በኢትዮጵያ ትከሻ ላይ የተቆለፈውን ቀምበር ለማላቀቅ ቍልፉ የትጥቅ ትግል መሆኑ በተነሣ ቍጥር ከአንዳንድ ሰዎች የሚሰጠው አስተያየት ግራ የሚያገባ ነው። ገዢዎቹና ደጋፊዎቻቸው ቢቃወሙ ይገባኛል። የሚሰጡት አስተያየት ግን ሕፃንን ሳይቀር የሚያሥቅ ነው። “ጦርነት በቃን” ይላሉ። “አትንኩን” ማለታቸውን የማናውቅ ይመስላቸዋል። ጦርነት ካላስፈለገ፥ ለምን ከንጉሣዊው አስተዳደር ጋር ተዋጉ? ለምን ከደርግ ጋር ተዋጉ? ጨቋኝ ገዢ የት አገር ነው በሌላ መንገድ ሥልጣን ለሕዝብ ሲለቅ የታየው? የምሥራቁ ዓለም ጨቋኞች የወደቁት በሕዝብ ዐመፅ ነው ማለት፥ የምዕራቡን ዓለም ከባድ እጅ ሚና መርሳት ይሆናል።
የኛዎቹ ጦርነት ከመረራቸው፥ ሕዝብን ወደጦርነት የሚመራ በደል አይሥሩበት። ምን ጊዜም ቢሆን የትጥቅ ትግል የመጨረሻው አማራጭ ነው። የትጥቅ ትግል የሚያደርሰው ጉዳት በአንዱ ወገን ላይ ብቻ አይደለም። መሣሪያ የሚያነሣ መሣሪያ ማንሣት የሚያመጣበትን ጉዳት ሳያውቅ አይነሣም። ሰው ሆኖ እንደከብት መገዛት ያልቻለ ሰው በቃኝ ሲል፥ ክብሩን በመጠበቁ ከተቀመጡበት ተነሥቶ “ነወር” የሚባል እንጂ፥ በባርነት ጥላ ሥር ተቀምጦ የሚተች አይደለም። “ጦርነት መርሮናል” የሚለውን ምክር መገዛት ለመረረው አይመክሩም።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ግራ አጋቢ አስተያየት “ጦርነትስ አስፈላጊ ነው፥ ግን . . .” የሚለው ነው። ይህ አስተያየት በቅን አሳብ፥ የተሰጠ ሊሆን ይችላል። ግን አዛኝ መስሎ፥ ቀምበረኛውን ለመደገፍ የተሰጠ አስተያየት አለመሆኑ በምን ይታወቃል? እውነተኛ አሳቢና ሠጊ ሰው አስተያየቱን የሚሰጠው ሲጠየቅ፥ ካልተጠየቀም በግሉ ትጥቅ ያነሡትን ፈልጎ በጨዋ ደምብ መንገር ነው። ሳይጠየቁ ተነሥቶ በይፋ ምክር መስጠት ግን ሰሚው ሕዝብ ትግሉን እንዳይደግፍ መገፋፋት ነው። የትጥቅ ትግል ከታመነበት እንዲፋፋም የማይፈለግበት ምክንያት ምንድን ነው?
ትጥቅ ትግል የራስን ሕይወት ለወገን ነፃነት መሠዋት ማድረግ ነው። ሌላ ዓለማ የሌለው ሰው መሣሪያ ሲያነሣ፥ እንዴት ይኸንን የሚሰነዘርበትንና የሚሰነዘርለትን ምክር ሳያስብበት ራሱን ለመሥዋዕትነት ያቀርባል? የሚካኼደው የትጥቅ ትግል የሚያዋጣ የመሰለው እርዳታውን ያቅርብ፤ የማያዋጣ የመሰለው ለምንድን ነው የሚቃወመው? ተቃውሞው ማንን ለመጥቀም ነው? ለታጋዮቹ አስቦ ከሆነ፥ ከባለቤት ያወቀ ቡዳ ነው። “የኔን ያህል የማሰብ ችሎታ የላችሁም” ማለት ነው። እንዴት ነው ለታጋዮቹ ያልተገለጠ ሥጋት ለምክር ሰጪዎቹ የተገለጠው?
አንዳንዱ ደግሞ፥ “ይኸው እንታገላለን ሲሉ ዓመታት አሳለፉ፥ ግን አንዳች ውጤት አላሳዩም” ይላል፤ ውጤት እንዲያሳዩ የቀጠራቸውና ካልሆነላቸው የሚያሰናብታቸው ሹም ይመስል። አርፎ መቀመጥ ስንት ውጤት አሳየ? ሌሎችን ሙከራዎችም “አንዳች ውጤት አላሳዩም” ብለን እንንቀፋቸዋ!ውይስ ውጤት አሳይተዋል?
“በመካሄድ ላይ ያለው የትጥቅ ትግል ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው” ከተባለ፥ እርግጥ ሊታሰብበት ይገባል። ግን አሳሳቢው ምክንያት ሊቀበሉት በሚገባ መልኩ አልተሰጠንም። ይህ ትግል የሚያመጣው ጉዳት ከተሸከምነው ቀምበር ይበልጥ ሊከብድ እንደሚችል አሳዩን።
የወያኔ ቀምበር መሰበር አለበት የምንል ሁሉ በመሰለንና በተቻለን መንገድ እንታገል። ካልተቻለን፥ ካልመሰለን፥ አርፈን እንቀመጥ፤ ታጋዮችን አለማደናቀፍ፥ እንደ ትግል እንዲቈጠርልን።
– See more at: http://www.satenaw.com/amharic/archives/10537#sthash.Kvap5EbS.dpuf