የብልፅግናችንን ፀሮች ሥውር ሤራ ሳይረፍድብን በመገንዘብ   ፍትህን ካላነገሥን በሥተቀር ፣ ነገ ከሞጣ የከፋ ቀራኒዮ ያጋጥመናል (ከትህዳ ኃሣኤ)

በአፍሪካ በጭላንጭል የማይታየው የቋንቋ አምልኮ “ጥቁር አፍሪካዊ በሆነቾው ” በኢትዮጵያ እጅግ ገዝፎ ይታያል። እንዲህ ገዝፎ መታየት የጀመረውም ከ1983 ዓ/ም በኋላ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ አይነት ነጣጣይ እና ከፋፋይ የሆነ የቋንቋ አምልኮን ፣በህገ መንግሥት አሣጅበው የሥርዓተ መንግሥቱ ምሰሶ እንዲሆን ያደረጉት ሺ ዓመት ለመንገሥ ያሰቡት ጥቂት የህወሓት  ሰዎች ናቸው።
      እነዚህ የህወሓት  ሰዎች ዓለም ወደአንድነት በመምጣት ህዝቦችን በኢኮኖሚ ካላሥተሳሰረች መጥፋቷን ፈፅሞ ያልተገነዘቡ በ15 ኛው ክ/ዘ አሥተሳሰብ ሀገር የሚመሩ ነበሩ።
  እጅግ በሚያሳዝን እና በሚያናድድ መልኩ ሰው ልጅ በበህል ሥም ሁሌም እንደነበረ እና እንደቀደመው ትውልድ ራቁቱን እንዲኖር ያበረታቱ ነበር።  በብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት  ሥም  በድህነት ሰበብ ራቁታቸውን የሚሄዱ ዛሬም ራቁታቸውን እንዲሄዱ የሚያበረታቱ ነበሩ። ሆኖም በተግባር ሥናሥተውለው፣ እነሱ ዘመናዊ እና የቅንጡ ኑሮ ነበር የሚኖሩት።
     በሚያሣዝን መልኩ ግን፣ የትግራይ አርሶ አደርን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ምንዱባን፣”በሴፍቲ ኔት “ታቅፎ   በምግብ ለሥራ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት መሰቃየቱን ቢያውቁም ይህንን ሥቃይ መሥምያ ጆሮ እና መመልከቻ አይን አልነበራቸውም ።
      ለእነሱ የሚታያቸው የግል ብልፅግና እንጂ የጋራ ብልፅግና ባለመሆኑ ፣አንድነትን  ፣ፍቅርን፣ ሰላምን ፣መቻቻልን፣እኩልነትን፣ሰብዓዊነትን፣ርህራሄን ለጥቅም አጋሮቻቸው ካልሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይመኙም ነበር። ።በመሆኑም እንዳይበለፅግ ድህነቱ አብሮት እንዲቀጥል እነዚህን የብልፅግና መሠረቶች አሳጥተውት፣በማይታይ የብሔር ብሔረሰብ አጥር ውሥጥ አሥረውት ነበር።
   ለመበልፀግ ህብረት ያሥፈልጋል።ለመበልፀግ መተሳሰብ ያሥፈልጋል።ለመበልፀግ ህወሓት ኢህአዴግ ብሔር ብሔረሰቦች ብሎ የገነባውን   የቋንቋ  አጥር ማፍረሥ ያሥፈልጋል።ግንቡንም አፍርሶ ሰው ሰው እና የአንድ ሀገር ባለቤት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ ያሥፈልጋል።
     ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የብሔር ብሔረሰቦች እሥር ቤትነት ሥትላቀቅ ነው ብልፅግና እውን የሚሆነው። አሁን ባለው የአሥተዳደር ሥርአት፣ብሔር ብሔረሰቦች ከክልላቸው እንዳይሻገሩ አጥር ታጥሮባቸዋል።ታሥረዋል። መላው የኢትዮጵያ ሰው በዜግነቱ ብቻ ተከብሮ ፣ያለ ገደብ   እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ከተራ ሥራ ጀምሮ መሥራት አይችልም።በተለይም በፊደራል ዩኒቨርስቲዎች በየዓመቱ የሚመረቀው ወጣት እንደእርጉም ራሱን የሚቆጥረው በዚህ የቋንቋ አጥር ምክንያት ነው።
           ዜጎች፣  ኦሮምኛ ፣አማርኛ ፣ሱማሊኛ ፣ኡፋርኛ፣ ሲዳምኛ፣ወላይትኛ፣ከንባታኛ፣ኃድይኛ፣ከፍኛ፣ጋሞኛ፣ዶርዝኛ፣ጉራጊኛ፣ቅማንትኛ ፣አገውኛ ወዘተ። ተናጋሪዎች ፣ትግሪኛ ተናጋሪው የሚኖርበት አካባቢ የእነሱም ሀገር መሆኑን አውቀው እንዳሻቸው ወጣ ገባ የሚሉበት።የሚኖሩበት።ሀብት የሚያፈሩበት። ሲሆን ነው።
     ከ86 በላይ የሆነ ቋንቋን የሚናገሩ ዜጎች  በሀገሪቱ በሞላ ተንቀሳቅሰው የመሥራትና ሀብት የማፍረት መብት በፓለቲከኞች አሻጥር፣ደባና ሤራ ሊገደብ ከቶም  አይገባም።
  በኢትዮጵያ ከ86 በላይ ቋንቋዎች እንዳሉ ቢረጋገጥም   አሻጥር፣ደባና እና የዘረፋ ሤራ በመኖሩ፣ ከሰማኒያ ሥድሥቱ ውሥጥ ቋንቋቸውን አግዝፈው የሌሎቹን አኮስሰው  የሚያዩ ምሁራን ይህንን የመነጣጠል፣ ሤራ ፣ከህወሓት  ጋር እጅና ጓንት ሆነው ለትግበራው፣ሐሰተኛ ትርክቶችን በመፍጠር ህዝብ ለህዝብ እንዲቃቃር አያሌ ሴራ ጎንጉነዋል።ዛሬም ከመጎንጎን አላባሩም።
   ህወሓትም ሆነች እበላባይ ምሁራኑ ፣ሲታገሉ የነበሩት ለቋንቋዎች እኩልነት ሳይሆን ለዘላቂ ብዝበዛቸው እንደሆነ የምናረጋግጠው ከኦሮምኛ፣አማርኛ፣ትግሪኛ በቀር ሌሎች 83 ቋንቋዎች ድምፅ አልባ ማድረጋቸውን ሥንረዳ ነው።
  ሲጀመር  ለምን እንዲህ ኢ-ፋትሃዊ እና በአለም የሌለ የቋንቋ ፊደራሊዝም በኢትዮጵያ ብቻ ተግባራዊ ተደረገ?  ብለን ብንጠይቅ ፣መልሱን ከደርግ ውድቀት እና ከህወሓት  ትንሳኤ ውስጥ እናገኘዋለን።
   ደርግ ወድቆ ህወሓት በትንሣኤ  አዲስ አበባ መግባቷን ስታረጋግጥ ፣ ንግሥናዋን የሚያጅቡ የብሔር ድርጅቶች ለመፍጠር አቀደች።ኦነግ ተገዳዳሪዋ እና በቀላሉ የማይተኛላት ባላንጣዋ መሆኑን ታውቃለችና በዙፋኖ ተረጋግታ ለመቀመጥ ፣ አምሳያውን በወጉ መፀነሥ እና ህያው አድርጎ መውለድ ያሥፈልጋል። ሥትል አሰበች።እናም የኦነግ ሃሳብን ሁሉ የያዘ  ኦነግን በቁሙ የሚቀብር ድርጅት አዋለደች። (  ከእውቁ ደራሲ ሮበርት ሉድለም  ” ዘ ቦርን አይደንትቲ ” ልብወለድ  መፅሀፍ ኮርጃ)  ኦህዴድን ፈጠረች።ማለት ይቀላል። መፅሐፉ እንደሚለው—ካርሎሥን ለማጥፋት ተመሣሣይ ካርሎሥን ትፈጥራለህ።ተመሣሣይ ድርጊትም በኮፒው ካርሎስ አማካኝነት ትፈጽማለህ።የዛን ጊዜ እውነተኛው ካርሎስ “ዘራፍ!! በሥሜ አይነገድም!” ብሎ ከምሽጉ ብቅ ሲል ግንባሩን ብለህ ወደመቃብር ትከተዋለህ—
    ህወሃት  የአማራ ተወካይን  በዚህ ዓይነት ጥበብ  አልፈጠረችም። ልትፈጥርም አትችልም ነበር።ምክንያቱም አማራ እንደ ኢትዮጵያ አንድነት ተምሳሌት እና እንደ ገዢ መደብ ይቆጠር ሥለነበር ነው። (ነፍጠኛ የተባለው ለዚህ ነው።ሆኖም ኢትዮጵያን በሥልጣን ተዋረድ ሁሉም  ነፍጥ አንግቦ ሲመራ እንደነበር ታሪክ ይመሠክራል። ሁሉም ሥል ትግሪኛ ተናጋሪውን ጨምሮ አማርኛ፣ኦሮምኛ ወዘተ ተናጋሪውን ጨምሮ ይብዛም ይነሥ  ባለነፍጥ እና ሥልጣን የነበራቸው ነበሩ።)  ደሞም የአማራ ነፃ አውጪ ድርጅት የሚባል ሥላልነበረ በአማራ ሥም ማደራጀት ከባድ ነበር።በዛን ወቅት  አማረ በክርስቲያንእነቱ እንጂ እንደ አንድ ዘር ራሱን አግሎ የሚመለከት ሥላልነበረ በቋንቋ ሥም ማደራጀት አዋጪ አልነበረም።ከዚህ ባሥ ሢል፣ አማራ  ማለት በግልፅ፣በእውነት እና በልበሙሉነት  ኢትዮጵያ ማለት ነበር።
     በነገራችን ላይ ይህ የትግሬ፣የኦሮሞ፣የኦጋዴን ወዘተ።ነፃ አውጫ አደረጃጀት ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው አደረጃጀት ነው።ወያኔ፣ሻቢያ፣ኦብነግም ሆነ ኦነግ ከጥንስሳቸው ጀምሮ በፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ሢመሩ ፣በትጥቅ እና ሥንቅ ሢደገፉ እንደነበር ይታወቃል። ዛሬም “የኢትዮጵያ ብልፅግና የእኛ ውድቀት ነው። “የሚል ፍፁም ሥህተት የሆነ አሥተሳሰብ ያላቸው የውጪ ኃይሎች መገልገያ ናቸው።በእኔ ድምዳሜ በነፃ አውጪ ሥም የተደራጀ ሁሉ የኢትዮጵያን ብልፅግናን የማይሻ፣ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሌም ሞት ከሚደግሥለት የውጪ ጠላት ጋር አባሪ እና ተባባሪ ነው።
      ህዝቡ ተጋብቶ እና ተዋልዱ በአንድነት እየኖረ የሚበለፅግበትን እና ትውልዱም የሰው እጅ የማያይበትን ወደ ከፍታ ወሳጅ መንገድ ሢሻ ፣ ሁሌም ሊያቆረቁዙት የሚፈልጉ ከውጪ ጠላቶቻችን ጋራ ለጥቅማቸው ሢሉ ያበሩ እነዚህ በነፃ አውጪ ሥም የተደራጁቱ ናቸው።
    እነዚህ የመገንጠል አቀንቃኝ ፓርቲዎች፣ ፀረ አንድነት፣ፀረ ፍቅር፣ፀረ ህብረት ከመሆናቸውም በላይ፣የኢትዮጵያን ጠላቶች  ራእይ የሰነቁ እንጂ የራሳቸው ራእይ የሌላቸው ናቸው።በመሆናቸውም በሆድ አደርነታቸው በሚያገኙት ረብጣ ዶላር በመታገዝ፣ንቃተ ህሊናቸውና ኑሯቸው ዝቅ ያለውን እየመረጡ በመሥበክ እና በገንዘብ እና በተሥፋ በመደለለ፣ የቋንቋ ፖለቲካውን አጥብቀው እንዲይዙ በማድረግ ፣ ቋንቋን በማዋደድ ያለማቋረጥ ንትርክ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። እንዲጋጩ ና እንዲገዳደሉም በየአይነቱ መሣሪያ በግልፅና በሥውር ያቀብላሉ። …
   ይህንን እውነት ህወሓት  ሥለምታውቅ፣ኦህዴድን በመፍጠር ኦነግን ማክሰም አዋጪነቱን ብትገነዘብም  “የአማራ ነፃ አውጪ ቅብርጥስዮ ” ብላ ፖርቲ ማቋቋም በወቅቱ በሣል እና ቋቅ  የነበሩትን  ከኢህአፓ ተገንጥለው በርሃ የቀሩትን   ጠንካራ አመራሮች በአንድ ጎራ ማሰለፍ የሞኝ ድርጊት ከመሆኑም በላይ፣ እራሥን ማሥበላት ነው። ብላ በሆዷ በማሰብ፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ኢህዴን ) የሚባል የኢህአፓን ምትክ መሰረተች።…
    እናም አሜሪካኖቹ  መንጌን  በሲአይ ኤ አማካኝነት ዙምባቡዌ    በወዳጁ በፕሬዚዳንት ሙጋቤ(…) እንክብካቤ ተንቀባሮ  በቅንጦት እንደሚቀመጥ አሳምነው በዘዴ ከወንበሩ አወረዱት። ለወንበሩ ሰሞነኛ ባለሥልጣን የነበሩት እነ ተሥፋዬ ገ/ኪዳንም የኢጣሊያን ኢምባሲ ዋሥትና ሰጣቸው።…
    ድራማው በዚህ መልኩ በልብ አንጠልጣይነት ቀጥሎ፣የወያኔም ሆነ የኢትዮጵያ እግረኛ ሰራዊት ጠመንጃውን በትከሻው ተሸክሞ አዲሥ አበባ ገባ።በተዝናኖትም ልብሱን አጥቦ ቤተመንግሥቱ አጥር ላይ አሰጣ እንጂ ፈርቶ በክላሸ እና በታንክ ዙሪያውን አላጠረም። መንገዱም ሥልጣኑም ጨረቅ ነበር የሆነለት …
    ከጥቂት ቀናቶች በኋላም  ጉባኤ ተደረገ።የሽግግር መንግሥት ተቋቋመ።1983 መለሥ  ዜናዊ ፕሬዝዳንት ሆኑ። ታምራት ላይኔ  ጠ/ሚ  ሆኑ። 1985  ጠቅላይ ሚኒሥቴር መለሥ ሆኑ ታምራት በሙሥና ሥም  ከርቸሌ ገባ  ። በነገራችን ላይ፣ሥንት ከእርሱ የበለጠ ሞላጫ እያለ ‘ ኮ ነው! “ሥኳር አታለለው።”የተባለው።እርሱም በክላሽ ፊት አልዋሽም ሢል በራሱ ላይ ሥኳር አታለለኝ ብሎ የመሰከረው።
     ታሪክ ቀጠለ። እንደምታሥታውሱት ነጋሶ፣ፕሬዝዳንት ሆኑ። እንደምታውቁት  የፕሬዝዳንቱ  ወንበር የጠቅላዩን ያህል ጉልበት ባይኖረውም ከዓለም ጋር የሚያገናኝና የሚያመካክር ሥለነበር ዶክተሩ መለሥን እና የአምባገነን መንገዱን ተቃወሙ።መለሥን    ከመንግሥቱ ጋር አመሳሥለው “አንዳንዴ ሣሥተውልህ መንጌን ትመሥላለህ ” በማለት በድፍረት  በመናገራቸው ገነት ዘውዴ እንዴት ከመንጌ ጋር መሌን አመሳሰልከው… ?”ብላ አለቀሰች ተባላ።ተባለ ነው።ልብ በሉ።ከዛስ ነጋሶ(…) የፈረሙበት ህገ መንግሥት ፀደቀ።ህዳር 29/1987። እናም ጮቤ ተረገጠ።በእርግጥም ህገመንግሥቱ ውሥጥ ያሉ አንዳንድ አንቀፆች ከግል ምኞት እና ከሥጋዊ ጥቅም አንፃር፣  ጮቤ የሚያሥረግጡ ነበሩ።ለምሳሌ አንቀፅ 39 ፣46-2፣47-2፣(በ70፣80፣በ90 ውስጥ ያሉ አንቀፆችም ማሻሻያ የሚያሥፈልጋቸው … ።ቃላቶቻቸው፣የአርፍተ ነገር ትርጉማቸው ሁሉ ሊፈተሽ፣ሊታረምና ሊሥተካከል የሚገባ ነው፣ይላሉ የህግ እና የህገ መንግሥት ምሁራኑ)።
  በበኩሌ እንደግለሰብ፣ ህገ መንግሥቱ ቋንቋን በአንቀፅ 46-2 ላይ አግዝፎ በማሥቀመጥ ክልሎችን ለማዋቀር መጠቀሚያ ማድረጉ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።በዓለም የሚኖር ሰው ሁሉ በሰውነቱ አፍቅሮ ተጋብቶ ህብረት ፈጥሮ መኖር እየቻለ፣በአንድ ሀገር ላይ የቋንቋ አጥር አጥሮ ይኽ  አካባቢ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ ነው።ማለት ዜግነትን ገደል የሚከት ነው።እናም ይህ የአከላለል ሥርአት ከህገ መንግሥቱ መውጣት እና ጆግራፊያዊ እና የአካባቢውን ህዝብ አሰሠፋፈር ከአሥተዳደራዊ ተደራሽነት አኳያ ያገናዘበ መሆን አለበት።  ቋንቋን አሥታኳ በላይህ ላይ ካልነገሥኩብህ በዚህ በ21ኛው ክ/ዘ አይሰራም።
     ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የቀበሌያቸውን ፣የወረዳቸውን፣የአውራጃቸውን የክልሎቻቸውን አሥተዳዳሪዎች የመምረጥ እና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው፣የመማር፣እና አሥተዳደራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አላቸው።በየከተሞች ያሉትም ድብልቅ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሆኖም የከተማ ህበርነት በአንድ ቋንቋ እንዲጠቀሙ በሌላ አባባል የፊደራሉን የሥራ ቋንቋ እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው ፣በእየአንዳንዱ ከተማ የአባት እና የእናታቸውን ቋንቋ ሳይጠየቁ በሚያግባባቸው የከተማው ሰው ሁሉ ቋንቋ በሆነው፣ቋንቋ  ሊሥተዳደሩ።ከንቲባቸውን ሊመርጡ እና ሊመረጡ ይገባል።ዴሞክራሲ የአብላጫው ህዝብ አመራር የሚከበርበት፣ የአናሳው መብትም ከብዙሃኑ እኩል የሚከበርበት  ሥርአት ነውና እንደአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብት በእኩል ደረጃ መከበር አለበት።
  ይሁን እንጂ ፣በኢትዮጵያ እጅግ  የበዙ   የቋንቋ አምላኪ ምሁራን የሀገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ተቆጣጥረው ቋንቋ፣ቋንቋ እያሉ  ቀንና ሌሊት ሲጮሁና ፣በቋንቋ ሥም ዴሞክራሲን ጨፍልቀው እየተደላቀቁ በመኖር በዜጎች ላይ ሲንዘባነኑ  እናሥተውላለን።
    እንዲህ የእናታቸውን ወይም የአሳዳጊያችን ቋንቋ ብቻ ሰማይ እንዲሠቅሉ ፣ ሌላውን ቋንቋ አኮሥምነው እንዲያዩ፣ ያደረጋቸው የጥቅም ጉዳይ እንደሆነ ብገነዘብም ፣ በዚህ በሥልጣኔ በመጠቀ  21ኛው ክ/ዘ  ፣ ዛሬም እንደ 19ኛው ና 20ኛው ክ/ዘ  ኢትዮጵያን “በሥዩመ ጠመንጃ”መግዛት አይቻልም።
   ዛሬ፣በዚህ 21ኛው ክ/ዘ ሆኖ ብቻዬን አድጋለሁ ማለትም ዘበት ነው።ዕድገትና ብልፅግና በተሥፋፋ ቁጥር ከተሜነት እየተሥፋፋ መሄዱ እርግጥ ነው።በዛን ጊዜ ደግሞ ሁሉንም ሰው የሚያግባባው ቋንቋ የሁሉም ከተሜ ቋንቋ ይሆናል።እናም በመጪው ዘመን አማርኛ የመላው ኢትዮጵያዊያን ቋንቋ ይሆናል።ተብሎ ይገመታል። አማርኛን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ቢያውቀው ምንችግር አለው?ችግር የለውም ።ሃሳብህን ፣ደስታናሐዘንህን፤ወዘተ።በመግለፅ ከሀገርህ ልጅ ጋር ታወጋበታለህ።በቃ።ይኸው ነው።እንግሊዘኛ፣ፈረንሳይኛ ሥታውቅ ደግሞ አለማቀፋዊ ግንኙነትህ ይሰፋል።ወንዝ ተሻግረህ ለመሄድ ይመችሃል።በሶሻል ሚዲያ ተፃፅፈህ፣ጓደኛ አፍርተህ ፓሪሥ፣እና አውሮፓን ቤትህ ታደርጋለህ።ወላ ትዳር መሥርተህ በጋብቻ ልትዛመድ ትችላለህ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በቋንቋዬ ላይ አትድረሱ የሚል አጥር ያጠረ ፖለቲካ ነው ያለው።( ለማሥተማር እንኮ ዝግጁነት የሌለው።)
   አማርኛ፣  በማህበራዊ ኑሮ አሥገዳጅነት፣የትላላቅ ከተሞቻችን  ፣የማህበራዊ ግንኙነት እና የከተማ ግብይት መግባብያ ቋንቋ በመሆኑ ከአፍ መፍቻ ቋንቋችን የእናት ቋንቋችን እኩል ብናውቀውም ፣ጥቂት የማንባል ጎምቱ ምሁራን ቋንቋውን በጠላትነት ፈርጀን ሌሎች ንቃተ ህሊናቸው ያልዳበረ ወንድምና እህቶቻችን ቋንቋውን በጠላትነት እንዲፈርጁት የቋንቋ ፈንጂ በመቅበር ፣በክልሌ ለመሥራት በቅድሚያ ቋንቋዬን እወቅ እንላለን።ይህንን የቋንቋ አፓርታይድ የፈጠርነው ህዝብና ህዝብ እንዳይዋሃዱ ፣ከአንድነት ይልቅ መለያየትን እንዲፈልጉ ነው።ይሁን እንጂ ኑሮ ከፓለቲካው በላይ ነውና በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ልዩ፣ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ተዋልደው ይኖራሉ።እነዚህን የተዋለዱ ሚሊዮኖች ለመለያየት እንዴት ይቻላል?አይቻልም።ደብረዘይትም ሆነ ናዝሬት ህዝቡ የቋንቋ አፓርታይድን በፅኑ የተቃወመው ለዚህ ነው።
     አመንም አላመንም ህወሓት  ኢህአዴግ ሲያሥተዳድረን  የነበረው በቋንቋ አፓርታይድ ከፋፍለህ ግዛ በተሰኘ ዘረኛ ሥርአት ነበር። ይህንንም ከንቱ እና የከንቱ ከንቱ ሥርአት፣  የሚደግፉት በቋንቋ እውቀት ብቻ ምንም ሳይሆኑ ምንም የሆኑ ዜጎች ብቻ ነበሩ። በ1983  ዓ/ም በየክልሉ ያሉ ጥቂት ምንዱባኖች እና ንዑሥ ከበርቴ አፈጮሌዎች በድንገት እጃቸው ላይ የወደቀውን ከመሬት አንሥቶ ንጉሥ የሚያደርግ የፈላጭ ቆራጭነት ወንበርን አይገባኝም።አላሉም።እንደ ተሥፋዬ ገ/አብ በሙሉጌታ ሉሌ ወንበር ላይ በመቀመጥ በሥልጣን አረቄ ሰከሩ እንጂ ። (የተሥፋዬ  ገ/አብን የጋዜጠኛው ማሥታወሻ መፅሐፍ አንብብ።)
    በእርግጥ ለሆዳቸው ብለው ከሆድ ባልዘለለ   ምክንያት ሥልጣንን በምስጋና መቀበላቸው ብዙም የሚያሥኮንናቸው ባይሆንም ዛሬ ላይ መጠቀሚያ መሆናቸው የሚቆጫቸው ጥቂቶች አይደሉም። የህወሓት  ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ መሆኑን ተገንዝበው የድርሻቸውን ይዘው፣ጎመን በጤና በማለት ከመድረኩ በዘዴ የወረዱም አሉ። ዛሬ ላይ ሆነው፣ሲያሥቡት ያለአዋቂነታቸው እና ደደብነታቸው ያናድዳቸዋል።
     ” በቆዳ ማዋደድድ እና መናናቅ ተጠፍረን ነው እንጂ  ሁላችንም የአማርኛ ቋንቋ እየተነጋገርን የሚያባላን ከቶም አንድም ምክንያት አይኖርም ነበር።  እንዴት ሰው አማርኛን  ከአፍመፍቻ  ቋንቋው በላይ አውቆት በመራቀቅ ቅኔ እየተቀኘበት ቋንቋውን እና የቋንቋ ተናጋሪውን ይጠላል?ምንድነው የጥላቸው ሰበብ?ለዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ጥላቻ የዳረገው ማነው? …ሀድ ነው።ከርስ ነው።አልጠግብባይነቱ እና ሆዳምነቱ ብቻ።”  በማለትም በምሬት ይናገራሉ።
    እውነት ብለዋል። ልብ ካላችሁ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ የክልል መሥተዳድሮች የተለያየ ውይይት እና   ኮንፍራሥ ሲዘጋጅ   ቋንቋው አማርኛ ነው። በየሥብሰባው ፣አወንታዊ እና አሉታዊ ሃሳቦች ሲቀነቀኑ  በየቴሌቪዢን መሥኮቱ የምናየው በሬዲዮ የምንሰማው በአማርኛ ቋንቋ ነው።
     በዚህ ቋንቋ በሶሻል ሚዲያው አያሌ በጎ እና ክፉ ሃሳቦችም በየቀኑ ሲጎርፉበት እናሥተውላለን።ይህንን ሥናሥተውል የሰላማችን እጦት ሰበብ የቋንቋ ጉዳይ፣የእኩልነት ጉዳይ፣የሀይማኖት ጉዳይ ፣የክልልነት ጉዳይ ወይም ራሥን በራሥ የማሥተዳደር ጉዳይ እንዳልሆነ እንገነዘባለን።
   ጉዳዩ በማን አለብኝነት  ፍትህን አሽቀንጥሮ በመጣል፣ሰብዓዊ ክብርን በመድፈቅ፣ በቋንቋ አምልኮ ሥርአት እና በሀይማኖት ሥም ሀገር የማፍረሥ ጉዳይ ነው።ጉዳዩ ምንም ጠብ ባላለለት ህዝብ እያመካኙ፣ብዝበዛን የማሥቀጠል ፍላጎት በአንድ በኩል በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ብልፅግና የማይሹትን የውጪ ኃይሎች አጀንዳ የማሥፈፀም  ተልእኮ መሆኑን ዛሬ ካልተገነዘብን ነገ ከሞጣ የከፋ ቀራንዮ ይገጥመናል።
    እናም
“ሞጣ ቀራንዮ ምነው አይታረሥ
ደንበጫ ደብረወርቅ ምነው አይታረሥ
በሬ ሣላይ መጣው ከዛ እስከዚህ ድረሥ።”
የሚል  ቅኔ እንቀኛለን።ለእኛ እኮ ሞት ብርቃችን አይደለም።ዛሬም የሞት ድግሥ ደጋሾችን  ፈጣሪ አልነሣንም።…
ተጨማሪ ያንብቡ:  በደልን መላመድ ባርነት ነው! አሥራደው (ከካናዳ)

1 Comment

  1. ወገን ሆይ! የጻፍከው ነገር ሁሉ ትክክል ነው። ለዚህ ብቸኛ መፍትሄ ከምርጫው ውጤት ማግስት አሸናፊው ፓርቲ ስርነቀል ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለሁ። የኔ ምኞት የነ ብልጽግና ሆኖ በ ፩ አጀንዳ ላይ ሪፈረንደም መጥራት፣

    ፩) የህውሃትን ቱባ ባለስልጣናት (ከ ሀያ በታች በቁጥር) ለፍርድ ይቅረቡ ወይስ አይቅረቡ? ህዝቡ ይቅረቡ ካለ እያንዳንዳቸውን በግድም ይሁን በውድ ባሉበት ተዘምቶ ቀፍድዶ አምጥቶ ማሰር። ወይም የሰረቁት ታስቦላቸው ወደፈለጉት አገር መሸኘት። እነሱ ከዛች ምድር ካልጠፉ የዜግነት ፖለቲካ ባገራችን ይመጣል ማለት ዘበት ነው። ይቅር ብለናችሁዋል ብሎ ካገር መሸኘት ነው። ጥንት የሚመኩባት ሱዳን ታስተናግዳቸው። እነሱ የዘረጉት መዋቅር እንዲህ በቀላል የሚበተን አይደለም። ይህ ካልሆነ እውነትም እነርሱም እንደሚሉት የመቶ አመት ሆምዎርካቸውን ስናካፍልና ስናባዛ ልንኖረው ነው። ይህው ነው መፍትሄው። አቢይ ይቺን ዘዴ ዛሬ ጠፍቷቸው ሳይሆን ከላይ እስከታች የማይፈታ የተወሳሰበ ሰንሰለት ሆኖባቸው ይመስለኛል። በዛ ላይ የወዳጅ ጠላቶቻቸው ብዙ ናቸው። አሁን እንኳን ይመስገነውና አይምሮ እየገዙ ይመስላል ። አቢይ እንኳ ባይደፍሩት ያ ከማንም ያልተነካካው ቆፍጣና ሙስጠፌን የብልጽግናው ሀላፊ ቢያረጉት ይህን እርምጃ ይወስዳል ባይ ነኝ። ሌላው ምርጫ የዘረፉትን ገንዘብ ካስመለስን እርቃናቸውን ስለሚቀሩ በግዳቸው ይንበረከኩና ሰላም ይሰጡናል። ይህ ከሆነ ማሰርም አያስፈልግም። የህሊናቸው እስረኛ ሆነው እንዲሁ ኖረው ይጠፋሉ። እነሱ ሲጠፉ የነሱ ጃንጥላ ያዦች በሙሉ ይከስማሉ። እነ ጫሚሶን ልብ ይሏል። ኢትዮጵያ ዳግም ታብባለች። ሰው በዜግነቱ እንጂ በጎሳው የሚሉት ታሪክ ይሆንና ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ይህን ክፉ ሙከራ ዳግም በኢትዮጵያ ላይደገም ይማሩበታል። ይህ ምርጫ ግን ቸኮለ። በጭራሽ አይታየኝም። ከሆነም በሰላም አስጀምሮ ያስጨርስልን።

Comments are closed.

Share