም:: አጭበርባሪነቱ : ውሸታምነቱ : አስመሳይነቱ : አረመኔነቱ : ትላንትና የተናገረውን ረስቶ ዛሬ የትላንትናውን ተቃራኒ ሲናገር የማያፍር : ካለሱ አዋቂ እንደሌለ በማስብ ጤነኛ ባልሆነ ራሱን በማግነን ስሜት የሚሰቃይና የሾማቸውን ሰዎች እንደሰው የማያከብር ግብዝ ሰው መሆኑን ግልፅ አድርጎ ከማሳየቱ በፊት : የኢትዮጵያ ዘር እንጂ : የኦሮሞ የአማራ የትግራይ ወዘተ ዘር የለም በማለት ስለእንድነት : ስለአብሮ መኖር : የፃፈውን ቲያትርና ትወናን ሁላችንም እውነት መስሎን በያለንበት በውስጥና በውጭ መድረኮችና : በሬድዮም : በዩቱዪቡም : በቲቪም : በኦንላይንም በደስታ አይተን : እንዴት ዓይነት ግሩም የምንፈልገው የቲያትር ደራሲ :አቀነባባሪና መሪ ተወናዋይ በኢትዮጲያ ውስጥ ተፈጠረ? በማለት አደነቅነው:: መከራና ሃዘንን የሚፈጥሩ ብቻ ቲያትሮች ሲቀርቡለት የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብይ አህመድ የመተዋወቅያው ቲያትር የተደሰተው ሰፊው ተመልካች : ተስፋውን አጣጥሞ ሳይጨርስ : አብይ አህመድም ሰፊውን ተመልካች የሚያስለቅስና ለምን ተፈጠርኩ የሚያሰኘውን ቲያትር ማሳየት ጀመረ::
አገርን አገር የሚያሰኘው ሕዝብ ነው:: ሕዝብን አጥፍቶ አገር መገንባት አይቻልም:: ቅድሚያ ለሕዝብ ደህንነት መሰጠት ይገባል:: የሚደረሰው : የሚቀነባበረውና የሚተወነው ቲያትር ለሕዝብ ደስታ ማድረግ የቲያትሩ ዓላማ መሆን አለበት:: አለበለዚያ ደራሲውና ቲያትሩ ተመልካች አልባ ይሆናሉ:: ዛሬ አብይ አህመድና ቲያትሩ ያጋጠማቸው እንዲ አይነት ውድቀት ነው::
ፈጣሪ ለአገራችን ሰላም : ለሕዝባችን አንድነት : ለመሪዎች ሰብዓዊነት : እስተዋይነትና ርህራሄነት ይለግሳቸው::