የዕውነትና የህይወት መንገድ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ኣሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ግዙፍ ወንጀለኛ ነበር። የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆኖ ኣብሮ ከርሟል። ከገበታውም ከትምህርቱም ተቋድሷል። መወለድ ወይም ኣብሮ መዋል ቋንቋ ነው እንዲሉ ጌታውን ለስቅላትና ለሞት ኣሳልፎ ለመስጠት ጊዜ ኣልፈጀበትም። ሰላሳ ዲናር ከታላቁና ከክቡሩ ጌታ በለጠበት። ጥቅም ኣሸነፈው። ላይበላበት፣ ላይጠጣበት ላያጌጥበት በሚጢጢ ገንዘብ ትልቁን ኃይል ለወጠበት።
ይሁዳ ሰው ነው። ለየት የሚያደርገው የእርሱ ዓይነት ሃሳብ ካላቸው ሰዎች ቀድሞ ወንጀሉን መፈጸሙ ነው። በድርጊት ለመግለጽ ከፊት ለፊት መሰለፉ።
ይሁዳ ሰው ነው። የሰው ህሊና ፈጥሮበታልና፣ ከእንስ ሳም ይለያልና የወሰደው እርምጃ ሳይውል ሳያድር ቆጠቆጠው። እንደ እሳት ፈጀው። ሰላሳ ዲናሩን ላይጠቀምበት ሰብስበው ለሰጡት የጊዜው ቀሳውስት ወይም ኣህዛብ መልሶ በተነላቸው። ሻሞ ኣላቸው። ዲናሩን ምን እናድርገው እስከሚሉ ኣዋከባቸው። ኣንድ ዲናር እንኳን ሊጠቀምበት የሚያስችልበት ህሊና ኣጥቷል ይሁዳ። መልሶ በበተነው ዲናር እንኳን ህሊናው ሊረካ ኣልቻለም። ስለዚህም በቁጭት የበገነው ይሁዳ በገመድ እራሱን ኣንቆ ገደለ።በኣንጻሩ ይሁዳ ዲናሩንም ተጠቅሞ፤ ጌታውንም ኣሳልፎ ሰጥቶ ተመሳስሎ መኖር ይችል ነበር። ይሁዳ ስለፈጸመው ወንጀል እንጂ በራሱ ላይ ስለወሰደው እርምጃ ለማናስተውል የጽሁፌ መልካም መግቢያ ሳት ሆን ኣትቀርም። ታዲያ የዲያስጶራ ይሁዳዎች ከዚህኛው ይሁዳ ለየት ይላሉ።የቅዱስ ቃሉን ‘ቃል’ ለሰባኪዎቹ ልተወው።
የዲያስጶራ ”ይሁዳዎች”
ካነበብነውና ካስተዋልነው የተለዩ ዲያስጶራ ኣጭቃለች። በሃገር ቤት የሰሩት ወንጀልና ጭቅቅት እንደ ዕውነተኛው ይሁዳ ታንቀው ወይም ታጥበው ኣያሳዩንም። ከነዕድፋቸው ተፊት ተፊት ይቀድማሉ። ትላንት ያስገረፉት፣ ያስገደሉት የተካኑበት የኑሮ ጌታቸው ሆኖላቸዋል። ኣውልቀውት ኣያውቁም። ሊያወልቁትም ኣይፈልጉም። በእርግጥ ከኣርባ ሰባተኛ ፎቅ ላይ ይከስከሱ ብለን ባናስገድ ድም በይቅርታ እንዲታጠቡት ኣለያም የማይሞላው ከርሳቸውን እያባበሉ ቢደበቁ ምርጫችን ነበር። ለዚህም ነው የዲያስጶራ ይሁዳዎች ከዕውነቱና ከከሃዲው ይሁዳ ይበጣሉ የምለው። ውስጣቸውን መመልከት የሚያስችል ህሊና የላቸውም በማለት የምደመድመው። በዲያስጶራ በሬው ካራጁ ጋር ይውላል።
ክርስቶስን ኣንድ ይሁዳ ኣሳልፎ ከሰጠው ብዙ ይሁዳዎች ያሏት ዲያስጶራን እንደምን መታደግ ይቻላል፧ ይሄ መልስም መፍትሔም የማይገኝለት ትልቁ ፈተናም ጥያቄም ነው። ኣንዱን ይሁዳ ማጋለጥ የተቻለበትን ዘመን እንደመመኘት ነው። በዲያስጶራ ኣንድ ይሁዳን ማጋለጥ ሲፈለግ፤ እንደ ኣሸን የፈሉት ይሁዳዎች እንደ ፊልም ትር ኢት ከፊት ለፊት ተደርድረው ይታያሉ። ነጭ ሽንኩር ሲገሸልጡ መዋል ያህል ይከብዳል። የማያልቅ ልጣጭ። እናም ከዲያስጶራ ይህዳዎች ጋር እንውላለን። እናመሻለን።ካንጀት ባያስቁንም የፎቶ ፈገግታ እየፈገግን እንገለፍጣለን። ከፊት ለፊት ስለሚቀድሙም እንከተላለን። እንደ ሃገር ቤቱ ባለንበት ቦታ ባይገርፉንም፤ በሃሳባቸው ሳማ እንለበለባለን። ይሄ የዲያስጶራ ይሁዳኖች ጉዞ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው።
ትንሽ ትንሽ መሞት
ትንንሾች ስለግለሰቦች ያወራሉ። ትልልቆች በጉዳዮችና በሃሳቦች ዙሪያ ላይ ያተኩራሉ። ይባላል። እርግጥ ነው ሃሳቦችንና ጉዳዮችን ይዘው የተነሱ ሰዎችን ስም መጥቀስ ትንሽነት ባይሆንም የሃሳቡን ኣውራዎች ማንሳት የሚያስገድ ድበት ጊዜ ይኖራል። ኣለበለዚያ ትልቁን ሃሳብ ይዞ የተነሳው ሶቅራጥስ እኔ የማውቀው ኣለማወቄን ነው በማለቱ ብቻ ግለ ፍልስፍናውን ዋጋ እንደመንፈግ ይቆጠራል።
በሃገራቸው የሚላስ የሚቀመስ በማጣታቸው ሳይሆን፣ እግራቸው መውጫ መግቢያ ሃሳባቸውን ማሳረጊያ፣ ድርጊታቸውን መፈጸሚያ ኣጥተውና ኢትዮጵያን በጉልበት በመያስተዳድሯት ገዥዎች ጫና መድረሻ ስላጡ የተሰደዱ ምርጥና የምር ወገኖችም ዲያስጶራ ኣሏት።
የኋልዮሽ ጥለዋት በመጡት ሃገር የሚብከነከኑ፤ ለመጠጊያቸው ወይም ለመቀመጫቸው ባረፉበት ሃገር ወረቀት ለማግኘት ያልዋሹ፣ ያልቀጠፉ ያላጭበረበሩ ከህሊናቸው ጋር ደፋ – ቀና የሚሉ። ጠዋት ማታ የወገናቸውና የሃገራቸውን ዕጣ ፈንታ ከግል ህይወታቸው ጋር ያዛመዱ፤ የነፍስያቸው ስንቅ ማዶ ያለችውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ብርቱዎች። ብዙ ይኑሩልን!… የምንላቸው፣ ሲሞቱብን የምንቆጭባቸው። በስደት ህይወታቸው ውስጥ የሚያወጡዋት ቃልና የሚተገብሩት ተግባራቸው ለኗሪው ትክክለኛ ስደተኛ ምግብ የሚሆኑ። ለሃገር ‘ብርም’-ኣድባርም የሆኑ። በእንዲህ ያሉ ዜጎች ትንሽ ትንሽ ሞት ኢትዮጵያ በዲያስጶራ በደማቁ ስትጻፍ፣ስትዘከር ትውላለች።
የዲያስጶራው በጥባጭ ማነው?
1. ” ስደትና ኣግዳሚ ወንበር እኩል ያስቀምጣሉ”
2. ”ጅብ በማይታወቅበት ሃገር ሄዶ ቁርበት ኣንጥፉልኝ ኣለ።”
1.1 ”ስደትና ኣግዳሚ ወንበር እኩል የሚያስቀምጡት” ሌባ፣ ገዳይ፣ ኣስገዳይ በዲያስጶራ ያለውን ንጹህ ኢትዮጵያዊ ሊከፋፍል በግዳጅ የወጣውም ወዘተ… የሃገሩን ድንበር ከተሻገረ በኋላ፣ የሚሰጠው ስም ”ስደተኛ” ነው። ኣግዳሚ ወንበር ሁሉንም ሰባስቦ እኩል እንደሚያስቀምጠው ሁሉ፤ ድንበር ተሻግሮ የወጣውም ”ስደተኛ” በሚለው ይጠቃለላልና ለተቀባዮቹም፣ ለኣቀባባዮቹም ከዚህ የተለየ ስም መስጠት ኣይቻልም። ኣግዳሚ ወንበሩ ላይ ንጹሃኖችም ወንጀለኞችም ኣብረው ይቀመጣሉ። በስርዓት መቀመጥ ኣይችሉም – ወንጀለኞቹ። ይገፈትራሉ። ሊጥሉህም ይችላሉ። ”ስደተኛ” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶኣቸዋልና ኣይሸማቀቁም። ዲያስጶራው ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያኖች ሊያሸማቅቁ፣ ሊጎነትሉ ተልከዋልና ኣግዳሚ ወንበሩ ኣብቃቅቶ ቢያስቀምጣቸውም…. እነሱ ግን ኣይበቃቸውም።
2.1 ”ጅብ በማይታወቅበት ሃገር ሄዶ…” ጅብ እንደሚታወቀው ጅብ ነው። ይከረፋልም። ኣይጠግብምም። የማይታወቀው በማይታወቅበት ሃገር በማረፉ ነው። የጅብ ባህሪውን ኣይስትም። ማንኛውንም ነገር ያግበሰብሳል። ሆዱን የሚሞላ የጥቅም ጉዳይ ሁላ ሞራል ኣልባ ጅብ ነውና ከነክርፋቱ ያጉራል። ድንክ-ድንክ ሃሳቦች ከዲያስጶራ ወደ ሃገር ቤትም፤ በዲያስጶራም እንዲወረወር የሚደረገው በነዚሁ ”ቁርበት ኣንጥፉልኝ…” በሚሉ ጅቦች ነው። የመንደር ፖለቲካ ቀርቶ፣ የጓሮ ፖለቲካም ቢሰጧቸው ሲያቅራሩ፣ ሲጮሁ ይውላሉ። ምክንያቱም ”ማኖ” ነክተዋል። ”ሰላሳ ዲናሩና የመበተን ያህል ቀላል ያልሆነ ማኖ ” በጥቅም ታውረዋል። የጅቡን ባህሪ ተላብሰዋል። ያረፉበትን ቁርበት እስኪበሉ በኣካባቢያቸው ያሉትንም ሆነ ሃገር ቤት ያለውን በጅብ ኣንደበታቸው ሲያመነዥጉ ይውላሉ። ከዕውነተኞቹ ጅቦች የሚለያቸው በሌሊት ብቻ ሳይሆን፤ በቀትርም መጮሃቸው ነው። ኣይ ኣበው!.. ለተረታችሁ ነፍሳችሁን ይማርልኝ።
ለዛሬ ይብቃኝ። በሚቀጥለው ጽሁፌ ኣንዳንድ ኣንኳር ይሁዳዎችን ለማንሳት እሞክራለሁ። ወንጀላቸውን እንዲያቆሙ ሳይሆን የይሁዳ ህሊና እንዲጋባባቸውና እራሳቸውን ይመለከቱ እንደሆን ለማመላከት። በጽሁፌ ቆሽታችሁ ያረረም፤ ኣንጀታችሁ ቅቤ የጠጣም ኢሜሌ ይሄውላች ሁ:- [email protected]