June 9, 2011
5 mins read

ዳልግሊሽ የዝውውር በጀቱን በጥንቃቄ ለመጠቀም አስቧል

ኬኒ ዳልግሊሽ በመጪው ክረምት ለተጨዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚመደብለት በሊቨርፑል ባለቤቶች ተነግሮታል፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኙ ገንዘቡን አላግባብ ወጪ ለማድረግ እንዳልተዘጋጀ ጠቁሟል፡፡ ሰንደይ ሚረር እንደዘገበው የክለቡ ባለቤት ኩባንያ ፌንዌይ ስፖርት ግሩፕ ባለፈው ጃንዋሪ ሮይ ሆጅሰንን በተካው አሰልጣኝ ብቃት በእጅጉ በመርካቱ ለዝውውር 50 ሚሊዮን ፓውንድ ሊመድብለት ተዘጋጅቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የክለቡ ባለቤት ስኮትላንዳዊው የሚፈልጋቸውን ተጨዋቾች እንደሚያስፈርም ሁሉ የማያስፈልጉትን ተጨዋቾች መርጦ ለሽያጭ እንዲያቀርብ ነግረውታል፡፡ ዳልግሊሽም በመጪው ክረምት አንፊልድን የሚሰናበቱ በርካታ ተጨዋቾች እንዳሉ ገልጿል፡፡ ነገር ግን አሰልጣኙ ክለቡ በቻምፒየንስ ሊግ ካለመሳተፉ ጋር በተገናኘ ለተጨዋቾች ዝውውር የተጋነነ ሂሳብ እንደማይፈልጉ ጠቁመዋል፡፡
ሊቨርፑል ሜዳው ላይ በቶተንሃም መሸነፉን ተከትሎ በዩሮፕ ሊግ የመሳተፍ እድሉ ተመናምኗል፡፡ ቢሆንም ዳልግሊሽ በቀጣይ ቡድኑን በሚያጠናክሩ ዝውውሮች ላይ ማተኮርን መርጧል፡፡ ‹‹በእርግጥም በአሁኑ ወቅት ለዝውውር ምን ያህል እንደምናወጣ መናገር አልችልም፡፡ ይህንን ተጨዋች እንፈልገዋለን ብዬም የምሰጣችሁ መረጃ አይኖርም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዘንደሮ ለክለቡ ውጤታማነት የተጉትን ተጨዋቾች ማመስገን ይኖርብኛል፡፡ ሆኖም በክረምቱ የሚለቁ እና ክለቡን የሚቀላቀሉ ተጨዋቾች ቢኖሩ አይገርምም፡፡ ምክንያቱም ይህ የእግር ኳስ ባህርይ ነው፡፡ እኔ መናገር የምፈልገው ዋናው ነገር የክለቡ ባለቤቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጡን መሆናቸው ነው፡፡ ክለቡ ስኬታማ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ማድረግ የማንችልበት ሁኔታ ካለ ደግሞ አዳዲስ ተጨዋቾች ያስፈልገናል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ገንዘብ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ተጨዋቾችን አናስፈርምም፡፡ ሰዎች በቻምፒየንስ ሊጉ ላይ አለመሳተፋችን የምንፈልገውን ተጨዋች እንዳናገኝ እንደሚያደርገን ይናገራሉ፡፡ ሁሉም የየራሱን አስተያት የመስጠት መብት አለው፡፡›› ብሏል ዳልግሊሽ፡፡
ዳልግሊሽ ባለፈው ጃንዋሪ አንዲ ካሮል እና ልዊስ ሱአሬዝን ለማስፈረም 58 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ ወጪ ግን የተሸፈነው ከፈርናንዶ ቶሬስ ሽያጭ በተገኘው 50 ሚሊዮን ፓውንድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሊቨርፑል ከስፐርስ ሽንፈት በፊት ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች አስሩን ማሸነፍ እና በሶስቱ አቻ መለያየቱ ወደ አምስተኛ ደረጃ አምጥቶት ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘም ዳልግሊሽ የሶስት ዓመት ኮንትራት ቀርቦለታል፡፡ ይህም ሆኖ አሰልጣኙ የሚያስፈርማቸው ተጨዋቾች በቡድኑ ውስጥ ካሉት የተሻሉ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁሟል፡፡ ከዝውውር መስኮቱም ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ መናገርን መርጠዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመትም በማንቸስተር ዩናይትድ የተነጠቁትን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሪከርድ ለማስተካከል እቅድ ይዘዋል፡፡ ‹‹በቀጣዩ የውድድር ዘመን ደረጃችንን ለማሳየት በሊጉ ጠንካራ ጉዞ አድርገናል፡፡ ዘንደሮ በሊጉ እስከ አራተኛ ደረጃ ከሚገኙት ክለቦች ሶስቱን አሸንፈናል፡፡ ለከርሞም ይህንን ስኬት መድገም ከቻልን የምንፈልገው ውጤት ላይ መድረስ እንችላለን፡፡››

Go toTop