ፖለቲካኛ ነኝ! (ዳዊት ዘሚካኤል)

ፍርሃት ስጋ ለብሶ፤
ፍቅርን ደርምሶ፤
ህሊናን አፍርሶ፤
ስስትን አንግሶ።
አንደኛው በቁንጣን፥ ሢተፋ እያደረ፤
ሌላኛው በረሃብ፥ እየተሣከረ፤
አንደኛው “የት ልብላ?”፥ ለምርጫ ሲጨነቅ፤
ሌላኛው “ምን ልብላ?” ፥ በማጣት ሲሳቀቅ፤
ሃገር ‘ወፍጮ’ ሆና መንፈሱን ብታደቅ፤
”ቤቴን አተርፍ” ባይ በስደት ሲማቅቅ፤
ባህር እየገባ ወጣት ሲተላለቅ፤
በነዲድ በረሃ፤
የሃገሬ ደሃ፤
አንገት ሲሞሸለቅ፤
ደልቶት ባለ ግዜ፥ በዕንባ ሲጨማለቅ።
ተስፋ የሸሸው ትውልድ በስጋት ደንዝዞ፤
ቁልቁል አቀርቅሮ ሲተክዝ እያየሁ፤
”ፖለቲካ በሩቅ!” እኔ እንዴት እላለሁ!?
ፖለቲከኛ ነኝ!
ወሠን አልቦ ምድር፥ ለ’ህታችን ጠቧት፤
‘ግርድና ሽጠናት’፥ የአረብ ንቀት ከቧት።
ያ! አርበኛ አባት፥ ‘ሚጦረው በማጣት፤
በሽበት ዘመኑ፥ እጁን ለምፅዋት
እንደ ‘አሮጌ አህያ’፥ ክምር ማገዶ አዝላ፤
የብዙሃን እናት፥ በመከራ ዝላ፤
ዋ!… ስትል እያየሁ፤
”እኔ ምን አገባኝ!”፥ ዛሬ እንዴት እላለሁ!?
ፖለቲከኛ ነኝ!
ፍትህ የተጠማ ሲሄድ ወደ ሸንጎ፤
‘በሆድ አደር’ ዳኛ እሪታው ተነጥቆ፤
በፍርድ አደባባይ ክብሩን ተነፍጎ፤
ለግርፋት ለእስር ሲጣል ወደ ፍርጎ!
”የምሁር” አጎብዳጅ
ከባለግዜ ፊት ሲታሽ እንደ ገረድ፤
በቀጣፊ ሸምጋይ እውነት ስትዋረድ፤
”የሀገር አብሠልሳይ” ሲቀጣ በሀሠት ፍርድ፤
እልፍ ላ’ገር አልቃሽ፥ ሀቁ ስትታረድ።
ይሉኝታችን ሻግቶ፥ እልፍ ‘ግፍ’ እያየሁ፤
”ጎመን በጤናዬን” ዛሬ እተርታለሁ!?
የድሃው መራቆት እረፍት የሚነሣኝ፤
የርሃብ ለከት ማጣት ዕንባ ‘ሚያሳረግፈኝ፤
የጨቅላዉ ሠቀቀን፥ አንጀቴን ‘ሚልጠኝ፤
ፖለቲከኛ ነኝ!
በጎጠኛ መዳፍ፥ ድንበር ሲመዠረጥ፤
‘ራሄል ሠሚ አጥታ፥ እንደ እንቧይ ስትፈርጥ
ሃገር ስትኮመሽሽ፥ እንደ ሠም ስትቀልጥ
አልጠግብ ባይነት፥ ንፍገትን አብቅላ፤
በመጠፋፋት ጫፍ፥ ‘ጦቢያ’ ተንጠልጥላ።
‘ቀዳሚት ሃገሬ’፥ ጭራ ሆና እያየሁ፤
”ፖለቲካ በሩቅ!”፥ እኔ እንዴት እላለሁ!?
ፖለቲካ ነኝ!
የእ’ህቶች ጩኸት፥ ከብዶኝ ‘ምርበተበት፤
”አይነጋም ወይ!?” እያልኩ ካምላክ የምሟገት
በነፃነት ማምለክ በቤቴ ያቃተኝ፤
በነፃነት ማሠብ ቅንጦት የሆነብኝ፤
የፍቅር ‘ረሃብ ልቤን ‘ሚያቃትተኝ፤
የሃገራችን ዕጣ፥ ዕንቅልፍ የሚነሳኝ፤
የእናታችን ዕንባ፥ አንጀቴን ‘ሚያጤሠኝ፤
ፖ.ለ.ቲ.ከ.ኛ. ነኝ!!!!!…..

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተያዘው የጸሎት ፕሮግራም እመኑኝ አይሠራም! - ፍርዱ ዘገዬ
Share