ከአቶ ገብሩ አስራት ጋር አጭር ቆይታ

አንዳንዴ ስምን መላዕክ ያወጣዋል ይባላል፡፡ ገብሩ ማለት ገበረ፣ ገብረ የሚለው የግዕዝ ቃል ርቢት ነው፡፡ ትርጉሙ ደግሞ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ገብሩ የማን አገልጋይ እንደሆነ ደግሞ ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ ገብረ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ገብሩ እውነተኛ አገልጋይ ለመሆን የታደለው ደግሞ አንድ ልዩ ብቃት ስላለው ነው፡፡ ራስን ማወቅ፣ በራስ መተማመንና ታማኝነት፡፡ በራሱ የማይታመን ሰው ለሌላ ይቅርና ለራሱም አይሆንምና፡፡ ገብሩ የዚህ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት አባል በነበረበት ጊዜ ከስርዓቱ ጋር በጋራ ለፈፀማቸው ጥፋቶች የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ በአደባባይ ይቅርታ የጠየቀው በራሱ ስለሚተማመን ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉ ራሳቸውን የሚያውቁ፣ ስህተታቸውን ያለማመንታት ለመቀበልና ኃላፊነት ለመውሰድ ድፍረት ያላቸው በአጠቃላይ በራሳቸው ላይ ስልጣን ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአደባባይ ጥፋትን በመቀበል ንስሀ ለመግባት በራሱ ላይ ስልጣን ካለው ሰው በቀር ማንም አያደርገውም፡፡ ለማንም አይቻለውምም፡፡ ገብሩ አስራት ማነው?
ጥያቄ- ገብሩ አስራት ማነው? የት ተወለደ እና አደገ? የትስ ተማረ?
አቶ ገብሩ፡- እኔ የተወለድኩት በ1943 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ነው፡፡ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት መቀሌ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በአፄ ዮሐንስ እና በወቅቱ መሰረተ ትምህርት ይባል በነበረው ነው የተማርኩት፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ በአፄ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የተማርኩ ሲሆን 12ኛ ክፍል ደግሞ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በእደ ማርያም ት/ቤት ወይም ላብራቶሪ ይባል በነበረው ት/ቤት በ1964 ዓ.ም ነው ያጠናከኩት፡፡ ከዚያም በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመት ተምሬያለሁ፡፡
ጥያቄ- ከልጅነትህ ጀምሮ አስተዳደግህ ምን ይመስል ነበር?
አቶ ገብሩ፡- ይሄ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡ ስለ እራሴ ብዙም የምገልፀው የለኝም፡፡ ከእኔ ይልቅ ሌሎች ቢናገሩ የተሻለ ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን እዚያ መቀሌ ሳድግ ከልጅነቴ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እሰራ ነበር፡፡ ከአባቴ ጋርም እነግድ ነበር፡፡ አባቴ የአቡጀዲ ነጋዴ ስለነበር ከእርሱ ጋር እሰራ ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ልጆች አስተምር ነበር፡፡ ፈረንጆችንም ትግርኛ አስተምር ነበር፡፡ እና ከልጅነቴ ጀምሮ ስራ እየሰራሁ ነው ያደኩት፡፡ ከዚያ ሌላ ግን ዋናው ትኩረቴ ትምህርት ላይ ነበር፡፡ አጠና ነበር፣ የሚሰጠኝን የቤት ስራ እሰራ ነበር፣ በክፍል የሚሰጠኝን መደበኛ ትምህርት ውጪም አነብ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ዩኤስአይኤስ የሚባል የአሜሪካን ላይብረሪ መቀሌ ውስጥ ነበር፡፡ መፅሐፍ እየተዋስኩም አነብ ነበር፡፡ ስለዚህ እውቀት በት/ቤት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ውጪም የማገኛቸው ማለትም በራሴ ጥረት በማንበብ እና ከጓደኞቼ ጋር በመወያየት ተጨማሪ እውቀት አገኝ ነበር፡፡ እንዲሁም ሰዎችን አዳምጥ ነበር፡፡ በተለይ ታሪክ የሚያውቁ ሰዎችን ማዳመጥ እወድ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥ በተለይም ሽማግሌዎች በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የነበሩ ሰዎች በህይወት ስለነበሩ እነሱም ስለ ታሪክ ብዙ ያወሩኝ ነበር፡፡ ይሄም ትልቅ ትምህርት እና እውቀት ሆኖ አገልግሎኛል፡፡
ጥያቄ- ፈረንጆችን ትግሪኛ ታስተምር የነበረው ስንተኛ ክፍል እያለህ ነው?
አቶ ገብሩ፡- ይህን አደርግ የነበረው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ፒስ ኮርፕስ የሚባሉ አሜሪካዊያን ነበሩ እነሱን ነበር የማስተምረው፡፡ ለአንድ ሰዓት አንድ ብር ነበር የሚከፈለኝ፡፡ በሳምንት አምስት ሰዓት ነበር የማስተምረው፡፡ በወር ደግሞ እስከ 20 ሰዓት አስተምሬ 20 ብር አገኝ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ 20 ብር ማለት በጣም ትልቅ ብር ነበር፡፡ እኔ እነሱን ሳስተምር እንግሊዝኛ ቋንቋ ለማሻሻልም እንዲረዳኝ ብዬ ነበር፡፡
ጥያቄ- የአሁኑ ገብሩ አስራት የልጅነት እና የተማሪነት የህይወት ፍልስፍና ውጤት ነው?
አቶ ገብሩ፡- ይሄም እጅግ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ እኔ እንግዲህ ሙሉ ትኩረቴ ትምህርት ላይ ነበር፡፡ ከዚያ ጎን ለጎን ግን በወቅቱ ከነበረው ዓለም አቀፍ ሁኔታ የአገራችን ሁኔታ አንፃር በትምህርት ብቻ በዚህች ሀገር ለውጥ እንደማይመጣ የተገነዘብኩበት ሁኔታ ነበር፡፡ እንግዲህ በመጀመሪያው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳታፊ ነበርኩኝ የምለው በ1961 ዓ.ም የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ወታደሮች ት/ቤታችን ገብተው ደበደቡን፡፡ እኔም ተመትቻለሁ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ታሪካዊ ሁኔታዎችን የሀገራችን እና የውጭ ሁኔታዎችን አገናዝብ ነበር፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ፈረንጅ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ በተለይም ሚስተር ቴይለር የተባለ አንዱ ነበር፡፡ እሱ ስርዓቱን በጣም ነበር የሚቃወመው፡፡ ያኔ የነበረው ስርዓት ፊውዳላዊ ነውና መለወጥ አለበት ይለኝ ነበር፡፡ ዓለም እየተሻሻለና እየተለወጠ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ በዚህ አይነት ሁኔታ መገኘቷ ለዕድገቷና ለብልፅግናዋ አይበጅም የሚል አስተያየት ነበረው፡፡ እኔም ይህንኑ አመለካከት በደንብ ነበር የምጋራው፡፡ መፅሐፍትም ይሰጠኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ በ1953 ዓ.ም በክቡር ዘበኛ ወታደሮች የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት አስመልክቶ ሪቻርድ ግሪን ፊልድ የፀሐፊው መፅሐፍ ስለሌሎች ኢምፓየሮች በታሪክ ውስጥም ስለ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ አብዮቶች ወዘተ… መፅሐፍትም ሰጥተውኝ አነብ ነበር፡፡ እናም ከትምህርቱም ሆነ ከማነባቸው መፅሐፍት በማገኘው እውቀት እና ግንዛቤ አኳያ የኢትዮጵያን ሁኔታ ስገመግመው እና ሳነፃፅረው ኢትዮጵያ መለወጥ እንዳለበት ተገንዝቤ ነበር፡፡ ሁለት ጊዜም ለአጭር ጊዜ ከጓደኛዬ ዘርአይ አስገዶም ጋር ፀረ ስርዓት ፅሑፍ አሰራጭታችኋል ተብለን ታስረናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ በፍ/ቤት የነበረ የክስ እና ፍርድ ሁኔታ ለማዳመጥ ሄደን ረብሻ ለመቀስቀስ ነው ወይ የመጣኸው ተብዬ ታስሬያለሁ፡፡ በዚህ ጊዜና ከዚያም በኋላ ሁኔታዎችን ስገመግማቸው ስርዓቱ ካልተለወጠ ችግሮች ማስወገድ አይቻልም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሼ ነበር፡፡ ከዚያም በመነሳት ነበር ኋላ ከፍ ወዳለ ፖለቲካ የገባሁት፡፡ እንግዲህ ይሄ ነገር አሁንም አልተለወጠም፡፡ በአገራችን ወደ 40 ዓመታት ያህል ወደኋላ መለስ ብዬ ስመለከተው እና ሳየው አሁንም ለውጥ እንዳልመጣና እንዳልተረጋገጠ ነው፡፡ እንግዲህ ያኔ ስርዓቱ የንጉስ አገዛዝ ነበር፡፡ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተገደቡ ነበሩ፡፡ አሁን ከ40 ዓመታት በኋላ ያለው ሁኔታ ሳየው የአንድ ግለሰብ እና የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት አገዛዝ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄን ሂሳብ ሳሰላ በዚያን ወቅት የነበረው ማለትም ከ40 ዓመት በፊት የነበረውና አሁን ያለው የተለወጠው ምኑ ላይ ነው? ከአገዛዝ ዘይቤ አንፃር ማለቴ ነው፡፡ ምንም ለውጥ እንደሌለውና ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ በአንድ ፓርቲና በአንድ ግለሰብ አገዛዝ መቆየቷ ታሪክ ንፅፅሩና ድግግሙ ይታየኛል፡፡ መልኩ ብቻ ነው የተለወጠው ማለት ነው፡፡ አሁን ያለውን የአገዛዝ ዘይቤ ንጉሳዊ አገዛዝ አይደለም፡፡ ግን የአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲና የአንድ ግለሰብ አገዛዝ ሆኗል፡፡ ይህን ሳይ ደግሞ መብቶችና ነፃነቶችስ አሉ ወይ? ብዬ ስል ስርዓቱን እስከደገፉ ድረስ ቀላል ነው፡፡ መኖር ይቻላል፡፡ ስልጣንም መያዝ ይቻላል፡፡ ስርዓቱን ከተቃወሙ ግን መብቶችና ነፃነቶች ይነፈጋሉ፡፡ እስርና ግድያ አለ፡፡ እንዲያውም አሁን ያለው እስርና ግድያ ከ40 ዓመታት በፊት በአፄ ኃይለሥላሴ ከነበረው የባሰ ነው፡፡ በአጼ ኃይለሥላሴ እስርና ግድያ በድብቅ ይካሄዱ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ስፋት ያለው እስር ወከባና ግድያ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የተለወጠው ምንድነው? ብዬ ራሴን ስጠይቅ መልሱ ይህ ነው ብዬ መመለስና መጨበጥ ይከብደኛል፡፡ እንግዲህ በኢትየጵያ ለውጥ ተረጋግጧል የሚባል ከሆነ በዚያን ጊዜ የነበረው የብሔር ብሔሰቦችን መብት እንደዱሮው ሙሉ በሙሉ መርገጥ ቀርቶ በጣም በተወሰኑ መልኩ መብቶቻቸው ተጎናፅፈዋል ሊባል ይችላል፡፡ ለብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ጎኑ ብቻ ትንሽ ለውጥ አለ፡፡ ይኸውም ቋንቋቸውን ተጠቅመው መናገራቸው፣ መማራቸውና መፃፋቸው ነው፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ግን አልተመለሰም፡፡ ፖለቲካዊ ነፃነት በሌለበት ዴሞክራሲያዊ መብት ባልተረጋገጠበት ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ማስተዳደርና መሪዎቻቸውን መምረጥ መለወጥ እስካልቻሉ ድረስ ይሄ ለውጥ በቦታው የለም፡፡ የልማት ጉዳይም እነሱ ራሳቸው መምራትና ማንቀሳቀስ እስካልቻሉ ድረስ ከአንድ ማዕከል የሚንቆረቆረውና የሚፈሰው ልማት ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድም መሰረታዊ ለውጥ ተረጋግጧል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ፓርቲው ነው ሁሉንም ነገር የሚይዘው፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ አሁን እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብና እያንዳንዱ ጎት በስለላና በፓርቲ መዋቅር ቁጥጥር ስር እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡ ይሄ በጣም ያሳስባል፡፡ ይህም ሁኔታም አጠቃላይ አገዛዝ (Totalitarian) ይሉታል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴም ይህን ለማድረግ አቅሙም ሆነ ብቃቱ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ያለው ስርዓት ግን በሀገሪቱ እያንዳንዱ ዜጋ በገዥው ፓርቲ አዕምሮና መንፈስ እንዲያስብና እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ አካሄድ ነው ያለው፡፡ ይሄ በመሰረቱ መታየትና መለወጥ ያለበት ነው፡፡ የ40 ዓመት ጉዞአችን ስንገመግመው እንዲህ ነው መታየት ያለበት፡፡ ያኔ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታው ለትግል የተመቻቸ ነበር፡፡ አሁን ግን ትግል ማካሄድ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን በዚህ አዳጋች የትግል ሁኔታም ቢሆን እኔ የተነሳሁለት እና የታገልኩለት አላማ ፍፁም አልተሳካም የሚል አስተያት ስላለኝ ይሄን አላማዬን ተግባራዊ ለማድረግ እና እግቡ ለማድረስ አሁንም እየተንቀሳቀስኩ ነኝ፡፡
ጥያቄ- ዩኒቨርሲቲ የገባኸው መቼ ነበር? በህወሓት ምስረታ ጊዜ በደቡብ ትግራይ ትልቅ የማደራጀት ስራ መስራትህ የሆነ ፅሑፍ ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ እና ይሄ እንዴት ነበር?
አቶ ገብሩ፡- ዩኒቨርሲቲ የገባሁት በ1965 ዓ.ም ነው፡፡ በ1965 ዓ.ም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነበርኩ፡፡ ሜጀሬ ጂኦግራፊ ማይነሬ ሂስትሪ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በ1966 የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበር፡፡ 66 የአብዮት ወቅት ስለነበር አልተማርንም፡፡ በ1967 ዓ.ም አልተማርንም፡፡ በዚሁ ጊዜም የዕድገት በህብረት ዘመቻ መጣ፡፡ እኔ እንኳ ዘመቻውን ላለመዝመት ወስኜ ነበር፡፡ በአማራጩ ወደ ትግል ሜዳ ለመሄድ አገኘሁ፡፡ የዕድገት በህብረት ዘመቻው መቀሌ ላይ ተመደብኩ፡፡ መቀሌ መመደቤ ደግሞ ለወደፊቱ ድርጅታዊ ስራ በጣም ነበር ተመቻቸልኝ፡፡ እና ለዚሁ ስራ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት በዘመቻው አማካይነት መቀሌ ሄድኩኝ፡፡ በዚያ ወቅት መቀሌ ውስጥ ሁለት አይነት የአደረጃጀት ስራ ነበር የተሰማራንበት፡፡ አንደኛው ሠራተኛውን ማደራጀት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተማሪዎችንና ወጣቶችን ማደራጀት ነበር፡፡ እኔ ተማሪዎችንና ወጣቶችን ነበር የማደራጀው፡፡ በዚያን ጊዜ አቅሜ የፈቀደውን ያህል በጣም በጣም ጠንክሬ ነበር የምሰራው፡፡ በዚሁም ጊዜ መቀሌ እያለሁ አምስት አውራጃዎች እንዳደራጅ ከድርጅቱ ተልዕኮ ተሰጠኝ፡፡ ተምቤን፣ አጋመ እስከ እዳጋሀሙስ ያለው፣ ክልተ አውላእሎ፣ እራያና እንደርታ አካባቢዎች እንዳደራጅ ኃላፊነት ተሰጥቶን በዚያ አካባቢዎች እየተንቀሰቀስኩኝ አደራጅ ነበር፡፡ ሕቡዕ መዋቅርም አቋቁሞ ነበር፡፡ ስራው በጣም የተሳካ ነበር፡፡ በኋላ ህወሓት ገብተው በከፍተኛ ደረጃ የታገሉና የተሰዉ ለውጥም እንዲመጣ ያደረጉ ያኔ የተደራጁ ወጣቶች በተለይም የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አንዳንድ ሠራተኞችም ነበሩ፡፡
ጥያቄ፡- ከእነዚሁ ያኔ ያደራጀሀቸው ወጣቶች እና ተማሪዎች ጥቂቶቹን ልትጠቅስልኝ ትችላለህ? ወደ ትግል ሜዳ የሄድከውስ መቼ ነበር?
አቶ ገብሩ፡- እንግዲህ አንዱን ጠርቶ ሌላውን መተው አይቻልም፡፡ ግን የተወሰኑትን ለማስታወስና ለመጥቀስ ያህል አሁን ባሉት ልጀምርና ሙሉጌታ ጫልቱ፣ ሙሉጌታ ገ/ሕይወት፣ ታደሰ አባዲ፣ አፈወርቂ የሚባል የጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሣኤ ወንድም (አሁን ተሰውቷል) ሌላም እንዲሁ አፈወርቂ የሚባል፣ ታርዛን (ተሰውቷል)፣ ሰለሞን ካሳ፣ ሮምሀ፣ ቀስቅስ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ በጣም በጣም ጠንካሮች የምላቸውና ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እያሉ በዕድገት በህብረት ሳይሆን ከዚያ በፊት መደራጀት የጀመሩት መድህን ኪሮስ (የትግራይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት) ጀነራል መስፍን አማረ፣ ዜናዊ ሀዱሽ (ተሰውቷል)፣ አርአያ ካህሱ (በቅርቡ ሞቷል)፡፡ እንግዲህ በጣም በጣም ብዙ ስለነበሩ እዚህ አስታውሼ አልጨርሳቸውም፡፡ ድንገት ስለጠየከኝ እነዚያ ያኔ ያደራጀኋቸው ወጣቶችና ተማሪዎች ሁሉን ልጠቅስልህ አልቻልኩም፡፡ አስታውሼ ስማቸውን ባልጠራም እነሱ ዝቅተኛ ተሳትፎና አስተዋፅኦ ነበራቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ከዚያ በኃላ በዕድገት በህብረት መቀሌና የአምስቱ አውራጃዎች የማደራጀቱ ስራ ላይ ስንቀሳቀስ ከቆየሁ በኋላ በዚሁ መቀጠል ስላልቻልኩኝ ማለትም የደርግ ደህንነት ክፍል አውቆኝ ስለነበር በመጋቢት 1968 ዓ.ም ወደ ሜዳ ገባሁ፡፡ ትጥቅ ትግሉን ተቀላቀልኩ፡፡ እና ማሩዋ ወደተባለውና አጋመ ውስጥ ሱባህ ሳእሲኢ የሚገኘው ማሰልጠኛ ማዕከል ገባሁ፡፡
ጥያቄ፡- ትግሉን ከተቀላቀልክ በኋላስ የነበረው እንቅስቃሴህና ተሳትፎህ ምን ይመስል ነበር?
አቶ ገብሩ፡- ትጥቅ ትግል ከገባሁ በኋላ እንደማንኛውም ሰው ሁሉ ወታደራዊ ስልጠና ነው የተሰጠኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ከስልጠና እንደወጣሁ የተመደብኩት እንደገና የከተማ ሰዎችን ወደ ማደራጀቱ ስራ ነበር፡፡ እኔ ያኔ ትልቁ የተሰጠኝ ተልዕኮ ቀድሞ አደርግ የነበረው ከተማ ያሉትን አደራጅ የሚል ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ኃላፊነት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ትግራይን በአራት ከፈልንና እኔ ከእነዚህ አራቱ መቀሌና ማይጨው ማዕከል ያደረገውን ደቡባዊ ግንባር የሚባለውን እንድመራ ተመደብኩ፡፡ ይህ ስራ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ደርግና ደህንነት ባለበትና እኔ በማውቀውና በምታወቅበት አካባቢ እንደገና ገብቼ እንድሰራ ማለት ነው፡፡ በዚህ ስራ ለአንድ ዓመት ተኩል የሚሆን ጊዜ ሰርቻለሁ፡፡ ወደ ሁሉ ከተማዎች እገባ ነበር፡፡ ወደነዚህ ከተማዎች የምገባው ግን በተለያዩ ሽፋኖች ነበር፡፡ አንዴ ገበሬ መስዬ ሌላ ጊዜ አስተማሪና ነጋዴ በመምሰል፡፡ ወደነዚህ ከተሞች እየገባሁ እንቀሳቀስና አደራጅ ነበር፡፡ ከዚህ ስራ ወጥቼ ደግሞ የሃይል 30 ኮሚሳር ሆኜ ተመደብኩ፡፡ የድርጅታዊ ጉባኤ አዘጋጅ ሆኜም ሰርቻለሁ፡፡ በ1971 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንድሆን ተመረጥኩ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካና የህዝብ ስራዎች ሰርቻለሁ፡፡ የሪጅን አመራር ሆኜም ሰርቻለሁ፡፡ በዛ ጊዜ ትግራይን በሶስት ሪጅኖች ከፍለናት ነበር፡፡ ለእነዚህ ሶስት ሪጅኖች ደግሞ እኔ የምዕራባዊውን ሪጅን እንዳስተዳድር ተመድቤ ነበር፡፡ በ1975 በተካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ ደግሞ የስራ አስፈፃሚ (ፖሊት ቢሮ) አባል ሆኜ ተመርጫለሁ፡፡ በኋላም ከማሌሊት ምርጫ በኋላ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እንድሰራ ተመድቤ ሰርቻለሁ፡፡ እንደገናም ትግራይን በአንድ ሪጅን ተጠቃሎ ደጀን ተብሎ በተሰየመበት ወቅት ዘጠኝ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያሉት የዚህ ደጀን አመራር ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እየሰራሁ ደርግ ወደቀ፡፡
ጥያቄ፡- የ1966 ዓ.ም የኢትየጵያ አብዮት መቼ ከሸፈ ትላለህ? ያ የእናንተ ትውልድ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት ዴሞክራሲያዊና የበለፀገች ኢትዮጵያ የመፍጠር ህልሙ ስለምን ከሸፈ ትላለህ?
አቶ ገብሩ፡- ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ በሚሰጠው ቃለ ምልልስ ተጠቃሎ የሚመለስ አይመስለኝም፡፡ ለወደፊቱ ጊዜ ካገኘሁ ሂደቱ እንዴት እንደነበርና ይህ ሂደት ለምን ከሸፈ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ እንዲሁ ሳየውና የሆነ ነገር ለማለት ያህል ግን እንቅስቃሴው በአጠቃላይ እንደሚታወቀው የግራ (የኮሚኒስት) እንቅስቃሴ ነበር፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ገዥው ሪዮተ ዓለም ኢትዮጵያ ማርክሳዊ ሌኒናዊ መስመር ተከትላ ብትጓዝ ነው የሚያዋጣት የሚል ነበር ዋናው አስተሳሰብ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ይሄ የግራው መስመር በእውነቱ በወቅቱ አንገብጋቢና ወቅታዊ ጥያቄ ነበር ወይ? በዚህም በግራው እንቅስቃሴ የሚታዩ በብዙ ሀገሮችም እንደተረጋገጠው መልሰው ወደአምባገነናዊ ስርዓቶች የሚወስዱት መስመሮች እና አቅጣጫዎች በውል ተለይተው ነበር ወይ? በአገራችንም ፍትህና ዴሞክራሲ የዜጎች ነፃነት ለማረጋገጥ ከአራቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በውል የተጤነ እንቅስቃሴ ነበር ወይ? ብሎ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አሁን በውል ይሄ ይሄ ጎድሎታል ብዬ በሰፊው መናገር ባልችልም፡፡ እኔ ኋላ እንዳየሁት እነዚህ የግራ እንቅስቃሴዎች ዞረው ዞረው አምባገነን ስርዓቶችን፣ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን፣ ግለሰቦች በእንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት ነው የነበረው፡፡ ዴሞክራሲ አሁን በምገነዘብበት መንገድ ዜጎች የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው በውል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሌሎችም መብቶች በፓርቲ ጫና ሳይሆን በህዝብ ውሳኔ ብቻ በፓርቲው ውሳኔ እኔን ተከተል፣ አለቃህና መሪህ እኔነኝ ብሎ የሚሄድ ሳይሆን ህዝቡ በነፃነት እንዲወስን የሚያደርግ የዴሞክራሲ ዘይቤ የተከተለ ነበር አልልም፡፡ እንቅስቃሴው ጠቅላላ አሁንም በአንዳንድ ፓርቲዎች አብሶ ደግሞ በገዥው ፓርቲ በኩል የሚታየው እኔ አውቅልሀለሁ የሚል ነው፡፡ ህዝብ እንደማያውቅ፣ ጭራ እንጂ የእንቅስቃሴው ማዕከል እንደሆነ አድርጎ የማያይ አካሄድ ነው ያለው፡፡ በእርግጥ ፓርቲዎች የህዝቡ ጭራ መሆን የለባቸውም፡፡ አቅጣጫዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ የመወሰን ስልጣን ግን ለህዝብ መተው አለበት፡፡ ህዝቡ ነው መወሰን ያለበት፡፡ ፓርቲዎች በምንም መንገድ ከወሰኑ የፓርቲ የበላይነትና አምባገነንነት እንጂ የህዝብ የበላይነት የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም፡፡ አሁን እያየነው እንዳለው ኢህአዴግ ዞሮ ዞሮ አምባገነን ነው የሆነው፡፡ ለዴሞክራሲ መሰረት የሚሆኑ መዋቅሮችን መገንባት አልቻለም፡፡ ለዴሞክራሲ መሰረት የሚሆኑ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦችንም ሆነ መርሆዎች አልያዘም ከመጀመሪያው ጀምሮ፡፡
ጥያቄ- የህወሓት ውድቀት ከፅንሱ (ከመጀመሪያው) ነበር ነው የምትለኝ ያለው?
አቶ ገብሩ፡- እንግዲህ እኔ እንደዛ ብዬ አላጠቃልልም፡፡ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ እንግዲህ ሕወሓት እንደ አማራጭ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ በዚህች ሀገር አንድ አማራጭ ሆኖ መቅረቡ በራሱ ጥሩ ነው፡፡ አማራጭ ያስፈልገናል፣ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል፣ ወታደራዊ አምባገነንነት አያስፈልገንም ብሎ ነው ጫካ የገባው፡፡ በዚህ ችግር የለበትም፡፡ ግን ይሄን ካለ በኋላ ድርጅቱን ያዋቀረበት በተለይ ደግሞ በኋላም መንግሥት ያዋቀረበት አገባብ ስመለከት ግን ወደደም ጠላም ወደ አምባገነንነት የሚወስድ ነበር፡፡ አንድ በአንድ ልነግርህ እችላለሁ፡፡
1. መንግሥት ሲያዋቅር ፓርቲው (ገዥው ፓርቲ) መሪ ድርጅት ይሆናል ነው ያለው፡፡ የእሱ አስተሳሰብ በህዝቦች ላይ ይጫናል ነው ያለን፡፡ ህብረተሰቡን ጠላትና ወዳጅ ብሎ ከፋፍሎታል፡፡ ህብረተሰብንና ዜጎችን ጠላትና ወዳጅ ብለህ የከፋፈልካቸው ዕለት ዴሞክራሲ ያኔ ያበቃል፡፡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተባሉ ነገሮች ያኔ ያከትማሉ፡፡ ስለዚህ በአስተሳሰብ ደረጃ ስር የሰደዱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ይዞ ነው ስልጣኑን ያቋቋመው፡፡ ይሄ የመንግሥት ተቋሞችንም ጭምር፡፡ በቃል ነፃ ፍ/ቤት ይላል፡፡ ሆኖም ግን በተግባር ፓርቲው የማይቆጣጠረው ነፃ ፍርድ ቤት እንዲኖር አልተደረገም፡፡ ምክር ቤቱ (የተወካዮች) ስራ አስፈፃሚውን የመቆጣጠር ስልጣን አለው ይላል፡፡ በተግባር ሲታይ ግን ተገላቢጦሽ ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚው ነው ምክር ቤቱን የሚቆጣጠረው፡፡ ስለዚህ የህዝብ የሉአላዊነት መገለጫ ከፍተኛው አካል የሚባለው ምክር ቤትም ቢሆን በተጨባጭ ስልጣን የለውም፡፡ ስራ አስፈፃሚው የበላይ ፓርቲውንና ሁሉንም ነገሮች የሚመራና የሚያሽከረክር ነው፡፡ እናም እንደዚሁ በአገራችን ፍርድ ቤቱ ብቻ አይደለም ነፃነት የሌለው፡፡ አቃቤ ህግም ነፃነት የለውም፡፡ ባለስልጣን መክሰስ አይችልም፡፡ ባለ ስልጣን ክሰስ ብሎ ያሰማራዋል እንጂ ራሱ በራሱ በተሰጠው የህግ ስልጣን ማዕቀፍ መሰረት መጠየቅ አይችልም፡፡ ደህንነቱም፣ ፖሊሱም፣ ሠራዊቱም፣ አወቃቀሩና የሚመራበት ፍልስፍና ራሱ አምባገነንነት በሚያሰፍን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ አምባገነን ስል መለስን ብቻ አይደለም፡፡ ወይ እዚያ ያለ አንድ ግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ተቋማዊ መልክ ይዟል፡፡ በተቋሙ ማንም ሰው በዚህ አስተሳሰብ በዚህ አወቃቀር ወደ ስልጣን የሚመጣ ወጣትም ይሁን ጎልማሳ አምባገነን ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይህን ስቶታል፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የሚሆኑ አስተሳሰቦችና መዋቅሮች ይዞ አልተነሳም፡፡
ጥያቄ- ሕወሓት ትግል ላይ ያለና ስልጣን ከያዘ በኋላ ከሻዕቢያ ጋር የነበረው ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነበር ትላለህ?
አቶ ገብሩ፡- ይሄም ሰፊ ማብራሪያ የሚፈልግ ነው፡፡ እንዲሁ ለጋዜጣ በሚሰጥ ቃለ ምልልስ ብቻ ለመግለፅ ያዳግታል፡፡ ሆኖም ግን የህወሓትና የሻዕቢያ ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ አልነበረም፡፡ ለሻዕቢያ ያደላ ነበር፡፡ በዚህም ሆነ በዛ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጥቅሞች ያካተተና ግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሲናገር እኛን (ተቃዋሚዎችን) ጦርነት ናፋቂዎች ይለናል፡፡ ይህ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የሚያጣላን ትንሽ ነገር ነው ይላል፡፡ ድንበር አካባቢ ያለ ትንሽ ነገር ነው የሚል የማወናበድ ስራ እየሰራነው ያለው፡፡ ነገር ግን ተገላቢጦሽ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያ አይደለችም፣ የኤርትራን ሉአላዊ መሬት ይዛና ተቆጣጥራ ያለችው ኤርትራ ናት የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት የሆነው አሰብን ተቆጣጥራ ይዛ ያለችው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይሄ መንግሥት የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ሉአላዊ መብት አሳልፎ የሰጠ ነው፡፡ ይህ ይቅር የማይባል ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ፍፁም ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡ ኢትየጵያ አሁን ባለው መንግሥት አማካይነት በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳችበት የባህር በር የባለቤትነት መብቷ ማሳጣቱ ነው፡፡ በአንፃሩ እነ ባድመና ሌሎች ሰበቦች ናቸው፡፡ እኔ አሁንም እምነቴ ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት የሆነውን አሰብ ይዟል ነው እንጂ ኢትዮጵያ የኤርትራ ሉአላዊ ግዛት ይዛለች ብዬ ፍፁም አላምንም፡፡ ጉዳዩ እስከዚህ ነው መታየት ያለበት፡፡ ስለዚህ ይሄን ሳያካትት ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም አስጠብቋል ልል አልችልም፡፡ ሌሎች በየጊዜው የተገለፁት ጉዳዮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በኢኮኖሚው መስክ የተደረጉ ውሎችና ስምምነቶች፣ በመከላለከያ ዘርፍ የተደረጉ ስምምነቶች፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ አልነበሩም፡፡ የሻዕቢያን ጥቅም የሚያስጠብቁ እንጂ፡፡
ጥያቄ፡- ለዚህ ማነው ተጠያቂው?
አቶ ገብሩ፡- ለዚህ ተጠያቂው ገዥው ፓርቲ ነው ያለ ጥርጥር፡፡ ያም ሆኖ ግን የተጠያቂነት እርከን ደግሞ አለ፡፡ ሀገሪቱን ጠቅላላ እንዲመራና እንዲያስተዳድር የተቀመጠው መሪ አለ፡፡ ፓርቲውን በአጠቃላይ ለመምራት የተቀመጠ መሪ አለ፡፡ እሱ ነው ዋናው ተጠያቂው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከመሪው ጋር እንዲሰሩ በስራ አስፈፃሚነት የተቀመጡ አሉ፡፡ ከዚያ ቀጥሎም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አሉ፡፡ እነዚህ ናቸው ዋና ዋናዎቹ ተጠያቂዎች፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሐገራዊ ጥሪ በዌኔፒግ ካናዳ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን
Share