በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ታዋቂ ታጋይ የሆኑትና በፓርላማ ለአምስት አመታት ጠንካራ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚታወቁት የ88 አመቱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ስለወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ተናገሩ፡፡
https://youtu.be/J8BZqY2t65c
አቶ ቡልቻ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የተገኘው ለውጥ የመጣው ከኢትዮጵያ ሁኔታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያገኘነው መሪ እግዚአብሄር የሰጠን ሰው ነው፡፡ በጣም ጥሩ ሰው አግኝተናል፡፡›› ያሉት አቶ ቡልቻ ስለዶ/ር አብይ ሲገልፁ ‹‹ኢህአዴግ ሳያውቅ ይህንን ሰው ሰጠን፡፡ እኔ ምርጫው ሲደረግ አልነበርኩም፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ዶክተር አብይን መረጡ፡፡ እኔ የተሻለ ሰው የሚገኝ አይመስለኝም ነበር፡፡ እና ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡›› ብለዋል፡፡ አሁን በአንዳንድ ቦታዎች በኦነግና በመንግስት መሀከል ግጭት እንዳለ መስማታቸው እንደሚያሳስባቸው ያስረዱት አቶ ቡልቻ ይህንን ጉዳይ በመሸማገል መፍታት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
ከኦነግ መሪው ዳውድ ኢብሳ ጋር በአስመራ ተገናኝተው እንደነበር የተናገሩት አቶ ቡልቻ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልፁ ደግሞ ‹‹የኦነግ መሪን ዳውድ ኢብሳን አውቀዋለሁ፡፡ ከአስመራ እንደመጣ አግኝቼዋለሁ፡፡ ታረቃችሁ አይደል? ብዬ ጠየቅኩት፡፡ አዎን በደንብ ታርቀን፣ የምንሰራውንና የምናደርገውን ሁሉ ተስማምተን ነው የመጣነው ብሎ መልሶልኛል፡፡ እኔም በምላሹ ተደስቼ ነበር፡፡ አንድ ላይ መሆናችን አስደስቶኝ ነበር፡፡ ግን የእርሱ ሰዎች በወለጋ በኩል ከመንግሥት ፖሊሶች ጋር ለምን እንደሚጣሉ አይገባኝም፡፡›› ብለዋል፡፡
ኦነግ በወለጋ በተመሰረተበት ወቅት ተጋብዘው እንደነበር፣ ገንዘብም ተጠይቀው እንደሰጡ፣ ነገር ግን የኦሮሞ ነፃነት የሚለው ጉዳይ እንዳልጣማቸው በወቅቱ ለነበሩት አመራሮች መግለፃቸውንም አብራርተዋል፡፡ ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ተለይቶ ሌላ አገር መሆን አለበት የሚለውን የኦነግን አቋም ተቃውመው ድርጅቱ ውስጥ ሳይገቡ መቅረታቸውንም አውስተዋል፡፡ ያለፈውን 27 ዓመታት እንዴት ይገልጹታል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ቡልቻ ሲመልሱ ‹‹ በእነርሱ ዘመን ድንቁ ርና ነው የሚበዛው፡፡ ሰው አያውቅም እንጂ እነርሱ አሁንም ጉልበት አላቸው፡፡ የሰሩት በድንቁርና ነው፡፡ ሰው ሲያስሩ፣ ሲገድሉ፣ ገንዘብ ሲሰርቁ ዓይን የላቸውም፡፡ ጊዜው ያልፍና እንቀጣለን አይሉም፡፡ እኔ ፓርላማ ውስጥ አቶ መለስን ብዙ ጥያቄ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡
እርሳቸው ስልጣን መጠቀምን እንጂ ሌላ ምንም የሚያስቡት ነገር የለም፡፡›› በማለት አስረድተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን አስተዳደር ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲናገሩ በተጠየቁበት ወቅት ደግሞ ‹‹መቼ ተጠናና፡፡ ደካማና ጠንካራ ጎንነው ብሎ ለማለት አይቻልም፡፡ ሰውዬው ጥሩ ነው ከማለት በስተቀር፡፡ ግን ሰውዬው እንዲሁ ሰው ይወደዋል፡፡ እርሱ ሲናገርም ሃሳቡ ግልጽ፣ጥሩም ነው፡፡ ገና ነው አሁን ምንም ማለት አይቻልም፡፡ ገና የድሮ ሥርዓት ወድቆ የአሁኑ አልተተካም፡፡›› ሲሉ መልሰዋል፡፡