የአብርሃ ደስታ የሰሞኑ ምርጥ ዘገባዎች

February 13, 2014

የህወሓት የኮብልስቶን ፖለቲካ (መቐለ)
========================

የመቐለ ወጣቶች (የዩኒቨርስቲ ምሩቃን) ተደራጅተው በኮብልስቶን ስራ ለመሳተፍ ቢወስኑም የህወሓት መንግስት ሊያስሰራቸው እንዳልቻለ ገለፁ። ወጣቶቹ በኮብልስቶን ስራ ተሰማርተው ስራ ለመፍጠርና ህይወታቸው ለመቀየር በተገባላቸው ቃል መሰረት ቢደራጁም መንግስት ግን በዝቅተኛ ዋጋ (ትርፍ የሚገኝበት ሳይሆን ለኪሳራ በሚዳርግ) እንዲሰሩ እያስገደዳቸው ይገኛል።

የኮብልስቶን ገንዘብ በእርዳታ ከዎርልድ ባንክ የሚገኝ ሲሆን የህወሓት ባለስልጣናት የኮብልስቶኑ ፕሮጀክት ተከናውኖ ለሚመለከተው አካል እንደለመዱት የዉሸት ሪፖርት ማቅረብ ይፈልጋሉ። ይህ እንዳለ ሁኖ ከዓለም ባንክ ከተገኘው ገንዘብ ከወጣቶቹ ተቀንሶ ለሐላፊዎቹ የሚተርፍበት ሁኔታም ያመቻቻሉ።

አሁን ግን አንድ ችግር ተፈጠረ። ወጣቶቹ በስራቸው ትርፍ ማግኘት ይፈልጋሉ። ወጣቶቹ ትርፍ ካገኙ ለባለስልጣናቱ የሚተርፍ ገንዘብ (የሚመዘበር ገንዘብ) አይኖርም። ባለስልጣናቱም የኮብልስቶን ገንዘቡ መመዝበር ይፈልጋሉ። የኮብልስቶን ገንዘቡ ከተመዘበረ ግን ለወጣቶቹ የሚሰጥ ገንዘብ ያንሳል። ካነሰ ደግሞ ወጣቶቹ ይከስራሉ። ወጣቶቹ ደግሞ ኪሳራውን አልፈለጉትም። እናም አሁን ከባድ ዉጥረት ነግሷል።

ባለስልጣናቱ የኮብልስቶን ተጫራቾች በትንሽ ዋጋ እንዲሰሩ ያስገድዳሉ፤ ምክንያቱም የኮብልስቶን ስራ መቋረጥ የለበትም። ምክንያቱም የዓለም ባንክ ገንዘቡ ስለሰጣቸው ስራው ተሰርቷል ብለው ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ገንዘብ ደግሞ ማትረፍ ይፈልጋሉ። ወጣቶቹም መክሰር አይፈልጉም። እናም ወጣቶቹ ፍቃደኞች አይደሉም። ባለስልጣናቱ ደግሞ ወጣቶቹን ባለስልጣናቱ በፈለጉት የዋጋ መጠን እንዲሰሩ ያስገድዷቸዋል።

ከዚህ አልፎ የህወሓት ባለስልጣናት የኮብልስቶን ገንዘብ ከዓለም ባንክ የተገኘው በህወሓት ትብብር ስለሆነ በኮብልስቶን ስራ የሚሰማራ ማንኛውም ወጣት የህወሓት አባል መሆን እንዳለበት ትእዛዝ አስተላልፈዋል። የህወሓት አባል መሆን ብቻ በራሱ በቂ እንዳልሆነና በኮብልስቶን ስራ ለመሰማራት ባለስልጣናቱ ባዘዙት የዋጋ መጠን መስራት እንዳለበትም አክለዋል። በተጨማሪም ወጣቶቹ የሚያገኙትን ገንዘብ በደደቢት ማይክሮፋይናንስ (የህወሓት ነው) ማስቀመጥ እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።

ወጣቶቹን እንዲሰሩ ማስገደድ ምን አመጣው? የሚያዋጣቸው ቢዝነስ ከሆነኮ በፍቃዳቸው ይሰራሉ? በዓለም ባንክ ገንዘብስ ለምን የፓርቲ አባል እንዲሆኑ ይገደዳሉ? የዓለም ባንክ ገንዘብ የሰጠው ለህወሓት አባላት ብቻ ነው እንዴ? ወጣቶቹ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩስ ለምን ማስፈራርያና ማስጠንቀቅያ ይሰጣቸዋል? ሐሳባቸው የመግለፅ መብት የላቸውም እንዴ?

እስከመቼ ነው በህወሓት የባርነት ቀንበር ስራ የምንኖረው? የህወሓት የአገዛዝ ስትራተጂ ከ”ከፋፍለህ ግዛ” ወደ “አስርበህ ግዛ” የተሸጋገረበት አጋጣሚ ነው ያለው። ህዝብ በሆዱ ተይዟል። ከተቃወመ የሚበላና የሚሰራ ያሳጡታል። በህወሓት አገዛዝ የወደቅንበት ምክንያት ድሆች ስለሆንን ነው። ህይወታችን በህወሓቶች (የመንግስት) እርዳታ ስለተጠለጠለ ነው። መቃወምን የሚያስፈራን ሆዳችን አቅፈን ስለምንኖር ነው።

ግን እስከመቼ? ከተባበርን ህወሓትን ከስልጣን ማውረድ እንችላለን። ከስልጣን ካወረድነው ደግሞ ነፃነታችን እናገኛለን። ነፃነታችን ካስመለስን የስራ ዕድል ይከፈትልናል። የስራ ዕድል ከተከፈተልን በልተን በሀገራችን በነፃነት መኖር እንችላለን።
__________________________________________________________________________________________

የመንግስት ጣልቃ ገብነት በሀይማኖት: የስብሃት ነጋ ምስክርነት
==========================

በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማሕበረሰብና በኢህአዴግ መንግስት መካከል አለመግባባት መስፈኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መንግስት በሀይማኖታቸው ጣልቃ መግባቱ እንዲያቆም ሲጠይቁ መንግስትም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ማሳሰሩ ይታወሳል። (ኮሚቴዎችን በማሳሰር የህዝብን ጥያቄዎች ማዳፈን ይቻል እንደሆነ እንጂ መመለስ ግን አይቻልም)።

መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ የሚገባው በተለያዩ መንገዶች ሊሆን ይችላል። አንዱና ዋነኛው ግን የሀይማኖት መሪዎችን በመደለል የፖለቲካ መሳርያ እንዲሆኑ ማድረግና የፖለቲካ ካድሬዎች የሀይማኖት መሪዎች አድርጎ መሾም ነው።

የፖለቲካ ሹመት (ካድሬነትና አገልጋይነት) ሌላ የሀይማኖት መሪነት ሌላ። ፖለቲካና መንፈሳዊ ህይወት የተለያዩ ናቸው። የፖለቲካ ሹመት ከሆነ በገዢው ፓርቲ ሊመረጥ ይችላል። የሀይማኖት መሪ ግን በምእመናን ነው መመረጥ ያለበት። ስራውም ፖለቲካ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ነው የሚሆነው። ሀይማኖታዊ መሪው በፖለቲካ ተፅዕኖ ስር መውደቅ የለበትም።

የኢህአዴግ መሪዎች ሁሉንም የሀይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠር የራሳቸው የፓርቲ አባላት የሀይማኖት መሪዎች አድርገው ይሾማሉ። ጓደኛዬ ናስሩዲን በፌስቡክ ገፁ እንዳስቀመጠው ከሆነ አቶ ስብሃት ነጋ እንዲህ ተናግረዋል:

“ቅድም የፌደራሉ መጅሊስ ምክትል ሰብሳቢው ሸህ ከድር እንዳለው የዱሮው እስልምና ሌላ ነው፡፡ እኔ ከድርን በፊት ጀምሮ ትግራይ ውስጥ አውቀዋለሁ፡፡ ምርጥ የሕወሓት ታጋይ ነበር፡፡ አብሮን ታግሏል፡፡ አሁን ደግሞ ሙስሊሙን እያገለገለ ነው፡፡ እስልምና እነዚህ የታሠሩት ሰዎች እንደሚሉት አይመስለኝም፡፡ እስልምና እነዚህ ሰዎች እንደሚያሳዩት ዓይነት እምነት ከሆነ እንደ እምነት አያስፈልግም፡፡ ፈፅሞ ሰዎቹ ለሀገር አይሆኑም፡፡”

ሼህ ከድር የሙስሊሞች ሀይማኖታዊ ተቋም የመጅሊስ ምክትል ሰብሳቢ ነው (ወይም ነበር)። ግን ሼህ ከድር የህወሓት ታጋይ ነበር። የህወሓት አባል ነው። ስለዚህ ሼህ ከድር የፖለቲካ መሪ እንጂ የሀይማኖት መሪ አይደለም። መጅሊስ የፖለቲካ ተቋም አይደለም። የፖለቲካ ሰው አይደለም የሚፈልገው። መጅሊስ የሀይማኖት ተቋም ነው። የሀይማኖት መሪ ይፈልጋል። እንደምናየው ግን የመጅሊስ አመራር አባላት የሀይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ ፖለቲከኞች (እንዲሁም የጉሪላ ታጋዮች) ናቸው። እንዴት ይሆናል? ይሄ ተግባር ጥያቄ አያስነሳም? በዚህ መሰረት የሙስሊሞች ጥያቄ ትክክል ነው ማለት ነው።

ሙስሊሞቹ እንደ ምእመናን የሀይማኖት መሪ አያስፈልጋቸውም? “በሀይማኖታችን የፖለቲካ ካድሬዎች አያስፈልጉንም። የሀይማኖቱ እውቀት ያላቸውና በምእመናኑ እውቅና ያላቸው ሀይማኖተኞች እንዲመሩን እንፈልጋለን!” ብለው ቢጠይቁ አግባብነት የለውም? ከመቼ ጀምሮ ነው በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ ያደገ የህወሓት ታጋይ ሀይማኖት ኖሮት የመጅሊስ ምክትል ሰብሳቢ የሚሆነው? ወይስ ሙስሊሞችን ለመቆጣጠር ነው የተፈለገው? ደግሞ የሀይማኖቱ ተከታዮች ሳይደግፉት?! የሀይማኖት መሪ’ኮ የምእመናኑ ድጋፍና እውቅና ያስፈልገዋል።

ሙስሊሞች ስለሀይማኖታቸው ሲጠይቂ ሌላ ስም ከመስጠት መጀመርያ መንግስት ከሀይማኖቱ እጁ ያንሳ። ካድሬዎቹን የሀይማኖት መሪዎች እያደረገ አይሹሙብን! ካድሬ በትምህርትቤት ይሾማል፣ በቤተክርስትያን ይሾማል፣ በመጅሊስ ይሾማል!??? ኧረ ተዉ ኢህአዴጎች! ፖለቲካና ሀይማኖት እንለይ!

ሁሉም ሃይማኖቶች ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ የሀይማኖት መሪዎች ያስፈልጉዋቸዋል። የሀይማኖት ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ሳይሆን የምእመናኑ ጉዳይ ነውና።

ሙስሊሞች (ና ክርስትያኖች) ሆይ! መንግስት በሀይማኖታቹ ጣልቃ እንዲገባ የማትፈልጉ ከሆነ የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ የመግባት ተግባሩ አጥብቃቹ ተቃወሙት። እየተቃወማችሁት ነው። ግን መፍትሔ የለም፣ ሰሚ የለም። ለጥያቅያቹ መልስ ከመስጠት ይልቅ መንግስት እያሰራቹ፣ እያሰቃያቹ ይገኛል። የመንግስት መፍትሔ ኮሚቴዎችን ማሳሰር ከሆነ በኢህአዴግ እምነት ሊኖራቹ አይገባም። እናም ኢህአዴግ መፍትሔ ሊያመጣላቹ እንደማይችል አረጋግጠዋል። ስለዚህ ምን ይደረግ? የሀይማኖት ጥያቄው ታፍኖ ይቅር?

የሀይማኖት ጥያቄማ መፍትሔ ይሻል። ምክንያቱም የሀይማኖት ጥያቄው ትክክለኛና አስፈላጊ ነው። ጥያቄው ሁላችን የምንደግፈው ነው። ጥያቄው ትክክል ከሆነ መልስ ያስፈልገዋል። መልስ የሚሰጥ አካል (መንግስት) ከሌለስ? መንግስት መልስ ሊሰጥ እንደማይችል ካረጋገጠልን ለህዝብ የሚቆረቆር፣ የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል፣ የሀይማኖት ችግሮች የሚፈታ፣ የሀይማኖት ነፃነት የሚፈቅድ፣ ሰብአዊ መብት የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያስፈልገናል ማለት ነው። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት ጥረት እናድርግ። የምርጫ ድምፃችን የህዝብን ጥያቄዎች ሊመልሱ ለሚችሉ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች እንስጥ። የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈራው ኢህአዴግ ከስልጣን (በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወይ ምርጫ) እናውረደው። ሌላ ፓርቲን በመምረጥ ኢህአዴግን አውርደን ጥያቄያችንን የሚመልስልን ሌላ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስልጣን እንዲይዝ እናድርግ። ከዛ የሀይማኖት ይሁን የሌላ ነፃነታችን ይከበርልናል። ካልተከበረ ትግላችን ይቀጥል።
__________________________________________________________________________________________

ኢትዮጵያዊው ዓረናና ኤርትራዊው ህወሓት!
=======================

ዓረናዎች “ህወሓት ኤርትራን ያስቀድማል። በመሆኑም ህወሓት የሻዕቢያ ተላላኪ ነው” ስንል ህወሓቶች ደግሞ “ዓረና ከትግራይን ህዝብ ጠላቶች ከሆኑ እንደነ አንድነት ፓርቲ ጋ ለመዋህድ ጥረት እያደረገ ነው” ይላሉ።

እርግጥ ነው፤ ዓረና ኢትዮጵያዊ ነው። ከኢትይጵያውያን ድርጅቶች ጋርም አብሮ ይሰራል። ከአንድነት፣ ደቡብ ሕብረት፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድና አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው።

ዓረና እንደ ህወሓት ኤርትራዊ አይደለም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ለመጉዳት ከሻዕብያ ጋር በማበር አይሰራም። ኢትዮጵያውያንን በጠላትነት እየፈረጀ የሻዕብያ አገልጋይ አይሆንም። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን እንጂ ኤርትራውያን አይደለንም። ኤርትራውያንን ለመጥቀም ኢትዮጵያውያንን አንበድልም። ስለዚህ ከሻዕብያ በላይ አንድነት ፓርቲን እናስቀድማለን። ምክንያቱም አንድነት ፓርቲ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያም የሁላችን የጋራ ነች። ምናልባት ከሻዕብያ ጋር አብረን የምንሰራው የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ጥቅም የሚከበርበት መድረክ ሲፈጠር ብቻ ነው።

ዓረናና ህወሓት አልተሳሳቱም። ዓረና ከኢትዮጵያውያን ጋር ይሰራል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነው። ህወሓት የሻዕብያ ተላላኪ ነው። ምክንያቱም ህወሓት ኤርትራዊ ነው። ህወሓት ኤርትራዊ መሆኑ ችግር የለውም። ችግር የሆነው ህወሓት ኤርትራዊ ሁኖ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ለኤርትራ አሳልፎ እየሰጠ ግን የኢትዮጵያ መንግስትነት መቆጣጠሩ ነው። ለኤርትራውያን እየሰራ ኢትዮጵያውያንን እወክላለሁ ማለቱ ነው ችግሩ። ህወሓት ለኤርትራ መቆም የሚያስደስተው ከሆነ ኤርትራን ያስተዳድር፤ የኤርትራን ህዝብ ይወክል። ኢትዮጵያን እያስተዳደረ፣ የኢትዮጵያ ህዝብን እወክላለሁ እያለ ለኤርትራ ጥቅም መስራቱ፣ ኤርትራውያንን መወከሉ ግን ወንጀል ነው። ህወሓት የኢትዮጵያ መንግስትነት ከተቆጣጠረ ለኢትዮጵያውያን ጥቅም መስራት ነበረበት።

ህወሓት የኢትዮጵያ ስልጣን ይዞ ኤርትራን ለማስገንጠል ይሰራል፣ ዓሰብን ለኤርትራ ይሰጣል፣ ዓሰብ የኛ መሆኑ ስንከራከር ህወሓት ከኤርትራውያን በላይ ዓሰብ የኤርትራ መሆኑ ይሟገታል። ለኤርትራውያን መቆም ካለበት ለምን ወደሚወክለው ኤርትራ አይሄድም?

ዓረና ከኢትዮጵያውያን ድርጅቶች መዋሃዱን ይቀጥላል። ህወሓትም ለኤርትራውያን ማገልገሉ ይቀጥል። በዚሁ መሰረት “ዓረና ከአንድነት ፓርቲ ጋር እየተወሃደ ነው” ብላች ሁ ክሰሱን። ለኛ ችግር አይሆንም፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያውነታችን አምነን በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን አማራጭ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚያቀርብ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ የመመስረት ዕቅድ አለን። ህወሓትም ሻዕብያን ማገልገሉ ይቀጥል ምክንያቱም ህወሓት የኤርትራ ተወካይ (በኢትዮጵያ) መሆኑ እናውቃለን።

ህወሓት ግን ዓረና ከአንድነት ጋር የመዋህዱ ዜና ሲሰማ እንዲህ ከተደናገጠ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጭምር ስንዋሃድስ ምን ሊሆን ነው? ዓረና ከአንድነት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብዙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋርም ይወሃዳል። ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት እንፈልጋለንና።

ህወሓት ኤርትራን ሲያስበልጥ ዓረና ግን ኢትዮጵያንን ያስቀድማል።
__________________________________________________________________________

“የካቲት 11″ን እናክብረው?!
=============

የየካቲት 11 ዓላማ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ ሰላምና ልማት ነበር። ህዝቦች ታገሉ፤ መስዋእት ከፈሉ፤ ለነፃነት ሲሉ። ግንቦት 20 ሆነና ስልጣን ተያዘ። መስዋእት የተከፈለበት ዓላማ ፍሬ አፍርቶ ከሆነ ለማረጋገጥ በህይወት የተረፉ ታጋዮች ጠየቁ። ታጋዮቹ በጠላትነት ተፈርጀው በ1985 ዓም ተባረሩ፣ ታሰሩ፣ ተገደሉ። የወላጆቻችን መስዋእትነት ፍሬ ለመቅመስ ሞከርን። በድንጋይ ተወገርን። ወላጆቻችን መስዋእት የከፈሉ ለኛ ነፃነት ነበር።

ነፃነት የመቃወም፣ የመደገፍ ወይም ከሁለቱም ዉጭ መሰለፍን ያጠቃልላል። ወላጆቻችን የተሰዉለት የነፃነት ዓላማ አለን ብለን የፈለግነውም ሐሳብ ለህዝብ ማቅረብ መረጥን። ስለተቃወምን ታፈንን። እናም የየካቲት 11 መነሻ ዓፈና ነበር፤ መድረሻውም ዓፈና ሆነ። ፀረ ዓፈና መታገል እንዳለብን ገባን። የወላጆቻችን ዓለማ ነፃነት ነበር። የኛ ዓላማም ነፃነት ነው። ስለዚህ የኛና የወላጆቻችን ዓላማ አንድ ነው፤ ነፃነት። ያሁኗ ህወሓት ዓላማ ግን ዓፈና ሆኗል።

ያሁኗ ህወሓት በተግባር እያፈነች በሚድያ ግን “የካቲት 11″ን ማክበሯ አይቀርም። “ለካቲት ብርሃን ዉፁዓት እያ!” እያለችም እንደተለመደው ማደንቆሯ አይቀርም። የየካቲት 11 ዓላማ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ የሰማእታት ልጆችን በድንጋይ መውገር ነበር ማለት ነው? ነፃነት ማለት ጭቆና ማለት ነው?

በተግባር ስንቃወም ታፈንን። ስንቃወም ከታፈንን መቃወማችን ትክክል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም እኛ ወጣቶች የመቃወም መብት አለን። “ስንቃወም ለምን እንታፈናለን?” ብለን መቃወም እንችላለን። የህወሓት የዓፈና ተግባር የኛን የመቃወም አስፈላጊነት የሚያረጋግጥ ነው።

ስለዚህ የወላጆቻችን የትግል ዓላማ ተጠልፎ ለስልጣን ማራዘምያ ሆኗል። ስልጣንም ልማት ለማፋጠንና ነፃነትን ለማረጋገጥ ከማዋል ይልቅ ዜጎችን ለማፈን እየዋለ ነው። ስለዚህ የወላጆቻችን መስዋእት ግቡ አልመታም።

በኔ አመለካከት ህወሓት በሁለት ይከፈላል፤ ስልጣን ፈላጊ መሪዎቹና ነፃነት ፈላጊ ታጋዮቹ። ስልጣን ፈላጊ የህወሓት መሪዎች ስልጣን ጨብጠው ህዝብ እየጨቆኑ ይገኛሉ። ነፃነት ፈላጊ ታጋዮቹ ደግሞ ለነፃነት ሲሉ መስዋእት ከፍለው ለራሳቸውም ነፃነት ተነፍገው እየተጨቆኑ ይገኛሉ። ጭቆናን መቃወም ሲጀምሩ ደግሞ በድንጋይ ይወገራሉ (አስገደ ገብረስላሴ በዓዲግራት)። ስለዚህ የህወሓት የነፃነት ታጋዮች ተጨቁነው ይኖራሉ። የህወሓት መሪዎች ደግሞ ታጋዮቹን በማባረር፣ የራሳቸውን ቤተሰብ ይዘው የሀገር ሃብት እየበዘበዙ ህዝቦችን በማሸበር ይገዛሉ።

ስለዚህ የህወሓት ታጋዮች የነፃነት ዓላማ ተኮላሽተዋል። የወላጆቻችን የነፃነት ተልእኮም ተጠልፏል። የወላጆቻችን ዓላማ አሁን ለምናየው ዓፈና የታለመ ነበር ካላችሁኝ አላምናችሁም። ካመንካችሁ ግን ዓላማው ስህተት ነበር እላችኋለሁ። ምክንያቱም የመስዋእትነት ዓላማ ነፃነት ነው። የወላጆቻችን ዓላማም ነፃነት ነበር። ስለዚህ ነፃነታችንን በተግባር መከወን አለብን። ነፃነታችንን ከተነፈግን ግን ነፃነታችንን ለማስመለስ መታገል ይኖርብናል።

ነፃነት የሌለው ህይወት አንፈልግም። እየኖርን አንሞትም።

1 Comment

  1. Its shameful act when you see such an idiot guy wrote a bull shit idea this guy never mentioned the need of tigray development.there is no good governance,there is no public transportation unlike ambesa bus no water,no electric,no industries,…….the city don’t have a plan no economic institutions…no.strong oppositios…..I know tplf is not better organizations but arena is the worst one because they never mentioned at least the abovementioned problems.

Comments are closed.

Previous Story

በሳንሆዜ ከተማ ለወራት የታቀደው የወያኔ የማጭበርበር ሴራ በሚያሳፍር መልኩ ተጠናቀቀ

Next Story

39ኛ የካቲት ለማክበር ሽርጉድ እና የተሟጠጠው የትግራይ ህዝብ ስሜት

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |
Go toTop

Don't Miss

የሶዶ ፖሊስ ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጸመ

የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ‹‹ስቴት ፈንድ›› በሚል በየወሩ የሚሰጣቸው 340
colesterol

health: ስለኮሌስትሮል ሊያውቁ የሚገባዎት 6 ነገሮች

6. ኮሌስትሮልን በጥቂቱ ኮሌስትሮል የሁሉም እንስሳት ህዋሳት አካል የሆነ የማይሟሟ