June 9, 2011
5 mins read

ስፐርስ ቤልን ለማቆየት እቅድ ይዟል

ቶተንሃም ሆትስፐር በመጪው ክረምት ለሚቀጥለው ውድድር ዘመን ተጨዋቾችን በማስፈረም ተጠናክሮ ለመቅረብ ከማሰብ ይልቅ ጋሬዝ ቤልን ለማቆየት ቀዳሚ እቅድ መያዙ ተነግሯል፡፡ ክለቡ ዘንድሮ ለተከታታይ በጣላቸው ነጥቦች ምክንያት የቻምፒየንስ ሊግን ተሳትፎ ለማንቸስተር ሲቲ አስረክቧል፡፡ ሆኖም ባለፈው እሁድ አንፊልድ ድረስ ተጉዞ ሊቨርፑልን ማሸነፉ ግን ለዩሮፓ ሊግ ለመሳተፍ ተስፋውን አለምልሞታል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የክለቡ ኃላፊዎች በስኳዱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ስፐርስ ሊቀመንበር ዳንኤል ሌቪም ቤልን በክለቡ በማቆየት ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡ ይህም ሆኖ በመጪው ክረምት አሰልጣኝ ሀሪ ሬድናፕ አዳዲስ ተጨዋቾችን እንዲያስፈርሙ ድጋፍ ይሰጧቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን ክለቡ አንዳንድ ተጨዋቾቹን ለመሸጥ እና አጠቃላይ የስኳዱን ደመወዝ ለመቀነስ እቅድ ነድፏል፡፡
ሊቪ በርካታ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን ተጨዋቾች መሸጥ ይፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በውሰት ሌሎች ክለቦች እየተጫወቱ የሚገኙት ሮቢ ኪን (ዌስት ሀም)፣ ጂሚ ኦሀራ (ዎልቭስ)፣ ጂኦቫኒ ዶስ ሳንቶስ (ሬሲንግ ሳንታንዴር) እና ዴቪድ ቤንትሌይ (በርሚንግሀም) ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ተከላካዩ ጆናታን ውድጌት እና ግብ ጠባቂው ካርሎ ኩዲቺኒ በመጪው ክረምት ከክለቡ ጋር ያላቸው ኮንትራት የሚጠናቀቅ ሲሆን አዲስ ውል ይቀርብላቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቶተንሃም ለሮማን ፓቭለዩቼንኮ፣ ኒኮ ክራንያካር፣ አለን ሀተን፣ ከራን ቼርሉካ እና ዊልሰን ፓላሲዮስን ለመሳሰሉ ተጨዋቾች የሚቀርብለትን የዝውውር ጥያቄ ለማድመጥ ዝግጁ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ክለቡ ከሚለቃቸው ተጨዋቾች በተጓዳኝ አጥቂ ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ ይህንን ለማሳካትም ላለፈው ጃንዋሪ የቪያሪያሉን አጥቂ ጁሴፔ ሮሲን በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ሙከራ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ከዚህ በኋላም በተለይ ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ መሆኑን ተከትሎ ታላላቅ ተጨዋቾችን ለመሳብ ይቸገራል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው ቢልን ለማቆየትም ከፍተኛ ትግል ይገጥመዋል የሚል እምነት አለ፡፡ በተለይ ደግሞ የዌልሱ አሰልጣኝ ጋሪ ስፒድ ተጨዋቹ በመጪው ክረምት ዋይት ሀርት ሌንን እንዲለቅ መገፋፋቱ ለስፐርስ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ባለፈው ዲሴምበር ዌልሰን በአሰልጣኝነት የተረከበው የቀድሞው የኒውካስል ኮከብ ቢልን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ቀጣዩን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ለየትኛውም ተጨዋች የሚበጀው ቻምፒየንስ ሊግን በመሰለ ታላላቅ ውድድር ላይ መሳተፍ ነው፡፡ ቤልም ዘንድሮ ነጥሮ መውጣት የቻለው በዚሁ ውድድር ላይ ነው፡፡ በየዓመቱ ተሳትፎውን ባገኘው ቁጥር ደግሞ ብቃቱ ይጎለብታል፡፡ በእርግጥ ተጨዋቹ የራሱ እምነት እና አመለካከት ይኖረዋል፡፡ ምናልባት ግን ቶተንሃም ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ለቻምፒየንስ ሊግ አልፎ ቢሆን ኖሮ ለውሳኔ አይቸገርም ነበር›› ሲል የመስመር አማካዩ ስፐርስን እንዲለቅ መክሮታል፡፡

Go toTop