የሚያሸንፈው ፋኖ ወይስ መንግስት?

Fano is the peopleተክሉ አባተ teklu.abate@gmail.com 

መቅድም

መንግስት በአማራ ክልል «ትጥቅ ለማስፈታት» የከፈተው ጦርነት ከሚጠብቀውና ከምንጠብቀው በላይ ገዝፎና ተወሳስቦ አግኝቶታል አግኝተነዋል። ጦርነቱ ተፋፍሞ ጎጃምን፣ ጎንደርን፣ ወሎንና ሸዋን በእምብርክክ እያስኬደ ነው። መንግስትም ድሮንን ጨምሮ ከባድ መሣሪያዎችን ሳይቀር ሥራ ላይ ቢያውልም የፋኖን ግስጋሴ መግታት አልቻለም። እንደታሰበው ባጭር ጊዜ ፋኖን ማሸነፍ ቀርቶ ጦርነቱ የመንግስትን ኅልውና ተገዳድሯል፣ የመከላከያን የሞራል ልእልናና ታማኝነትም ክፉኛ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል። የአማራ ክልላዊ መንግስት ተበትኗል። እንደገና የተዋቀረውም ቢሆን ከባህር ዳር መውጣት የማይችል፣ የመወሰንና የማስፈጸም፣ የመፈጸምም አቅም የሌለው ሁለት ክንፎቹ እንደተሰበሩበት ዳክዬ ግቢ ውስጥ ሲያጠቅስ የሚውል ሆኗል። አዲስ የተሾሙት ፕሬዚዳንትም ቀደም ብሎ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ የነበረውን ያህል ሥልጣን እንኳን የላቸውም። በመሆኑም የአማራ ብልጽግና ከፍተኛ የሞራል ስብራት ብቻ ሳይሆን ኅልውናውም ለመጠበቅ የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። በሌሎቹ የብልጽግና አቻዎቹ ዓይን ሳይቀር ንቀትና ውርደት ደርሶበታል። በአጠቃላይ ሲታይ የብልጽግና መንግስትና ፓርቲ ኅልውናቸው አደጋ ላይ እንደሆነ በሚገባይ የተገነዘቡ ይመስላሉ። በአሁኑ ጊዜ ትልቁና አንገብጋቢው ጥያቄ ጦርነቱን ማን እንደሚያሸንፍ መገመቱ ላይ ነው። ሁሉቱም አካላት ድሉ የየራሳቸው እንደሆነ ደጋግመው ይናገራሉ። በእርስዎ አተያይ የሚያሸንፈው ፋኖ ነው ወይስ መንግስት? እንዴት?

የዚች ክታብ ዋና ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጦርነቱን ዕለታዊ ክስተት ከመዘገብና በዚያም ስሜትን ከመጉዳት ተላቅቆ ታላቅ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ለማነሳሳት ነው። የጦርነቱን ፍጻሜ ቀድመን በመገመት እጅግ የተሻሉ አማራጮችን ማውጠንጠን እንደሚገባን ይህች ጽሑፍ ለማስገንዘብ ትሞክራለች። አንዱን አካል ደግፎ ሌላኛውን መንቀፍ የጽሑፏ ዓላማ አይደለም። በአሁኑ ጊዜ እየተካሄዱ ያሉ ክስተቶችን በማያዳላ መልኩ በመፈተሽ ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሚበጅ አዋጭ መንገድ ትጠቁማለች። ማንም የተሻለ አተያይ ያለው ቢኖር ሀሳቡን በጥራትና በሓላፊነት እንዲያካፍል ታነሳሳለች። የክታቧ የመጀመሪያ ክፍል ጦርነቱን ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ባጭሩ አትታለች። ቀጥሎም አሸናፊው ማንም ይሁን ማን ሊመጣ ያለውን ከፍተኛ እልቂትና ውድመት በማንሳት ታስጠነቅቃለች። የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ሊመጣ ካለው እልቂትና ውድመት ሊታደግ የሚችል አማራጭ መንገድ እንዳለ ጠቁማለች።

ለመሆኑ ጦርነቱን የሚያሸንፈው ማን ሊሆን ይችላል? እዚህ ላይ ማሸነፍ ወይም ድል ከተፋላሚ ወገኖች እይታ መታየት አለበት። መንግስት ጦርነቱን ሲያውጅ ዓላማ አድርጎ ያስቀመጠው ቢኖር በአማራ ክልል ያለውን ልዩ ኃይል ትጥቅ በማስፈታት ሰላም ማስፈን ነው። ማስፈጸሚያ ስልት ተደርጎ የተቀመጠው ደግሞ ፋኖን በኃይል ጨርሶ ማጥፋት ነው። በአንጻሩ ደግሞ ፋኖ የሚዋጋው የአማራን ሕዝብ ኅልውና ለመታደግ ነው። ዋናው ስልት ደግሞ ነፍጥ አንስቶ መንግስትን መጣልና ሁሉንም በእኩልነት የምታይ ሀገር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን መገንባት ነው። ሁለቱም አካላት ያስቀመጧቸውን ዓላማዎች እንደሚያሳኩ ደጋግመው ያስረዳሉ። ነገር ግን ጉዳዩን ጠጋ ብለን ስንመረምረው የተለየ ምልከታ ሊኖረን ይችላል።

መንግስት ያሸንፋል?

ይህን ጥያቄ በሆነ ደረጃ ለመመለስ ከመንግስትና ከፋኖ አንጻር የሚታዩ አስቻይና ጨቋኝ ኩነቶችን ባጭሩ እንደሚከተለው እንመልከት።

 • መንግስት ጦርነቱን የጀመረበት ምክንያት ለብዙ ሰዎች አሳማኝ ካለመሆኑም ባሻገር ልዩ አጀንዳ እንዳለው ያሳብቅበታል
 • ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም የመከላከያ አባላት በአማራ ክልል የፈጸማቸው አሰቃቂ ግፎች (ለምሳሌ ንጹሐንን መግደል፣ መድፈር፣ አፍኖ መውሰድ፣ ንብረታቸውን መውሰድ) ወያኔ ከዓመት በፊት በዚሁ ክልል ከፈጸማቸው ግፎች ጋር ሊስተካከሉ ተቃርበውል
 • ምንም እንኳን ዘመናዊ ትጥቅ በአየርና በየብስ ማዝመት የቻለ ቢሆንም በዘላቂነት መዋጋት የሚያስችል የኢኮኖሚ፣ የሞራልና የሥነ ልቡና አቅም አይኖርም
 • የመንግስት ተቀባይነት በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል
 • ሌሎች ታጣቂዎችም ለምሳሌ ሸኔ መንግስትን ይበልጥ ያዳክሙታል
 • ሌሎች ብሶት ያለባቸው ክልሎች ለምሳሌ ሶማሌ፣ ጉራጌ፣ አፋር ወዘተ የፋኖን አጀንዳ ሊጋሩ ይችላሉ
 • ፋኖ በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለ ኃይል እንደሆነ ገልጿል። የሚፈራው፣ የሚያጣው፣ የሚያጓጓው ጉዳይ ስለሌለ ጦርነቱን ይቀጥልበታል
 • በአማራ ኢትዮጵያውያን ላይ የተደረጉት ግፎች እንዲሁም በታሪክ የተጻፉ ተመሳሳይ ክስተቶች ፋኖ የአርበኝነት ሥነ ልቡናውን ከፍ እንዲያደርግ አስችለውታል
 • መንግስት ለመቀበል ባይፈልግም በአማራ ክልል እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ፋኖ የሕዝብ ድጋፍ እያገኘ መጥቷል
 • በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ ይበልጥ ተደራጅተው ለፋኖ ደጀን ሆነዋል
 • በመሆኑም ለቅንጅት ፓርቲ ይባል እንደነበረው ፋኖ መንፈስ ሆኗል
 • ፋኖ የሚያሳየው የሞራል ልዕልና (ምርኮኛ ሰብአዊ በሆነ መልኩ ይይዛል፣ አይዘርፍም፣ አይደፍርም፣ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰላም ያስጠብቃል)የብዙዎችን ቀልብና አድናቆት ችሯል
 • ፋኖ ለጥቃት የማይመች አደረጃጀትና አሠራር አመራር አለው የተወሰኑት ቢሰውም ትግሉ አይቆምም
 • ፋኖ መልክአ ምድሩን እንደ እጁ መዳፍ ስለሚያውቀው መከላከያን ግራ አጋብቶታል
 • መከላከያ ካለው ትጥቅ ጋር ፈጽሞ የማይወዳደር ቢሆንም ፋኖ በተለያዩ መንገዶች ትጥቅ አካብቷል
 • የፋኖ ዓላማ እንደሚሳካ የአማራ መንግስትን፣ ብልጽግናን በመበታተን አሳይቷል

 

ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በሙሉ ወደፋኖ ያጋደሉ መልካም እድሎች ናቸው። በመሆኑም መንግስት ጦርነቱን ማሸነፍ አይችልም። መንግስት የሚደመስሰው ወይም የሚያሸንፈው የፋኖ መሪ ወይም ቡድን የለም። ፋኖ ሀሳብ ወይም መንፈስ ሆኗልና። ሀሳብን ማሸነፍ የሚቻለው ደግሞ በሀሳብ ብቻ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ፋኖ ያሸንፋል ብሎ ደፍሮ ለመናገርም አዳጋች ነው። እስካሁን እንደታየው የአማራን ክልል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደሚችል በተግባር አሳይቷል። በዚያም ክልል የራሱን አስተዳደር መመስረት ሊችል ይችል ይሆናል። ይህ ግን ፋኖ ከተነሳበት ዓላማ አኳያ ሲታይ አመርቂ አይሆንም። አማራ ክልልን ብቻ ይዞ የአማራን ኅልውና ማስቀጠልም ሆነ ሰላም ማስፈን ፈጽሞ አይቻልም። ግቡን የሚመታው የፌደራል መንግስት ሙሉ በሙሉ ሲሸነፍ ወይም ደግሞ በራሱ ፈቃድ ሥልጣን ለሕዝብ ሲመልስ ነው። የኢሕአዴግን እንዲሁም የብልጽግናን ተፈጥሯዊ ማንነትና ምንንነት ስንፈትሽ መንግስት ሁለተኛውን አማራጭ ይወስዳል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድ ነው። መንግስትን ሙሉ በሙሉ በኃይል ለማንበርከክ ደግሞ ከአባይ መልስ ያሉ የሌሎች ክልሎች ይሁንታና ትብብር ወሳኝነት አለው። ፋኖ የኦሮሚያን ክልል ተሻግሮ አራት ኪሎ ለመድረስ ቢያንስ ከመከላከያ ሙሉ ኃይል፣ ከኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አንዲሁም ከካድሬዎችና ባንዳዎች ጋር መፋለም ይኖርበታል። እነዚህን እስካችንጫቸው የታጠቁ አካላትን ጥሶ ወይም ደምሶስ ወደ አራት ኪሎ ለመገስገስ ከፍተኛ የሆነ ትጥቅ፣ የሰው ኃይልና አስተማማኝ ደጀን ይፈልጋል። በሂደትም ዘግናኝ የሆነ እልቂት፣ ውድመትና ማኅበራዊ ቀውስ ሊሰፍን ይችላል። ለዘመናት ሊቀጥል የሚችል የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ምንም ሆነ ምን የጦርነቱ ፍጻሜ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ትብብርና ይሁንታ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው።

ከላይ የታተቱትን ጉዳዮች ሁሉ ግምት ውስጥ ስናስገባ አንድ ግልጽ የሆነ ምናልባትም ለጊዜው ለመቀበል የሚያስቸግር መሪር እውነታ ከፊታችን ቆሞ እናየዋለን። በጦርነቱ ፍጹም የሆነ አሸናፊ አይኖርም። እርግጥ የሆነው ነገር ቢኖር መንግስት እንደማያሸንፍ ነው። የፋኖ አጀንዳ የማንኛውም ፍትሕ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አጀንዳ ሆኗልና። የአማራን፣ የትግራይን እንዲሁም በርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎችን መቆጣጠር የማይችል መንግስት እንዲሁም ከራሱ ግዛት የሌላ ሀገሮች ኃይሎችን ለማስወጣት ያልቻለ መንግስት እንዳለ አይቆጠርም። በአንጻሩ የፋኖ ድል እውን የሚሆነው በአማራ ክልል ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከፋኖ የኅልውና ጥያቄ አኳያ ሲታይ በቂ አይደለም። የፌደራል መንግስትን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አቅም ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ክልሎች ትብብርና ድጋፍም ይሁንታም ያስፈልጋል። የመንግስት መሸነፍም ሆነ የፋኖ ግማሽ ድል በከፍተኛ መስዋእትነትና ውድመት የሚመጡ ከመሆናቸውም በላይ የሀገራችንን የነገ እጣ ፋንታ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው። በመሆኑም ከዚህ ሁሉ ማጥ ሊያወጣ የሚችል የተሻለ መንገድ መፈለግ አለበት።

ከጦርነት የተሻለ አማራጭ አለ?

ሀገራችን ከገባችበት ማጥ ፈጥና ልትወጣ የምትችለው ሀሳብን መሠረት ባደረጉ አካሄዶች ብቻ ነው። ምክንያቱም መሠረታዊም የሀገራችን ችግር የሚመነጨው መሠረት ወይም ማስረጃ ከሌለው ሀሳብ ነውና። በመሆኑም ተኩስ አቁም ተደርጎ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ ውይይትና ድርድር መደረግ ይኖርበታል። ሂደቱን ፍጹም ተአማኒና ዘላቂ ለማድረግ ቀጥለው የተዘረዘሩት ነጥቦች ግን ግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል።

 • መከላከያ ከሁሉም የአማራ አካባቢዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለቅቆ ይውጣ
 • መከላከያ በአማራ ክልል በከፈተው ጦርነት የተነሳ የፈጸማቸውን ግፎች አምኖ ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቅ፣ ለተጎዱት ካሳና ፍትሕ ይሰጣቸው
 • በሕዝብ ብቻ የተሰየመ ጊዜያዊ አስተዳደር በአማራ ክልል ይመስረት
 • ባለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች በአማራዎችና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ላይ የተደረገውን ዘግናኝ ግድያ መንግስት ይመን፣ መከላከል ባለመቻሉም ይቅርታ ይጠይቅ፣ በጉልበተኞች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን መልሶ ያስፍር፣ የተዘረፈ ንብረታቸውን ያስመልስ
 • ሀገራችን ለገባችበት ማጥ ዋናው መነሻ ዘረኝነትን የሚሰብከው ሕገ መንግስት ስለሆነ እሱን የሚያሻሽል አካታችና አስታፊች ብሔራዊ ኮሚቴ ይቋቋም
 • አዲስ ሕገ መንግስት እስኪኖር ድረስ በዘር መደራጀት ፈጽሞ ይወገዝ፣
 • የሁሉንም ክልሎች ነጻነት የሚያጎናጽፍ እውነተኛ የፌደራል ሥርዓት ይመስረት
 • ሕገ መግስቱ በሕዝብ እስኪጸድቅ ድረስ መንግስት ማንኛውንም አይነት ዐብይ ሀገራዊ ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ መስጠት እንዳይችል መብቱን መገደብ
 • ሕገ መግስቱ በሕዝብ ከጸደቀ በኋላ ብሔራዊ ምርጫ ማካሄድ

ሲጠቃለል መንግስት የሚያሸንፈው የፋኖ መሪ ወይም ቡድን የለም። የፋኖ አጀንዳ ሊነቀል በማይችል መልኩ በሕዝቡ ውስጥ ተዘርቶ በቅሏል። ሕዝብን ማሸነፍ ደግሞ ፈጽሞ አይቻልም። መንግስት ይህን መሪር ሐቅ ውጦ እንደ መንግስት የተጣለበትን ሓላፊነት ይወጣ ዘንድ ብቸኛው መንገድ ነው። ነፍጥ አስቀምጦ ከላይ በተዘረዘሩትና መሳይ አጀንዳዎች ላይ መወያየት መጀመር ስልታዊነትና ለሀገር አርቆ አሳቢነት እንጅ ሽንፈት አይደለም። ጃንሆይ ኃይለ ሥላሴ ተመሳሳይ ኩነት ገጥሟቸው እድሉን ስላልተጠቀሙበት መጨረሻቸው የውርደት ሞት ሆነባቸው። መንግስቱ ኃይለ ማርያምም በመጨረሻዎች ዘመናት ተመሳሳይ ኩነት ገጥሟቸው እድሉን አባከኑት። ምርጥ ኢትዮጵያውያንን አስፈጅተው እሳቸው በስደት እስካሁ ኑሯቸውን ይገፋሉ። የብልጽግና ወላጅ አባት ኢሕአዴግም በሰላም መንገዱ አልተጓዘበትም። በአጉል ጀብደኝነቱ ሲኩራራ ስንቱን ሕዝብ ከጨረሰ በኋላ ራሱ ባሳደገው ልጅ ተገፍቶ ወድቋል። አሁን ደግሞ ኳሷ ተለግታ ብልጽግና ሜዳ ላይ አርፋለች። የብልጽግና አጥቂዎች ኩሷን መቼ፣ እንዴትና ወዴት እንደሚመቷት የመወሰን ሙሉ መብት አላቸው። ፈጥነው ካልመቷት ግን በተፎካካሪ ተጫዋች ይነጠቃሉ። ያኔ ኳሷም አትኖርም፣ ጨዋታውም ፈጽሞ ባልጠበቁት ሁኔታ ይጠናቀቃል።

ሰላም ለኢትዮጵያ!

1 Comment

 1. You*re indeed a very nasty monkey. Ur preaching is mainly to save the Bantustan apartheid Galla OLF and the savage Beja-Tigre Setttler’s TPLF. However, Amhara FANO gonna crush these house ” Negro” paid agents in Ethiopia.
  You better stop jabbering. FANO prevailes! OLF and TPLF will perish. Very soon Addis Ababa will be free from Galla barbarians lead by Fadcist Abiy Ahemeds’s fadcist regime.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Abiys dron
Previous Story

የአብይ አህመድና የቲያትሩ ውድቀት

image 11 1 1 1
Next Story

የበደኖና የአሰቦት ገዳማት የ1984 አሰቃቂ ጭፍጨፋ በደብረሊባኖስ ሊደገም ነው እንድረስላቸው

Go toTop