የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫና የቀረበ ጥሪ

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከሐምሌ 22 – 28 2008 ዓመተ ምህረት ድረስ ተካሂዷል፡፡ ይህን የአሁኑን የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ልዩ የሚያደርገዉ የኦሮሞ ሕዝብ በመላዉ ኦሮሚያ በሚያስደንቅ የአንድነት፣ የቆራጥነትና የጀግንነት ስሜት እያካሄደ ያለዉንና ለዘጠኝ ወራት የዘለቀዉን የነፃነት፣ የዲሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የሰብዓዊ መብት እና ራሱን በራሱ የማስተዳደር ጥያቄዎቹን እጅግ አጠናክሮ በቀጠለበት ታሪካዊ ወቅት የተካሄደ መሆኑ ነዉ፡፡ የኦዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በመላዉ ኦሮሚያ የሚካሄደዉ ሰላማዊ የሕዝብ ተቃዉሞ በገዢዉ ቡድን የተደረጉበትንና የሚደረጉበትን አስከፊ ጫናዎችና የመሣሪያ አፈናዎች ሁሉ ተቋቁሞ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እየተሸጋገረና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹንም ለተመሣሣይ ትግል እያነሣሣ መሆኑን በአድናቆት እንመለከታለን፤ በሚቻለን መንገድ ሁሉም ለሰላማዊ ትግሉ ድጋፍ ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት ደግመን ደጋግመን እናረጋግጣለን፡፡ ሕዝባችን የጠየቃቸዉን የዲሞክራሲ መብቶች ሙሉ በሙሉ እስኪጎናፀፍ ድረስ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዉን አጠናክሮ እንደቀጥልም ልናበረታታዉ እንወዳለን፡፡

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰፊ ጊዜ በመዉሰድ ወቅታዊዉን የአገራችንን ሁኔታ በአጠቃላይ በመላዉ ኦሮሚያ እየተካሄደ ያለዉን ታሪካዊ የሆነ ሕዝባዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ደግሞ በተለይ እንደሚከተለዉ ገምግሟል፤

የኦሮሞ ሕዝብን ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በተመለከተ፡-
በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) የሚመራዉ የኢሕአዴግ መንግሥት ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት በብቸኝነት ሥልጣን ይዞ ቢቆይም ወይ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን አላደረገም፤ ወይንም ደግሞ ጧትና ማታ የሚመፃደቅበትን ልማትና ዕድገት አስገኝቶ ሕዝባችንን ከአስከፊ የድህነት ኑሮ ለማላቀቅ አልቻለም፡፡ ይልቁንም የሥርዓቱ የግፍና የጭቆና ድርጊቶች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ በመምጣታቸዉና በአገሪቱ የሰፈነዉ የሕዝቦች ድህነት፣ መከራና ስቃይ ከምን ጊዜዉም በላይ እየከፋ በመምጣቱ የኢሕአዴግ የአገዛዝ ሥርዓት የመፈናቀል፣ የረሃብ፣ የስደት፣ የዘወትር ስጋት፣ የጉስቅልናና የአስከፊ ድህነት መገለጫ ሥርዓት ሆኗል፡፡ እንደሚታወቀዉ የኦሮሞን ሕዝብ ለተጠናከረና ካለማቋረጥ ለረዥም ጊዜ ለዘለቀ ሰላማዊ የአመፅ እንቅስቃሴ ያነሣሣዉ ይህ ከልክ ያለፈ የኢሕአዴግ የግፍ አገዛዝ ሥርዓት ነዉ፡፡ የህወሐት/ኢሕአዴግ ሥርዓት በፈጠራቸዉ ችግሮች የተጎዳዉና ግንባር ቀደም ተጠቂ የሆነዉ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ባለመሆኑም የተቃዉሞ እንቅስቃሴዉ ወደተለያዩ የአገራችን ክልሎች በመስፋፋት አገር-አቀፍ አመፅ ከመሆን ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ ሕዝባዊ ተቃዉሞዉ በኦሮሚያ ክልል ተጠናክሮ በመቀጠል ወደሌሎች የአገራችን ክፍሎችም ቢስፋፋም ከገዢዉ ቡድን የሚሰጠዉ መልስ እንደተለመደዉ በጉልበትና በጦር መሣሪያ ለማፈን ከመሞከር ያለፈ ሆኖ አልታየም፡፡ የሕዝብን ስቃይና መከራ ለማስወገድ ሳይሆን ለራሳቸዉ ድሎትና ለተሠማሩበት የሕዝብ ሀብት ዝርፊያ ብቻ ቅድሚያ የሚሠጡት የገዢዉ ቡድን ቁንጮዎች ግን ለሕዝባችን ጥያቆዎች ተገቢዉን መልስ መስጠት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም እስከአፍንጫዉ የታጠቀና ወገንተኝነቱን ለሕዝቡ ሳይሆን ለገዢዉ ቡድን ብቻ ያደረገ ገዳይና ጨፍጫፊ ሠራዊት አሠማርተዉ የብዙ ሺህዎችን ደም ማፍሰስ፣ የብዙ መቶዎችን ሕይወት ማጥፋትና በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ በጅምላ እስር ቤት ማጎርን እንደመፍትሄ አድርገዉ ወስደዋል፡፡ ይህ የገዢዉ ቡድን ጭፍንነት ደግሞ ሕዝባችን በልበ-ሙሉነት የጀመረዉንና በሚያስደንቅ ቆራጥነት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያካሄደዉን ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል እየደረገዉ ስለሆነ በዚያች አገር የመንግሥት ሥርዓት ለዉጥ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን ያረጋገጠ ሂደት ሆኗል፡፡ ስለሆነም የኦሮሞን ሕዝብ በርታ፣ ሰላማዊ የተቃዉሞ ትግልህን አጠናክረህ ቀጥል፣ እኛም በተቻለን ሁሉ ከጎንህ ነን፤ በገዢዉ ቡድን “የከፋፍሎ መግዛት” ዕኩይ ፖሊሲ ተታለህ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖችህ ጋር ምንም ዓይነት አለአስፈላጊ ቅራኔ ዉስጥ ላለመግባት እስከአሁን እንዳደረከዉ ሁሉ ለወደፊቱም ተገቢዉን ጥንቃቄ ሁሉ አድርግ እንላለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታላቅ ሕዝባዊ የስብሰባ ጥሪ ኢትዮጵያን እናድን አንድነት ማህበር በእስራኤል

የጎንደርን ሕዝብ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በተመለከተ፡-
ከዘጠኝ ወራት በፊት በመላዉ ኦሮሚያ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በአገራችን ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት በሚካሄደዉ ሕዝባዊ ትግል ዉስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ግንባር-ቀደም ሥፍራ እንዲይዝ ከማድረጉም በላይ ለሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹም በጥሩ አርዓያነት የሚታይ ስለሆነ የተለያዩ ሕዝባዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እንዲቀጣጠሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ጎንደር ዉስጥ በቅርቡ የተጀመረዉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴም ለሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ ተገዢ የሆነና ለመብት ጥያቄዎች ተገቢ የሆነ አፋጣኝ መልስ የሚሠጥ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች አካል ነዉ፡፡ የጎንደርን ሕዝብ ጥያቄ ታሪካዊ ከሚያደርጉትና የሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላማዊ የመብት ትግል አካል መሆኑን ከሚያረጋግጡት እርምጃዎች አንዱ ጀግናዉ የጎንደር ሕዝብ ከመነሻዉ በኦሮሞ ወገኖቹ ላይ በገዢዉ ቡድን የተወሰደዉን ኢሰብዓዊ እርምጃ ማዉገዙና የፈሰሰዉ የኦሮሞ ሕዝብ ደም ደሙ፣ ያለፈዉ የኦሮሞ ታጋዮች ሕይወትም ሕይወቱ መሆኑን መግለፁ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄም የራሱ ጥያቄ አካል መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ማረጋገጡ ነዉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ የሕዝቦች የትግል አንድነትና አጋርነት በሰላማዊ ሕዝባዊ አመፅ አማካይነት መገለፅ ሕዝባችንን ከምን ጊዜዉም በላይ በተጠናከረ መንገድ ከማስተሣሠሩም በላይ የተጀመረዉ ሕዝባዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት እንዲስፋፋ የሚያደርግ በመሆኑ የጎንደርን ሕዝብ ሰላማዊ የሆነ የዲሞክራሲ ትግል እጅግ ታሪካዊና የሚመሰገን ጅምር ያደርገዋል፡፡ እኛ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ለጀግናዉ የጎንደር ሕዝብ እንቅስቃሴ ያለንን ልባዊ አድናቆትና አክብሮት እየገለፅን የተጀመረዉ ሰላማዊ የአመፅ እንቅስቃሴ ሕዝቡ የሚፈልገዉን ዉጤት እስኪያስገኝ ድረስ በሚቻለን ሁሉ ከጎኑ እንቆማለን፡፡ በዚህ አጋጣሚም ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲን ናፋቂ የሆናችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሕወሐት/ኢሕአዴግ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሳትዘናጉ በጋራ በመቆም ይህን የሁሉም ችግሮቻችን ምንጭ የሆነዉን ጨቋኝ ሥርዓት ከሥሩ ለመገርሰስና በሥርዓቱ ጭፍን አከሄድ ምክንያት የተፈጠሩት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በሕዝባዊ ትግል ተወግደዉ ወደማይቀርላቸዉ መቃብር እንዲወርዱ ለማድረግ ከምንጊዜዉም በላይ እንድትተባበሩና በአንድነት እንድትቆሙ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

አገር-አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት መመሥረትን በሚመለከት፡-
የኦዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ትብብር ለመመሥረት ይቻል ዘንድ በድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ አካል የተደረጉትን ጥረቶችና የተገኙትን አበረታች ዉጤቶች በጥልቀት ገምግሟል፡፡ እስከአሁን የተደረጉት ጥረቶችና የተገኙትም ዉጤቶች አበረታች ብቻ ሳይሆኑ ወደምንፈልገዉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመረማመድ ተስፋ ሰጪዎችም ናቸዉ፡፡ ስለሆነም የድርጅታችን የሥራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ የተጀመሩትን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአገር ዉስጥ እየተካሄዱ ያሉት ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ይቻል ዘንድም የተጀመረዉን ከልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅች ጋር ትብብር ለመመሥረት ያስቻለ ጥረት የበለጠ በማስፋትም አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ-አቀፍ የተቃዋሚ ኃይሎች ህብረት ለመመሥረት የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሙሉ ኃላፊነት ሰጥተነዋል፡፡ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ዕዉን ለማድረግ በተለያዩ መንገዶች ትግል እያካሄዱ ያሉትን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ያሰባሰበ አንድ አገር-አቀፍ የተቃዋሚዎች ትብብር በአስቸኳይ መመሥረት እየተካሄደ ያለዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ የበለጠ ለማጠናከርና ለትግሉ የተማከለ የፖለቲካ አመራር ለመስጠት ከማስቻሉም በላይ የሕወሐት/ኢሕአዴግ መዉደቅ አይቀሬ በመሆኑ ለሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መሠረት ለመጣልም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነዉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከሀገር ወጡ፥ በፍኖተሰላምና ቡሬ መሀል ውጊያው ቀጥሏል፥ ብልጽግና ስለአማራ ክልል እየመከረ ነው

ሰፊ መሠረት ያለዉና አገር-አቀፍ የሆነ የተቃዋሚ ድርጅቶች ህብረት ለመመሥረት ይቻል ዘንድ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በኩል ረዥም ጊዜ የወሰዱ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን የእነዚህ እንቅስቃሴዎችና ጥረቶች ዉጤትም በቅርብ ጊዜ ለመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይፋ እንደሚደረግ ስናበስር ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፡፡ በዚህ አጋጣሚም የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የምትሉ ድርጅቶች ሁሉ አሁን አገር ዉስጥ እየተካሄዱ ያሉትን ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በቅርበት እንድትከታተሉና የሕወሐት/ኢሕአዴግን በሕዝባዊ ትግል መዉደቅ ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለዉን ክፍተት ለመሙላትና አገራችን ወደአስከፊ ብጥብጥና ደም መፋሰስ እንዳትገባ ለማድረግ እንዲቻል እየተፈጠረ ወዳለዉ አገር-አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት በመምጣት የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡

እንደ ኦዲግ እምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነቶቻችንን አቻችለን በሚያግባቡን ዓላማዎች ሥር ብንሰባሰብና የተባበረ ትግል ማካሄድ ብንችል ያለምንም ጥርጥር እናሸንፋለን፤ እንደ የእስከአሁኑ አካሄዳችን የየራሳችንን መንገድ ብቻ ተከትለን በተበታተነ ሁኔታ እንቀጥል የምንል ከሆነ ግን መሸነፍ ብቻ ሳይሆን እንታገልለታለን የምንለዉን ሕዝብም ሆነ የጋራ ቤታችን ናት የምንላትን አገር ለከፋ ችግር እንዳርጋለን፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም የታሪክ ተጠያቂ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ከላይ እንዳልነዉ የሕወሐት/ኢሕአዴግ አገዛዝ መዉደቅ አይቀሬ ነዉ፡፡ አሁን ያለዉ ጥያቄ “የሕወሐት/ኢሕአዴግ መንግሥት ይወድቅ ይሆን?” የሚል ሳይሆን “መቼ ይወድቃል?” የሚለዉ ነዉ፡፡ በኦሮሚያ ተጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ ያለዉ ሕዝባዊ አመፅ ተጠናክሮ ከቀጠለ የዚህ ግፈኛ ሥርዓት መዉደቂያ ጊዜ ረዥም ስለማይሆን ይህን የታሪክ አጋጣሚ በሚገባ ለመጠቀም መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

ሁላችንም እንደምናስታዉሰዉ በአገራችን እንዲገነባ የምንፈልገዉን ዓይነት እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ያስችሉ የነበሩ ብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች አምልጠዉናል፡፡ በሕዝቦቻችን የደምና የሕይወት መስዋዕትነት የምንፈልገዉን ለዉጥ ሊያመጣ የተቃረበዉ ይህ የአሁኑ የታሪክ አጋጣሚ ግን በምንም ዓይነት መንገድ ሊያመልጠን አይገባም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የምንል ኃይሎች ሁሉ ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተዉ ተቀራርበን በመነጋገር በሚያስማሙን ጉዳዮቸ ላይ በጋራ ለመታገልና የሕዝባችንን መስዋዕትነት ፍሬያማ ለማድረግ የሚያስችሉንን ወሳኝ እርምጃዎች እንድንወስድ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕወሓት ስድስት የኦሮሞ ተወላጆች አለባቸው ጫካ ወስዶ እንደረሸናቸው ተጋለጠ፤ በትግራይ 14 የኦሮሞ ተወላጆች ከጨለማ ክፍል ታስረዋል

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በተመለከተ፡-
የኦዲግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላት ለሕወሐት መራሹ የኢትዮጵያ ጨቋኝና ኢ-ዲሞክራሲያዊ መንግሥት የሚያደርጉትን የገንዘብም ሆነ የወታደራዊ መሣሪያዎች እርዳታ እንዲያቆሙ አጥብቆ ይጠይል፡፡ በተደጋጋሚ እንደታየዉ ሕወሐት መራሹ የኢትዮጵያ አምባገነን አገዛዝ በአገር ዉስጥ ምንም ዓይነት ሕዝባዊ መሠረትም ሆነ የሕዝብ ድጋፍ ስለሌለዉ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለዉን የገንዘብም ሆነ የወታደራዊ መሣሪያዎች ድጋፍ የሚያገኘዉ የአሜሪካን መንግሥት ጨምሮ ፅንፈኝነትን ለመዋጋት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ትብብር ከሚፈልጉ የዓለም-አቀፍ ማህበረሰብ አባላት ነዉ፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የምዕራብ አገራት መንግሥታት መገንዘብ ያለባቸዉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መቆም ሲገባቸዉ ከአምባገነን ጨቋኝ ገዢዎች ጋር በመቆም በየአገሮቻቸዉ የሚያራምዱትንና የሚያምኑበትን የዲሞክራሲ ሥርዓት እየተቃረኑ መሆናቸዉን ነዉ፡፡ ለዚህ ጨቋኝና አምባገነን መንግሥት የሚሠጡት ማንኛዉም ድጋፍም የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ሰላምና ፀጥታ ችግር ላይ የሚጥል መሆኑን ተገንዝበዉ ድጋፋቸዉን ለሕዝብ ቢያደርጉ በዚያ አካባቢ እንዲኖር የሚፈልጉትን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂነት ባለዉ ሁኔታ ሊያረጋግጡ ይችላሉ፡፡ በተለይም የአሜሪካ መንግሥት ምንም ዓይነት የሕዝብ ድጋፍም ሆነ ተቀባይነት ከሌለዉ ከአምባገነኑ ሕወሐት መራሽ የኢሕአዴግ መንግሥት ጋር በመተባበር የራሱን የረዥም ጊዜ የሰላምና የፀጥታ ፍላጎት ለአደጋ ከመዳረግ ይልቅ የኢሕአዴግ መንግሥት ለሕዝቡ የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ተገቢዉን መልስ እንዲሰጥ ጫና በማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መቆም ይኖርበታል፡፡

በተደጋጋሚ እንደታየዉ ሕወሐት/ኢሕአዴግ የሚያዳምጠዉ አስተዳድረዋለሁ የሚለዉን ሕዝብ የልብ ትርታና የመብት ጥያቄ ሳይሆን የገንዘብም ሆነ የመሣሪያ ትራፊ የሚወረዉሩለትን ምዕራባዉያን መንግሥታት ስለሆነ የአሜሪካ መንግሥትና ሌሎች ምዕራባዉያን መንግሥታት የገንዘብና የወታደራዊ መሣሪያ ዕርዳታ በመስጠት ሕዝባችንን ከማስረገጥ ይልቅ በሥርዓቱ ዘንድ ያላቸዉን ተሰሚነት ተጠቅመዉ ገዢዉ ቡድን ለሕዝቡ ጥያቄዎች ተገቢ የሆኑ መልሶችን በአስቸኳይ እንዲሰጥ ጫና ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ ለሕወሐት/ኢሕአዴግ መንግሥት ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ምዕራባዉያን መንግሥታት የሚሰጠዉ የገንዘብም ሆነ የወታደራዊ መሣሪያ ዕርዳታም በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የሚሰጠዉ የገንዘብም ሆነ የመሣሪያ እገዛ ገዢዉን ቡድን አጠናክሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስቃይና መከራ ከማራዘም ዉጭ ለሕዝቡ የሚጠቅመዉ ነገር ስለሌለ ነዉ፡፡ ሰለሆነም ምናልባት ለተራቡ ወገኖቻችን የሚሠጥ የነፍስ ማዳን ዕርዳታ ካልሆነ በስተቀር አሁን በሥልጣን ላይ ላለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሠጥ ማንኛዉም የገንዘብም ሆነ የመሣሪያ ዕርዳታ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ፍትህና ነፃነት ለሁሉም ሕዝቦች!

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ
ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ. ም.

8 Comments

  1. እጅግ የሚመሰገን ዓላማ እና እቅድ ይዛቹሃል። ወጣቱ ጃዋርና መሰሎቹ ከናንተ ይማራሉ የህዝብ ሃላፊነት እና በስር ይቆዩ። የግንቦት 7 ህብረት ሌሎችም ግንባር መፍጠር ግዜ ኣይውሰድ። ኢህኣዴግ ሲወድቅ መምራት የሚችል ተዘጋጅቶ ማስተማር መጀመር ኣለበት። ተስፋ ሁኑን። ሃገር እና ህዝብ ከናንተ ሆደ ሰፊነት ይጠይቃል። በርቱ።

  2. tplf has moved more than 20 thanks at the south western barracks in Jimma to Mekele yesterday. they are looting ethiopian military hardware. please follow and tell us where they take them

  3. እኔ የምለው የጎንደር ሕብረት እንዴት የጥምረቱ አካል አልሆነም ። አሃ አንቦ ላይ ሰልፍ ሲኖር አሩሲ ሲያምጽ ቦረና ሲቃወም ሁላችንስ የኦሮምያ ሕዝብ ተቃውሞ ብለን ነው የምንጠራው ። ኦዴፎች መግለጫችሁ መልካም ነው። ለቀጣዩ የሕዝባችን ትግል አጋዥ እንደሚሆን እምነቴ ነው። ነገር ግን በመግልጫችሁ አጽዕኖት በመስጠት ለጎንደር /የጎንደር ሕዝብ እያላችሁ ያቀረባችሁት አገላለጽ የተሳሳተ በመሆኑ ሊታረም ይገባል። በጎንደር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ንቅናቄ የመላው የአማራ ሕዝብ ትግል በመሆኑ ምስጋናም ይሁን እርግማን መገልጽ ያለበት በአማራው ተጋድሎ ስም ነው። ለዚህ የአገላለጽ ግድፈት በር የከፈትው ራሱ የትግሉ አላማና አቅጣጫ በቅጡ ያልገባው አማራ ተብዬው በመሆኑ ልወቅሳችሁ አልችልም።
    በርቱ

  4. ye Ethiopia Hizb Bandera

    ye Neftegnoch new yetbalew

    zare be Oromo Bandera tekeyere ende ?

    Ethiopia negn yemel mechew be wenetegnaw Bandera ayderaderim

    ke G7 besteker !!

  5. amhara cool down this is not you’re time we don’t forget you’re past history how to rape women and children of all Ethiopian don’t forget we are different regions but one country you’re flag not represent our nation and nationality like Oromo afar Somali etc your flag is only for Ethiopian churchs and amhara regimes if believe it

  6. yaa Somali persedant Oromo wandimochu inda honuu yaaqal naftagaa yalawe amaaraa naa bandirawin naw inge Oromon aydalam batarki yaa Oromo hizib itobiyawiyan wandimochun yachafachafabt wayim yagazabate tarke yalame Oromo degimo ka Somali afar gar ande yazer gind kush mahonachowin atirisa .

  7. Oromo people have questions for you. You divide our organisation olf dividing organisation is the evil thing it is tplf fascist job to eliminate others to make possible for them and to keep themselves in power. You always run to sign you run to sing with tplf. Now you rung to sign with Ginbot 7 without wait for our original big ABO olf. We do not know why you run what you have to hide. Lencho Oromo people never had forgotten what have done. Your signature brought harm to us. You sing with tplf do disarm our children and tplf mas-scared Oromo children just because they have guns. Oromo mothers and fathers sisters and brothers have unlimited questions for you. it is not simple just like some of you thinks. There are mothers and fathers who lost from one family two three kids. Because of you signed with tplf without proper analysis.

    We are not saying why you unite with our brothers Amhara group or others Ethiopians, but there is our organisation ABO who is Oromo national organisation and can represent all Ethiopians. We do not know why you rung to sign when all Oromo people are angry with you for the mistake you have done. We do not want you to represent us and repeat the mistake you have done in the past. What we want is that the unity that make oromo people happy and unity all Ethiopians.

Comments are closed.

Share