ሕዝብ እንዲሰማህ ሰፊ አፍ ይኑርህ!

 

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

እንደሚታወቀው ለመስማት ተናጋሪና ሰሚ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ተመራምሮና መጻሕፍት አገላብጦ ሳይሆን ተባራሪ ዜናና አሉቧልታ በጀሮው ከጣራ እንደተቸከለ አንቴና እየቃረመ ያወቀ ለሚመስለው መንጋ ለመስማት እንደ ዲሽ የተንከረፈፈ ጆሮ ለመናገርም እንደ ሰማይ የተከፈተ አፍ ያስፈጋል፡፡ የፊደል ቆጣሪ ማይም እንደ ዝናብ አብራ በፈላባት ኢትዮጵያ ቀርቶ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች በሞሉበት አሜሪካና አውሮፓም ሰፊ አፍ ዘወትር ያሸንፋል፡፡ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ ሰፊ አፍ አሸንፏል፤ እስከ ዳግም ምጣትም ሰፊ አፍ ያሸንፋል፤ ምንጊዜም ሰፊ አፍ ያሸንፋል፡፡

ጠቢቡ ሶቅራጥስ መርዝ እንዲጠጣ የተደረገው በድልዱም ገዥዎች ሰፊ አፍ ቅስቀሳ የተነዳ ሕዝብ “ሶቅራጥስ ይገደል” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነው፡፡ የአቴንስ ሕዝብ ይህ ጠቢብ እንዲሞት ድምፅ የሰጠው ብችኛ መተማመኛው ጀሮው ስለነበርና  በዘመኑ የነበሩት አረመኔና ዱልዱም ገዥዎች ዋና መሳርያም ሰፊ አፍ ስለነበረ ነው፡፡ የጠቢቡን ሐሳብ የፈሩት ዱልዱም ገዥዎች “ሶቅራጥስ ወጣቱን እያበላሸና አማልክቶችንም እየከዳ ነው” እያሉ እንደ ታምራት ላይኔና በረከት ስሞን ያሉ ካድሬዎች ሲሰብኩ መንጋው ጆሮውን እንደ ሰፌድ እየዘረጋ ሰማቸው፡፡ የሕዝቡን መታለል የተገነዘበው የገዥው ቡድንም ሶቅራጥስ ሔምሎክ ጠጥቶ እንዲሞት አደረገው፡፡

እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለውም እንደ ኢሀዴጎች ሕግን እያነበነቡ ከሕግ ግን አንዲቱንም በማይፈጥሙ ፈሪሳውያን ሰፊ አፍ የተሰበከ ጆሯማ መንጋ “ስቀለው! ስቀለው! ስቀለው!” የሚል ድምፅ ሶስቴ ስላሰማ ነው፡፡ ሰፊ አፊ እንደዚህ ነው! ጠቢቡንም መለኮትንም የማጥፋት ኃይል አለው! ተቀናቃኝ አፍ በልጓም ካልገታው ሰፊ አፍ እንኳንስ የሰውን ሐሳብ መንፈስ ቅዱስንም የማጣጥፋት ጉልበት አለው፡፡ 

አውሮጳውያን አፍሪካን፣ ኤሽያንና ላቲን አሜሪካን ለክፍለ-ዘመናት የገዙት በጠመንጃ ሳይሆን በሰፊ አፍ ነው፡፡ ሕዝቡም የተገዛላቸውን ጉልበት ስለሌለው ሳይሆን ይተማመን የነበረው በጉልበቱ ሳይሆን በጆሮው ስለነበረ ነው፡፡ አውሮጳውያን “ልናሰለጥንህ ከመለኮት ተላክን!” እያሉ የማያምኑበትን መጽሐፍ ቅዱስ ተቀናቃኝ በሌለው ሰፊ አፋቸው ሲሰብኩት የመኪና የጎን መስታዎት በመሰለው ጆሮው እየጠቀለለ ከልቡና ከመንፈሱ አስገባው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያውያን ኢሐዴግ የሚባለው ከሀዲ እስከመጣ ድረስ በአሮጳውያን በቀጥታንም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልተገዙት እንደ ዓባይ በርሃ የተከፈተውን የአውሮጳውያን አፍ የሚዘጉ እንደ መምህር አካለ ወልድ፣ አራት ዓይናው ጉሹ፣ አስረስ የኔሰው፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ፣ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ ቀኝ ጌታ ፍታሄ ንጉሴና ሀዲስ አለማየሁ ያሉ አፈወርቆች ስለነበሯት ነው፡፡ ሰይጣን የከፈተውን የኢሀዴግ አፍ እሚዘጋው ለገሰ ያሰለጠነው የኢሀዴጉ ፓስተር ሳይሆን መለኮት የከፈተው የዮሐንስ አፈወርቅ አፍ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት አለበት ሲባል…..…. መስከረም አበራ: ከቃሉቲ ማጎሪያ

ጨፍጫፊው ስታሊን በሩሲያ እንደ አምላክ ይታይ የነበረው ሬዲዮኑን፣ ጋዜጣውና ሌላውንም የሕዝብ መገናኛ ስለተቆጣጠረው ነበር፡፡ አረመኔው ሂትለርም ብዙ ተከታይ ያፈራውና አውሮጳን ያንበረከከው በጠምንጃው ሳይሆን በሰፊ አፉ ነበር፡፡

ሰይጣኑ ለገሰ ዜናዊ ኢትዮጵያን እየሸጠ ጃርት የጋጣት ድንች አስመስሎ በስልጣን የሰነበተው እንደ ዳሎል ጉድጓድ በጠለቀውና በሰፋው ይሉኝታ ቢስ አፉ ነበር፡፡ ለገሰ ተቀናቃኝ አፎችን ጥርቅም አርጎ የዘጋው ሕዝብ እርሱ እሚለውን ብቻ እንዲሰማና እንዲቀበለው ነበር፡፡ ለገሰ ባሪያዎቹ በተከሉለት ቴሌቪዥንና ሬዴዮ የሚለቀውን ውሸት ሃያ አምስት ዓመታት ስለሰማ ከልቡ “ባለራዕይ መሪ” እንደነበር ዛሬም የሚያስበውን ጎጋ ቤት ይቁጠረው፡፡ ለገሰ በሞተበት ወቅት ልጆቻቸው ሊጠይቁ የመጡ እናቶች “አቶ መለስ ስለ ልማት ተናግረው የማያባሩ ሩህሩህና ለሕዝብ አሳቢ መሪ ነበሩ” ብለው እንባ ያፈሰሱ አማራ እናቶች አይቻለሁ፡፡

ለገሰ እንደ ጠላት በሚቆጥራቸው አማሮች ሳይቀር “ባለ ራዕይ መሪ” እስከ መባል መድረሱ የሚያሳየው ሶቅራጥስን መርዝ ያስጠጣውና ክርስቶስን ያሰቀለው ሰፊ አፍ ሰይጣንንም የማንገስ ትልቅ ኃይል እንዳለው ነው፡፡ ለገሰ ዜናዊ ሰይጣን በመለኮትን አምላኪው አማራ የላከው ሰይፍ እንደነበር ሥራው ምስክር ነው፡፡ ሥራው ቢመሰክርም ተቀናቃኝ ያልነበረው ሰፊ አፉ በአካልና በመንፈስ አኮስምኖ ሊያጠፋቸው በመጣው አማራ ሳይቀር ቅዱስ ሆኖ እንዲታይ አደረገው፡፡ የአውሮጳን ወገብ ሰብሮ የዘላለም ሕመምና ውርደት የሰጠው አማራ በለገሰ መሸወዱ የሚያሳየው ኔቶ እንኳን የአፍን አንድ አስረኛ ኃይል እንደሌለው ነው፡፡ ለገሰ አማራን የጎዳው ብአዴን በሚባል ማፈኛ አፍኖ ዲዳ በማድረግ ነው፡፡ የለገሰን ወንበር የወረሰው ፓስተርም አማራን መግዛት የሚሻው ይኸንኑ ማፈኛ ከድሮውም የበለጠ በማጥበቅ ነው፡፡ የአማራ ጉዳቱ እሚጠገነውና ከመጥፋትም እሚድነው ይኸንን ብአዴን የሚባል ማፈኛ ቦጭቆ ዲዳነቱ ሲቀርና ራሱ ስለ ራሱ መናገር ሲጀምር ብቻ ነው፡፡ ያልታፈነ አፍ ሶስቴ “ስቀለው! ስቀለው! ስቀለው! ” እያለ የማሰቀልና የመግደል ኃይል እንዳለው ሁሉ ሶስቴ “አድነው! አድነው! አድነው!” ብሎ የማዳንና ዘርን የማትረፍ ኃይልም አለው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማካሪ የሌለው መንግስት አገር እያፈረሰ ነው - ገለታው ዘለቀ

ለገሰ አማራን በብአዴን አፍኖ ሲጨረግድ በጆሮ ጠቢነት፣ በስልክ ጠላፊነትና በታማኝ “ኮሎኔልነት” ሲያገለግለው እንዳልኖረ ሁሉ ፓስተር አቢይ በአማሮች “ከሰማይ የወረደ መሲህና ወንዝ አሻጋሪው ሙሴ!” እስከ መባል የደረሰው በሕዝብ ደም ተሻግሮና በሰማእታት አጥንት ተንጠልጥሎ ከሃያ አመታት ባርነት ተላቆ አፉን ስላሰፋ ነው፡፡ ከወንጀለኞች ፊት እንደ ሊማሊሞ ገደል የተቦረገደ አፍ ሳይቀር ግዙፍ ኃይል አለው! የተቦረገደ አፍ ጆሮ እየጠባና ፖሊስ እያዘዘ ሕዝብ ያሰጨረገደውን የይድረስ ይድረስ ሎሌ ኮሎኔልም መሲህ አደረገው፡፡ 

አፍ ለጮሌው ብርሃኑ ነጋም ለሃምሳ ዓመታት የተጠቀመበት ትልቁ መሳርያው ነው፡፡ ብርሃኑ ነጋ አሻሮ ይዞ ወደ ቆሎ እየተጠጋ ቆሎውን ቀምቶ እየቃመ ባለቆሎን አሻሮ አስታቅፎ የሚሰድ ጩልሌ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይኸንን ጩልሌነቱን ያልተረዳ አቶ ኃይሉ ሻውልንና በግንቦት ሰባት ስም የተረሸኑትን ዜጎች ከሰማይ ቤት፣ የአርበኞች ግንባርን ሰራዊትን ወረታ፣ በእርሱ ስም ሽባ፣ ዓይነ-ስውርና ስልብ የሆኑትን የአማራ ልጆች ቤጌምድር፣ ጎጃም፣ ወሎና ሸዋ ሄዶ መጠየቅ ነው፡፡ ብርሃኑ ነጋ አዲስ አበባ በቀይ ምንጣፍ በገባ በማግስቱ ለእነዚህ ሰማእታት ፍትህ ይጠይቃል ብለን ተስፋ ስናደርግ ከገዳያቸውና ከአሰቃያቸው ኢሀዴግ ጋር አስረሺ ምቺ የሚጨፍር ዓይን አውጣ ማገወልድ ሆኖ አገኘነው፡፡ 

ይኸንን ታሪክና ትውልድ የማይረሳው ክህደት የፈጠመው አብያው ብርሃኑ የወለደ አይጨክንም በሚል የጫት ቁማር ኢትዮጵያ እሚባል የመርካቶ ሙዚቃ ኢትዮጵያን አምጦ ወልዶ ባሳደገው በአማራ ጆሮ በሰፊ አፉ እያንባረቀ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እሚባለው የብርሃኑ የንግድ ሙዚቃ የማይጣፍጠው ቡድን ከደቡብ በቆንጨራ ሲያባርረው እየተመለሰ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ባህርዳርና ደብረ ማርቆስ እየተንከባለለ ይደንሳል፡፡ ወልዶ ያሳደጋት ኢትዮጵያ አንጀቱን እንደ ሰለሊት የምትበላው አማራም እንደ ውዷ እናቴ አንጀቱ እየተንሰፈሰፈ ያዳምጠዋል፡፡ ይህ ብርሃኑ እንደ ማይክል ጃክሰን እየተንከባለለ የሚደንስበት ሕዝብ ደሞ ብርሃኑ በአስራ ሰባት ዕድሜ ትግል ሲጀምር “ብሔራዊ ጨቋኝ” ሲል የኮነነውና ስልጣን ለመቆናጠጥ የፈለገ ጆቢራ ሁሉ ባጎረሰ የሚነከሰው መከረኛ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ብርሃኑ አሜሪካ በጠፈጠው ድርጅት ሥም ጥፍራቸው በጉጠት የወጣ፣ ህብለ-ሰረሰራቸው በጥይት ተቦድሶ ሽባ የሆኑና መፀዳዳት የተሳናቸው፣ ተሰልበው የመነኮሱና እንደ ሙጃ የተጨረገዱ ልጆች ወላጅ፣ ወንድምና እህት ነው፡፡ 

ተጨማሪ ያንብቡ:     ህወሃት የመከላከያ ሠራዊቱን  የገቢ ምንጭ በማድረግ ይጠቀምበታል፦

ብርሃኑ በድርጅቱ ሥም ለሞቱትና አካለ ስንኩላን ለሆኑት ፍትህ ይጠይቃል ብለን ስንጠብቀው ከገዳዮቻቸው ጋር በቁርባን ተጋብቶ “ጨቋኝ ብሔር” ባለው ሕዝብ ስም የወንበር ቅስቀሳ ሊያደርግ ልኻጩን ሲያዝረበርብ ተመለከትነው፡፡ በዚህ የስልጣን ቅስቀሳውም ጧት ጧት እንደ አሰፋ ማሩ፣ ፕሮፌሰር አስራትና ሳሙኤል አወቀ ያሉ ጀግኖችን ሥም እያነሳ ሕዝብ ሲያታል ያረፍዳል፡፡ ከሰዓትና ምሽት ደሞ እነዚህን ሰማእታት ከገደለው ኢሀዴግ ጋር  ሲሞዳሞድና እንደ ቀበጥ ልጃገረድ ሲወባራ ያመሻል፡፡ ይኸንን የመሰለ ዳግ ያጣ የፖለቲካ አመንዝራነት እየፈፀመም ሰፊ አፍ ስላለው ጆሮውን ተማምኖ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ይሰማዋል፡፡ ሰፊ አፍ በሬን መጥለፊያ መጫኛ ከያዘ አሳራጅና ካራ ከጨበጠ አራጅ ጋርም ያሳድራል፡፡ የሰፊ አፍ ኃይሉ ያስደንቃል!

እንደ ለገሰ፣ አቢይና ብርሃኑ ያሉ ዓይናውጣ ቅርድ አፎችን እየሰማ ሕዝብ ሶቅራጥስን ሲያስገድል የተመለከተውና ጆሮውን ብቻ በሚያምን ሕዝብ ተስፋ የቆረጠው ፕላቶ በሶፊስቶችና በደነዝ ገዥዎች የሚገዙትን ምሁራን ሲመክር “ከፖለቲካ ከሸሸህ በቀረጨጩ አይምሮዎች ትገዛለህ” ሲል መክሯል፡፡ 

እኔም እንደ አቅሜ አገራችን ካበረከተቻቸው ብቁ ጸሐፊዎች በተጨማሪ ከሶቅራጥስ በፊት የእነ ቴልስንና ፓይታጎረስን፤ በሶቅራጥስ ዘመንም የእነ ፕላቶንና አርስቶትልን፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላም የእነ ፍራንሲስ ቤኮንን፣ ትሆማስ ሆብስን፣ ሎክን፣ ስፓይኖዛን፣ ቮልቴርን፣ ዳቪድ ሆምን፣ ሮዙን፣ በርክሌየን፣ ኢማኖኤል ካንትን፣ ኒቼን፣ ሚልስን፣ ሄግልን፣ ማርክስና ሌሎችም ጨልፌ አንብቤ በዚህ መነፅር ዓለምን ሳጤናት ከጉልበተኞችና ከአፈ ሰፊዎች መዳፍ ወጥታ እንደማታውቅ፤ ወደፌትም ከጉልበተኞች ክንድና ከአፈ ሰፊዎች እጅ እንደማትወጣ ተገንዝቤአለሁ፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ ሰፊ አፍ እንኳን ጉልበትን መንፈስ ቅዱስንም አቅቶ ዓለምን ሲገዛ እንደሚኖር ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ እሚሰማ ከተገኘ ለሕዝብ በተለይም ልሳኑ ተዘግቶ ለእርድ ለተዘጋጀው አማራ “እንዳየኸው አፍህን ከዘጋህ ባለቤት እንደሌለው ጫካ የጨረገደህ መሲህ ነኝ! ፃድቅ ነኝ! ሙሴ ነኝ! ኢያሱ ነኝ” እያለ ሊሰብክህ ይመጣል!” ስል እመክራለሁ፡፡ “እንደ ስታሊን፣ ሂትለር፣ ለገሰ ዜናዊ፣ አቢይ አህመድ፣ ብርሃኑ ነጋና ሌሎችም ይሉኝታ ቢሶች ለመደመጥና ስልጣን ለመጨበት ከፈለክ እንደ ዓባይ ሸለቆ የተቦረገደ ሰፊ አፍ ይኑርህ!” ስልም አስጠነቅቃለሁ፡፡ 

ሰምታችሁ ይኸንን ምክር ለሕዝባችሁ ላደረሳችሁና ሕዝባችሁን ከመጥፋት ላዳናችሁ ምስጋናየን አቀርባለሁ፡፡  

የካቲት ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

4 Comments

  1. የ ብርሃኑ ነጋን ሰው ተቀብሎት ከሆነ ፣ ‘የቸገረው እርጉዝ ያገባል’ ስለሆነበትና ሰውየውን በቅጡ ካለማወቅ ነው። ዋናው የአድማጩ አናሳ ኝዛቤ ነው ለዚህ ያበቃው።
    ስለዚህ የዚህን ሰውዬ ከወያኔ ጋር ለዘመናት ማለቅለቅና፣ ከነርሱ ጠቡ የስልጣን ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ነው፣
    ተሞዳምዶ፣ ከ40፣000-50,000 ፟፟፟ ካሪመትር የተቀማን መሬት ደብረዜት በወራሪ ወያኔ በኢንቨስትመንት ስም ተቀብሎ የቸበቸበ ጀኛም ነው።
    አማራ ጨቋኝ ነው የሚል ትሪክት አቀንቃኝ መንግስት ባልደረባ የነበረ ነው።
    በ 1997 ምርጫ ” ኢኔን ነፍተኛ ይላሉ፣ የጉራጌ ነፍተኛ ከቶ የነበረ ይመስል” ኢያለ የተመጻደቀ፣ የጉራጌን ታላቅነት ፣ ነፍተኘትን ጨምሮ የካደ፣ ተራ ወራዳ ፍጡር ነው። በአርበኞች ስም የፈጸመው ዘረፋ፣ በአባላቱም የፈጸመው ግፍ ኢልቆ መሳፍርት ነው።
    ይህ ሰው ለፍርድ መቅረብ ያለበት ነው። በደረሰበት ሊከሰስ የሚገባው ነው በተለይ በየአማራው አካባቢ።

  2. እርግጥ ነው አንተም እኮ ሠፊ አፍ ነው ያለህ፡፡ ሠፊው አፍህ ግን ለመጉረስና ለመሳደብ እንጂ ቁም-ነገር ለመናገር የተዘጋ ሆኖ አግኝቼዋሁ፡፡ “ብርሃኑ ነጋ አሻሮ ይዞ ወደ ቆሎ እየተጠጋ ቆሎውን ቀምቶ እየቃመ ባለቆሎን አሻሮ አስታቅፎ የሚሰድ ጩልሌ መሆኑ የታወቀ ነው” ብለሃል፡፡ ዕውነቱ ግን አንተ አሻሮ ይዘህ ሳይሆን ባዶ እጅህን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ዘንድ መጥተህ ሰልፍ መያዝ ትችላለህ፡፡ ይለቀቅብሃል፡፡ ችግርህን መናዘዝም አይጠበቅብህም፡፡ ችግርህ የስልጣን ጥማት መሆኑን ከእንቶ ፈንቶህ መረዳት ይቻላልና፡፡ “ይኸንን ጩልሌነቱን ያልተረዳ አቶ ኃይሉ ሻውልንና በግንቦት ሰባት ስም የተረሸኑትን ዜጎች ከሰማይ ቤት ሄዶ መጠየቅ ነው” ብለሃል፡፡ ይኸው ከአንተ ከሰማን አይበቃም እንዴ ለምን እነሱን በመጠየቅ ልታደክመን ተጋህ? ለሙታን ለሙታን አንተ በቂ ነህ ብዬ ነው፡፡ “ይህንን ምክር ለሕዝባችሁ ላደረሳችሁና ሕዝባችሁን ከመጥፋት ላዳናችሁ ምስጋናየን አቀርባለሁ” ብለሃል፡፡ ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ፡፡ ይህን የደሃ አጥር የመሰለ ዘባተሎህን ነው ምክር ያልከው? አየህ እናንተ ያ ስሙን መጥራት የማልሻው ድርጅት ደጋፊና አባላት ለአማራ ህዝብ ያላችሁ ንቀት እጅጉን ይገርመኛል፡፡ ለማንኛውም አማራ የሚበጀውን ያውቃል፡፡ ሰሞኑን የደብረ ማርቆስ ወገናችንም ይህንን በማያሻማ ቋንቋ ነግሯችኋል፡፡ እናንተም ስድባችሁን ቀጥሉበት፡፡ ስልጣን ግን በባይናኩላር ትሾፉት እንደሁ እንጂ አጠገቡ አትደርሱም፡፡

  3. በጎ ነገር የማይታያቸውን ጌታ አይን አላቸው አያዩ ጆር አላቸውን አይሰሙም የሚለው በሃገራችን የሚታየውን በጎ ለውጥ ለማይቀበሉና ጭራሽ ለሚያጣጥሉ አባተና መሰሎቹ ይመጥናል::የዶ/ር አብይን ስም ከሃይማኖቱ ጋር በማያያዝ ያልሆነውን ፓስተር ብሎ በመጥራት የሃሰት ዘመቻ የጀመረ ሰው ታርጌቱ ምን መሆኑን መረዳት ይቻላል:: እባብን ያየ በልጥ በረየ ተብሎ ይህን ተችት ለመቀበል ብሞክር የዚህ ጽንፈኛ ጠሃፊን እኩይ ስራ ማለሳለስ ይሆንብኛል:: የእባቡን ለገሰ ዜናዊን ሟርት ኦሮሞና አማራ ባንድ ከቆሙ ወያኔ ያልቅላታል ያለውን ተግባራዊ ያደረገ የመቻቻል የምህረት ሰው ዶ/ር አብይ ያደረጋቸውን ለውጦች ከመደገፍና ለሚቀጥለው ርምጃው ተባባሪ ከመሆን ውጭ ለጨለምተኞች ህዝባችን ጆርሞ ጊዜ የለውም እላለሁ::

  4. በጎ ነገር የማይታያቸውን ጌታ አይን አላቸው አያዩ ጆር አላቸውን አይሰሙም የሚለው በሃገራችን የሚታየውን በጎ ለውጥ ለማይቀበሉና ጭራሽ ለሚያጣጥሉ በላይነህ አባተና መሰሎቹ ይመጥናል::የዶ/ር አብይን ስም ከሃይማኖቱ ጋር በማያያዝ ያልሆነውን ፓስተር ብሎ በመጥራት የሃሰት ዘመቻ የጀመረ ሰው ታርጌቱን መረዳት ይቻላል:: እባብን ያየ በልጥ በረየ ብዬ ይህን ተችት ለመቀበል ብሞክር የዚህ ጽንፈኛ ጠሃፊን እኩይ ስራ ማለሳለስ ይሆንብኛል:: የእባቡን ለገሰ ዜናዊ ሟርት ኦሮሞና አማራ ባንድ ከቆሙ ወያኔ ያልቅላታል ያለውን ተግባራዊ ያደረገ የመቻቻል የምህረት ሰው ዶ/ር አብይ ያደረጋቸውን ለውጦች ከመደገፍና ለሚቀጥለው ርምጃው ተባባሪ ከመሆን ውጭ ለጨለምተኞች ህዝባችን ጆርሞ ጊዜ የለውም እላለሁ::

Comments are closed.

Share