የኢዮብ መኮንን የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

/

(ዘ-ሐበሻ) በሬጌ የሙዚቃ ስልት አጨዋወቱ በበርካቶች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈው ድምጻዊ እዮብ መኮንን ባሳለፍነው ቅዳሜ ለህክምና በሄደበት ኬኒያ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አጋ-ካሃን የተሰኘ ሆስፒታል ህይወቱ ማለፉን ዘ-ሐበሻ መዘገቧ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ዛሬ ከቀኑ በ9ሰዓት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ በርከት ያሉ አድናቂዎቹ፣ የሙያ አጋሮቹ እና ቤተሰቦቹ በተገኙበት ተፈጽሟል።
“እንደቃል” በተሰኘው ብቸኛና የመጀመሪያ አልበሙ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፎ የነበረው ድምፃዊ እዮብ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የእህቱን ልጅ ትምህርት ቤት አስመዝግቦ ከተመለሰ በኋላ የግቢውን በር በማንኳኳት ላይ ሳለ ራሱን ስቶ መውደቁና በዚህ የተነሳም በተገኘበት ስትሮክ ለሞት እንደበቃ በዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ ከታመመበት ጊዜ ጀምሮ ሲዘገብ ሰንብቷል። የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ (stroke) መሆኑ ታውቋል።
በተወለደ በ38 ዓመቱ እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት 3፡45 አካባቢ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ድምፃዊው ድምጻዊው ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበር። በተጨማሪም በቅርቡ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቅ የሙዚቃ ስራውን ከ70 በመቶ በላይ አጠናቆ እንደነበር በተለያዩ ሚድያዎች የተዘገበ ሲሆን ለድምፃዊው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተጠናቀቁትን ሙዚቃዎች ለማሳተም እቅድ እንዳለም ለዘ-ሐበሻ ከደረሰው መረጃ መረዳት ተችሏል።
http://www.youtube.com/watch?v=-G1IXShtPLM

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዓባይ ሊያለማን ወይስ ሊያጠፋን? - የሕዳሴው ግድብና ዐባይ፣ የሚሊኒየሙ ዐባይ ተጋቦት
Share