February 19, 2013
45 mins read

ስለ መንበረ ፕትርክናው ዕጩዎች የቅድመ ምርጫ ግምት

(የሐራ ተዋሕዶ ድረ ገጽ ዘገባ) ኀምሳ አራት ዓመት ወደ ኋላ፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያሪክ ለኢትዮጵያ የተገኘው ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ዕጨጌ ወጳጳስ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም በ116ው የእስክንድርያ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ በተቀቡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው ለከፍተኛው ማዕርግ በበቁበት የፓትርያሪክነት ሢመታቸው ወቅት እዚያው ግብጽ ካይሮ ይገኙ በነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ፊት ካሰሙት ታሪካዊ ንግግር መካከል÷ ‹‹ወደዚህ ወደ ከፍተኛው ማዕርግ ለመድረስ ሲፈቀድልኝ ለግርማዊነትዎ ያለኝን የታማኝነት ቃል ኪዳን በፊትዎ ቆሜ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ምክንያት አግኝቻለኹ፤›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከ1951 – 62 ዓ.ም በፓትርያሪክነት ሲያገለግሉ ቆይተው በተወለዱ በ73 ዓመታቸው ጥቅምት 2 ቀን 1962 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ተቀብረዋል፡፡ ከዚያ ወዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ፓትርያሪክ እየተመራች ኤጲስ ቆጶሳትን ትሾማለች፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ካረፉና መዋዕለ ሐዘኑ በመላ ኢትዮጵያ ለአርባ ቀናት ከተፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የመጀመሪያውን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ሁለተኛውን ፓትርያሪክ ለመሾም መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት በዕጩነት ቀረቡ፡፡ የሦስቱ አባቶች ስም ዝርዝር ከመጋቢት 26 – 29 ቀን 1963 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንበር ላይ ተቀምጦ ጸሎተ ቅዳሴ ሲደረግበት ቆይቶ መጋቢት 29 ቀን በመንበረ ፓትርያሪኩ በተደረገው ምርጫ፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደራሴና የሐረርጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከፍተኛውን ድምፅ ማለትም 80 በመቶ አግኝተው ተመርጠዋል፡፡ ምርጫው ለንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡

በፍጥነት ወደፊት – ጥር 6 ቀን 2005 ዓ.ም፤ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ በዳላስ ቴክሳስ ስለተደረገው ሦስተኛው ዙር ጉባኤ አበው የዕርቀ ሰላም ልኡካኑን ሪፖርት ለማዳመጥ፣ በቀጣይነት በካሊፎርኒያ ሎሳንጀለስ ስለታቀደው አራተኛው ዙር ጉባኤ አበው ለመወሰን በተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጠረጴዛ ‹‹ከፓትርያሪክ ሹመት በፊት ዕርቀ ሰላሙ ይቅደም›› የሚሉ አባቶች በብዛትም በአቋምም የበላይነቱን ይዘው ጠንክረው እየወጡ ነው፡፡ ከስብሰባው መካከል በሹልክታ የወጡ አንድ አባት ‹‹አግዙን እንጂ›› ሲሉ እንዳስተላለፉት በተዘገበው የስልክ ጥሪ፣ በዚያው ዕለት ቀንና ምሽት ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠንክረው ሲከራከሩ በዋሉ አባቶች ላይ በተለያዩ መንገዶች ርብርብ ተደረገ፡፡

በስብሰባው መጀመሪያው ላይ ጠንክረው የተሰሙ የዕርቀ ሰላሙ ይቅደም ድምፆች በቀጣዩ ቀን ስብሰባ ላይ ጸጥ ረጭ አሉ፤ ‹‹በስብሰባችን በአካል የተገኘ ባለሥልጣን አልነበረም፤ ቀደም ሲናገሩ የነበሩ አባቶች በሁለተኛው ቀን አስቀድመው ዝም ሲሉ ግን መንግሥት በአንዳች መንገድ ሰተት ብሎ እንደገባበት ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፡፡ በዚህ ኹኔታ ታኅሣሥ 10 ቀን አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም የተጀመረው የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ዝግጅት እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ባወጣው የምርጫ መርሐ ግብር መሠረት÷ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ይካሄዳል፤ በዓለ ሢመቱም የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡ ከምርጫው ቀን ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚያሳልፈው ውሳኔ ለዕጩ ፓትርያሪክነት ይኹንታ ያገኙ አምስት ዕጩ ፓትርያሪኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝቡ በይፋ ይገለጻሉ፡፡

ሐራዊ ምንጮች ከተለያዩ ማእዘናት ያሰባሰቧቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በዕጩ ፓትርያሪክነት እንደሚቀርቡ ከተገመቱት አባቶች ብዙዎቹ በአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ የተሾሙ ሲኾኑ ሦስቱ ደግሞ በሦስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ በተለያየ ጊዜ የተሾሙ ናቸው፡፡ በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንቡ ስለ ፓትርያሪክነት መመዘኛ በይፋ ከምናውቀው ባሻገር፣ ስለ ዕጩ ፓትርያሪኮች ልየታና ስለ ፓትርያሪክ ምርጫው የተለያዩ ነገር ግን በእምነት የሚነገሩ አስተያየቶች (theories) ተሰምተዋል፡፡

በዕጩነት የሚካተቱ ተወዳዳሪዎች ሁሉ በተቀራራቢ የትምህርት ዝግጅት፣ ችሎታና ልምድ ላይ እንዲገኙ አይፈለግም የሚለው አንዱ የመላ ጣዮች አስተያየት፣ ምርጫው ‹‹አንዱ ሥዩም ፓትርያሪክ ለውድድር በማያዳግቱ የተቆጠሩ ዕጩዎቹ የሚታጀብበት ነው፤›› ይላሉ፡፡ የዕጩዎች ልየታውና ምርጫው የተሻሉትንና ተቀራራቢ ብቃት ያላቸውን በመያዝ በአንጻራዊ ነጻነት ውስጥ እንደሚካሄድ የሚያምነው ሌላው የመላ ጣዮች አስተያየት ደግሞ፣ ‹‹የተመረጠው ቢመረጥ ዋናው ነገር አቋሙ የሚያሰጋ አለመኖሩ ነው፤›› ይላል፡፡ ሁለቱንም አስተያየቶች አንድ የሚያደርጋቸው ግን ከውጫዊ ኹኔታ አኳያ የመንግሥት ፍላጎት፣ በውስጣዊ ኹኔታዎች ረገድ ደግሞ አካባቢያዊነትና ጥቅምን ማስጠበቅ በምርጫው ሂደት ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ወሳኝ ማድረጋቸው ነው፡፡

በተቃራኒው፣ በታሳቢ ዕጩዎች የትምህርት ዝግጅት፣ የአገልግሎት ልምድና ብቃት ላይ በመመሥረት÷ ‹‹ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ታማኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚኾነውን አባት ለመምረጥ አጋጣሚውን መጠቀም አለብን፤›› የሚሉ ቀናዒና የወሃት ኦርቶዶክሳውያን የሉም ለማለት አይቻልም፡፡ የኾነው ኾኖ የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ የካቲት 14 ቀን ለቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ለማቅረብ በሚለያቸው ዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ እነማን ካትቱ ይችላሉ? በጥቆማው ሳምንትና ከዚያም በፊት በየፊናው ሲደረጉ በቆዩና አሁንም በቀጠሉት የድጋፍ እንቅስቃሴዎች፣ መልክ አውጥተው ከሚታዩት ቡድናዊ ሽኩቻዎችም አንጻር ዕጩዎቹ ከሚከተሉት አባቶች መካከል ሊኾኑ እንደሚችሉ በስፋት ተገምቷል፡፡

  1. ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም፡- በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በመጀመሪያው ዙር ከተሾሙት ቀደምት አባቶች አንዱ ናቸው፡፡ የፊት ስማቸው አባ ተክለ ማርያም ዐሥራት ይባል ነበር፡፡ አሁን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ ለአምስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ በተደረገው ዝግጅት ትግራይን ለመወከል ከብፁዕ አቡነ ጳውሎስ (በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ) ጋራ ተጠቁመው ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ለዕጩ ተወዳዳሪነት በመመረጣቸው ከዕጩነት ሳይካተቱ ቀርተዋል፡፡

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ

ዕድሜያቸውና አሜሪካዊ ዜግነታቸው በምርጫ ሕገ ደንቡ ከተዘረዘረው መመዘኛ አንጻር እንደማያስመርጣቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ዘግይተው የወጡ መረጃዎች ግን ብፁዕነታቸው የአሜሪካ ዜግነታቸውን መመለሳቸውን ያመለክታሉ፤ የሚመረጠው ፓትርያሪክ ዕድሜ ጣሪያም ወደ 75 ከፍ ተደርጓል በመባሉ በዕጩነት ከመካተት የሚከለክላቸው አይኾንም ተብሏል፡፡ ብፁዕነታቸው በዕጩነት እንዲካተቱ የአስመራጭ ኮሚቴው አባል ከኾኑት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ግልጽ ድጋፍ ተሰጥቷቸዋል፤ በእርሳቸው በኩል በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩትን መንፈሳዊ ኮሌጅ ሁለት ድምፅ (አንድ የደቀ መዛሙርት አንድ የመምህር ድምፅ) እንዲያገኙ ማግባባት እየተደረገላቸው መኾኑ ተሰምቷል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ከኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጋራም የጠበቀ መቀራረብ እንዳላቸው ይነገራል፤ እንዲያውም በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ሀ/ስብከት ሰፊ ቅስቀሳ እየተደረገላቸው ስለመኾኑ ተዘግቧል፡፡ ከሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ከዕድሜያቸውና ተክለ ሰውነታቸው በሚታይባቸው የአባትነት ጸጋና ሞገስ የተነሣ የአንዳንድ ብፁዓን አበው ምርጫ መኾናቸው ነው የተመለከተው፡፡

ከጠ/ቤ/ክህነቱ የውስጥ ‹ፖሊቲካ› ርቀው መቆየታቸውም አዲስ ፊት እስኪለመድ ወርቅ ነውና አንዳንድ የመምሪያና የድርጅት ሓላፊዎችን ድምፅ እንደሚያስገኝላቸው ይታሰባል፡፡ ለብፁዕነታቸው የሚደረገውን የድጋፍ ቅስቀሳ የሚያስተባብሩት÷ ቀድሞ እርሳቸውን በመቃወም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መመረጥ ድጋፍ በሰጡት መጋቤ ካህናቱ ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ እነንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ እጅጋየሁ በየነ (የትኛውን ቤት እንደኾነ ባይታወቅም ለቅስቀሳው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ቤቴን እሸጣለኹ ብላለች)፣ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፣ መ/ር ዕንቊባሕርይ ተከሥተ የታወቁት ሙሰኞች ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ፣ የአሲራ መቲራው መምህር አባ ገብረ መድኅን ኀይለ ጊዮርጊስ የመሳሰሉት መኾናቸው ተገልጧል፡፡

የቡድኖቹ የድጋፍ ቅስቀሳ ስልት በምርጫው ድምፃቸውን የሚሰጡትን ካህናት፣ የታላላቅ አድባራትና ገዳማት አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች በመለየት፣ መንግሥት በጉዳዩ እንደገባበት፣ ለፓትርያሪክነት የሚፈልገውም ብፁዕ አቡነ ማቲያስን እንደኾነ በመጥቀስ ሽብርና ስጋት በመፍጠር ነው ተብሏል፡፡ ከዚህም ጋራ ከበላይ አካል ተሰጥቷል በተባለ መመሪያ የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ለመራጭነት የተመዘገቡ ካህናትን በመሰብሰብ ድምፃቸውን ለአቡነ ማቲያስ እንዲሰጡ ማሳሰባቸው ተገልጧል፡፡ ትኩረቱ ከሰንበት ት/ቤቶች እና ከምእመናን መራጭ ተወካዮች ይልቅ በካህናት ላይ ያረፈበት ምክንያት ለክህነታዊ አገልግሎታቸው ራሳቸውንና ቤተ ሰባቸውን ከሚመሩበት የኑሮ ዋስትና ጋራ የተገናኘ መኾኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

ብፁዕነታቸው የሚነቀፍባቸው ነገር በአመራርና ለአስተዳደራዊ ችግሮች ፈጣን መፍትሔ በመስጠት ረገድ ይታይባቸዋል የሚባለው ዳተኝነት ነው፡፡ በምርጫው እንደሚሳተፉ የሚጠበቁት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አራት ተወካዮች፣ ድምፃቸውን ለብፁዕነታቸው ሊሰጡ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ ይህም ሊቀ ጳጳሱ ለመንፈሳዊው አገልግሎት ብቻ በማድላታቸውና ተቋማዊ አስተዳደሩን ችላ በማለታቸው÷ አንድም ፕትርክናው ለሚሻው ሚና ይመቻሉ፤ አንድም በምትካቸው የገዳማቱንና የሀ/ስብከቱን አስተዳደር አጠንክሮ የሚመራ አባት እናገኛለን በሚል ነው፡፡

ፕትርክናው የሚሻው ሚና በራሱ ወደፊት በሚሻሻለውና የፓትርያሪኩን ሥልጣንና ተግባራት ወስኖ በሚነግረን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ልናየው ካልኾነ በቀር አሁን ባለው ኹኔታ ‹‹በጸሎትና ቡራኬ የተወሰነ፣ ከአስተዳደር የማይገባ አባት ነው የሚያስፈልገን›› የሚለው ለአረጋውያኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሳይቀር የሚዋጥላቸው አይመስልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከደርዘን የማያንሱት በአስተዳደር ረገድ ድኩም ከኾኑት ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ይልቅ ተመራጩ ፓትርያሪክ ‹‹የልማት አባት››ም መኾን አለበት የሚሉት፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘኢየሩሳሌም ለቀድሞው ሥርዐተ መንግሥት በነበራቸው ተቃውሞ፣ ተጠርተውም ወደ አገር ባለመመለሳቸው ከሦስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ በተፈጠረ አለመግባባት በስማቸው ሌላ አባት (የካናዳው ብፁዕ አቡነ ማቲያስ) በመሠየም ጠንካራ ውሳኔ ተላልፎባቸው ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው በአሁኑ መንግሥት ዘንድ እንዳላቸው ተደጋግሞ የተነገረው ቅቡልነትም በአንዳንድ ወገኖች ጥያቄ የሚነሣበት ቢኾንም በዕጩነት ከመካተት፣ በፓትርያሪክነትም ከመሾም እንደማይከለክላቸው አረጋግጠው የሚናገሩ አሉ፡፡ የካናዳ፣ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ (ዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ) አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሲኾን ከጥቅምቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኋላ በዚያው በኢየሩሳሌም የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ረቡዕ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ታውቋል፡ 

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል

2. ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፡- በአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም ከተሾሙት 17 ኤጲስ ቆጶሳት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የቀድሞ ስማቸው መምህር ተከሥተ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ይባል ነበር፡፡ እንደተሾሙ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ሠርተዋል፤ በዕሥራ ምእቱ መባቻና በ2001 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሙስናንና ዐምናገነናዊ አስተዳደርን ለመታገል የተደረገው ጥረት የቀድሞው ፓትርያሪክ ባስወሰዱት የኀይል ርምጃ ሲከሽፍ ብፁዕነታቸው የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን በሊቀ ጳጳስነት እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡

ብዙዎች በወቅቱ ሙስናንና ዐምባገነናዊ አስተዳደርን ለማረም የተካሄደውን ጥረት በጥሩ መንፈስ በመቀበል ለብፁዕነታቸው ከፍ ያለ አስተያየት እንደነበራቸው ይታወሳል፤ እኩሌታዎችም ውዝግቡ ብፁዕነታቸውን በተተኪ ፓትርያሪክነት ለማስተዋወቅና አጉልቶ  ለማሳየት በመንግሥት የተሠራ ድራማ አልያም የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሳይኾን የሥልጣን ጥምና የግል ጥቅም የፈጠረው ሽኩቻ ነበር ሲሉ ይተቹታል፡፡

ብፁዕነታቸው በአስተሳሰባቸው ይኹን በአስተዳደራቸው ዘመናዊና ባለራእይ፣ ከሙስናና ጎጠኝነት የራቁ፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የሚያምኑ ናቸው፤ ከቍልፍ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ያላቸው መቀራረብም ይረዳል በማለት ከማመስገን አልፈው በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ የሚያደርጓቸው እንዳሉ ሁሉ፤ የዕድሜያቸውን ረፋድነት፣ ለዕርቀ ሰላሙ መክሸፍ አራምደውታል የሚባለውን አፍራሽ አቋም፣ የጠባዮቻቸውን ተገማች ያለመኾን (ችኵልነት ይሉታል)፣ በአክራሪነት ዙሪያ የጻፏቸውን መጻሕፍት በማየት ለቁልፍ የውስጥ ተግባራት እንጂ ለመንበረ ፕትርክናው የዐደባባይ ተግባራት የማያጯቸው አሉ፡፡

በበዓለ ሢመታቸው ቀን የወጣው ኅትመት እንደሚያትተው፣ በትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ አውራጃ በ1955 ዓ.ም (አሁን ፶ ዓመታቸው ነው) የተወለዱት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በደብረ ዓባይ የቅዳሴ ትምህርት ከመምህር ዬኔታ ኄኖክና ከመምህር ገብረ ሊባኖስ በመማር ዜማውን ከነምልክቱ ጠንቅቀው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ በገዳመ ዋልድባ ማዕርገ ምንኵስና ተቀብለዋል፡፡ ማዕርገ ዲቁና የተቀበሉት ከብፁዕ አቡነ ናትናኤል ሲኾን ማዕርገ ቅስና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ተቀብለዋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በአውራጃ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናትነት፣ በሀገረ ስብከት በዋና ጸሐፊነት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በስብከተ ወንጌል መምሪያ ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በአሜሪካ ጆርጂያቴክ አደልት ኤጁኬሽን ሴንተር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል፡፡ በዚያው በምትገኘው በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ የጀመሩትን ዘመናዊ ትምህርት በጥሩ ውጤት አጠናቀው የጂኢዲ ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ በዚያው በአሜሪካ በቡልሃ ሐየስት ኮሌጅ ገብተው ቴዎሎጂ በመማር ባችለር ዲግሪ፣ በዲካብ ኮሌጅ የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግና አድሚንስትሬሽን በመማር በዲፕሎማ ተመርቀዋል፤ በተጨማሪም የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በፍልስፍና ዘርፍ ለሁለት ዓመታት ከተከታተሉ በኋላ ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል በ1994 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ኾነው አያሌ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡

ካህናትና ምእመናን ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ጥቆማ እንዲሰጡ በተጠየቀበት ሳምንት፣ ቡድናዊ መልክ ይዟል የተባለው መጠነ ሰፊ የማግባባት ዘመቻ የአስመራጭ ኮሚቴውን አባላት አስጨንቋል ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ አለብን በሚልም ብፁዕነታቸው የመመዘኛ መስፈርቱን ቢያሟሉም ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ውስጥ ላለማስገባት የዛቱ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት መኖራቸው ተጠቁሟል፤

አንዳንድ ብፁዓን አባቶችንም አስቆጥቷል፤ ጉዳዩም በቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ ላይ ሊያነጋግር እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ይህም ኾኖ ብፁዕነታቸው በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ ከሚካተቱት አንዱ እንደሚኾኑ ነው የሚጠበቀው፡፡

3. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም 17 ኤጲስ ቆጶሳት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተሾሙበት ወቅት ተሿሚዎችን በመወከል ባሰሙት የንግግር ቃል÷ ‹‹እኛ በዛሬው ዕለት በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠን የተሾምን ኤጲስ ቆጶሳት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታመንን ትሑት አገልጋይ በመኾን እንዲያጸናን እግዚአብሔርን እንማፀናለን፤›› ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ሊቀ ካህናት አባ ኀይለ ሥላሴ ይግዛው÷ በኋላ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ÷ ለዓመታት በሥራ አስኪያጅነት ባገለገሉበት የሲዳሞ ሀ/ስብከት ስለ ኤጲስ ቆጶስ ሹመታቸው በደብረ ኀይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በተዘጋጀላቸው መርሐ ግብር ላይም የሚከተለውን ተናግረው ነበር፡- ‹‹ሰው ሲደሰት ያለቅሳል፤ ይሥቃል፤ አንዳንዴም ያስነጥሳል፤ እኔ ዛሬ ኤጲስ ቆጶስ ኾኜ በመሾሜ አላለቀስኁም፤ አልተደሰትኁም፤ ወደ ከፍተኛ ተጋድሎ ነው የመጣኹት፤ ይህ ሹመት ቤተ ክርስቲያን ጠርታ የሰጠችኝ ነው፡፡ በዚህ ሹመት የማመሰግነው ማንም የለም፤ ከዚህ በኋላ አባ ጳውሎስን ለማስደሰት የማደርገው ነገር የለም፤ ትላንትም ቤተ ክርስቲያኔን ብዬ ነው ስሠራ የነበረው፤ ዛሬም ቤተ ክርስቲያኔን ብዬ ነው የማገለግለው፡፡››

ታይታንና መታጀርን የሚጠሉት አባ ኀይለ ሥላሴ ይግዛው ለብዙ ጊዜ ምንኵናቸውን ሳይገልጡ ቆይተዋል፡፡ በማእከል በሚካሄዱ ስብሰባዎች በተቀመመ ንግግራቸው የቀድሞውን ፓትርያሪክ ጭምር በመሞገት ይታወቃሉ፡፡ የማዕርገ ጵጵስናው ሹመት በተደጋጋሚ እንዳለፋቸውና ለሹመትም የበቁት በቅ/ሲኖዶሱ ጫና እንደኾነ ይነገራል፡፡ በተሾሙበት ቀን የሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ጳጳስ ኾነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በኋላ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱን ለማጠናከር ከተመረጡት ስምንት ብፁዓን አባቶች አንዱ ናቸው፡፡ ዕርቀ ሰላሙ እንዲሳካና የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንዲረጋገጥ ያስተጋቡትን አቋም አጽንተው የሚገኙ አባት ናቸው፡፡

በበዓለ ሢመታቸው ቀን የወጣው ኅትመት እንደሚያትተው÷ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የተወለዱት በ1942 ዓ.ም (አሁን ዕድሜያቸው 63 ዓመት ነው) በትግራይ ማእከላዊ ዞን ነው፡፡ የፊደልና የግብረ ዲቁና ትምህርት በተወለዱበት አካባቢ ከአጠናቀቄ በኋላ በዋግ ሕምራ ሀ/ስብከት በአመላ ቅድስት ማርያም ከዬኔታ መኰንን ዜማ፣ በአዞላ ቅዱስ ሚካኤል ከዬኔታ ሐዋዝ አቋቋም፣ ከዬኔታ ዓምደ ሥላሴ ቅኔ፤ ከዬኔታ ዕፁብ በበለሳ፣ ከመምህር ሐረገ ወይን በጎንደር የአቋቋም ትምህርት፣ በዓምደ ወርቅ ከዬኔታ ታምራት ዝማሬ መዋስዕት ተምረዋል፡፡

በአዲስ አበባ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመሪጌትነት እያገለገሉ ዘመናዊ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው ለአራት ዓመት በተከታተሉት መንፈሳዊ ትምህርት ዲፕሎማ አግኝተዋል፤ የ12ኛ ክፍል ዘመናዊ ትምህርትም አጠናቀዋል፡፡ ከ1965 ዓ.ም በሲዳሞ ሀ/ስብከት በሐዋሳ ከተማ ከ1-6 ክፍል በተከፈተው የቤተ ክህነት ት/ቤት በመምህርነት፣ በርእሰ መምህርነት፣ በመሠረተ ትምህርት ሊቀ መንበርነት፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በአደራጅነት፤ በሲዳሞ፣ በባሌና በጋሞጎፋ በአንድነት ላደራጇቸው የሰንበት ት/ቤቶች በሥራ አስፈጻሚ ሊቀ መንበር በመኾን እንዲሁም በስብከተ ወንጌል፣ በሰበካ ጉባኤ አደራጅነትና አስፈጻሚነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአዋሳ መምህራን ማሠልጠኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡

በሶቭየት ኅብረት ተልከው ትምህርታቸውን በመከታተል በቴዎሎጂ የማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ከዚያም በሲዳሞ ሀ/ስብከት ለሲዳሞ፣ ለባሌና ለጋሞጎፋ በተቋቋሙት የካህናት ማሠልጠኛ ሥራ አስኪያጅ፣ በኋላም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመኾን ለ17 ዓመታት ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እና በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የምንኵስናን ሥርዐት የፈጸሙ ሲኾን ከብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ ደግሞ የቅስና ማዕርገና ቁምስና ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በካበተ የሥራ ዕውቀታቸውና ልምዳቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂና ጠበቃ ለመኾን በተጨባጭ ባስመሰከሩት አቋማቸውና መንፈሳዊነታቸው ስለዚህም በተቀበሉት ፈተና በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ

4.ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፡- በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በአስተዋይነታቸው፣ ውጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ ለማግባባት ባላቸው ተሰጥኦ፣ በተረጋጋ አመራራቸውና መንፈሳዊነት በተመላበት ሰብእናቸው ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ እኒህ ችሎታዎቻቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በነበሩበት 2001 ዓ.ም በተግባር መታየቱን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ ከአስመራጭ ኮሚቴው መካከል እንደ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ካሉት አባቶች ድጋፍ እንዳላቸው ቢነገርም በመንግሥት ዘንድ ስላላቸው ቅቡልነት በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ብፁዕነታቸው በአሁን ወቅት የወላይታ ዳውሮ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

የዋግ ሕምራ ሀ/ስብከት ጳጳስ ኾነው በተመደቡበት ነሐሴ 22 ቀን 1997 ዓ.ም – የበዓለ ሢመታቸው ቀን – በወጣው ዝርዝር ታሪካቸው፣ በፊት ስማቸው አባ አፈ ወርቅ ጌታነህ በሰሜን ሸዋ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ልዩ ስሙ ምንታምር ቀበሌ በ1955 ዓ.ም (አሁን ዕድሜያቸው ፶ ዓመት) ነው የተወለዱት፡፡ ከአባ ገብረ ጻድቅ መኰንን ከፊደል እስከ ዳዊት በሚጢኮራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በሸንኰራ ወረዳ ባልጭ ቅዱስ ዐማኑኤል ከመምህር መዝገበ ሥላሴ አበበ ከውዳሴ ማርያም ዜማ እስከ ሠለስት አርያም፣ ጾመ ድጓ፣ ቁም ዜማ፤ ከመምህር ስቡሕ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡ በናዝሬት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በ1969 ዓ.ም የዲቁና ማዕርግ፣ ማዕርገ ቅስና ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ተቀብለዋል፡፡

ጉር ዐምባ ቅድስት ማርያም ከመምህር መስፍን ዜማና አቋቋም፣ ናዝሬት መድኃኔዓለም ከአባ ወልደ ሥላሴ መኰንን ዜማውን በመከለስ፣ ኢቲሳ ደብረ ጽላልሽ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ከመምህር መስፍን አቋቋም፣ መናገሻ ዐምባ ማርያም ከመምህር ቀለመ ወርቅ ተሰማ ቅኔ ከነአገባቡ፣ አሰቦት ገዳም ከመምህር ዮሐንስ ቅዳሴ፣ ከመሪጌታ በዜና ከዬኔታ መዘምር ቅኔ፤ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያምና ትምህርተ ኅቡአት፣ ኪዳን አንድምታ ከመምህር ጌዴዎን ተምረዋል፡፡ በደብረ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በ1975 ዓ.ም ሥርዐተ ምንኵስና ከመምህር ገብረ መድኅን ተቀብለዋል፡፡

በዝዋይ ሐመረ ኖኅ የካህናት ማሠልጠኛ ገዳም በብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ የሚሰጠውን ኮርስ ተከታትለዋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት የአራት ዓመቱን መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት በሰበካ ጉባኤ አደራጅነት፣ በሰንበት ት/ቤት ሓላፊነት፣ በአዲስ አበባ በሽሮ ሜዳ መንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሰባኪነት አገልግለዋል፡፡ ወደ ውጭ አገር ለትምህርት በመሄድ በሆላንድ ሆህ ስኵል የቴዎሎጂ ት/ቤት ገብተው ለአራት ዓመት ትምህርታቸውን ተከታትለው በቴዎሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን አግኝተዋል፡፡

በሐረር ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ በአቃቂ መድኃኔዓለም፣ በቃሊቲ ቅዱስ ገብርኤልና በሳሎ ደብረ ፀሐይ ቅ/ጊዮርጊስ፣ በመካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ አብያተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት፤ በአሜሪካ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል፣ በስዊዘርላንድ ጄኔቭ፣ በሎዛን፣ በዙሪክና በበርን ባዝል ከተሞች ለሚገኙ ክርስቲያኖች ትምህርተ ወንጌል በመስጠት፣ በመቀደስና በማቍረብ አገልግለዋል

ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል

5.ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል፡- በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ጥር 14 ቀን 1972 ዓ.ም ከተሾሙት አባቶች አንዱ ናቸው፡፡ በፊት ስማቸው ዶ/ር አባ ኢያሱ ገብሬ ይባል ነበር፡፡ እንደተሾሙ የኤርትራ ሀ/ስብከት ጳጳስ ኾነው ሠርተዋል፡፡ የሹመት ቅድምና፣ የትምህርት ዝግጅት፣ ሰፊ የአገልግሎት ልምድ፣ የቋንቋ ክህሎትና ርቱዕ አንደበት በዕጩ ፓትርያሪክነት ሊያስመርጣቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያናችንን በመወከል ሠርተዋል፡፡ በአቋም ረገድ ብዙዎች ብፁዕነታቸውን በወላዋይነት ያሟቸዋል፤ እርሳቸው ግን የውይይትና ተዋስኦ ሰው መኾናቸውን ይናገራሉ፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ሁሉ በዕጩነት የሚታሰቡት ሌላው አባት የካናዳው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ናቸው፡፡ በተሾሙበት ቀን የተመደቡበት ሀ/ስብከት ወሎ ሲኾን የከፋ ሊቀ ጳጳስም ነበሩ፡፡ በዚህ ቡድን ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ከጤና እና ዕርግና (ዕድሜያቸው 82 ደርሷል) አንጻር በዕጩነት ይካተታሉ ተብሎ ባይገመትም በአስመራጭ ኮሚቴው ውስጥ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሚኖራቸው ሚናም በቀላሉ አይታይም፡፡

የምሥራቅ ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ፣ የዓዲግራት ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅ/ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅና የሰበካ ጉባኤ ማ/መምሪያ የበላይ ሓላፊ የሶማሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ (በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ዞን በደገም ወረዳ ልዩ ስሙ ሌመን ሥላሴ ቀሬ ኮራ ገበሬ ማኅበር ከአቶ ሆዶታ ዋቅጅራና ከወ/ሮ አሰለፈች ታዬ በ1957 ዓ.ም የተወለዱት ብፁዕነታቸው አሁን 48 ዓመታቸው ከመኾኑ አንጻር በዕጩነት መካተታቸው አጠራጣሪ ነው፤ ነገር ግን ሊቅነታቸው፣ በርጉዕና የማይታወክ ሰብእናቸው እንዲሁም በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪነታቸው ተተኩሮባቸዋል)፣ የባሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ (መንፈሳዊነት፣ አቋምና ኦሮምኛ ቋንቋ) እንዲሁም ሌሎች ታሳቢዎች ናቸው፡፡

ከእኒህም ውጭ ፈጽሞ ያልታሰቡ ዕጩዎች ሊታዩ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ነው፡፡ ዋናው ነገር በጥብቅ ምስጢራዊነት በመከናወን ላይ የሚገኘው ዕጩዎችን በመለየቱ ሂደት ስለ ዕጩዎች የተያዙት መረጃዎች ከአድልዎና ወገንተኝነት በራቀ መልኩ በአግባቡ መጣራት፣ መረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ በምርጫ ሕጉ የመራጮች ቃለ መሐላ ላይ እንደተመለከተው ዕጩዎችን የመለየቱ ተግባር÷ በዝምድናና በጓደኝነት ትስስር ለጎጤ፣ ለእህል ውኃዬ፣ ለወንበሬ ተብሎ ወይም የመንግሥትን ጨምሮ የማንኛውም ውጫዊ አካል ድጋፍ አለው ለሚባል አባት በሚሰጥ ድሉል ድምፅ ሳይኾን፣ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እረኛና ጠበቃ ለመኾን ካህኑና ምእመኑ በጣለባቸው አመኔታና ባላቸው ብቃት የሚመረጡ አባቶችን እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡

 

ምንጭ፡ ሐራ ተዋሕዶ

Go toTop