“የኢቲቪ ጀሃዳዊ ሀረካት የፈጠራ ድራማ የመብት ትግላችንን አይገታም” ሲሉ በሚኒሶታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ባወጡት ባለ5 ነጥብ የአቋም መግለጫ ላይ አስታወቁ።
ሙሉ መግለጫው የሚከተለው ነው። ( መግለጫውን በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ)
በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጀሀዳዊ ሀረካት በሚል ስያሜ ተራ የፈጠራ ተራኪ ፊልም ለህዝብ መተላለፉ ይታወቃል። በማናቸውም መመዘኛ ቅንጣት እውነታን ያላዘለ አግባብነት የሌለው ውንጀላ የሞላበት ለመሆኑ ለመረዳት አያዳግትም፤ የፊልሙ አዘጋጆች ምን ያህል የወረደ የሞራል ዝቅጠት ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ የሚያመላክት ነው።
በዚህ ዓይነት የፈጠራ ተውኔት የሙስሊሙ የመብታችን ይከበር ጥያቄ ለማዳፈን ከንቱነት ነው። ሙስሊሙ ሕብረተሰባችን ትግሉን በስፉት ከጀመረበት ከ፩ አመት በላይ ፍጹም ሰላማዊ ጥያቄውን እያቀረበ ያለበት ስልት የሰለጠነና ሕግና ስርአትን የተከተለ ለመሆኑ የማያሻማ እውነታ ነው። በተገላቢጦሽ የመንግስትን ስልጣን የያዘው አካል ግን ሙስሊሙን ማሸበር፣ ማሰርና መግደል የእለት ተግባር አድርጎታል። በእስር ላይ በሚገኙ በመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትም ላይ እየደረሰ ያለው የአካል ጉዳትና የአእምሮ ሰቆቃ እጅግ ከፍተኛ ነው።
ይባስ ተብሎም ቅጥ ያጣው የመንግስት ድርጊት የሚያሳየን በፍርድ ቤት ለህዝብ እንዳይታይ እገዳ የተጣለበትን የኢቲቪ የፈጠራ ፊልም በግለሰብ ቀጭን ትእዛዝ ተሽሮ መቅረቡ ታውቋል። ይሕም ገዢው መንግስት ራሱን ከሕግ በላይ ማድረጉ እና ራሱ ህግን እንደፈለገው የሚያዘው መሆኑን ነው።
ሪሳላ ኢንተርናሽናል ከዚህ በታች የሚገለጸው አቋም ላይ መድረሱን ለሁሉም አበክርን እንገልፃለን።
፩ኛ. በእስርና በእንግልት ስር የሚገኙት የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጎን ሁሌም በጽናት የምንቆም ሲሆን ያለንን አንድነት እንገልፃለን።
፪ኛ. በኢቲቪ ቴሌቭዥን የቀረበው ጅሐዳዊ ሀረካት የሀሰት ቅንብር ፊልም ህብረተሰቡን ለማደናገር ታስቦ የቀረበ በመሆኑ ይህንኑ እናወግዛለን። ከህዝብ በተሰበሰበ የታክስ ገንዘብ ለዚህ መሰሉ አሳፋሪ ተግባር በመዋሉ አሣዝኖናል።
፫ኛ. በግፍ በእስርና በእንግልት የሚገኙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና በየእስር ቤቱ የተሰሩ ሙስሊሞች በሙሉ ያላ ምንምቅድመ ሁኔታ በነፃ እንዲላቀቁ እንጠይቀለን።
፬ኛ. በሃገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሙስሊም ተማሪዎችን አፍኖ ማሰር ከትምህርት ገበታቸው ያለአግባብ ማገድና ማሸማቀቅ በአስቸኳይ እንዲገታ እንጠይቃለን።
፭ኛ. በሙስሊሙ ህብረተሰባችን የቀረበው ግልፅና መሰረታዊ የመብት ጥያቄ አሁንም ምላሽ የሚሹ በመሆኑ ለዚሁ ሰላማዊ ትግል ሙሉ ድጋፋችን እንገልፃለን ።
ኢስላም የሰላም ሃይማኖት ነዉ!!
እምነትን በነፃነት መተግበር ሰባዊ መብት ነዉ!
አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! አላሁ አክበር!