በምድራችን ካላፉት የሥርዓተ መንግሥታት ታሪክ ውስጥ በራሳቸው ሕዝብ መካከል ተቃርኖን እየሸመኑ አንዱን የማኅበረሰብ ክፍል ከሳሽ፣ ሌላኛውን ደግሞ ተከሳሽ የሚያደርግ ጥልፍ በመጎንጎን የሀገረ መንግሥትነት ሕልውናቸውን ያጸኑም ሆነ ዘላቂ ሰላምና እድገታቸውን ያረጋገጡ መንግሥታት ተብለው ለአብነት ያህል እንኳ ስማቸው የሚጠቀስ ነገሥታትም ሆኑ መንግሥታት የሉም።
እንዳለመታደል ሆኖ ከታሪክም ሆነ ከአሁናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ የአንድ ሀገር ሕዝብን በአንድነት እና እኩልነት ላይ በተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሕዝብና ሀገራቸውን ለመለወጥ ከመታተር ይልቅ፤ በየሚዲያው የጥላቻ ተረክን እየነዙ ፖለቲከኞች በፖለቲካ ገበያው ውስጥ ናኝተው ይታያሉ፡፡
መታወቅ ያለበት ሃቅ የትላንት መጥፎ ታሪክ ጠበቃዎች አይደለንም። ልንሆንም አንችልም። ሁኖም ግን ታሪክ ትምህርት ቤት መሆኑን እናምናለን። የትላንት ታሪካችንም ቢሆን መጥፎ ብቻ አይደለም። መጥፎ ታሪክ ካለም ለመጥፎ ታሪኩ ጠበቃ የመሆን ፍላጎት የለንም። ይልቁንም የትናንትናውን መጥፎ ታሪክ ላለመድገም እንጥራለን አብዛኛውን በጎውን የጋራ ታሪካችንን ደግሞ አሻሽለን ትውልድን ለመጥቀም እንተጋለን። ነገር ግን የትላንት የታሪክ ምርኮኞች ሆነን ህዝባችንን ለፖለቲካ በሽታ የማጋለጥ ፍላጎቱም ትልሙም የለንም። አላማችንም አይደለም።
ይሁን እንጅ አሁን አሁን የትላንት ታሪክ ምርኮኛ ፖለቲከኞች ታሪክን እያዛቡ በማመንዠክ ዛሬያችንን ስለነገው ተስፋችን ከመሥራት ይልቅ ስለትላንቱ ተረከ-ታሪክ እሰጥ-አገባ መቆም የትውልዳችን ወትሯዊ ውሎ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
የትላንት ታሪክ ምርኮኛዎች ትናንትን ከዛሬ በዉል ለይቶ ወደ ነገ መሻገር ሲሳናቸዉ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ቁሞ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰብን ማመንዠክ ልዩ ክህሎትና መገለጫቸው እየሆነ መጥቷል፡፡
ጀንበር መሽቶ በጠባ ቁጥር ልብስና ወንበር እየቀየሩ በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ የሚረጩት መርዛማነቱ ከልብስና ወንበራቸው ጋር አብሮ ያልተቀየረ የከፋፋይነት እርካሽ ፖለቲካዊ ብያኔና ፍረጃ የሀገርና የሕዝብን ሰላም፣ አብሮነት እና ልማት ምን ያህል እያቀነጨረው እንደሆነ ሊገነዘቡት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም፡፡
ይህን መሰሉ ፖለቲካዊ ግልሙትና በሕዝብ ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ ስሁት ትርክት እየነዙ ደም አፋሳሽ በሆነ መንገድ በሥልጣን ለመኖር ወይም ወደ ስልጣን ለመምጣት ቅጽበታዊ እድል ለማግኘት ካልጠቀመ በስተቀር ለሀገር አንድነትና ሕልውና ፋይዳ ቢስ ስለመሆኑ ከሥርዓተ መንግሥታትና ከነገሥታቱ ታሪክም ሆነ ከዘመናዊው የፖለቲካ ሳይንስ አስተምህሮት መማር ይቻላል፡፡
በዚህ ወቅት በሰፊ ሀገርና በታላቅ ሕዝብ ውስጥ እየኖሩ የጠበበ ግላዊና ቡድናዊ የጥቅም ፍላጎትን የሕዝብ አስመስሎ በማቅረብ፣ በጥላቻ ላይ ተመስርቶ ፤ ስሁት ትርክትን ተደግፎ ግጭት እየዘሩ፤ መከራን ኮትኩተው ሞት እያሳጨዱ ቡድናዊ ጥቅሜን አስቀጥላለሁ ብሎ ማመን ከትናንቱ ታሪክና ከነገው ተስፋ ጋር ተጻራሪ መሆንን ከማስረገጡ ባሻገር ዛሬን በሕይወት የመኖር ጸጋን ለመንፈግ የፖለቲካ ቁማር ቋሚ ሰልፈኝነትን ያስረዳል፡፡
ይህን መሰሉ አሰላለፍ የአፍታ ተዝናኖት ይሰጥ ካልሆነ በቀር የጀንበር ማብቂያ ያህል እድሜ ያለው ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ሕልውነትን አይሰጥም፡፡ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ያደረ ጥያቄ እና ያልበረደ ፍላጎት ያለውን ሕዝብ እየመሩና ለመምራት እየሻቱ በተቃራኒው የሴራ ፖለቲካ እየሸመኑ፤ ዘረኝነትን እያቦኩ መኖር የሚቻልበት እድልም ጊዜም የለንም፡፡
ለዘመናት ተዋዶና ተዋህዶ በፍቅርና በአንድነት፣ በብሔርና በጎሳ ሳይከፋፈል፣ በቋንቋና ባህል ልዩነት ሳይለያይ፣ ብዙኅነቱን ተቀብሎ ለዘመናት ክብሩንና ታሪኩን ጠብቆ የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የትላንት ታሪክ ምርኮኞች የሚከውኗቸውን ኢትዮጵያውያንን በቋንቋ እና በዘር የሚከፋፍሉና ሕዝባችን ውስጥ ቅራኔና ጥላቻ የሚፈጥሩ ንግግሮችንና ተግባራትን እንደ አንድ ሕዝብ አምርሮ ሊቃወም፣ ሊታገልና ከውስጡ ሊያገላቸው ይገባል፡፡
ይህ ወቅት መላው ኢትዮጵያዊ እንደ አንድ ልብ ተባብሮ የታሪክ ምርኮኞችን መታገል የሚያስፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ እየሆነ መጥቷል። ሞቅ ቀዝቀዝ በሚል የትግል ሂደት ጠማማ የታሪክ ምርኮኞችና ቅን ልቦና የተሳናቸው የፖለቲካ ቆማሪዎች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ የጋረጡትን አደጋ ማስቀረት የሚቻለው ለእውነትና መርህ በመገዛት መታገል ሲቻል ነው።
ስለሆነም የእስካሁኑ የትግል ስልትና አካሄድ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ፣ ተጠያቂነት ያለው ህዝባችንን ያማከለ፣ በመልካም ዓላማ ሀገር ግንባታን ማዕከል ያደረገ፣ ወጥነት ያለው፣ የሀሳብና ዴሞክራሲያዊ ፍትሐዊ ትግል ማድረግ የሁላችንም የሁል ግዜ መደበኛ ሥራ ሊሆን ግድ ይላል።
በትላንት የታሪክ ምርኮኞችና በነገው ተስፋችን ቁማርተኞች ሕልውናዋን የማታጣ፤ በጠንካራ የሕዝብ አንድነትና እኩልነት ላይ የፀና ሀገረ መንግሥት ለማቆም መረባረብ ከሁላችንም የሚጠበቅ ሃላፊነት ነው፡፡
የምናልመው ለውጥና ስኬትም ሆነ የሕዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች በምኞትና በፍላጎት ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ አለመሆናቸው ታውቆ ሁሉም ዜጋ ችግሮቻችንን ውጫዊ በማድረግ የሆነን አካል ብቻ እንዲፈታ ከመጠበቅ ወጥቶ፤ የበኩሉን ድርሻ በማድረግና በመተጋገዝ ተደማምጦ በአንድነት ለለውጥና ስኬት በመታገል ተስፋና ለጋ ውጤቶቻችንን በማዝለቅ እንደ ሕዝብ ለገጠመን ፈተና ደግሞ የጋራ መፍትሔ እያበጁ መሄድ ይገባል። አማራጩም ይሄው ነው!!
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
514
\