September 30, 2015
4 mins read

ይድነቃቸው ነፍስ ይማር !

[ቴዲ ድንቅ – አትላንታ]

ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ የተወለዱት መስከረም አንድ ቀን ነበረ። በዚህ ወር መጀመሪያም ልደታቸው ታስቧል። አቶ ይድነቃቸውን የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ ፣ ስለ ሥራቸው ጥቀስ ቢባል፣ ጋዜጠኞችም አውሩ ቢባሉ፣ ዘፋኙም ዝፈን ቢባል፣ በርግጠኝነት፣ የአፍሪካን ስፖርት ከአልኮል የጸዳ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት መጠቀሱ አይቀርም። ከኢትዮጵያም አልፈው በአፍሪካ ደረጃ፣ በኳስ ሜዳዎች ውስጥ የአልኮልና ሲጋራ ማስታወቂያዎች እንዳይኖሩ ጥረዋል።

በዚህ ነገር ሁሉም ያደንቃቸዋል – ዛሬም ድረስ። የሚገርመው ግን ይድነቃቸው ይደነቁበት እንጂ፣ ዛሬ ነገር ሲገለበጥ ማንም ምንም አላለም። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፣ ከእንግዲህ በኋላ” ካስትል [ቢራ] ፕሪሚየር ሊግ” መባሉ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ምክንያቱም ፣ የቢራ ፋብሪካው የፌዴሬሽኑ ትልቅ ስፖንሰር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ድርጅቶች የተለያዩ ዝግጅቶችን፣ ግለሰብን፣ የግለሰብን ሥራ ስፖንስር ሊያደርጉ ይችላሉ። ቢራ ፋብሪካም ይሁን ወተት ፋብሪካ ፣ ያለ ገንዝብ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ዝግጅቶችን፣ ግለሰቦችን ስፖንሰር ቢያደርጉ፣ ያንን ተጠቅመውም ራሳቸውን ቢያስተዋውቁ በግሌ አልከራከርም።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ የኢትዮጵያ፣ ለዚያውም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለ ተቋምን “ስፖንሰር” አደረጉ ተብሎ ስሙን እስከማስቀየር መድረስ፣ ለዚያም አንድ ወቅት ይድነቃቸው ተሰማ ሲመሩት ለነበረውና ብዙ የደከሙበት ፣ እንኳን ስሙን አሳልፈው ሊሰጡ፣ ከሜዳው ሁሉ ሊያርቁት የሞከሩትን ቢራ ስም ይዞ ሲመጣ ያስደነግጣል።

ይህን ያህል ፌዴሬሽኑ ገንዘብ አስፈልጎታል ማለት ነው? አንዳንዴ እኮ ባለው መንቀሳቀስ እንጂ፣ ያልታሰበና ከሰማይ ገንዘብ ዱብ ስላለ ብቻ ወስዶ ፣ ራስን ማስረከብ ተገቢ አይመስልም። ዛሬ ዛሬ የአንድ የአገር ቤት ክለብ ተጫዋቾች እንኳን የወር ደሞዛቸው ከ80ሺ ብር በላይ በደረሰበት ጊዜ፣ ያን ያህል ስምን በቢራ ፋብሪካ እስከማስቀየር ድረስ ለመድረስ ምን መዓት መጣ?

እንደተሰማውም፣ ለዚህ ስም መቀየር ፌዴሬሽኑ በዓመት 6 ሚሊዮን ብር ይከፈለዋል። ግን 6 ሚሊዮኑን ብር ምን እንደሚያደርገው ገና አላወቀም። ቀድመን ዕቅድና ፕላን አውጥተን፣ ይህን ይህን ልንሰራ ነው.፣ ግን ይህን ያህል ብር ያስፈልገናል ብለን ያላሰብንበት ነገር ከሆነ ፣ ገንዘቡ ያን ያህል አንገብጋቢ አይደለም ማለት ነው። ብር ስለተገኘ ብቻ አይወሰድም እኮ!

ነገ ደግሞ “ሲጋራ አጭሱ” የሚል ስም ያለው ፋብሪካ ስፖንስር ላድርግና 10 ሚሊዮን ልክፈል ቢልስ? “ሲጋራ አጭሱ ፕሪሚየር ሊግ” ሊባል ነው? በ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ስፖርቱ የት ድረስ ነው ራሱን የሚጠብቀው?

ከ እንግዲህ በኋላ “ይድነቃቸው ተሳስተዋል” ልንል ነው ማለት ነው? እሳቸውን ነፍስ ይማር ማለት አሁን ነው።

Go toTop