ኢትዮጵያኒዝም (Utopia ምድረ ገነት) የእኛ ፍትሀዊ መንግሥት – በገ/ክርስቶስ ዓባይ        

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ነሐሴ 15 ቀን 2011ዓ/ም

ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ማርክሲዝም ሌኒኒዝምም፤ ሊበራሊዝም ሆነ ኒዖሊበራሊዝም የአስተዳደር ፖሊሲ አይደለም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያኒዝም ወይም ዩቶጵያ በመባል የሚታወቀው አሁን ምዕራባዊያን እንደሚሉት ተምኔታዊ (እውን የማይሆን) ሳይሆን ጥንት ተግባራዊ የነበረ፤ አሁንም ቢሆን ቁርጠኝነት ያለው መሪ ካለ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል፤ ፍትሀዊ የአስተዳደር ዘይቤ ነው፤ (ሊበራሊዝምና የኒዖ ሊበራሊዝምን አስተሳሰብ በተመለከተ ወደፊት በዝርዝር እንመለስበታለን)። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን እስላምም ይሁኑ ክርስቲያን ፈሪሃ እግዚአብሔር አላቸው። ከገንዘብ በላይ ለሰው ልጅ ሕይወት ይጨነቃሉ።

በመሠረቱ የየትኛውም አገር መሪዎች፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትም ሆነ በሕይወት የሌሉት መሪዎች ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተለያዩ ሕዝብ የሚያማልሉ ‘ብትመርጡኝ እንዲህ፤ እንዲህ ያሉ በጎ ተግባራትን አደርግላችኋለሁ’ በማለት ምለው ተገዝተው ቃል ኪዳን ይገባሉ። የተወራው ሁሉ ተፈጻሚ እንደ እማይደረግ ጥርጣሬው ስላለ፤ ሕዝብም ለምርጫ ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከል በሚናገሩት ብቻ ሳይሆን የጀርባ ታሪካቸውን እና ቀደም ሲል ያከናወኗቸውን፤ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ተግባራት በማገናዘብ፤ ቅንነትና ተአማኒነት ያላቸውን ሰዎች በቡድንና በኅብረት በሚደረግ ውይይት መርምሮ፤ ውሳኔውን በምርጫ ካርዱ ያረጋግጣል

በጣም የሚያሳዝነውና የሚገርመው ደግሞ 99% በመቶ የሚሆኑ ፖለቲከኞች ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ቃላቸውን አክብረው ሲሠሩ አይታዩም። ልክ ሥልጣኑን በቁጥጥር ሥር ማድረጋቸውን እንዳረጋገጡ ሁሉንም ሽረው የራሳቸውን የግል አጀንዳ ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ መታየታቸው ነው። ሕዝብ የተሻለ መሪ አገኘን ብሎ አጨብጭቦ ድጋፉን ከሰጠ በኋላ፤ ወዲያው በነጻነት ፋንታ ወደ ባርነት ያጋደለ፤ የመሥራት፤የመጻፍ፤ የመናገርና እንደ ልብ፤ በነፃነት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶችን ሁሉ መገደብ ይጀምራሉ።

የእኛው ዶ/ር ዓቢይ አህመድ አንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ለሕዝብ የገቡት ቃል ኪዳን ከሰው አእምሮ ሳይጠፋ በተደጋጋሚ ክህደት በመፈጸማቸው፤ ከነበሩበት የክብር ኮረብታ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ቁልቁል እየወረዱ ናቸው። አይ የሰው ነገር! አሁንማ ሕዝቡ በሴራም፤በዘረፋም እየጠረጠራቸው በመሆኑ ‘ኅሊና ቢኖራቸው ሥልጣናቸውን ይለቁ ነበር’ በማለት እጁን አፉ ላይ ጭኖ በመገረም መንሾካሾክ ጀምሯል።

ሎሬት የትነበርሽ ንጉሤ እንዳሉት ፖለቲከኞች ሁሌም በቃላቸው አይገኙም። የሆነው ሆኖ ግን ሕዝብን ማታለል እግዚአብሔርን እንደ ማታለል ይቆጠራል፤ ‘በማን ላይ ቆመሽ …………..’ እንዲሉ። ምናልባት ጥቂት መሻሻል የሚታይባቸው፤ አንዳንድ መንግሥታት፤ አገሪቱ የተዋቀረችበትን ሕገ መንግሥት በማክበር ሠፊ ልምድ ባካበቱ፤ የሕግ የበላይነትን እንደ ባህል ባዳበሩ አገሮች፤ በአንፃራዊነት የተሻለ ተሞክሮ እንዳለ አንክድም። ይሁን እንጂ በእነዚህ አገሮችም ቢሆንም የአስተዳደር ሕጸፅ የለም ማለት አይደለም።

ሁሉም መሪዎች የያዙት ሥልጣንም ሆነ የሚያዙበትና የሚናዙበት ኃይልም፤ ወይም አጠቃላይ የአገሪቱ ሀብትና ንብረት፤ የግላቸው ሳይሆን የሕዝብ መሆኑን ይረሱታል። ከዚህም የተነሳ አንዱን ወገን ሲያቀርቡ ሌላውን ደግሞ እየገፈተሩ ሲያርቁ ይታያሉ። ለዕቅድ፤ ለፕሮግራም፤ ለበጀት፤ ለፕሮጀክት እያሉ ላይ ታች ሲሉ ሥራ የሠሩ ይመስላቸዋል። ምክንያቱም የአገሪቱን ሀብት በፍትሀዊነት ለሕዝብ እንዲዳረስ በማድረጉ በኩል የሚያዩበት ልቦናቸው ግን የተደናበረ፤ ዓይናቸው የተንሸዋረረ፤ስለሚሆን ነው። ይህ ብቻም አይደለም በአማካሪነት የሚመድቧቸው ሰዎች ከእነርሱ የተሻሉትን ስላልሆነ ‘ግም ለግም አብረህ አዝግም’ እንዲሉ ደካማዎችን በዙሪያቸው ያሰባስቡና ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ምክር አይለግሷቸውም። ስህተት እንኳ ሲሠሩ እያዩ ደፍረው ለማረም አይሞክሩም፤ ይልቁንም ትክክል እንደሆኑ አድርገው ድጋፋቸውን ስለሚሰጡ መሪዎቹ ወደ ባሰ ችግር ይገቡና ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ይጋጫሉ።

የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ በድፍረት የሚተቹትን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና፤ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ አክቲቪስቶችን፤ እንዲሁም የነፃ ፕሪስ ጋዜጠኞችን፤ የተለያዬ ታፔላ በመለጠፍ እያደኑ ማሠር ይጀምራሉ። እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ መንግሥት ተረጋግቶ መሥራት የሚገባውን እየተወ በእንዲህ ዓይነት እኩይ ተግባር ላይ በመጠመድ ወርቃማ ጊዜውን ያሳልፋል። በዚህ ዓይነቱ ፍጥጫ ወቅት መንግሥት በመዋቅር ደረጃ አምባገነን እየሆነ ስለሚሄድ ሕዝብ ይበደላል፤ ዕድገትም ፈጽሞ ይገታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከአሜሪካ መልስ - ከተስፋዬ ገ/አብ

የውጭ ቱሪስቶችም ሆነ የመዋዕለ ንዋይ ባለሀቶች እንደዚህ ያለ ‘እሰጥ አገባ’ ባለበት አገር ውስጥ ገንዘባቸውን ለማፍሰስና ኢንዱስትሪ ለማቋቋም አይደፍሩም። የውጭ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ለማስገባት ከመወሰናቸው በፊት የሚመለከቱት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ፤ በአገሪቱ፤ የሕዝብ መረጋጋትና የሰከነ መንግሥታዊ አስተዳደር መኖሩን ማረጋገጥ ስለሆነ ነው።

የብዙ መንግሥታት ችግር፤ ንፉግነትና ቅንነት የሌለው የአስተዳደር መርህን መከተል ሲሆን ሕዝብ ከእነርሱ የሚጠብቀውን ወይም የሚገባውን ፍትሀዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ስለማያሰፍኑ ነው። ምክንያቱም መሪዎቹ የሀብት ክፍፍል ጽንሰ ሐሳብ አንድም አልገባቸውም፤ ወይም እንዴት እንደሚተገብሩት ዘዴውን አልተረዱትም፤ አልያም እንዲሁ በጭፍን ንፉግነት ተተብትበዋል ማለት ይቻላል።

ቅንነትና ቁርጠኝነት ካለ ዘዴው እጅግ በጣም ቀላል ነው። በተለይ ወደ እኛዋ አገር ስንመጣ ጉዳዩን የበለጠ ቀላል ያደርገዋል። ሟቹ ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ ግን ሆነ ብለው የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ በችጋር ሲያሠቃዩ እንደነበር ለማንም የተሰወረ አይደለም። ይህንንኑ አስመልክቶ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ‘የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ፖሊሲ ቀርጾ በችጋር የሚጠብስ እንደእርሳቸው ያለ መሪ በዓለም ላይ እንደሌለ’ ለማስገንዘብ የተሞከረ መሆኑ አይረሳም።

ነገር ግን እንዲህ ያለውን ዓቢይ ተግባር ለመፈጸም ሲሞከር የውጭ አገራት ጣልቃ እንደሚገቡ ምንም አጠራጣሪ አይሆንም። ይሁን እንጂ ‘እኛ ኢትዮጵያውያን  ስለሆን እንደ ኢትዮጵያዊነታችን እንተገብራለን’ በማለት ማስረዳትና ጸንቶ መቆም ተገቢ ይሆናል። ነገር ግን ‘የእኔ መንግሥት እንዲህ ነው፤ እንዲህ እንዲህ ያደርጋል፤ በሌላ አገር እንዲህ ያለ አሠራር የለም፤’ እያሉ በመመጻደቅ ጉራ መቸርቸርና ጠላት ማብዛትም ተገቢ አይደለም። እንዲያውም ድምፅን አጥፍቶ በሥራው ላይ ብቻ ማተኮር ይመከራል።

ለመሆኑ አንድ መንግሥት የሀብት ክፍፍልን በሥራ ለመተርጎም  የሚችለው ምን ዓይነት ፖሊሲዎችን ቢከተል ነው?

በቅድሚያ የሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች የሆኑትን ለይቶ መንቀስና እንደ አንገብጋቢነታቸው ቅደም ተከተል በዝርዝር ማውጣት ተገቢ ይሆናል።

ለምሳሌም፡

ሀ. ምግብ

ለ. ጤና

ሐ. ልብስ

መ. መጠለያ

ሠ. ትምህርት ወዘተ. ናቸው።

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ለአንድ ሀገር ሕዝብ እንደ መሠረታዊ ፍላጎቶች አድርገን ብንወስዳቸው በመንግሥት በኩል እንዴት ተደርገው ለሕዝብ ሊዳረሱ እንደሚችሉ ግራ ሊያጋባ ይችላል። በእርግጥ የአንድ ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች እነዚህ ብቻም አይደሉም፤ ግን ለአሁኑ ምሳሌያችን በቂ ስለሆኑ እስኪ ከላይ ያሉትን ሁለቱን ብቻ በየተራ እንመልከታቸው።

ሀ. ምግብን በተመለከተ መንግሥት የሚከተለውን እርምጃ በመውሰድ እያንዳንዱ ዜጋ ጦሙን አንዳያድር ቢያንስ እንኳ ዳቦ እንዲበላ ማስቻል ተገቢ ይሆናል። ይህንን እውን ለማድረግ የስንዴ ዋጋ በመንግስት እንዲደጎም ሆኖ ዳቦ ጋጋሪዎች ለጉልበታቸው ብቻ መጠነኛ የአገልግሎት ዋጋ በማስከፈል ለተጠቃሚው ሕዝብ እንዲሸጡ በማድረግ ነው። የዳቦውን ዋጋ፤ መጠን እና ጥራት መንግሥት በአዋጅ በመደንገግ በንቃት እየተከታተለ በቂ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል።

ለ. ጤናን በተመለከተ፤ መንግሥት መጠነኛ የጤና ታክስ አዋጅ አውጆ ማንኛውም ዜጋ የጤና ታክሱን እንዲከፍል በማድረግ፤ መንግሥት ለጤና በሚመድበው በጀት ላይ ጥሩ ተጨማሪ አቅም እንዲፈጥር በማስቻል፤ በኢትዮጵያ ምድር ማንኛውም ዜጋ የነፃ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። በተለይ እነዚህ ሁለቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መሠራታዊ የሕዝብ ጉዳዩች ናቸው።

የጤና ታክስ፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረ ሲሆን ለካርድ ማውጫ ሁለት ብር ብቻ ይከፈልና ሕክምና 100% ነፃ እንደነበር አይዘነጋም። ምግብ የሚያገኝ እና ጤና ያለው ዜጋ ለአንድ አገር መንግሥት የሚሰጠው የሞራል ድጋፍ እጅግ በጣም ጠንካራ ነው። ሁኔታዎችን በጨረፍታ ብናያቸው እንኳ፤ የምግብና ጤና አገልግሎት ያለው ሕዝብ፤ ሠራተኛና አምራች ይሆናል። አምራች ከሆነ ደግሞ እራሱንና ቤተሰቡን ከመርዳት አልፎ ለአገር የሚያበረክተው አስትዋጽዖ ከፍተኛ ነው። በሌላም አንፃር፤ ለአገር ሰላም የሚያደርገውም ተሳትፎ እንዲሁ በቀላሉ መታየት የለበትም። ይኸውም ሌብነትና የተለያዩ ወንጀሎች ላይ የመሠማራቱ ሁኔታ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ስለሚሆን፤ ለአለው መንግሥት ችግር ፈጣሪ ሳይሆን፤ ለሰላምና መረጋጋት ታላቅ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ገረብ ገረብ ትግራይ መቃብር አምሃራይ

በሦስተኛ ደረጃ መንግሥት የሚያስተዳድረውን ሀገር ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት በበለጠ ለማቀላጠፍ የወረቀትን አቅርቦት ከቀረጥ ነፃ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም ዕውቀት የሚገኘው የግድ ትምህርት ቤት በመሄድ ብቻ አይደለም። የተለያዩ መጻሕፍት በቀላሉ እንዲታተሙና ለሕዝብም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲዳረሱ ከተደረገ፤ ሕዝቡ ከመደበኛ ሥራው ሳይለይ መጽሐፍ በማንበብ ዕውቀቱን ማዳበር ይችላል። እዚህ ላይ መጽሐፍ ሲባል የግድ ልብወለድ ብቻ ላይ ማታኮር የለብንም።

አገራችን ብዙ ምሁራን አሏት፤ የወረቀት ዋጋ ዝቅተኛ ከሆነ እነዚህ ምሁራን በየተሠማሩባቸው የሙያ ዘርፍ ሕዝባችን ማወቅ አለበት የሚሉትን ሁሉ በባዕድ ሳይሆን በራሱ ቋንቋ በመጻፍና በማሳተም ስለሚበረታቱ አገርን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

በመሠረቱ ወረቀት ሲባል መንግሥት ላብ ላብ ይለዋል፤ ምክንያቱም የወረቀት ዋጋ የሚቀንስ ከሆነ ጋዜጣና መጽሔት በስፋት ይታተማሉ፤ እነዚህም መንግሥትን በመተቸት ‘ችግር ይፈጥሩብኛል’ ከሚል እጅግ ኋላ ቀር አመለካከት ወጥቶ ጨከን ብሎ ለኅብረተሰብ ዕድገት አመዛኝ በሆነው ውሳኔ ላይ ቢሠማራ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም። መንግሥት ግን ከሚሰጠው የተሳሳተ ትርጉምና ከአለበት ከወረቀት ጋር  የተያያዘ ጭንቀትና የፍርሃት አመለካከት ወጥቶ፤ ለዕድገት በሚበጀው ላይ ትኩረት በመስጠት ሊሠራ ይገባዋል። የወረቀትን ዋጋ ጣራ ላይ ሰቅሎ አገር አሳድጋለሁ ማለት ‘የሕልም እሩጫ’ ከመሆን ያለፈ አይሆንም።

ከአሁን ቀደም በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፤ ኮምፒውተር በዓለም ብርቅ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ የኮምፒውተር ተጠቃሚ ከነበሩ ጥቂት የዓለም አገሮች አንዷ ነበረች። ነገር ግን ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ‘ኮምፒውተርን መጠቀም መረጃን ለባዕድ አገር አሳልፎ መስጠት ነው’ በሚል ፍርሃት ሲንቀጠቀጥ ስለነበር፤ ኮምፒውተር ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ማዕቀብ በማድረጉ፤ አገራችን በኮምፒውተር ሣይንስ ጭራ ሆና እንድትዘልቅ አሳፋሪ ድርጊት ፈጽሞ አልፏል። ነገር ግን በንጉሡ ጊዜ የነበረው እንቅስቃሴ በዚያው ቢቀጥል ኖሮ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያችን የኮምፒውተር ጠበብት ባህር በሆነች ነበር። የሆነው ሆኖ፤ ደርግ ቢያዘገየውም ዕድገቱን እስከመጨረሻው ግን ለመግታት እንዳልቻለ በገሐድ የሚታይ ሐቅ ነው። ሆኖም አገራችንን ምን ያህል ወደ ኋላ እንዳስቀረ መገመት አይከብድም።

አሁንም የሚታየው የዚያው ዓይነት ባህል ነው። ሰዎች በትረ መንግሥትን ሲጨብጡ ሕዝቡን እንደ አገልጋያቸው፤ አገሪቱን ደግሞ እንደ ግል ሀብታቸው አድርገው ስለሚያስቡ፤ እነርሱ የሚፈልጉትን አንጂ አገርና ሕዝብ የሚፈልገውን ቅድሚያ ሰጥተው አይሠሩም። ይህም በጣም ያሳዝናል፤ ምክንያቱም እራሳቸውን ዘለዓለማዊ እንጂ ጊዜያዊ ሰዎች መሆናቸውን ስለሚዘነጉ ነው።

ሌላው አንድ ሰላማዊ ዜጋ ያለምንም ችግርና እንግልት ከአገሪቱ አንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ በነፃነት የመንቀሳቀስና ተዘዋውሮ ነግዶና ሠርቶ የመኖር መብቱ ሊረጋገጥለት ይገባል። መንግሥት ግን በራሱ የሚተማመን ከሆነ እንዲህ ያሉትን ዓበይት ተግባራት በጽናትና በቆራጥነት በመወሰን ማስፈጸም ይኖርበታል። ከዚያም የሕዝብ አመኔታን፤ፍቅርን አና ክብርን ይጎናጸፋል። በመላ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ይሠፍናል መንግሥቱም የጸና ይሆናል።

ፈረንጅ አምላኪዎችና የምዕራባዊያን ጥራዝ ነጠቅ ምሁራን ነን ባዮች፤ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ሊቀበሉት እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ምክንያቱም የራሳቸውን ባህል እንደ ነውር የሚቆጥሩና የሚያቃልሉ ስለሆነ ተግባራዊ የሚሆን መስሎ አይታያቸውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፋፋዮች አማራን የማዳን ኢትዮጵያን የመታደግ ትግል አታደናቅፉ

ዛሬ በዓለም በሀብቷም ሆነ በዕድገት ደረጃዋ አንደኛ መሆኗ በሚነገርላት አሜሪካ፤ ብዙ ዜጎቿ መጠለያ አልባ ሆነው በረንዳ ላይ እንደሚያድሩና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦቿ ደግሞ በገንዘብ እጥረት ምክንያት በቂ ሕክምና ሊያገኙ ባለመቻላቸው ያለጊዜያቸው ለሞት እንደሚዳረጉ በሠፊው ይነገራል። ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ የሚከተሉት ፖሊሲ ኢኮኖሚን እንጂ ሰብአዊነትን ያላገናዘበ በመሆኑ፤ አሜሪካ እንኳን ለሕዝቧ ለሌላው የዓለም ሕዝብም ሊበቃ የሚችል የመድኃኒት፤ የገንዘብ፤ የቴክኖሎጂ እና የሠለጠነ የባለሙያ አቅርቦት እንዳላት መጠራጠር ሞኝነት ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ግን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዓለም ሕዝብ የሚለይበት የራሱ የሆነ ባህልና እሴት ያለው ጨዋ ሕዝብ መሆኑን ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያውቀዋል። ለምሳሌም ብንጠቅስ፤በዕድር፤ በእቁብ፤ በማኅበር፤ በመ/ቤት ባልደረባነት፤ በአገር ልጅነት፤ በሃይማኖት፤ በጎረቤት እና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ዘርፎች የተሳሠረ በመሆኑ በደስታ ጊዜ፤የአንዱ ደስታ የሌላው ጭምር ሲሆን፤ በኅዘን ጊዜም እንዲሁ የአንዱ ኅዘን የሌላውም ጭምር መሆኑን በመረዳት ያጽናናል፤ ያስተዛዝናል። ሌላው ቀርቶ ወያኔ የሚባል አይቶ ያማያውቅ ችጋራም ቅጥረኛ፤ሥልጣኑን ከጨበጠ ወዲህ እየቀነሰ ቢመጣም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር ፤ በቋንቋ እና በሃይማኖት ሳይገደብ፤ ቡና እንኳ ብቻውን የሚጠጣ አልነበረም።

አንድ ሰው ድንገተኛ ችግር አጋጥሞታልና እንርዳው ሲባል፤ ሁሉም ሰው ተረጅውን ይወቀውም አይወቀውም አቅሙ የፈቀደውን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ፍቅርና ‘የነግ በእኔ’ አስተሳሰብ እሴት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑን ልብ ይሏል። እንግዲህ ባህላችንና እሴታችን ይህ መሆኑን ከተማመን፤ መንግሥት ይህንን የሕዝብ ባህል እና እሴት ወደ ፖሊሲ ቀይሮ ተግባራዊ ቢያደርገው ምን ይጎዳል?

ዞሮ ዞሮ የመንግሥት ዋናው ተግባር የሕዝቡን ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ደኅንነቱን ማስከበር እስከሆነ ድረስ፤ ከላይ ለተጠቀሱት መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶች የሚመደበው የመደጎሚያ በጀትም ሆነ ከቀረጥ ነፃ በማድረግ በሚከፍለው መስዋዕትነት አቅም የሌላቸውን የኅብረትሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። መንግሥት በሚወስደው እንዲህ ያለው በጎ እርምጃ ሕዝቡ ከሞላ ጎደል ፍትሀዊ የሆነ የሀብት ክፍፍልን እንዳገኘ መረዳት ይቻላል።

እንግዲህ አንድ ፖሊሲ ሲቀረጽ የአገራችንን ባህልና እሴት ያገናዘበ እንዲሆን፤ መንግሥት በጥልቅ እያጠናና እየመረመረ ሊሠራበት ይገባል እንላለን። ነገር ግን የሰውን ልጅ ክቡርነት ከማይቀበሉና ገንዘብ ከሚያመልኩ የምዕራብ አገሮች ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቅዳት በዚያ እንመራለን ማለት አግባብ ሊሆን አይችልም።

ኢትዮጵያኒዝም (Utopia) የእኛን ፍትሀዊ መንግሥት ልዩ የሚያደርገው ሌላም እሴት አለን። ይኽውም ኢትዮጵያውያን ቤተስቦች ልጆቻቸውን 18 ዓመት ሞላህ ብለው ከቤት አያባርሩም። ልጆችም ተምሬአለሁ በቂ ደመወዝም አለኝ በማለት ቤተሰባቸውን ጥለው አይሄዱም። ምናልባት ሊለያዩ የሚችሉት ወይ በሥራ አጋጣሚ እርቀው ሲሄዱ፤ አለበለዚያም ትዳር ይዘው የራሳቸውን ጎጆ ሲመሠርቱ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ወደ ምዕራቡ ዓለም የሄድን እንደሆነ፤ አንድ ልጅ 18 ዓመት ከሞላው የራሱን ኑሮ እንዲጀምር በወላጆቹ ግፊት ይደረግበታል። አንዳንዶቹም ልጆች ገና 17 ዓመት ሲሆናቸው ከቤተሰብ ወጥተው ይሄዳሉ። ከዚያም በኋላ ግንኙነታቸው በስልክ ብቻ ይሆንና ፍቅራቸው እየላላ ከመሄዱም በላይ ጊዜ ወስደው የሚጠያየቁት ቁጥራቸው እጅግ በጣም ዓነስተኛ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ሌላው ቀርቶ ጎረቤቶቻቸውን እንኳ አይረሱም። መንግሥታችንም በዚሁ በዳበረውና በበለጸገው እሴታችንና ባህላችን የተቃኘ ፖሊሲ ሊነድፍና መመሪያ ሊያወጣ ይገባዋል። በአጭሩ ኢትዮጵያኒዝም (ምድረ ገነት) ማለት እንዲህ ሲሆን ነው።

2 Comments

 1. ነገረ ስራችን ሁሉ የቸገረው እርጉዝ ያገባል አይነት ነው ።
  እኔ ወንድሜ በጽሑፍ ያስቀመጥካቸው የአብሮነትና የትብብር እሴቶቻችን እያደነኩ በተቃራኒው የተጠናወቱን መጥፎ የስነ ልቦና ህመሞች ቁራኛ መሆናችን ያመጣብን ጣጣ እንጂ የችግሩ ምንጭ ኢዝም(የአስተዳደር ፖሊስ) አይመስለኝም። ምክንያቱም የጠቀሷቸውን ስርአቶች ተጠቅመው የተለወጡና ያደጉ አገሮች አሉና ነው ።

  የተቆራኙን ህመሞች ፦
  1 ራስ ወዳድነት (ለሀገርና ሕዝብ ግድ የሌለው መሆን)
  2 የበላይና የበታችኝነት ስሜት (ኮምፕሌክስ )
  3 ሰው አምላኪነት (ስልጣን የጨበጠን አካል ሁሉንም አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ መውስድ )
  4 በራስ አለመተማመን ( ሁሉንም ወይ ከፈጣሪ አሊያም ከሌላው መጠበቅ ) ሕዝባችን ለዚህ ለውጥ መምጣት ያልከፈለው መስዋእትነት የለም ነገር ግን የበሬውን ምስጋና ወስደው ፈረሱ አይነት ነገር ሆነና የለውጡ ባለቤት በመሆን የሚያቅራራው ሌላ ነው ይህንን ውሸታም ሁላ በቃህ እረፍ የሚል በራስ የሚተማመን ሕዝብ ያስፈልጋል።

 2. ፍጹም ባዶ የሆነና ከንቱ እኛ ኢትዮጵያዊያን ምንም ሳይኖረን ሁሉም አለን የሚል ባዶ ፕራይድ የሞላበት አስተሳሰብ ነዉ- ሊብራሊዝም የብዙ በከፍተኛ ደረጃ የሚያስቡ ሰዎች የዘመናት የስራ ዉጤት ነዉ፥ ደሞም በጽሁፍ የተቀመጠና በየዘመኑ አሁንም ድረስ እየተሻሻለ የመጣ ፍልስፍና ነዉ- አስኪ ምንድነዉ ኢትዮጵያዊነት ማለት? ምን የተጻፈ ነገር አለዉ? መጻፍ ብቻ አይደለም ብዙዎች በሃሳቡ ሊከራከሩና እያደገም የመጣ ነገር መሆን አለበት?በነገራችን ላይ በስም ስለሚመሳሰል ብቻ Utopian-ism ኢትዮጵያኒዝም ነዉ ብለህ ከሆነ ተሳስተሃል-እሱም ቢሆን የምዕራባዊያን ሃሳብ ነዉ። እኛ በፍልስፍና ደረጃ አስበን የቀመርነዉ ወይም በዘመናት እየተቀባበልን ያዳባርነዉ ፍልስፍና የለም! ምንም ሳይኖረን አለን ብለህ በሃሳብ ነጥረዉ የጠሩ አስተሳሰቦችን ከመቀበል የተለየ ሌላ አማራጭ የለህም። ደሞም ሊብራሊዝም ብቻ አይደለም ዛሬ አለማችን ያላት አማራጭ ብዙ ነዉ፥ አንተ እሱም የገባህ አይመስለኝም። ባጠቃላይ ኢትዮጵያኒዝም ብሎ ፍልስፍና የለም!!! የምዕራቡ በተለይ የአዉሮፓ Thinkers ሊብራልዝምን ሲቀምሩ እኛ ከሃይማኖት የራቀ ምንም አስተሳሰብ አልነበረንም- ዛሬም ከሃይማኖት ብዙ የራቅን ሰዎች አይደለንም! ስለዚህ ወንድሜ የሌለን ነገር እንዳለ አድረገዉ አትንገረን- ወይስ ስለክብረነገስት ነው የምታወራዉ? ኢትዮጵያዊያን ከምዕራቡ አለም ይልቅ ለሰዉ ልጅ ነብስ ያስባሉ አልክ- ለዚህ ነዉ ታሪካችን በሙሉ የመግደል የሆነዉ? አታፍርም? ነገስትታቱ መግደል፥ ደርግ መግደል፥የመሬት ባለቤቱ መግደል፥ ህወሓት መግደል፥ ኢህአፓ መግደል፥ ሻዕቢያ መግደል፥ መኢሶን፥ ኦነግ ሁሉም መግደል ስራቸዉ የሆነዉ? ባለፉት አንድ አመታት እንኩና በሰሜን፥ በምስራቅ፥ በደቡብ በምዕራብ ሰዉ አንደ እንስሳ ያልታረደብት በድንጋይ ተወርዉሮ ያልተገደለበት ወይም ያልተሰቀለበት አካባቢ አለ?

Comments are closed.

Share