በምዕራብ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ለፌዴራል መንግሥቱ ጥያቄ ማቅረቡ ታወቀ፡፡ በዚህ መሰረት የመከላከያ ሠራዊቱ የአካባቢውን ሠላም ለማስከበር ከዛሬ ጀምሮ ተሰማርቷል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=Fu1uIyUHtps&t=186s
በፀጥታ ኃይሉ አስተማማኝ ሰላም እስኪገኝ ድረስ በአካባቢው የተከለከለከሉ ተግባራትም ዛሬ ይፋ ተደርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከጎንደር-መተማ መስመር ከመንገድ 5 ኪ.ሜ ክልል በቡድንም ይሁን በግል ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም፤ በሁመራ መስመርም በተመሳሳይ ክልከላ ተደርጓል፡፡ በጎንደር ከተማ ከፀጥታ አካላት ውጭ ማንኛውም ሰው መሣሪያ ታጥቆ መንቀሳቀስ እንደማይችልም ታውቋል፡፡ ማንኛውም በፀጥታ መደፍረስ ተሳትፎ ያደረገ ኃይል እርምጃ እንደሚወሰድበትና ‹‹ሰላም ለማስከበር›› በሚል ሰበብ ማንኛውም ግለሰብ ከኮሚሽኑ ፈቃድ ውጭ መሣሪያ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተላልፏል፡፡ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጎንደር ወጣቶችና አክቲቪስቶች በጎንደር እና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ከፀጥታ ኃይሉ ጋር እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከቀናት በፊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አቶ ብርሀኑ ጁላ በጎንደር ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት መከላከያ ያልገባው የክልሉ መንግስት ጥያቄ ስላላቀረበ ነው ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡