የምንጠብቀው ሌላ፥ የሚሆነው ሌላ – ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ስለ ኢትዮጵያ በፍቅር ተነድፈን የምንጠብቀው አንድም ትንሳሄ (ተስፋ) ወይም መበታተን (ስጋት) ነው።  ግን ሁለቱም እየሆነ አይደለም።  ወደፊትም እነዚህ አይሆኑምና ከመንፈስ መዋዥቅ ለመውጣት ምናልባት ራሳችንን መርምረን የምንጠበቀውን ተስፋም ሆነ ስጋት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አስታርቀን የሚሆን የሚሆነው ላይ ማተኮር ይሻል ይሆን እላለሁ።

 

እንደ ባለ አዕምሮ ሲታይ በኢትዮጵያ ምድር እንኳን ምርጫ ማድረግ ቀርቶ፥ በሰላም አብሮ መኖር ያልተቻለበት፥ በመፈናቀል አንደኛ ደረጃ በመያዝ ዓለምን የምትመራ ሰላም የደፈረሰባት ምድር እንደሆነ ሁሉም ያውቃል።  የፖለቲካ ፓርቲ የተባሉትም ምንና ስለምን እንደሚቆሙ ውሉ የማይታወቅበትና መድረክ አግኝተው በማያስተዋውቁበት አሁን ወቅት ላይ ቆመው በማግስት ምርጫ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለው ማወጃቸው ይገርማል የሚል ያልገባው ብቻ ነው።  ግራ የሚገባን የምንጠብቀው ከሚሆነው ጋር ስለሚጋጭ ነው።

 

ዶ/ር አብይ መራሹ ፓርቲ (ግንባር) ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ (ማለትም ሶማሌ፥ ጋንቤላ ወዘተ ጨምሮ) አዲስ ስም ይዞ ብቅ ሊል በስራ ላይ መሆኑን ተነግሮናል።  ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎችም እየተደመሩ (እየተዋሃዱ) በተባባሪነት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ እያየን ነው።  ኢትዮጵያዊነት እና ዘረኝነት (እንደ ውሃና ዘይት መቀላቀል ባይችሉም) በምድረ ኢትዮጵያ በአብሮነት ታቅፈው እየተሰበኩ እዚህ ደርሰናል፥ ይቀጥላልም።  ሀገር ላይ ብሔራዊ መግባባት ይኑር እያልን በየቦታው የምንጮህ ሁሉ ዲሞክራሲ ኖሮ በመናገራችን ብቻ ረክተን መቀመጥ ሳይሻለን አይቀርም።

 

ምርጫው የዛሬ ዓመት እንዳሰቡት ይካሄዳል።  የዛሬ ዓመት አዲሱ ኢሕአዴግ ራሱን ለውጦና ሌላውን ውጦ ለምርጫ ያለ ሁነኛ አማራጭ ራሱን ለሕዝብ ያቀርባል።  ለዚያ ዓይነት ምርጫ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ እንቅፋት አይሆንም።  እኛ በባዶ ሜዳ የምንጨነቀው የሚሆነውን ሳይሆን የማይሆነውን እያሰበን ግራ ስለሚገባን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ - ትናንት እና ዛሬ !

 

ሕገ መንግስቱንም በውል ያወቅነው አይመስለኝም።  ጭራሽ ይጥፋና አዲስ ሕገ መንግስት እንፃፍ የምንልም ሆነ በሕጋዊ መንገድ በሂደት ይሻሻል ብለን የምንከራከረው አሁንም በባዶ ቦታ ነው።  ሁለቱም እንዳይሆን ተደርጎ ተቆልፎ ነው የተሰራው።  በሕጋዊ መንገድ ይሻሻል ቢባል፥ በተለመደው የማሻሻያ ሂደት ሳይሆን በልዩ ድንጋጌ እንዳይቻል ተደርጎ እንደተቀመመ የሚያውቅ ማን ነው? ጭራሽ ይጥፋና አዲስ ሕገ መንግስት እንፃፍ ቢባል፥ ለሶስት አስርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የተዘራው መርዝ ምን ያህል እንደቦረቦረን የሚያውቅ ማን ነው?  ከዚህ ሁሉ ወደ ብሔራዊ መግባባት መጥተን መውጫ መንገድ እንዳንፈልግ መካከለኛውንና የሚሆን የሚሆነውን ማየት ደግሞ እንደተሰወረብን የሚያውቅ ማን ነው?

 

እውቀቱ ጠፍቶን ሳይሆን፥ ከትንሳሄ ተስፋና ከመበታተን ስጋት እየዋዥቅን የምንላተመውና በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከምንጠብቀው ጋር የሚጋጨው፥ የኢትዮጵያ ፍቅር አሳውሮን ይሆን?  የኢትዮጵያ ነገር የሚፈታው ዛሬ ሳይሆን በትውልድ ዘልቆ ቢሆንስ?  ለዚያ ራሳችንን አዘጋጅተን፥ ለሚሆን ነገር ብንተልም ይበጅ ይሆንን? የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን ያስባታል።  ትዕግስት ይስጠን።

2 Comments

  1. Cheer up Dr. You are not alone. The strategy is that extremists in all sides are/will be cancelling each other. The [for now] creeping “moderate and democratic forces” with the support of the “silent majority” shall emerge winners in flying colors, and the madness will come to a halt. In your part make sure that you personally will not be dragged into one side of the aisle – it may feel tempting/compelling for the emotional mind, but not difficult for the rational, cool and level-headed mind.

    የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያን ያስባታል። ትዕግስት ይስጠን።
    Amen!!!!

  2. “የምንጠብቀው ሌላ፥ የሚሆነው ሌላ” What you are waiting for is the restoration of Amhara hegemony. To your disappointment, what is happening is creating a state of fairness and equality among ALL Ethiopians. That is why you are hallucinating all the time. Adios! Your ancien regime will NEVER come back. But you keep on dreaming my Brother.

Comments are closed.

Share