March 7, 2013
30 mins read

ቪቫ ኢትዮጵያ! ቪቫ ምኒልክ! (የአድዋው ድል)

በሰሎሞን ተሰማ ጂ.
semnaworeq.blogspot.com
የዐድዋ ጦርነት እስከዛሬ በአፍሪካም ምድርና በአፍሪካ ታሪክ ከተከናወኑት ጦርነቶች ከፍተኛውን የዋጋና የክብር ድልድል የያዘ ጦርነት ነው፡፡ አኒባል የአልፕን ተራሮች ዞሮ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት ካሸነፈ ወዲህ፣ አንድ አውሮፓዊ ጦር በአፍሪካውያን ጦር ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ ጦርነቱ ብዙ መልክና ብዙ ቅጽል ተሰጥቶታል፡፡ ጦርነቱን የአቤልና የቃዬል ጦርነት አካል አድርገው የገለጹትም ነበሩ፡፡ ሆኖም፣ ይላሉ ተመልካቾቹ “ነፍሰ-በላው ቃዬል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአቤል እውነትና ጽድቅ ተሸንፏል፤” ሲሉ መስክረዋል፡፡ ገሚሱ የስልጡኗ አውሮፓና የኋላ-ቀሯ አፍሪካ ጦርነት ነው፤ ከማለትም አልፈውና ተርፈው “የዘር ታፔላ” ለጥፈውበት፣ የጥቁሮችና የነጮች ፍልሚያ አድርገው ያራገቡትም አልጠፋም፡፡ ገሚሶቹ ደግሞ፣ የካቶሊካዊቷ ሮማና የኦርቶዶክሳዊቷ ኢትዮጵያ ፍልሚያ አድርገው አስበውታል፡፡ እርግጥ ነው የአራዳው ጊዮርጊስ ጽላትና አቡኑም በጦርነቱ ሥፍራ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል፣ በዐድዋው ጦርነት ወቅትና ከአርባ አመታት በኋላም በተደረገው የአምስት ዓመቱ የወረራም ዘመን ጊዜ የሮማ ሊቃነ-ጳጳሳት በአደባባይ ተገኝተው በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ስም ባርከው ልከዋል፡፡ በመሆኑም፣ ጦርነቱ የአራዳውን ጊዮርጊስ ጽላት/ታቦት ተሸክመው የዘመቱት ኦርቶዶክሳዊያንና በሊቀ-ጳጳሳቶቻቸው የተባረኩት ካቶሊኮች ጦርነት ሆነ፡፡ ውጤቱም ለኦርቶዶክሳውያኑ ያደላ ሆነ፡፡
ምንም እንኳን- ጓንዴ፣ ውጅግራና ሰኔኔ የመሳሰሉትን “ኋላ-ቀር” መሳርያዎችን የታጠቀው የኢትዮጵያ/የአፍሪካ ጦር፣ እጅግ ሜካናይዝድ ከሆነው አውሮፓዊ ጦር ጋር ጦርነት የገጠመ ቢሆንም፤ ጦርነቱን በወኔና በቁጣ የተነሳሳው የአፍሪካ ጦር ለዓላማውና ለሉዓላዊነቱ ሲል ወራሪውን ኃይል መሣሪያና ትጥቅ “ኢምንት አድርጎ” አንኮታኮተው፡፡ ዜናውም፣ በቅኝ ግዛትና በባርነት ጥላ ስር ለነበሩት ከደቡብ አሜሪካ እስከ አላስካና ደቡባዊ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያ እስከ አውስትራልያና እስያ ያሉትን ቅኝ-የተገዙ ህዝቦች ሁሉ ለሰብዓዊ ክብራቸውና ለነፃነታቸው እንዲታገሉ የአዋጅ አንቢልታውን፣ ከዐድዋ ተራሮች አናት ላይ ስለነፋው፣ አድማሳትን ተሻግሮ አስተጋባ፡፡ ዐድዋም የመላው ጭቁን/ተወራሪ ህዝቦች የ“ነፃነት ፋና” ተለኩሶ የበራባት፣ የሰብዓዊ እኩልነትና የዘር መድሎ ቀንበር የተሰበረባት፣ ድሉም ዳር እስከዳርም ለዓለም የተሰበከባት ደጀሰላም ሆነች፡፡ የጥቁር ሕዝብ የዜማ፣ የግጥም፣ የስዕልና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ማጠንጠኛ የሆነ እንደአድዋ ማን አለ? (ነፍስ ሔር ለክቡር እመ ክቡራት – ሰማዕታት!)
ከላይ እንዳልነው፣ የዐድዋ ጦርነት የሥልጡኗ አውሮፓና “የኋላ-ቀሯ” አፍሪካ ፍልሚያ ተደርጎ መታየቱ ጥርጥር የለውም፡፡ (“ኋላ-ቀሯ” የሚለው ቅጽል የአውሮፓውያኑ ስያሜ ስለሆነ ፈጽሞ ስለማልቀበለው ነው በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የቀነበብኩት፡፡ ሥልጡንነትና “ኋላ-ቀርነት” ራሳቸው ተምታትተው-የሚያምታቱ ሃሳቦች ስለሆኑ፣ ፍረጃውን አምኖ መቀበሉም ይከብዳል፡፡ አንድ ጥያቄ ብቻ ብናነሳ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ለመሆኑ በማን ዐይን ነው “ይኼ የሠለጠነ ነው፤ ያኛው ደግሞ ያልሠለጠነ ነው!” ለማለት የሚቻለው?) ይህንን ጉዳይ በተመለከተ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በጻፉት “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው (2005፣ ገጽ 137 ላይ) እንደገለጹት “በዐድዋው ጦርነትና በኢትዮጵያም ድል አድራጊነት የአውሮፓ መንግሥታት በእጅጉ ተረበሹ፡፡ ኢጣሊያ በአድዋ ላይ የደረሰባት ውርደት የአውሮፓም ውርደት ሆነ፡፡ የኢትዮጵያም ድል የአፍሪካውያንና የጥቁር ሕዝቦች ድል ሆነ፡፡ የኢትዮጵያውያንም የነጻነት፣ የአገር ፍቅር፣ ቆራጥነትና የውጊያ ችሎታ ተደማምረው አንድን የአውሮፓ ኃይል ለማንበርከክ ወኔና ቁርጠኝነት ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ለሌሎችም የአፍሪካ ክፍሎች አርአያ ሆኖ እንዳይደጋገም የአውሮፓ ቄሳራውያን ኃይሎች ፈሩ፡፡ በተለይም ብሪታኒያና ፈረንሣይ ከባድ ሥጋት አድሮባቸው ነበር፡፡” ስለሆነም፣ በጣሊያን ጎትጓችነትና በእንግሊዝና በፈረንሣይ መንግሥታት አሽቃላጭነት (sponsorship)፣ እንዲሁም በካቶሊካዊቷ ቫቲካን መሰሪነት የተቀነባበረ የዕርቅ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ተሯሩጠውም፣ ኔራዚኒን የተባለውን መልዕክተኛም ደብዳቤ አሲይዘው ወደአዲስ አበባ ላኩ፡፡
የካቶሊኩን ጳጳስ፣ የሊዮ 13ኛን ያህል የተንገበገበም ያለ አይመስልም፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በ1983 ዓ.ም ባሳተሙት “አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በተባለው መጽሐፋቸው (በገጽ 523 ላይ እንደገለጹት)፣ ሊዮ 13ኛ በጣሊያን ያሉት የምርኮኞቹ ቤተሰቦችና ወዳጆች ፈጥረው ስለያዟቸው ለአፄ ምኒልክ ደብዳቤ ጻፈና ላከ፡፡ ደብዳቤው እንዲህ ይላል፤ “እኛም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበልነው አደራ እንደልጆቻችን ያኽል እንወዳቸዋለንና እነዚህን ምርኮኞች በቶሎ በነፃ እንዲለቋቸው በቅድስት ሥላሴና በድንግል ማርያም እየለመንኩኝ፣ በዓለም ካለው በሚወዱት ነገር ሁሉ ስም እማጸንዎታለሁ፤” ሲል ይሽቆጠቆጣል፡፡
ቢሳካላቸው ኖሮ፣ ከዘመቻቸው በፊት በካቶሊክ ኃይማኖት ሰባኪነት ስም በገቡ “ሰባኪ-ነን” ባይ ሰላዮች አማካኝነት በተጠናው መሠረት፣ በቅኝ ሊገዙት በወጠኑት አገርና ህዝብ ላይ በቀላሉ አስተዳደራቸውን እንደቆዳ ሊገደግዱት ነበር፡፡ በዚሁ ቀቢጸ-ተስፋም የተነሳሳው የኢጣልያና የእንግሊዝ መንግሥታት በርካታ አገር አሳሾችን (Explorers) እና ቀሳውስቱን (እነአባ ማስያስንና ሌሎችንም) ልኮ ከሰለለ በኋላ ነበር፣ ድሉን በወታደራዊ መስክም ለማረጋገጥ ቆርጦ የተነሳው፡፡ የኢትዮጵያውያን ወኔና ጀግንነት ግን ይህንን ዓላማቸውን “አከሸፈው!” (ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፤ “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ገጽ 31)፡፡
በዚህ የከሸፈ የቅኝ-ግዛት እቅድና የተኮላሸ የአውሮፓውያን ተስፋፊነት የተደሰቱ ሶሻሊስት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በጣሊያን፣ በእንግሊዝና በፈረንሣይም ነበሩ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን፣ እንደኢጣሊያኑ ክሪቲካ ሶሻሌ (Critica Sociale) ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ እንደ ቱራቲ በድፍረት የጻፈ አይገኝም፡፡ ጋዜጠኛው ቱራቲ እንዲህ ሲል በወኔና በምልዓት ለእውነት ስለእውነት ጻፈ፡፡ “ጣሊያን ወደዐድዋውና ወደሌሎችም ከኢትዮጵያ ጋር ወደተደረጉት ጦርነቶች የገባችው፣ ለእንግሊዛውያን አገልጋይና አሽከር ሆኖ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የኢጣሊያናውያን ሀብትና ደም ያላግባብ ፈሰሰ፡፡” ሲል በእጅጉ ተቸ፡፡ ቀጠል አድርጎም፣ “የጣሊያንና የእንግሊዝ መንግሥታት በአፍሪካ ስለተቀዳጁት የቅኝ-ግዛትና የተስፋፊነት ድል እንደጽጌረዳ የፈካ ውሸት እየፈበረኩ ይመጻደቁ’ጂ፣ በእርግጥ ኢትዮጵያ ድል አድርጋለች፡፡….ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ኢትዮጵያ!” ሲል አወድሷል (ሪቻርድ ፓንክረስት፤ (1998 እ.አ.አ) ገጽ-531)፡፡ ይኼንን የእንግሊዝ መንግሥት ሸርና ተንኮል የተረዳቸው አንጎራጓሪም እንዲህ ብላ ነበር፡፡
እንግሊዝ፣ እንግሊዝ
ይገባሃል መርዝ፡፡
ሸሞንሟና፣ ሸሞንሟና
ይፈላልህ ቡና፡፡

(ለዚያች አንጎራጓሪ፣ “ሸሞንሟናው ሰው” ያገሯ ልጅ ነው፡፡) (ምንጭ፣ ግጥሙ ቅድመ-አያቴ ከነገሩኝ ማስወሻዬ ላይ የተገኘ ነው፡፡)
ይህ ሀሳብ የጋዜጠኛው ቱራቲ ብቻ አልነበረም፡፡ በተለይም፣ በኢጣሊያን ፓርላማ ውስጥ የነበሩትን በሶሻሊስት ፓርቲ አባልነት የተደራጁ ከሕሊናቸው ጋር ያልተጣሉ ጣሊያናውያንም በየመድረኩና በየአደባባዩ “ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ምኒልክ!” እያሉ ፀረ-ቅኝ ግዛት አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ ከላይ እንደገለጽነው፣ የክሪቲካ ሶሻሌ ዋና አዘጋጅ-ቱራቲ “አቤልአውያን” ያላቸውን ኢትዮጵያውያንና መሪያቸውን አፄ ምኒልክንም ካወደሰ በኋላ፣ የኢጣሊያንንና የአውሮፓውያኑንም ስልጣኔ “የቃዬልአውያን ሥልጣኔ” ነው ሲል ኮንኖታል፡፡ ቱራቲ አጽንኦት ሰጥቶ እንደገለፀው፣ “የኢጣሊያን ሥልጣኔ-የነፍሰ በላው የቃየል ሥልጣኔ ነው አካል ስለሆነ የተሸናፊነትና የጨካኝነት ሥልጣኔ ነው፤” ሲል አትቷል፡፡

የቱራቲንም ሆነ የሌሎቹን ተቺዎች ሃሳብ የሚያጠናክሩ በርካታ ግጥሞችና አባባሎች በአማርኛም አሉ፡፡ ትልቁ ገጣሚ ሐሰን አማኑ እንደተጠበበው፣ የአፄ ምኒልክ ጀግንነት እንዲህ ነበር የተወደሰው፡፡
“ሸዋ ነው ሲሉት፣ ዐድዋ የታየው፤
“ሺናሻ መላሽ፣ ወንዱ አባ ዳኘው፡፡”
ይልና ለጠቅ አድርጎም፤
“ወዳጁም ሣቀ፣ ጠላቱም ከሳ፤
“ተንቀሳቀሰ ዳኘው ተነሣ፤
“አራቱም አህጉር፣ ለሱ እጅ ነሣ፡፡” (ዝክረ ነገር፤ ገጽ 880)
ሐሰን አማኑ እንዲሁም ቱራቲ እንዳሉት፣ በአፄ ምኒልክ መሪነት የተደረገው የዐድዋ ጦርነት ከፍተኛ ዝናን ለመሪው ለአፄ ምኒልክም ሆነ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል፡፡ ሐሰን አማኑ እንዳለው፣ ወንዱ ምኒልክ አራቱንም አህጉራት እጅ አስነስቷል፡፡ የኢትዮጵያና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ወዳጆች በደስታ ፍንክንክ ብለው ከመሳቅም አልፈው፣ የአብሲኒያን ባቢቲስት ቸርቾችን በሰሜንና በደቡብ አሜረካን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ተመሥርተዋል፡፡ ዳዊት ለመድገምና ውዳሴ ማርያምም ለማንበልበል ሲሉ ግዕዝ ማጥናት የጀመሩ ጥቁር አሜሪካውያንና ደቡብ አፍሪካውያን ቁትር ቀላል አልነበረም፡፡ ዝርዝሩን “Adwa፡ Victory Centenary Conference 26 Feb.- 2 March 1996” published in1998-AAU” እና “Adwa: A Dialogue between the Past and the Present (1997)” የተባለውና የማይምሬ መናሰማይ (Maimire Mennasemay) ጥናት ሰፊ ሃተታን የሚያቀርብ ስለሆነ ማንበቡ የበለጠ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡
በተመሣሣይ መልኩም፣ ከዐድዋ ጋር በተያያዘ ስለወሎው ንጉሥ ሚካኤልና ስለታላቁ ጀግና ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) ሐሰን አማኑ የሚከተሉትን የሙገሳ ግጥሞች ተቀኝቷል፡፡ ስለንጉሥ ሚካኤል እንዲህ አለ፡-

“ማን በነገረው ለጣሊያን ደርሶ፤

“ሚካኤል መጣ ረመጥ ለብሶ፡፡ (ዝክረ ነገር፤ ገጽ 883)
(መጪው “ሚካኤል” ሰውም መልአክም ነው፡፡ ሰው ሲሆን፣ ንጉሥ ሚካኤል ነው፡፡ መልአኩ ሚካኤል ሲሆን ደግሞ ቅዱስ ጎርጊስን አትጊና አጽኚም ነው፡፡)
ስለፊታውራሪ ገበየሁ የተገጠሙት ሁለት መንቶዎች ግን በስፋት የሚታወቁ ናቸው፡፡ የነዚህም ገጣሚ ሐሰን አማኑ ነው፡፡
“ታጭዶ ሲወቃ፣ ዐድዋ ላይ ገብስ፤
“አናፋው ዘልቆ፣ (ጎራው) በመትረየስ፡፡
“ዐድዋ ሥላሴን፣ ጥሊያን አረከሰው፤
“ገበየሁ በሞቴ፣ ግባና ቀድሰው፡፡” (ዝክረ ነገር፤ ገጽ 885)

ተብሎለታል፡፡ ገጣሚው ሐሰን አማኑ፣ ከአስር ሰላይ “የካቶሊክ ቄሶችና ሚሽነሪ ነን ባዮች” ይልቅ፤ ዳዊት ደጋሚው፣ ጾምና ጸሎት አዘውታሪው ፊራውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) የተሻለ ቀዳሽነትና ብጽዕና አለው፣ ለማለት (ሊል) ፈልጓል፡፡ ወዶ አይደለም፡፡ በካቶሊካዊ አስተምህሮትና ስብከት ያደጉት የጣሊያን ወታደሮች በየሄዱበት ሁሉ የኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያነትን የጦር ግምጃ ቤትና ምሽግ አድርገው ስለተጠቀሙበት፣ የፈረስና የበቅሎዎችም ማሰሪያ አድርገውት ስለነበረ ነው፡፡ ሐሰን አማኑ የሕይወት ታሪኩ እንደሚያመለክተው ቦሩ ሜዳ ላይ ከነንጉሥ ሚካኤል ጋር ወደኦርቶዶክስ ክርስቲያንነት አማኒነት የተመለሰ ሰው ስለነበር፣ ጣሊያን ያንን በማድረጉ ከፍተኛ ቁጭትና እልህ ተሰምቶታል፡፡ ወይም ደግሞ አጠገቡ የነበሩትን ሰዎች እልህና ብስጭት አስተውሏል፡፡ አስተውሎም አላበቃ፣ “ጥሊያን (ጠላት) አረከሰው” ሲል ይንገበገባል፡፡ መፍትሔውም፣ ገበየሁ (ጎበዝ አየሁ!) ገብቶ ቢቀድሰው እንደሚሻል፣ “በሞቴ” ሲል ተማጽኖ ይጠይቀዋል፡፡
ጣሊያኖች በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸሙት ድርጊት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ አይነት አልነበረም፡፡ በተለይም ማጆር (ሻለቃ) ቶዞሊ በሐላይ በተባለ ቦታ-ደጃዝማች ባሕታ ሐጎስን ተዋግቶ ከገደለው በኋላ ለሌሎች የኢትዮጵያ ተዋጊዎች መቀጣጫ እንዲሆን ብሎ አስክሬኑን እንዳይቀበር አደረገው፡፡ አሞራና ጥንብ አንሣ ተጫወተበት፡፡ (ይህንኑ ኢ-ሰብአዊ የሆነ አውሮፓዊ ሥልጣኔ ይዘው ነው እንግዲህ፣ እኛን ኋላ-ቀር የሚሉን፡፡) ሆኖም፣ በኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም አላጌ ላይ በተደረገው ጦርነት ማጆር ቶዞሊም በሰባት ዐረር ተመትቶ ተገደለ፡፡ ራስ መኮንንና ፊታውራሪ ገበየሁም በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አስክሬኑን አጅበውና ወታደራዊ ሰልፍ አዘው በክብር ቀበሩት፡፡ በቶዞሊ መገደል አንጀቱ ቅቤ የጠጣው አዝማሪ/ገጣሚ እንዲህ ሲል ተቀኘ፤
“አላጌ አገሩ ላይ፣ ሲወድቅ ማጆር፤

“እንደግራኝ ሁሉ፤ በሰባት ዐረር፡፡”

ተባለ፡፡ ልብ በሉ፣ መጆር ቶዞሊም እንደግራኝ በሰባት ዐረር እንዲገደል የተደረገው በዘፈቀደ አይደለም፡፡ ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ግራኝ ማህመድ ያንን ሁሉ አብያተ-ክርስቲያን ሲዘርፍና ሲያቃጥል፣ እነዚያን ሁሉ መነኮሳትና ቀሳውስት ካልሰለማችሁ እያለ ከ15 ዓመታት በላይ ሲያጠፋና ሲያቃጥል ቆይቶ እንዴት በሰባት ዐረር “ብቻ” እንዲገደል እንደተደረገ መገመት ይቻላል፡፡ በዘመኑ፣ የክርስቲያኖቹ ተዋጊዎች ፈሪሃ-እግዚአብሔር ስለነበራቸው ነው፡፡

በተቃራኒው፣ ምንም ፈሪሃ-እግዚአብሔርም ሆነ ርዕዮተ-ዓለም ያልነበረው የንጉሥ ኡምቤርቶና የጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ጦር፣ ደጋግመው አፄ ምኒልክና ራስ መኮንን የጻፉላቸውን ደብዳቤዎች ከፍርሃት ቆጥረው ከሰሜን/ከኤርትራ ወደመኻል አገር መትመም/መግፋት ጀመሩ፡፡ አፄ ምኒልክና ራስ መኮንንም በተደጋጋሚ ስለሁለት መርሆዎች ብለው ያልተገሩትንና ለእንግሊዝ መንግሥት ሎሌነት የገቡትን የጣሊያን መሪዎች በክብር ጠይቀዋል፡፡ የደብዳቤዎቻቸው ሁለቱ ሃይለ-ሃሳቦች እንዲህ ይላሉ፤ “አንደኛ፣ ጉዳያችንን በሰላምና በወዳጅነት መንፈሥ እንጨርስ፤” የሚል ሲሆን፣ “ሁለተኛው ደግሞ፣ የክርስቲያኖችን ደም በከንቱ እንዳይፈስ እናድርግ!” የሚል ነበር፡፡ ሆኖም፣ ተደጋጋሚዎቹ ጥያቄዎችና የደብዳቤ መልዕክቶች በጣሊያን መሪዎች ዘንድ እንደፍርሃት ሳይቆጠሩም አልቀሩ፡፡ ስለሆነም፣ የጣሊያን መሪዎች፣ እንደጽጌረዳ አበባ የፈካና ያማረ መረጃ ለፓርላማ አባላቶቻቸው እየቆነጠሩ በመስጠት፣ ምክር ቤቱ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ወረራ በከፍተኛ ድምጽ እንዲደግፍ አደረጉት (ክሪቲካ ሶሻሌ)፡፡

መደምደሚያ፣
ከጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስቶ በ87ኛ ቀኑ መቀሌ የገባው የኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ የሆነ የሞራልም የሰብዕናም አቅም የነበረው ጦር ነው፡፡ በተለይም፣ “አፄ ምኒልክ የመንፈሥ ልዕልናና ቆራጥነት የሚያስከብራቸውና የኢትዮጵያን ሕዝብም የሚያከራ ነበር፡፡” (መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገጽ 136)፡፡ አፄ ምኒልክ ለጋሊያኖና ለሚመራው ጦር 500 ግመሎችና በቅሎዎችን እንዲገዙ ፈቅደውላቸው ሲያበቁ፣ ለሻለቃ ጋሊያኖም “በማለፊያ መርገፍ ኮርቻ የተጫነች በቅሎ ሰጥተው ወደእናት ክፍለ-ጦሩ እንዲሄድ አደረጉት፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከላይ በጠቀስነው መጽሐፍ በገጽ 135 ላይ እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ “በየት አገር ነው ጠላቱን ካሸነፈና ካንበረከከው በኋላ እንዲህ ያለ ንክብካቤ የሚደረግለት?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እውነት አላቸው፡፡ ይህም እውነተኛ ጨዋነትና ፈሪሃ-እግዚአብሔር ነው የጣሊያናዊውን ቱራቲን ልብ ማርኮና ለአድናቆት አነሳስቶ “ቪቫ ምኒልክ!” ያሰኘው፡፡ (በነገራችን ላይ፣ በጣሊያንኛ “ቪቫ” ማለት “ረጅም እድሜ ይስጥህ!” እንደማለት ነው፡፡ ስለሆነም፣ “ቪቫ ምኒልክ” ሲባል፣ “ረጅም ዕድሜ-ለምኒልክ!” እንደማለት ነው፡፡)

ሌላም መታወስ ያለበት ነጥብ አለ፡፡ የአድዋን ድል ተከትሎ ስለመጣው የኢትዮጵያ ወሰን ጉዳይ ነው፡፡ በግንቦት 1889ዓ.ም ጣሊያኖቹ ከአፄ ምኒልክ ጋር ስለወሰን ጉዳይ እንዲነጋገር ኔራዚኒ የተባለውን መልዕከተኛ ላኩት፡፡ አፄ ምኒልክ ራሳቸው፣ በአንድ ካርታ ላይ የኢትዮጵያን ወሰን አስመልክተው መስመር አሰመሩና ማስመሩም ላይ ማኅተማቸውን አድርገውበት ሲያበቁ፣ “የኢትዮጵያ ወሰን ከዚህ እስከዚህ ድረስ ነው፤” ብለው ለኔራዚኒ ሰጡት፡፡ ከሁለት ወራት በኋላም የጣሊያን መንግሥት የአፄ ምኒልክን የወሰን ካርታ እንደተቀበለው አስታወቀ፡፡ ሆኖም፣ አፄ ምኒልክ አንድ ትልቅ ስኅተት ሠሩ፡፡ ለኔራዚኒ ካርታውን ሲሠጡት ለራሳቸው ቅጂ አላስቀሩም ነበር (መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገጽ 148)፡፡ ከዚህም ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ወሰን በሰሜን-ከኤርትራ፣ በምስራቅ ከሶማሊያ እና በምዕራብም ከሱዳን ጋር እንደላስቲክ እንዳንዴ ሲሳብ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲሰበሰብ አንድ መቶ አስራ አምስት አመታት ተቆጠሩ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ1999 ዓ.ም ባሳተመው፣ ፊ/ሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም “የሕይወቴ ታሪክ/ኦቶባዮግራፊ” ብለው በጻፉት መጽሐፋቸው በገጽ 73 ላይ እንደገለጹት፣ “ራስ መኮንንና አፄ ምኒልክ በዘመናቸው የሠሩት ሥራ የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን፤ ስኅተታቸውን አውሮፓ ለትምህርት ከሔድኩ በኋላ እየገመትኩት መገረሜ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዚያን ጊዜ ዕውቀትና ኃይል በማነሱ ይቅርታ ሊደረግላቸው የተገባ ነው፡፡ እነሱ በደከሙበት ሥራ ብዙ ተጠቅመናል፡፡ በስህተታቸውም አደጋ ተቀብለንበታል፡፡ …የጣሊያን መንግሥት በዐድዋ ጊዜ ዕውቀቱም ኃይሉም ትንሽ ነበር፡፡ …በእኛ ስህተት አገር በጁ እንደሆነ ስለቀረ (ኤርትራን ማለታቸው ነው፤) ሃምሳ ዓመታት ያህል ቆይቶ ተሰናዳና አጠቃን፤….” ሲሉ እርር ድብን ይላሉ፡፡ ከፍ ብለውም፣ “ዐድዋ ላይ ያን ያህል ሰዎች ተላለቁና፣ ጣሊያን የወሰደብንን አገር ሳናስለቅቅ ሄድን፡፡…የድሉን ዋጋ ዐደዋ ከራስ መኮንን ጋር በዘመትኩ ጊዜ ለመገመቻ የሚሆን ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ ኋላ፣ በአውሮፓ መማር ከጀመርኩ በኋላ ግን እያስታወስኩት እንደ እሳት ያቃጥለኝ ጀመር፡፡” እያሉ ስለዐድዋ ድልና ጥሎት ስላለፈው ጠባሳ ይገልጻሉ፡፡ (የሳምንት ሰዎች ይበለን፡፡)

በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ. 153 ላይ፤ በየካቲት 23 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣ ነው::

Latest from Blog

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ “ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና

ጀልባዋ አትሰምጥም፤ የሚሰምጥ ግን አለ!

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] (https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/) ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

Go toTop