የኢትዮጵያ የምጣኔ-ሐብት ማሻሻያ ምን ይዞ ይመጣል? – እሸቴ በቀለ(DW)

/

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ምን ያክል አገር በቀል ነው? መዋቅራዊ ችግር አለበት ለሚባለው ኤኮኖሚስ ምን ዓይነት መፍትሔ ይዞ ይመጣል? በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን ሊመጣ የሚችለውን የብር የመግዛት አቅም መዳከም እና የዋጋ መናር ኢትዮጵያ እንዴት ትቋቋማለች?

ኢትዮጵያ ለሶስት አመታት የሚዘልቀውን እና ባለሥልጣናቱ አገር በቀል የሚል ስያሜ የሰጡትን የኤኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ማድረግ ጀምራለች። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የምጣኔ-ሐብት ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚሰጠውን 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጽድቋል። ከብድሩ 308.4 ሚሊዮን ዶላር በአፋጣኝ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ የዓለም የገንዘብ ድርጅት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት አስር አመታት የድኅነት መጠንን የቀነሰ እና የዜጎቿን የአኗኗር ደረጃ የቀየረ ፈጣን ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እንደነበራት ያስታወሱት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ተቀዳሚ ምክትል የአስተዳደር ዳይሬክተር ዴቪድ ሊፕተን «መንግሥት መር የዕድገት ሥልት ከገደቡ ደርሷል» ብለዋል። ከዓለም የገንዘብ ድርጅት በተጨማሪ የዓለም ባንክ እና የልማት አጋሮች ለኢትዮጵያ ገንዘብ ሰጥተዋል።
በሶስቱ አመታት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋት፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ፤ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማጠናከር፤ የመንግሥትን ወጪ መንገድ ማቀላጠፍ የመሳሰሉ ለውጦች ተግባራዊ ይደረጋሉ።

እነዚህ ማሻሻያዎች የምርታማነት ችግር ላለበት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ምን ይፈይዳሉ? በውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚደረገው ለውጥ ከመሠረታዊ ሸቀጦች እስከ ግዙፍ ማሽኖች ከውጭ በሚሸምተው የኢትዮጵያ ገበያ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ያሳድራሉ? ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም፤  የቻይና አፍሪቃ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ እና ዴሎይት የተሰኘ የኦዲት እና ማማከር ሥራ ኩባንያ የምስራቅ አፍሪቃ አገሮች ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሲሳይን አወያይቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  (ሰበር ዜና) ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከሀገር እንዳይወጣ በኢሚግሬሽን ታገተ

ውይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

Share