የግዙፉ የአሜሪካ የአይሮፕልን መገጣጠሚይ እና ሻጭ ፣ቦይንግ ከባንያ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ዴኒስ ሙይሉንበርግ በኢትዮጵያ እና በኡንዶኔዢያ አየር መንገዶች ላይ በደረሰው አደጋ ሳቢይ ከደረሰባቸው ውስጣዊ እና ውጫዊ ግፊቶች ሳቢያ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ።
ባለፈው ጥቅምት ወር በኢንዶኔዢያ የጃቫ ባህር ላይ ተከስክሶ ለ189 ተሳፍሪዎች መሞት ምክንያት የሆነው በተመሳሳሳይ ሁኔታ ባለፈው መጋቢት ወር ከአ/አ ወደ ናይሮቢ፣ ኬንያ የአይሮፕላኑ ሰራተኞችን ጨምሮ ከሰላሳ አምስት አገራት የመጡ 157 ሰዋችን አሳፍሮ ደብር ዘይት (ቢሾፍቱ) ላይ የተከሰከሰው የቦይንግ ዘመናዊ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን መዘዙ ዛሬም ድረስ የተጎጂዎች ቤተሰቦችን ለብርቱ ሀዘን፣ ኩባንያውን ደግሞ ለከፍተኛ ትችት እና ቀውስ ዳርጎታል።
ላለፉት አስራ አራት ወራት ከአሜሪካ የበረራ ቁጥጥር ባለስልጣን መ/ቤት ፣ከኮንግረስ አባላት እና ከሟቾች ቤተሰቦች ከፍተኛ ወቀሳ እና የካሳ ጥያቄዎች የተደቀነበት ፣ የ 737 ማክስ አውሮፕላን የምርት አገልግሎቱንም ሰሞኑን ሙሉ በሙሉ ያቋረጠው፣ የቦይንግ ኩባንያ ቦርድ ውብ ሀላፊው የ55 አመቱ ዴኒስን እሁድ እለት ስልጣን እንዲለቁ ሲስማማ ሀላፊው በባዶ እጃቸው እንዲሸኙ አልነበረም።
“በኩባንያ ውስጥ የአመራር ድፍረት ለማስላጥ” ሲባል ከሀላፊነት የተነሱት የቀድሞው የቦይንግ ስራ አስኪያጁ ዴኒስ በጥሬ ገንዘብ ወደ ሀያ ስድስት ሚሊዮን ዶላር፣ በአመት ደግሞ በግምት ወደ ስምንት መቶ ሺህ ዶላር የሚጠጋ ጡረታ ያገኛሉ።ከዚህም በኩባንያ ውስጥ ወደ አስራ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሽርክና ይኖራቸዋል። ባጠቃላይ የኩባንያው የመጪው ሶስት አመት የትርፍ ሂደት ታይቶ ዴኒስ ወደ ሀምሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ንግድ ነክ የአሜሪካ ጋዜጦች በትላንትናው እለት ዘግበዋል።
ባለፈው መጋቢት 10,2019 እኤአ በኢትዮጵያው ቦይንግ እፕውሮፕላን በረራ ቁጥር 302 ተሳፍረው ከውጥናቸው ሳይርሱ ከቀሩት መካከል የሀያ አራት አመቷ ሳማያ ወላጅ አባት የሆኑት ሚካኤል ስተሞ” የዴኒስ መባረር አንድ እርምጃ ፣ሲሆን ኩባንያውን ለኪሳራ እና ለትች የዳረጉ ፣በአንድ አመት ውስጥ የሶስት መቶ አርባ ስድስት ተሳፋሪዎች ህይወት እንዲቀጠፍ ያደረጉ የቦይንግ ከፍተኛ ሹማምንቶች መባረር አለባቸው”ሲሉ እኤእ ከ2015 ጀምሮ ቦይንግን የመሩት የዴኒስ ስልጣን መልቀቅን በአውንታዊ ጎኑ ተመልክተውታል። ቦይንግ እስከ አሁን ድረስ ከ112 ሟቾች ቤተሰቤች 114 የክስ ፋይሎች በቺካጎ ፍ/ቤት ተከፍቶበታል።
(በታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)