May 19, 2013
131 mins read

በአካል ቅኝ ሳንገዛ፣ ለምን የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች ሆን? – ከተክሌ የሻው

ከተክሌ የሻው

በዘመነ ቅኝ አገዛዝ፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥ ኃይሎች ያልተገዛች፣እንዲያውም የቅኝ ገዥዎችን ቅስም በመስበር ነፃነቷንና ማንነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ መሆኗን የዓለም ታሪክ የሚያውቀው ብቻ ሳይሆን፣የሚደነቅበት ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዘመነ ቅኝ አገዛዝ ቀደም ባሉት ዓመታትም የግዛት ማስፋፋት ዓላማን ተከትለው ኢትዮጵያን በተፅዕኖዋቸው ሥር ለማድረግ የተነሱ ወራሪና ተስፋፊ ኃይሎችን ማለትም ፡-
• ከ1521 እስከ 1535 በቱርኮች ሁለንተናዊ ትብብር ብቻ ሳይሆን፣ በቀጥተኛ የጦር መሣሪያና የሰለጠነ ወታደር ለግራኝ መሐመድ በማቅረብ አገሪቱን በቱርኮች አገዛዝ ሥር ለማዋል የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ጦርነት፣
• በ1571 የቱርኮችን ቀጥተኛ ወረራ ድሆኖ ላይ፣
• በ1824፣ በ1826፣ በ1829፣ በ1830፣ በ1832፣ ግብፆችን በተደጋጋሚ በባሕረ-ነጋሽ እና በትግራይ ሜዳና ሸንተረሮች ላይ፣
• በ1867 እና በ1868 ግብፆችን ጉንዳጉንዲትና ጉራዕ ላይ፣
• በ1877 ድርቡሾችን ኩንፊት ላይ፤ የወራሪዎችና የተስፋፊዎችን አከርካሪ በመስበር አይደፈሬዎቹ አባቶቻችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን አስከብረው ለትውልድ በኩራት ማሸጋገራቸውን እናውቃል፡፡ ዓለምም በዚህ አኩሪ የማንነት ተጋድሎ ኢትዮጵያውያንን ሲያደንቅና ሲያከብር መኖሩ ሐቅ ነው፡፡(ተክሌ የሻው፣2003፡16)
በኋላም በዘመነ ቅኝ አገዛዝ ጀግኖች አባቶቻችን በ1896 ጣሊያንን አምባላጌ፣ መቀሌና ዐድዋ ላይ፣ ከ1928 እስከ 1933 የጣሊያንን ፋሽስት ጦር በኢትዮጵያ ዱር ገደሎች ባካሄደው ተከታታይ የነፃነትና ማንነትን የማስከበር ጦርነት፣ በዚህም በከፈሉት ወድር የለሽ ሁለንተናዊ መስዋዕትነት አገራችን የቅኝ ገዥዎች ፍላጎት ተሸካሚ እንዳትሆንና ማንነቷን አስከብራ እንድትዘልቅ ሆኗል፡፡ ይህ የነፃነትና ማንነትን አስጠብቆ የመዝለቅ ተጋድሎ አገራችን ኢትዮጵያ “የነፃነት ምሽግ” የተሰኘ ውድ ስም እንድታተርፍ አድርጓታል፡፡ ይህን የነፃነት ምሽግነቷን በተመለከተ በ17ኛው ምዕተ ዓመት የኖረው ፖርቹጋላዊው የታሪክ ሊቅ ሉዊስ ኡሬታ ሐበሻ የሚለውን ቃል በአረብኛ፣በቱርክ፣ እና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትርጉሙ የባዕድ ንጉሥ ግዛት የማታውቅ ነፃና ራስ ገዝ ማለት ነው፤ኢትዮጵያ የምትባለውም ልክ እንደምነግራችሁ ናት፤(ሚሊዮን ነቅንቅ 1993፡13) በማለት የነፃነት ምሽግነቷን መስክሮላታል፡፡
ይህን ተከታታነት ጠብቆ የዘለቀን የነፃነት ምሽግነት የናይጀሪያ መሪ የነበሩት ናምዲ አዚክዊ “ኢትዮጵያ በዓለም ገጽ ከጠፉ የጥቁር ግዛቶች የተረፈች ብቸኛ የተስፋ ችቦ ነች፡፡ የአፍሪካውን አባቶችና አያቶች በዚህ አህጉር አቋቁመውት ለነበረው ሥርዓተ-መንግሥት ሀውልት ነች፡፡ ጓደኞቿ አገሮችና ወራሾቻቸው ከፖለቲካ ታሪክ ገጽ ከተሰረዙ በኋላ ፣ኢትዮጵያ በነፃነት መቆየቷ እጅግ የሚያስደንቅ ነው” (ሚሊዮን ነቅንቅ፣ 1993፡14) በማለት የአባቶቻችን የነፃነት ተጋድሎ አኩሪ ብቻ ሳይሆን፣ ለጥቁሮች ማንነት ምሳሌ መሆኗን ገልጠውታል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ጆርጅ ኤድመንድ ሄይንስ የተባሉ ጥቁር አሜሪካዊ የኢትዮጵያን በነፃነት ተጠብቆ መዝለቅ እንዲህ በማለት ገልጸውታየመል፡፡ “ኩሩዋና ነፃዋ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ደም ላላቸው ጥቁሮች የነፃነት፣የራስ መቻል፣ከዘመናዊ ሥልጣኔ መልካም መልካሙን የመቅሰምና የንቃተ-ኅሊና ምልክት ሆናለች፡፡”( ሚሊዮን ነቅንቅ፣1993፡15) ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ ከቅኝ ገዥዎች ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮች የባንዲራዎቻቸውን ቀለሞች አረናጓዴ፣ ብጫና ቀይ ቀለማት ያደረጉት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት( የአፍሪካ ኅብረት) እና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽ/ቤቶች አዲስ አበባ ላይ የተመሠረቱትና ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና ለመባል ያበቃት ነፃተቷን ጠብቃ በማቆየት ለአፍሪካ የነፃነት ተጋዮች ባበረከተችው የቁሳቁስና የሞራል ድጋፍ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ያለፈ መልካምሙና አኩሪው ታሪካችን ነው፡፡
ቅኝ ገዥ ኃይሎች የቅኝ ግዛት ዓላማቸውን ያስፋፉት በቀጥተኛ የኃይል ወረራና ጦርነት ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እንዳውም አብዛኛዎቹን አገሮች በቅኝ ግዛታቸው ቀንበር ሥር ያዋሉዋቸው፣ የየአካባቢውን የጎሣና የነገድ መሪዎችን በመናኛ ጥቅማ-ጥቅሞች በመደለል መሬቶችን በመግዛት የራሳቸው በማድረግ፣ሃይመኖታቸውን በማስቀየርና በአገር አሳሽነት ስም በመግባት የየአገሮቹን ባህል፣ቋንቋና ታሪክ በማጥናት ሥልጣኔን እናስፋፋለን በሚል ሽፋን ማንነታቸውን አስጥለው የሌላቸውንና ከእነርሱም ጋር ሊዋሐድ የማይችል ማንነትን እንዲላበሱ በማድረግ እንደሆነ የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ለዚህ አባባል ታማኒነት የቀድሞው የኬንያ መሪና የኬንያ የነፃነት አባት የሚባሉት ጆሞ ኬንያታ “ማኦ ማኦ” በተሰኘው የነፃነት እንቅስቃሴ ወቅት የተናገሩትን መጥቅሱ ተገቢ ነው፡፡ “እንግሊዞች ወደ አገራችን ሲመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው መጡ፤ እነርሱም ዐይናችን ጨፍነን፣ አንገታችን ደፍተን እንድንጸልይ አስተማሩን፣አንገታችን ደፍተን ዐይናችን ጨፍነን ከጸለይን በኋላ ፣ዐይናችን ገልጠን አንገታችን ስናቀና፣ መጽሐፍ ቅዱሱ የኛ፣መሬቱ የነርሱ ሆኖ አገኘነው፡፡” ሲሉ የተናገሩት ቅኝ ገዥዎች በምን መልክ ሕዝቦችን ቅኝ ተገዥ እንዳደረጓቸው በተጨባጭ ያስረዳል፡፡ አገላለጹ ዕውነኛውን የአፍሪካን የቅኝ አያያዝ ስልት በሚገባ ያሳያል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር የወደቁት ከፍሲል ጆሞ ኬንያታ በገለጡትና የጎሣ መሪዎቹ በሸጡት መሬት ላይ በመቆናጠጥ ይዞታቸውን በልዩ ልዩ መንገዶች በማስፋት ነው፡፡ በእኛም ታሪክ ጣሊያን ኤርትራን ለ50 ዓመታት በቅኝ ግዛት እንዲይዛትና ለተከታታዮቹ የዐድዋና የአምስቱ አመታት የአርበኝነት ትግል የዳረገን ፣ሡልጣን ኢብራሂም የተባለው የአፋር ባላባት አሰብን ለጣሊያን የቅኝ ገዥ አስፋፊ ቡድን በመሸጡና ቅኝ ገዥው ኃይል መላዋ ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ ሥር ሊያውልበት የሚችልበትን መንገድ ያመቻቸ መቆናጠጫ መሬት በማግኘቱ እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡
በሌላም በኩል ኢትዮጵያውያን ከፍ ሲል በተጠቀሱት በቀጥታ ወረራ ቅኝ ተገዥ ሊያደርጓቸው የቃጡትን ኃይሎች ድል ነስተው የመለሷቸውን ያህል፣በሃማኖት፣ በአገር አሳሽነትና በሥልጣኔ አስፋፊነት ስም የፍላጎታቸው ተገዥዎች ሊያደርጓቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የመጡ አስመሳይ ወንጌላውያንን፣ አባቶቻችን “ መጽሐፍ ቅዱሱም ሊቃውንቱም በአገራችን አሉ፤ ከእናንተ የምንሻው የዕደጥበብ ሙያተኞችን ነው፤” በማለት መልሰዋቸዋል፡፡ ይኸም ብቻ አይደለም፡፡ የክርስቶስን መወለድና መጠመቅ ያልሰሙትንና ሊሰሙም ያልፈለጉትን የአሕዛብ አገር ትታችሁ ከዚህ ምን ልትሠሩ መጣችሁ/የሚሉ አፋጣጭ ጥያቄዎችን በማቅረብ ለአስመሳይ ወንጌላውያኑ ከንቱ ስብከት ኅሊናቸውን ቀርቶ ጆሮአቸውን ባለመስጠት ወደመጡበት እንዲመለሱ ማድረጋቸው ግልጽ ነው፡፡ በአገር አሳሽነትና በሥልጣኔ አስፋፊነት ስም የገቡትንም አገሪቱ ካሏት የከበሩ ነገሮች የተመረጡትን በገጸ-በረከትነት በመስጠት፣ የአገራቸውን አፈር ግን ከምንም በላይ የሚወዱትና በማንም ሊወሰድ እንደማይችል ለማሳየት በጫማቸው አፈር ይዘው እንዳይሄዱ እግራቸውን አሳጥበው እንደሸኙዋቸው ታሪካችን ያስረዳናል፡፡ እነዚህንና መሰል አባቶቻችን ለነፃነትና ማንነትን አስጠብቆ ለመዝለቅ ያደረጓቸው ተጋድሎዎች ከአካላዊና ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት ተጠብቀን ፣ማንነታችንና ነፃነታችን አረጋግጠን እንደንቆይ እንዳደረጉን እንረዳለን፡፡ ይህ የታሪካችን እጅግ መልካሙ፣አስደናቂውና አንፀባራቂው ምዕራፍ ነው፡፡ ታሪኩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን የጥቁር ዘር ያኮራና ያስመካ ነው፡፡
ከዚህ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህን የነፃነት ምሳሌነትና የኢትዮጵያዊነት ምንነት መገለጫ የሆኑ ዕሴቶቻቸውን ምን ያህል ጠብቀው ይዘዋቸዋል? የቱንስ ያህል አዳብረዋቸዋል? ጉዞ አቸው ወደ ፊት ነው ወይስ ወደ ኋላ? የሚሉት ናቸው፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ መልሶች ለመስጠት በአምስት ኣመቱ የአርበኝነት የተጋደሎ ዘመን የነበረውን የሕዝቡን አመለካከትና ከድል በኋላ የተፈጠረውን ትውልድ አመለካከት የተቀረጸባቸውን ነባራዊና ኅሊናዊ ሁኔታዎች በቅጡ ማገናዘብ ይጠይቃል፡፡ ለተነሱት ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ለማግኘት ዕውነት እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች ሆነናል? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ አለብን፡፡ አጭሩ መልስ አዎ! ኢትዮጵያውያን የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች ሆነናል የሚል ነው፡፡ ከዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግን በምን በምን ምክንያቶች ለኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት እንድንዳረግ ያደረጉንን መሠረታዊ ምክንያቶች ማባራራቱ ብዥታ የሌለበት ግንዛቤ እንድንጨብጥ ይረዳናል፡፡
1. ከድል በኋላ የመንግሥቱ ቢሮክራሲ በስደተኛውና በባንዳው ቡድን ጥምር ጥምረት መዋቀር፤
ማንም የአርበኝነት ትግሉን ዘመን ታሪክ በአግባቡ የተከታተለ ሰው ሊረዳው እንደሚችል፣ያ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከሦስት የተከፈሉበት ነበር፡፡ አርበኛ፣ስደተኛና ባንዳ፡፡ አርበኞቹ እንደጥንት አባቶቻቸው እምነታቸውን ያልለወጡ፣ማንነታቸወን ያልካዱ፣በዕለታዊ ጥቅማ-ጥቅሞች ባንዲራቸውንና አገራቸውን ያልካዱ፣ ሃይማኖታቸውን ያልለወጡ፣ኢትዮጵያ ወይ ሞቴ ብለው በቁርጠኝነት የቆሙና ነፃነታችንን ተጋድለው ያረጋገጡልን ናቸው፡፡ ከነዚህ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች ደረሱ ዱኬ፣ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር፣ ራስ አሞራው ዉብነህ፣ደዝማች በላይ ዘለቀ፣ደጃዝማች ታደሰ ይማም፣ፊታውራሪ ሽፈራው ጌታሁን፣ደጃዝማች አድማሱ ብሩ፣ደጃዝማች ወንደወሰን ካሣ፣ደጃዝማች አበራ ካሣ፣ ራስ ሙሉጌታ ይገዙ፣ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ብጹዕ አቡነ ሚካኤል እና አያሌ ስማቸው ተዘርዝሮ የማያልቅ፣ግን ስለተጋድሎአቸው ምንም ያልተባለላቸው ዕውነተኛ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡
ስደተኞች የሚባሉት በጠላት ከመገዛት መሰደድን የመረጡና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ወጥተው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ኑረው፣ ከድል በኋላ ቀድመው ካገር የወጡትን ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው የገቡ ናቸው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የንጉሠ ነገሥቱ ቤተሰቦች፣መሣፍንቱና መኳንንቱ ማለትም ፡-
1. ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣
2. ልዑል አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ኃይለሥላሴ፣
3. ልዕልት ወለተ-እስራኤል ሥዩም የአልጋወራሹ ባለቤት (ከልጆቻቸው ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴና ከእግጋየሁ አስፋወሰን ጋር)
4. ልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ ከአምሰት ልጆቻቸው ጋር፣
5. ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ የሐረር መሥፍን፣
6. ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ፣
7. ልዑል ሣህለሥላሴ ኃይለሥላሴ፣
8. ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ፣
9. ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ፣
10. ወይዘሮ ጽጌ-ማርያም በሻህ የልዑል ራስ ካሣ ባለቤት፣ከሁለት ልጆቻቸው ጋር፣
11. ልዕልት የሻሽ ወርቅ ይልማ ፣
12. ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣
13. ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፣
14. አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ፣
15. አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ፣
16. ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፣
17. ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ፣
18. ልጅ አበበ አርኣያ፣
19. አባ ሓና ጅማ፣
20. ደጃዝማች ነሲቡ ዘማኔል፣
21. ደጃዝማች መኮንን እንዳልካቸው፣
22. ደጃዝማች አበበ ዳምጠው፣
23. ደጃዝማች ዐምደ ሚካኤል፣
24. ፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተሚካኤል
25. ፊታውራሪ ተሰማ ባንቴ ፣ ወዘተ ያካተተ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡(ገብረወልድ እንድዳ ወርቅ 2000፣105-106)
ባንደው በቁጥሩ ከሁሉም ከፍተኛ የሆነ፣ ሁለመናውን ለጣሊያን ፍላጎት ያስገዛ፣የአንድነታችንና የማንነታችን አውራ ጠላት የነበረው ነው፡፡ ስም ከነበራቸው ታላላቅ ሰዎች ከሚባሉት ሁለንተናቸውን ለጣሊያን ሰጥተው ማንነታችን በእጅጉ ከጎዱት ባንዳዎች መካከል ለአብነት፣ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት፣ራስ ሥዩም መንገሻ፣ደጃዝማች አያሌው ብሩ፣ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ፣አቶ አምደ ሚካኤል ደሳለኝ፣አቶ አድማሱ ረታ፣አቶ ለማ ወልደ ገብርኤል፣አቶ ተፈሪ ሻውል፣ አቶ ገብረ ወልድ እንግዳ ወርቅ፣ብላት ዳዊት እቁበ እግዚእ፣ደጃዝማች አስፍሃ ወልደ ሚካኤል፣ጄኔራል መኮንን ደነቀ፣አቶ ብርሃኑ ድንቄ፣ሻለቃ አሰፋ ለማ፣ሼክ አል ሆጆሌ፣ሡልጣን መሐመድ ሃንፋሪ፣ ደጃዝማች ሆሣዕና ጆቴ፣ ደጃዝማች ዮሐንስ ጆቴ፣ሡልጣን አብዱላሂ ጂፋር፣ሡልጣን አባ ጆቢር አብዱላሂ፣ ራስ ጌታቸው ናደው፣ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣አቶ ይልማ ዴሬሳ፣ብላታ አየለ ገብሬ፣ነጋድራስ ወዳጆ አሊ፣አቡነ አብርሃ፣አቡነ ይስሐቅ ( ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ-ማርያም፣2005፣16) ደጃዝማች እጅጉ አያሌው፣ ፊታውራሪ ነገደ ዘገዬ እና አያሌ ሆድ አደር ባንዳዎች ወዘተ ይገኙበታል፡፡ ልብ በሉ! እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል የአገርና የሕዝብ ሚስጢሮችን ለጣሊያን በመንገር የማንነታችን አሻራዎች እንዲወድሙ ያደረጉ፣አርበኞች የሚወጡ የሚገቡበትን በመሰለል ያስገደሉ፣ ያሳሰሩ፣የአገርና የሕዝብ ሀብት ያዘረፉ፣ማንነታችን ጥላሸት የቀቡ ፣ ሕዝቡ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ክዶ ጣሊናዊ ማንነትን እንዲላበስ ኅሊናዊ ጫና ሲያሳድሩ የነበሩ የአገርና የትውልድ አውራ ጠላቶች ናቸው፡፡
ከዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ቁምነገር አለ፡፡ ባንዳዎች ወደውና ፈቅደው ነፃነታቸውንና መብታቸውን ለቅኝ ገዥው ኃይል የሰጡ ናቸው፡፡ ማንነታቸውን ክደው የቅኝ ገዥውን ሁለንተናዊ ማንነት ለመላበስ የጣሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከወራሪው ኃይል በላይ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጠላቶች ናቸው፡፡ የባንዳው ኃይል፣ለፋሽስቱ ቢሮክራሲ በመረጃ አቅርቦት፣በተላላኪነት፣በሹፌርነት፣ በዘበኝነት፣በቤት ውስጥ አሽከርነት፣በአስተርጓሚነት በመሳሰሉት ሥራዎች ተሰማርቶ ይሠራ የነበር ስለነበር፣ የማንበብና የመጻፍ፣ልምድና ችሎታ እንዲያዳብር አድርጎታል፡፡ እግረ መንገዱንም ከአማርኛና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች በተጨማሪ የቅኝ ገዥ ቋንቋዎችን የማንበብና የመጻፍ ዕውቀት እንዲጨብጥ ሆኗል፡፡ ይህም የዘመናዊ ቢሮክራሲን አሠራር እንዲለማመድ በር የከፈተለት መሆኑ ግልጥ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ስደተኛው ቡድን ተሰዶ በኖረባቸው አገሮች የዘመናዊ ቢሮክራሲን አሠራርና ሌሎች ቋንቋዎችን በተለይም እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛን ቋንቋዎች እንዲውቅ ሁኔታዎች ግድ እንዳሉት እንረዳለን፡፡
ከድል በኋላ የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ሲዋቀር፣ ላገር የሠሩ ሰዎች መሾም መሸለም ሲገባቸው፣በአገር ላይ የሠሩት ከሐዲዎቹና ባንዳዎቹ ተሹዋሚና ተሸላሚ ሆኑ፡፡ወሳኝ ለሆኑት ሕግ የማውጣት፣ሕግ የመተርጎምና የወጡትን ሕጎች የማስፈጸም ኃላፊነቶችን የሚረከቡ ሰዎች መመዘኛ ለኢትዮጵያዊነት ያለ ታማኝነት፣ በነፃነት ትግሉ ዘመን የተከፈለ መስዋዕትነት ሳይሆን፣ ከዘመናዊ ቢሮክራሲ ጋር ያለው ቁርኝት፣የውጭ አገር ቋንቋና የጽሕፈት ችሎታ ሆነው ቀረቡ፡፡ በዚህም የተነሳ ስደተኛውና ባንዳው ቡድን የአንበሣ ድርሻውን ወሰደ፡፡ የነፃነት ታጋዩና ዕውነተኛው ኢትዮጵዊ የበለል ተጣለ፡፡ ይህ ድርጊት ያሳዘናቸው አርበኞችም ደርጊቱን እንዲህ ሲሉ ገለጡት፡፡
አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፤
ዳር ድንበር ጠብቀን ባቆየናት አገር፣
ውጤቱ ተረፈን ባፍንጫ መናገር፤
ይህ ስደተኛና ባንዳ ቡድን የቀሰመው ዕውቀት ከኢትዮጵያዊነት ዕሴቶች ፣ማንነት፣ባህል፣ቋንቋ፣ሃይማኖትና አጠቃላይ ሁለንተናዊ መስተጋብር ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት የሌለው ስለነበር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ከማንነት የሚያፋታ እንጂ፣ማንነትን የሚያዳብር ባለመሆኑ ትውልዱን ቀስ በቀስ ወደ ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት ቦይ አንኮልኩሎ እንዳስገባው እናያለን፡፡ ወሳኝ የመንግሥት መዋቅሮች በባንዳዎችና በስደተኞች መያዝ፣ ባንዳነትና አገር ክዳት ወንጀል መሆኑ ቀርቶ እንደመልካም ሥራ እንዲታይ አስገደደ፡፡ ይህም በተተኪው ትውልድ አመለካካት ላይ አርበኝነት፣ለማንነት መቆምና መታግለ እርባናቢስ እንደሆነ፣በኅብረተሰቡ ውስጥ ክብርና ሞገስ የማያስቸር፣ በአንፃሩ ከሐዲነትና ባንዳነት አሹአሚና አሸላሚ መሆኑን በተጨባጭ እንዲያይ በማድረጉ ኅሊናውን ለቅኝ ተገዥነት ማመቻቸት እንዳለበት በአገሪቱ የሚካሄዱት ድርጊቶች ጠጣር ዕውነት ሆነው ታዩት፡፡በአገሪቱና በሕዝቡ አንጡራ ሀብት ወንጀለኞችና ባንዳዎች እንደፈለጉ ሲናኙበት፣ ቤተሰባቸውን ሲያስተምሩበት፣ ልጆቻቸውን ለቀጣዩ ትውልድ ገዥነት ሲያሰለጥኑበት፣ አርበኛው የበይ ተመልካች መሆኑንን በገሐድ አየ፡፡ የአርበኛው ልጆች በአባቶቻቸው ተጋድሎ የሚያፍሩ እንጂ፣ የሚመኩና የሚኮሩ እንዳይሆን ተመለከተ፡፡ ባንዳነት ማሳፈሩ ቀርቶ መኩሪያ ሆነ፡፡ አርበኝነትና አገር ወዳድነት አዋራጅና የደህነት መገለጫ ሆኖ ታዬ፡፡ ይህ ሁኔታ ትውልዱ ባንዳነትን እንደተገቢ ተግባር እንዲቆጥረው ገሐዳዊ ምሳሌ ሆኖ ቀረበ፡፡ ውጤቱም ከድል በኋላ የተዋቀረው የንጉሠ ነገሥቱ አስተዳደራዊ መዋቅርና በመዋቅሩ የተካተቱ ሰዎች ማንነት ተከታዩን ትውልድ የኅሊና ቅኝ ተገዥነትን እንዲለማመድ አመቻቸው፡፡
2. የትምህርት ፖሊስ በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ አለመመሥረት፣
በስደተኛውና በባንዳ የተዋቀረው የንጉሠ ነገሥቱ ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር የቀየሰው የትምህርት ፖሊሲ ትውልዱ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ላይ ተመሥርቶ፣ በሂሳብ ዕውቀት ላይ መሠረቱን የጣለ፣ለምርምርና አዳዲስ ቴክኖሎጂን አፍላቂ በሚሆንበት መልኩ እንዲሆን አላደረገም፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ትውልዱን ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ፈጽሞ የሚያፋታ፣የራሱን ማንነት እየናቀ የሌሎችን አድናቂና ተከታይ በሚያደርግ መልኩ የተቀየሰ ነበር፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ለፈረንሣና ለእንግሊዝኛ ቋንቋዎች፣እንዲሁም ለማኅበራዊ ሣይንሶች ልዩ ትኩረት የሰጠና ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ለዘመናት ይዛው ከመጣችው አሠራር ጋር የማይገናኝ ስለነበር፣ ትውልዱ ውጭ አምላኪና የራሱን ማንነት ሳያውቀው ቀስበቀስ እያወለቀ እንዲጥል ሠፊ በር ከፈተለት፡፡ ይህም በመሆኑ፣ “የዐዳም ቋንቋ እንደሆነ የሚነገርለት፣እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደተነጋገረበት ብዙ” የሚባልለት የግዕዝ ቋንቋ ከትምህርት ቤትና ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን በቤተክረስቲያንም አገልግሎት ሊሰጥበት ከማይቻልበት ደረጃ ተደሷል፡፡ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ባህል፣ሥነ-ምግባርና አመለካከት በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ባለመካተቱ ፣ወጣቱ ትውልድ የእርሱ የሆነውን ወርቁን ነገር እየጣለ፣ የርሱ ያልሆነውን ኩበቱን ሙጭጭ ብሎ እንዲያዝ ተነገረው፡፡የኢትዮጵያዊነት ልዩ መታወቂያ የሆነው የጽሑፍ ቋንቋ አማርኛ ቀስበቀስ ከትምህርት መገናኛነቱ እንዲወጣ ተደረ ፡፡ የትምህርቱ ይዘት የኢትዮጵያን ባህል፣ታሪክ፣መልከዐ-ምድር፣ቋንቋ፣ ሥነ-ልቦና፣የሕዝብ አደረጃጀትና የአጠቃላይ ማኅበራዊ ግንኙነት ምንነትን ፈጽሞ ግንዛቤ ያስገባ አልነበረም፡፡
የታሪክ ትምህርት ስለግሪክ፣ስለአውሮፓ፣ስለሮም ፣ስለሜሶፖታሚያ፣ስለግብፅ፣ ወዘተ እንጂ፣ ስለኛው ረጅምና አኩሪ ታሪክቻችን፣ስለአርበኞቻችን ማንነትና ተጋድሎ የሚያወሱ ትምህርቶች ለትውልዱ አይሰጡም ነበር፡፡አባቶቻችን ከፖራቹጋሎች፣ከቱርኮች፣ከመሐዲስቶች፣ከግብፆች፣ ከጣሊያኖችና ከአውሮፓ ኃያላን ጋር ስላደረጉት የነፃነትና ማንነትን የማስከበር ተጋድሎ፣የተጋድሎው መሪ ተዋንያን ማንነት ትውልዱ እነዲያወቅ አልተደረገም፡፡ የነካሌብን፣የነኢዛናን፣የነላሊበላን፣ የነዘርዐ-ያዕቆብ፣የነሠርጸድንግል፣የነዐምደ-ጽዮን፣የነልብነድንግል፣የነገላውዲዮስ፣የነቴዎድሮስ፤የነዮሐንስና የነምኒልክ ወዘተ ፖለቲካዊና ወታደራዊ የአመራር ጥበብና ችሎታ፣የነገብርዬ፣የነአሉላ አባነጋ፣የነሀብተጊዮርጊስ ዲነግዲ፣የነገበየሁ ተክሌ የነኮሎኔል አቢሳ አጋ የጦር ሥልትን ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ወዘተ ታሪክ ትውልዱ በቅጡ እንዲያውቀውና እንዲመካበት አልተደረገም፡፡ እንኳን ያን ጊዜ ዛሬም የለም፡፡
የመልከዐ-ምድሩ(ጂኦግራፊ) ትምህርት ስለዓለምና አሕጉሮች እንጂ ፣ስለኢትዮጵያ ወንዞችና ተራሮች፣ ማዕድን፣የውኃ ሀብት፣ የአየር ጠባይ፣የእንስሳት ሀብት፣የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ፣የሕዝብ መብትና ግዴታ፣ ወዘተ በየደረጃው የሚሰጡ አልነበረም፡፡ የትምህርቱ አጠቃላይ ዓላማ ወደ ውጭ የሚያይ እንጂ፣ ወደ ውስጥ ማሳየት የማይችል ስለነበር፣ትውልዱ ወደ ውጭ እንጂ ወደ ውስጥ እንዲመለከት አላስቻለውም፡፡ ወደ ውጭ መመልከት ደግም፣ማንነትን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ሌላ ማንነትን ለመላበስ የሚያመቻች በገዛ ፈቃድ ለቅኝ ተገዥነት ራስን ማመቻቸት እንደሆነ በተጨባጭ እያን ነው፡፡ በትምህርቱ ውስጥ የሚካተቱት የመልካም ነገሮች ማመላከቻዎች ኢትዮጵያዊ አለመሆን፣ትውልዱ የራሱ የሆነ፣የተሻለ ነገር እንዳለው ሊገነዘብ ባለመቻሉ፣በተነገረው ምሳሌና ማነፃፀሪያ መሠረት አሻግሮ እንዲመለከት ግድ አለው፡፡ በመሆኑም የ1960 ዎቹ ለውጥ ናፋቂ የነበረው ትውልድ የሽምቅ ውጊያን ከቴዎድሮስ ፣ከምኒልክ፣ከዮሐንስ ከነአሉላ፣ገብርዬ አቢሳ አጋነ፣ አበበ አረጋይ ወዘተ ለመቅሰም ባለመቻሉ የተከተለው የማኦን፣የሆቺሚንንና የቼጉቬራን የሽምቅ ውጊያ ስልት ነበር፡፡ የዘመረውም “ፋኖ ተሰማራ ፣እንደነ ሆቺሚን እንደቼጉቬራ” ሲል ነበር፡፡ የአገሩን ፋኖዎች ልዩ ዕውቀትና ችሎታቸውን ባለማወቁ በቃል በተነገረውና ተጽፎ ባገኛቸው በውጭዎቹ ሰዎች ማንነት ተከታይ ለማፍራት ቀሰቀሰባቸው፡፡ይህም ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት ራሱን እንዲያመቻች እንዳደረገው መገንዘብ ይቻላል፡
በሌላ በኩል፣ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጪ የሚላኩት ፣ ወጥ በሆነ መንገድ ላገሪቱ የሚያስፈልጓትን ሙያተኞች ከራሷ ፍላጎት አኳያ በምትፈልገው የዕውቀት መሥክ የሚሰለጥኑ አልነበሩም፡፡ የሚሰለጥኑት በየግለሰቦቹ ፍላጎትና የትምህርቱን ዕድል በፈቀደው መንግሥት ፕሮግራም መሠረት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህም በመሆኑ፣ሰልጣኞቹ የሚሰለጥኑት ከአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ግንኙነት በሌላቸው፣የትምህርቱን ዕድል በሰጡ አገሮቸ የትምህርት ፖሊሲ ላይ የተመሠረቱና ከነዚያ አገሮች ታሪክና ባህል፣እንዲሁም ሊደርሱበት ወደ አለሙት ግብ ሊያመራ በሚችል መልኩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ሠልጣኞቹ ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ተመሳሳይ የፖሊሲ አቅጣጫ ለመንደፍም ሆነ ለማስተማር ግብቡ አልነበሩም፡፡ ፈረንሣይ፣ምዕራብ ጀርመን፣እንግሊዝ፣አሜሪካ፣ሶቭዬት ኅብረት፣ምሥራቅ ጀርመን፣ቼኮዝሎቫኪያ፣ቡልጋሪያ፣ሀንጋሪ፣ዩጎዝላቪያ፣ጣሊያን፣ ወዘተ የተማሩት ለየቅል ቆሙ፡፡ ልዩነታቸው በተማሩበት አገር ብቻ ሣይሆን፣በተማሩበት ተቋምና በተማሩት የትምህርት ዓይነት ጭምር ሆነ፡፡ ይህ ልዩነት ደግሞ እንደ ኢትዮጵያዊነት፣ከኢትዮጵያዊነት ዕሴቶች ተነስቶ፣ኢትዮጵያ ጠቀም ወደ ሆነ አስተሳሰብ ለማምራት መንገዱን ዘጋው፡፡ ከዚህ ላይ ርዕዮተዓለማዊ ልዩነት ተርከፍክፎበት ከድል በኋላ ቀለም የቆጠረው ትውልድ ኢትዮጵያን በየራሱ ፍላጎት በመሳል፣ “እኔ ለኢትዮጵያ የተሻለ አስባለሁ፣ከእኔ ውጭ ያሉት ትክክል አይደሉም” ብለው እንዲያስቡና እርስ በራሱ እንዲጠፋፋ መንገዱን አመቻቸ፡፡ የመጠፋፋቱ ግብግብ በከፋ መልኩ መቀጠል ትውልዱ የእርሱነቱ መታወቂያ የሆነች አገሩን እየሸሸ በመገደድና በመውደድ ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት ራሱን እንደዳረገ በገሀድ እያየን ነው፡፡
3. የአዲስ ገብ ሃይማኖቶች መሥፋፋት፣
ማንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ የመረመረ ሰው ሊገነዘበው እንደሚችል፣የሕዝቡ መሠረታዊ ሃይማኖቶች፣ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ሱኒ እስልምና፣አይሁድና ባህላዊ እምነቶች ናቸው፡፡ እንዚህ ሃይማኖቶች አንዱ በሌላው ውስጥ ያለ በመሆኑ፣ኢትዮጵያዊ ማንነትን ፣የአገርና የቤተሰብ ፍቅር፣ነፃነትና አልበገርም ባነይነት፣ በኢትዮጵያዊነት መመካትና መኩራት ልዩ ዕሴቶቻቸው አድርገው የተቀበሉና ለነርሱም ዳብሮ መቀጠል የየእምነቶቹ ተከታዮች አይከፍሉ መስዋዕትነት በጋራ እየከፈሉ የኖሩ መሆኑ ግልጥ ነው፡፡
ከድል ኋላ “ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው “ በሚለው የንጉሠ ነገሥቱ የሃይማኖት ፖሊሲ ምክንያት በርካታ አዳዲስ ሃይማኖቶች ወደ አገራችን እንዲገቡ ሠፊ በር ከፈቱ፡፡ ቀደም ሲል ገብተው የነበሩትም ተልዕኮአቸውን ያላንዳች ሥጋት እንዲወጡ ሁኔታዎች የበለጠ ተመቻቸላቸው፡፡ “ገንፎ ሲያምርበት ተንከባሎ ከቅቤ ማሰሮ ይገባል” እንደሚባለው ሆኖ፣ ቀደም ሲል በሃይማኖት፣በአገር አሳሽነት፣በመሬት ግዥና በቀጥታ ወረራ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ ያልቻሉ ኃይሎች ፣ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ የኅሊና ቅኝ ተገዥ የሚሆንበት መንገድ በስፋት ተከፈተላቸው፡፡ ንጉሠ-ነገሥቱ ኢትዮጵዊነትን መጠበቅ የሚያስችል ስልት ሳይነድፉ፣ በሃይመኖት ነፃነት ስም ትውልዱ ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት የሚመቻችበትን መንገድ በስፋት ከፈቱ፡፡ በመሆኑም በርካታ የሃይማኖት ድርጅቶች ወደ አገራችን ገቡ፡፡
አዲስ ገቦቹ ሃይማኖቶች ቀደም ሲል ቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት በአፍሪካና በእስያ የተሠማሩ ስለነበሩ የተጠናከ መዋቅር፣በከፍተኛ የመረጃና የሰው ኃይል የተደራጁ ከመሆናቸውም በላይ፣ የቅኝ ገዥ ኃይሎች መዋዕለ ንዋይ በገፍ የሚጎርፍላቸው በመሆኑ ነባሮቹ ኢትዮጵያዊ ሃይማኖቶች ከሚሰጡት መንፈሳዊና ሥጋዊ አገልግሎቶች በላይ ለሕዝቡ በስፋት መስጠት ጀመሩ፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው በሙዚቃ ፣በጭብጨባና በዳንስ የታጀበ በመሆኑ የአድማጮችን ኅሊና በቀላሉ ሳበ፡፡ ከመንፈሳዊ ትምህርቱ፣ዝማሬውና ሽብሸባው በተጓዳኝ፣ የአውሮፓን ታሪክና ስልጣኔ፣ ሕዝቡ የደረሰበትን የዕደገት ደረጃ የሚያሳዩ ፊልሞችን በብዛት አሰራጩ፡፡ ኢትጵያውያንን የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች የሚያደርጉበትን ሁነኛ መሣሪያ የሆነውን የዘመናዊ ትምህርትን ከሃይማኖት ጋር አቀላቅለው የሚያስተምሩበትን የትምህርት ሥርዓት ዘረጉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በነፃና አልፎ አልፎም በተመጣጣኝ ክፍያ የሕክምና አገልግሎት መሥጠት ጀመሩ፡፡ ዘወትር እሑድ የዕለት ምግብ አጥተው ለሚራቡ ሰዎች የምግብ ፕሮግራም ዘርግተው መመገብ የዘወትር ተግባራቸው አድርገው ያዙት፡፡ የዓመት ልብስ ለሌላቸው የአውሮፓና የአሜሪካ ልባሾችን እየሰበሰቡ በነፃ በማደል እርቃናቸውን እንዲከልሉ አደረጉ፡፡ “ይህም የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉ ሆኖ፣የበርካታ ሰዎችን ኅሊና እንዲገዙ አስቻላቸው፡፡
ነባሮቹ ሃይማኖቶች አማኙ የሚከተላቸው በመወለድ እንጂ፣በመማር ካለመሆኑም ሌላ፣ሃማኖቶቹ እንዲስፋፉ የሚያስችል የአደረጃጃት፣የሰው፣ የገንዘብና በዕወቀት ላይ የተመሠረተ የመረጃ ፍሰትና ልውውጥ አቅም የሌላቸው በመሆኑ ፣ከአዲስ ገቢዎቹ ሃማኖቶች ጋር ከታሪክ ርዝመት አንፃር ሲመዘን አቻ ለመሆነ ቀርቶ ለመከተል እንኳ እንዳልቻሉ ሁኔታዎች ያሳሉ፡፡
የአዲስ ገብ ሃይማኖቶቹ መሠረታዊ ተልዕኮ ሕዝቡ የኢትዮጵያዊነት ማንነቱ መገለጫ የሆኑ ዕሴቶቹን ቀስ በቀስ በፈቃዱ አውልቆ ጥሎ የአውሮፓዊ ማንነትን ጥብቆ እንዲያጠልቅ በመሆኑ፣ባቋቋሙዋቸው ትምህርት ቤቶች የተማሩትንና ብሩኅ አዕምሮ ያላቸውን በስኮላር ሽፕ መልክ ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመላክ አውሮፓዊና አሜሪካዊ አስተሳሰብና አመለካከል አዳብረውና ይዘው እንዲመለሱና መልስው ወገናቸውን በነርሱ ሥር እንዲሰለፍ እንዲያደርጉ አደራጁዋቸው፡፡ ”እስ በሱ ሥጋን በኩበት ጠበሱ” እንዲሉ፣መልሰው የገዛ ወገኖቻቸውን የራሳቸውን ማንነት ትተው ሌላ ማንነትን እንዲላበሱ እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ አደረጉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በከፈቱዋቸው የጤና ጣቢያዎች የቀጠሩዋቸውን ሰዎች ወደ ውጭ በመላክ ህክምናን ከሃይማኖት ዕውቀት ጋር አጣምረው የሚሠሩ ሰባኪና ሐኪሞችን በብዛት አሰለጠኑ፡፡ በዚህ የተጠናከረ ሂደት የደቡብ፣የምዕራብ፣የደቡብ ምዕራብና የመሀል ኢትዮጵያ ነዋሪ ነባር ሃይማኖቱን እየተዎ የአዲስ ገብ ሃይማኖቶች ተከታይ ሆነ፡፡ ይህም ያለጥርጥር ኢትጵያዊው ኅሊናውን ለቅኝ ተገዥነት ወዶ እንዲያመቻች እንዳደረገው መገንዘብ ይቻላል፡፡ የተግንጣይ ብሔርተኞች ድርጅቶች መሪዎች ተኮትኩተው ያደጉት በነዚህ የአዲስ ገብ ሃይማኖቶች ባቋቋሟቸው ትምህርት ቤቶች መሆኑን ልብ ስንል፣እነዚህ ሃይማኖቶች የቱን ያህል ሕዝቡን ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት እንዳመቻቹት እንረዳለን፡፡
4. የኢትዮጵያ አብዮት ያስከተለው የኅሊና ስብራት፣
ሚሽነሪዎቹ በቂ ተከታይ ማግኘታቸውን ካረጋገጡ በኋላ፣ሕዝቡ በኅሊና ቅኝ ተገዥነት ሥር ወዶና ፈቅዶ ለዘመናት መኖር የሚችለው የትኞቹን ተቋሞች ብናፈርስ ነው/ እንዚህን መዋቅሮችስ እንዴት እናፈርሳለን/ በሚል ጥናት ላይ ተሰማሩ፡፡ በዚህ ጥናታቸውም የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መሠረትና ምሰሶ የሆኑ ተቋሞችን ምንነት ለይተው በማወቅ ተቋሞቹ ሊፈርሱባቸው የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ መጽሐፍትን በጥናትና ምርምር ስም ለዓለም አሰራጩ፡፡ የሃይማኖት ተከታዮቻቸውም እንዚህን በኢትዮጵያ መሠረታዊ ጠላቶች ማር ቀብተው ያዘጋጁዋቸውን በርዞች እንደ ደረቅ ሐቅ በመውሰድ ያላንዳች ማመዛዘንና አድሮ እየው ጥያቄ ዋጡዋቸው፡፡
ሚሽነሪዎቹ ባደረጉት ጥናት የኢትዮጵያዊነት መሠረት የሆኑት ተቋሞች “የሥልጣን ምንጭና የአንድነት ምልክት የሆነ ዘውዳዊ ሥርዓት፣የዘውዳዊ ሥርዓቱ ርዕዮተ-ዓለማዊ ክንድ የሆነ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት እና ራሱን በቋንቋ ትስስር ያላደራጀ፣ በመሠረታዊ አደረጀደጀት ደረጃ በአጥቢያ ቤተ እምነቶች ዙሪያ የሚደራጅ፤ከፍ ሲል በአስተዳደራዊ ክልሎቸ ማንነቱን የሚገልጥ፣በሠፊዋ ኢትዮጵያ በበቂ መጠን ተሰራጭቶ የሚኖርና በኢትዮጵያዊነት በጽኑ የሚያምን፣በተፈጥሮው ተዋጊና የአገር ዘብ የሆነ ዐማራ የተሰኘ ነገድ እንደሆኑ ተረዱ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነትም ሲባል የዐማረው እንጂ፣የሌሎችን ነገዶች የሚጨምር አይለም፣ኢትዮጵያዊነት በሌሎች ላይ ዐማራው የጫነባቸው ዕዳ ነው ሲሉም ጨመሩበት፡፡” እነዚህ ተቋሞች ካልጠፉ ወይም በሕዝቡ ላይ የሚያሳድሩት ሁለንተናዊ ተፅዕኖ ካልተወገደ ኢትዮጵያን በውጭ ኃይሎች ሥር ለማዋል እንደማቻል እርግጠኛ ሆኑ፡፡
ተከታዩ ሥራቸው እንዚህን ተቋሞች እንዴት ማጥፋት ይቻላል? በሚለው ዙሪያ ወጥሮ መሥራት ነበር፡፡ ባደረጉት ጥረትም የነርሱን ዓላማ የሚጋሩ ብቻ ሳይሆን፣ብዙ ማይል ርቀው የኢትዮጵያን የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ በመቶ ዓመት የገደቡ ብሔርተኛ ግለሰቦችንና በሚሽነሪ ትምህርት ቤቶች በፀረ ኢትዮጵያነት ተኮተረኩተው ያደጉ በርካታ ሰዎችን አገኙ፡፡ እንዚህን ግለሰቦች በተለያዩ መሰባሰቢያ መድረኮች ስም እንዲደራጁና የሰው ኃይል እንዲያሰባስቡ፤ፍላጎታቸውን በየጸሎት ቤቱና ባመቻቸው አጋጣሚ ሁሉ እንዲያሰራጩ አበረታቱ፡፡የኦነግ መሠረት የሆነው የሜጫና ቱሉማ ማኅበር የተመሠረተው በዚህ መልክ ሲሆን፣ የኦነግ መሪዎችም ወለጋ ጊንቢ አውራጃ ውስጥ በተከፈተ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮችና ተማሪዎች በነበሩ ግለሰቦች መሆኑን ስንገነዘብ የአዲስ ገብ ሃማኖቶች ተልዕኮ ምን እንደነበር በቅጡ ልንገነዘብ እንችልለን፡፡ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ድርጅት የተመሠረተውም በትግራይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ስም እንደሆነ ይታወቃል፡፡የወያኔ መሥራቾችም በዐድዋ አውራጃ ተወላጆች መያዝ ፣ ዐድዋ ከተማ ውስጥ ከነበረ የሚሽነሪ ትምህርት ቤት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ከሁሉም በላይ መያዝ ያለበት መሠረታዊ ጉዳይ የብሔረሰብ ጥያቄ አንስተው የተደራጁ ብሔርተኛ ሰዎች የባንዳ ልጆች መሆናቸው ነው፡፡ሚሽነሪዎቹ በዚህ መልክ አደራጅተው ኢትዮጵያን ለመናድ በሚጥሩበት ወቅት ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከ1960ዎቹ መባቻ ጀምሮ ማርክሳዊ-ሌኒናዊ ርዕዮተዓለምን በተቀበሉ ቡድኖች አቀንቃኝነት የሚያራምዱት የፍትሕና የዲሞክራሲ ጥያቄ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ በሁለቱ ወገኖች እንቅስቃሴ የሚፈልጉትን ሳያሟሉ ወይም ሳያገኙ ፣ የየካቲት 1966ዓ.ም ሕዝባዊ አብዮት በድንገት በሕዝብ ብሶት ፈነዳ፡፡
የሕዝቡን ቁጣና ብሶት መሠረታዊ ምክንያቶች በቅጡ ለይቶና አውቆ፣ ሕዝባዊው አብዮቱ በኢትዮጵያዊነት ማንነት ላይ መሠረቱን ጥሎ ወደ ፊት መጓዝ የሚችልበነትን መንገድ የሚያመቻችና የሚመራ ሕዝባዊ ኃይል በወሳኝነት መልኩ ሳይወጣ የፈነዳው አብዮት፣ቅኝ ገዥ ኃይሎቹ ባላሰቡትና ባልጠበቁት ፍጥነት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ፣ የአንድነትና የሥልጣን ምንጭ የነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት በራሱ ዐወቅን ባይ ልጆች እንዲወድም ተደረገ፡፡ የቅኝ አገዛዝ ተልዕኮን አንግበው በሃይማኖት ስም ወደ አገራችን የገቡ ሰዎች የመጀመሪያ ዓላማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሳካለቸው፡፡ ተያይዞም የኢትዮጵያዊነት መሠረታዊ ተቋምና የዘውዳዊ ሥርዓቱ ርዕዮተ ዓለማዊ ክንድና የበርካታው ሕዝብ መንፈሳዊ መሪ የነበረው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በመንግሥትና በሕዝብ ውስጥ የነበረውን ከፍተኛ ኃላፊነት አሳጣ፡፡ ቀሪው ተግባር እምብዛም አድካሚ የማይሆንባቸው የቁልቁለት መንገድ የሆነው፣ሌሎችን ብሔረሰቦች በዐማራው ላይ በጠላትነት ማስነሳትና እርስ በርሳቸው በማበጣበጥ የወል ዕሴቶቻቸውን በራሳቸው በማሳጣት፣ የቅኝ ገዥዎችን ማንነት እንዲላበሱ የማድረጉ ነው፡፡
ለዚህ ተግባርም ትውልዱ ምቹ ሆኖ ቀረበላቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ዐማራው ራሱን ለእርድ አመቻችቶ ቀረበ፡፡ ሌሎቹ በአዲስ ገብ ሃይማኖቶች ተኮትኩተው ያደጉ የሌሎች ነገድ አባል ልጆች ዐማራውን በጠላትነትና በቅኝ ገዥነት ፈርጀው እንደሚመለከቱትና ሊያጠፉት በዝግጅት ላይ ያሉ መሆናቸውን የዐማራው ቀለም ቀመስ ትውልድ አልተረዳም፡፡ ቀደም ሲል ኤርትራን ለመገንጠል የተደራጀው የጀብሃ እና የሻዕቢያ ቡድኖች ፀረ-ዐማራ መሆናቸውን ፈጽሞ የተገነዘበ አልነበረም፤ ይህ ብዥታ ዛሬም የጠራ አይደልም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኦሮሞን እገነጥላለሁ የሚል ቡድን በመካከሉ ያቆጠቆጠ መሆኑን የዐማራው ነገድ ምሁራን ልብ አላሉም፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ሕዝባዊ አብዮቱን ለመምራት በተነሳ የሥልጣን ጥያቄ ኢትዮጵያውያን አግባቢ መልስ ላይ ለመድረስ አልቻሉም፡፡ ሁሉ ባፈተተው ተጓዘ፡፡ በጉዞው በርካታ ፀረ-ዐማራና ፀረ- ኢትዮጵያ የሆኑ ድርጅቶች በቅኝ ገዥዎች ፍላጎት ላይ ተመሥርተው ተደራጁ፡፡ ነባሮቹ ጀብሓና ሻዕቢያ፣ሕወሓት፣ ኦነግ፣እስላሚያ ኦሮሞያ፣የኦጋዴን ነፃ አውጭ፣የአፋር፣የጉራጌ የከምባታ፣የወላይታ፣ የሲዳማ፣ ወዘተ እንደ አሸን ፈሉ፡፡ በሌላ በኩል ኅብረ-ብሔራው ድርጅቶች እንደ መኢሶን፣ኢሕአፓ፣ኢዲኅ፣ወዝሊግ፣አብዮታዊ ሰደድ፣ማሌሪድ፣ኢጭአት፣ የመሳሰሉት ተፈጠሩ፡፡ጉዞው ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ብዙ ሕይዎትን የጠየቀ፣ማንነትን በእጅጉ የሚፈታተን፣ መወለድን የሚያስጠላ ሆነ፡፡ በዚህ ጉዞው ውስጥም የውጭ ድጋፍ በማግኘት የበላይነትን እናገኛልን በሚል ስሌት ኢትዮጵያውያን ራሳችን ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት አመቻቸን፡፡ የጉዞው ክፋት ያስከተለው ተስፋ መቁረጥ የናቅነውንና አባቶቻችን ድል ነስተው የመለሱትን ቅኝ ገዥ ኃይል ለምነንና ደጅ ጠንተን ቅኝ ተገዥ ለመሆን ስደትን እንድነመርጥ አደረገን፡፡ ይህ አጠቃላይ ሁኔታም ኢትዮጵያውያን ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት እንድንዳረግ አድርጎናል፡፡
በሌላ በኩል፣በአገሪቱ የተለያየ ዓላማና ግብ ይዘው፣በብሔርና በኅብረ-ብሔር ስም የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች የጠላትነት ደረጃውንና ስሙን ይለዋውጡት እንጂ፣ሁሉም የዐማራውን ነገድ “በገዥ መደብና በጨቋኝ ብሔርነት” በመፈረጅ የጥፋት ክንዳቸውን አነሱበት፡፡ በነገዱ ላይ በእርዳ ተራዳ ከደረሰበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅምና መብት ነጠቃ በተጨማሪ፣በኢትዮጵያ ምድር ሠርቶ የመኖር መብቱን እንዲነጠቅ ሆነ፡፡ ስልታዊ በሆነ መንገድ በተከፈተበት የዘር ማጽዳት ዘመቻም ባለፉት የወያኔ አገዛዝ 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ የደረሰበት አለመታወቁን የራሱ የወያኔ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባለሥልጣን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ይህም ቅኝ ገዥዎች ኢትዮጵያን በፈለጉት መንገድ በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል እንቅፋት ሆነውብናል ያሏቸውን ተቋሞች “እሾህን በሾህ “ እንዲሉ ራሳችን፣እራሳችንን እንድናጠፋና የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች እንድንሆን እንዳደረጉን እያየን ነው፡፡ በዚህ ራስን በራስ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ከዐማራ ነገድ ውጭ ያሉ ምሁራን በዘር ተደራጅተው የዘራችን አውራ ጠላት ነው ብለው በፈረጁት የዐማራ ነገድ ላይ የጥፋት ክንዳቸውን ሲያነሱ፣የዐማራው ነገድ ምሁራን ራሱን አደራጅቶ ዘሩን ከጥፋት ለመከላከል ካለማሰቡም ሌላ፣የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባል በመሆን በራሱ ነገድ ላይ የጥፋቱ ተባባሪ ሆኖ ይታያል፡፡ ለአብነት ያህል በኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ ተደራጅተው የነበሩት የዐማራው ምሁራን የገዥ መደብ ነው ብለው በፈረጁት ዐማራ ላይ ያለፍርድ ሂደት አያሌ ዐማሮች ንብረታቸውንና ሕያዎታቸውን እንዲያጡ አድርገዋል፤ ተባብረዋል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ “እስ በሱ ሥጋን በኩበት ጠበሱ” የሚያሰኘው፡፡
5. የኅሊና ቅኝ ተገዥነት የሚገልጽባቸው መልኮች፣
የቅኝ ገዥነት መሠረታዊ ግብ የቅኝ ተገዢውን ቋንቋ፣ባህል፣ሃይማኖት፣ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት፣ተቋሞች፣አጠቃላይ ሁለንተናዊ ማንነትን ማስለወጥና የቅኝ ገዥውን ቋንቋ፣ባህል፣ሃይማኖት፣ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት፣ተቋሞችና ማንነት መተካት ነው፡፡ይህም በሁለት መልኩ ተግባራዊ እንደሚሆን የቅኝ አገዛዝ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ እነዚህም አካል እና ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት ናቸው፡፡ አካላዊ ቅኝ ተገዥነት ከአቅም በላይ በሆኑ አስገዳጅ ምክንያቶች፣ ቅኝ ተገዥ ወገኖች፣ በቅኝ ገዥው ኃይል ሁለንተናዊ ፍላጎት ቁጥጥር ሥር የሚውሉበት ሁኔታ ነው፡፡ አካላዊ ቅኝ ተገዥነት በእንስሳና በሰዎች መካከል ባለግንኙነት መመሰል ይቻላል፡፡ ቅኝ ተገዥው ለአገልጋይነት፣ቅኝ ገዥው ለተገልጋይነት የተፈጠሩ ዓይነት ሆነው የሚታዩበት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በውዴታ፣ወይም በተፈጥሮ ሕግ የተገዛ ባለመሆኑ፣ በቅኝ ተገዥው ኅሊና ውስጥ ምንጊዜም የማይጠፋ፣ጊዜና አጋጣሚን የሚጠብቅ የታመቀ አመጽ የቋጠረ ነው፡፡ አመጹ በራሱ ወይም በተከታዩ ትውልድ ለመቀስቀስ የሚያስችልና ለተቀሰቀሰው አመጽም የሞራል፣ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ ሕግ ጊዜ የማይሽረው ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም አካላዊ ቅኝ ተገዥነት የሁለንተናዊ አቅም ማጣት ወይም ማነስ የሚያስከትለው በመሆኑ ቅኝ ተገዥው ማንነቱን ከውስጡ አያጠፋም፡፡ የእርሱነቱ መገለጫዎችን በልዩ ልዩ ዘዴዎች ለትውልዱ ያስተላልፋል፤በሚስጢር ይጠብቃል፡፡ የቅኝ ገዥዎች የሆኑ ማናቸውንም ነገሮች በውስጡ ይጠላቸዋል፤ይጠየፋቸዋል፤ይንቃቸዋል፡፡
ለምሳሌ ሕንዶች ከመቶ አምሳ ዓመታት ያላነሰ በእንግሊዞች ተገዝተዋል፡፡ ባህላቸውን፣ቋንቋቸውን፣እምነታቸውን እንዲለውጡ አያሌ ማስገደጃዎች ጭነውባቸው እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ሆኖም፣ ሕንዶች የተጣለባቸውን ጫና ተቋቁመው፣ባሕላቸውን፣ቋንቋቸውንና ሃይማኖታቸውን አስጠብቀው ለነፃነት በቅተዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እስራኤላውያን ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ በኃይል አገራቸውን ተገደው በዓለም አገሮች እንደጨው ተዘርው ሲኖሩ፣ ቋንቋቸውንና ሃይማኖታቸውን በሰው አገር አሰጠብቀው አገር ለመመሥረት ችለዋል፡፡ በሌሎች በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር የነበሩ አገሮችም የምናየው ተመሳሳይ ነው፡፡ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን መሠረታዊ ጉዳይ የትኛውም ዓይነት ቅኝ አገዛዝ ግቡ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው፣ የቅኝ ተገዥዎችን ባህል፣ሃይማኖት፣ቋንቋ፣ታሪክና አጠቃላይ ማንነትን አስጥሎ፣ የቅኝ ገዥውን ሁለንተናዊ ማንነት እንዲላበስ ማድረግ መሆኑን ነው፡፡
በአንፃሩ ኅላናዊ ቅኝ ተገዥነት በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች በቡድን ወይም በተናጠል የራሳቸውን ማንነት በገዛ ፈቃዳቸው በመተው የሌሎችን ማንነት መላበስ ነው፡፡ የኅሊና ቅኝ ተገዥነት ራስን በራስ ሰቅሎ በመግደል ይመሰላል፡፡ ራሱን ሰቅሎ የሞተሰው በክርስቲያን ሃይማኖት ፍታት አይፈታም፤ ነፍሱም እንደማትማር የሃይማኖቱ ሕግ ያስተምራል፡፡ ይህም ማለት ራስን በራስ መስቀል የሞራል፣ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ ሕጎች ድጋፍ የለውም ማለት ነው፡፡ በተመሣሣይ መልኩ፣ራሱን ወዶ ለቅኝ ተገዥነት ያቀረበና የተገዛ ሰው በውስጡ በራሱ ቁጭት የለውም፤ ወዶ ውርደትን የተቀበለ በመሆኑ፣ውርደቱ አይሰማውም፣ባለመሰማቱም ነፃ ለመውጣት አያስብም፤ ቢያስብም የሞራል፣የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሕጎች ድጋፍ አይኖረውም፡፡ የሚገፋፋው ውስጣዊ ምክንያት የሌለው በመሆኑም፤ለተከታዩ ትውልድ የሚያቀብለው ነገር ስለሌለው ትውልዱ የወላጆቹን ይዞ እንዲቀጥል ይገደዳል፡፡ ስለሆነም የኅሊና ቅኝ ተገዥነት ከአካላዊ ቅኝ ተገዥነት እጅግ የከፋ ነው፡፡ የከፋ የሚሆነው ወዶ የተቀበለው በመሆኑ፣መውጫ ቀዳዳ የሌለው መሆኑና ቅኝ የተገዛላቸው ፣ቅኝ በመገዛቱ የሚንቁት እንጂ፣የሚያከብሩት አለመሆኑን አለመገንዘቡ ነው፡፡ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ የአካላዊና የኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት ምንነት በመጠኑም ካየን፣ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት የሚገለጥባቸው መልኮች ምን እንደሆኑ ማየቱ፣የኅሊናን ቅኝ ተገዥነት በተጨባጭ በእኛ ሁኔታ ለማየት ያስችለናል፡፡
ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት በሚከተሉት መልኮች ራሱን ይገልጻል፡፡
(1) በባህል፣ (2) በስም፣ (3) በቋንቋ፣ (4) አገርን በመጥላት፣ (5) በስደት፣
1. ባህል፡- ባህል የሰው ልጅ በማምረት፣በማከፋፈልና በመጠቀም ሂደት ውስጥ፣ ሰዎች ከሰዎች እና ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር በሚፈጥሩት መስተጋብር ተገቢና ትክክል ነው ብለው በተደጋጋሚ በግልና በቡድን የሚፈጽሙት ተግባር ነው፡፡ አመራረት፣አመጋገብ፣በዐላት አከባበር፣ሰላምታ አሰጣጥ፣አለባበስ፣ደስታና መከራ የሚገለጽባቸው መንገዶች( ዘዴዎች) ፣የጋብቻ ሥርዓት፣ ምግብ አዘገጃጀት፣የአመጋገብ ሥርዓት፣ወዘት ባህል የሚገለጽባቸው ናቸው፡፡

ከነዚህ የባህል መከሰቻ መልኮች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ብዙም ያለወጥነውና አጥብቀን የያዝነው የምግብ አዘገጃጀታችን፣ አመጋገባችንና ሃይማኖታዊ የበዐል አከባበር ሥርዐታችን ነው፡፡ አለባበሳችን በአብዛኛው የምዕራባዊው አለባበስ ባህል የተጫነው ነው ፡፡ ካባ፣በርኖስ፣ተነፋነፍ፣ባት ተሁለትና ወንጨሬ ሱሪዎች፣ጋቢ፣አግድሞሽ፣ኩታና ነጠላ ፣ዙሪያ ገብ እና ኋላ ግማሽ እዳይት ቀሚስና ጎዳ፣ጀበርባሬ ኩታ፣ባለጃኖ ጋቢ ወዘት ለወግ በተወሰኑ ሰዎች ካልሆነ ሕዝቡ የኔ ብሎ የያዛቸው አለባበሶች ከሆኑ ዘመን አስቆጥረዋል፡፡ በገና እና በትንሣዔ በአሎች ይደረጉ የነበሩ የአማትና የአማች መገናኛ ዝግጅቶችና በውስጡ ይከናወኑ የነበሩ ሥርዐቶች ፈጽሞ ተረስተዋል፡፡
በገና የክስቶስን መወለድ የደስታ ስሜት መግለጫ በወጣቶች መካከል ይደረግ የነበረ የገና ጨዋታ፣ ዛሬ እንኳን ስለጨዋታው ፣ስለመኖሩም የሚያውቁ መኖራቸውም አጠራጣሪ ነው፡፡ እንደ ዳቢሎስ ተመስሎ በገና ሰሞን በአዋቂዎችና በጎልማሶች ይጨወት የነበረ “ኃይሚሎ” የተሰኘ የጉግስ ጨዋታ ከተረሳ ዘመን የለውም፡፡ በዚሁ ሰሞን ይዘወተር የነበረው የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ከጠፋ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
በፍልሰታ ታዳጊ ወጣቶች ተሰባስበው ሆያ ሆየ እያሉ እየዘፈኑ በሚሰበስቡት ገንዘብና እህል የመስቀል ዕለት ደግሰው የአካባቢውን ሰው የሚመግቡበት፣ ከኅብረተሰቡ ይቸራቸው የነበረ የእደጉ ተመንደጉ ምርቃት፣ ደመራው ከተቃጠለ በኋላ፣በፍሙ በስሎ የሚበላው እርምጦ ዛሬ የለም፡፡ ሴት ወጣቶች በቋግሜ ሳምንት አሸንድየ ታጥቀው፣ አሻንድዬ አበባዬ እያሉ ወቅትን መሠረት አድርጎ ይጨወት የነበር የጨዋታ ባህል ዛሬ በድሮው መልኩ በስፋት አይታይም፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት አንዳንዶቹ በምዕራባውያኑ ሲተኩ ሌሎቹ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ተሰርዘዋል፡፡ ገና ጨዋታ በእግር ኳስ የተተካ ይመስላል፡፡ ኃይሚሎ፣ጦር ውርወራ ለኢትዮጵያውያን አዲስም እንግዳም ባይሆንም፣ በዳርትና በጦር ውርወራ የተተካ ይመስላል፡፡ የአማትና የአማች ግንኙነት ሌላ መልክ ይዟል፡፡ አማት ፣ምራት፣አይት፣አማች፣አገቡኝ፣ ዋርሳ የሚሉት ቃላት ራሳቸው በአማትና በአማች ግንኙነት መላላት የተነሳ ትርጉማቸው ከማይታወቅበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ የምዕራባውያኑ ግንኙነት የበላይነቱን በመያዙ የእኛ ማንነት መገለጫ ተረሳ፤ ወይም ተጣለ፡፡ የጋብቻ ሥርዓታችን በእጅጉ ተለውጧል፡፡ በለቅሶ ጊዜ እንደ ሟቹ ማንነት ይደረጉ የነበሩ ፉከራዎችና ቀረርቶዎች ዛሬ አይደመጡም፡፡ ይህም ኅሊና የራሱን እየተወ የሌሎችን እየያዘ መምጣቱን አመልካች ነው ፡፡ የኅሊና ቅኝ ተገዥነት የሚባለው ይኸነው፡፡
2. ስም፡- ስም መጠሪያ ፣መታወቂያ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር ከሌላው የሚለይበት የወል፣የጥቅልና የተጸውዖ ስሞች አሉት፡፡ ስሞችም የሚወጡት በዘፈቀደ ሳይሆን፣ ስም አውጨዎቹ በኖሩበት ማኅበረሰብ ባህል፣ቋንቋና እምነት ጋር ተያይዞ የሚሰጥ ነው፡፡( ከዚህ ላይ ስም ስንል ልዩ ትኩረት የምንሰጠው የሰው መሆኑን እናስተውል፡፡) ስለሆነም የአንድ ሰው ስም በወላጆቹ ፈቃድና ውሳኔ የሚሰጥ ነው፡፡ ውሳኔው መሠረት የሚያደርገውም ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ባህልን፣እምነትንና ስም የሚወጣለት ሰው በተወለደበት ወቅት በአካባቢው በተፈጠሩ ሁኔታዎች ላይ ተመርኮዞ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከዐማራ ነገድ የተወለደ ወይም የተወለደች ሰው፣አበበ፣አበበች፣ላቀው፣ላቀች፣በላቸው፣በላይነሽ፣አስፋው-ወሰን፣ወሰን-የለሽ፣ ወርቁ፣ወርቂቱ (ወርቅነሽ)፣በላቸው ፣በላይነሽ፣አግርደው፣አግርጅው፣አስካበ፣አስካበች፣ፀጋው፣ፀጋነሽ፣ ብሬ፣ ብሪቱ፣ ወዘተ እያሉ ስም ይሰጧቸዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚወጡ ስሞች የአባትየውን ፍላጎት በሚገልጥ መልኩ፣የልጅና የአባት ስም ባንድነት ሲጠሩ የተለየ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ይሰይሟቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ሰውበሰው ደረጀ፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ፣ቁምነገር ገበየሁ፣በዓለምላይ ገበየሁ፣ኃይለሥላሴ ቀለጠ፣ ወገን በለጠ፣ አማላጅ በለጠ፣ወዘተ፣ እነዚህ ስሞች የኢትዮጵያዊነት
በተለይም የዐማራ ነገድ ማንነት መገለጫዎች እንደሆኑ በቀጥታ ከስማቸው መረዳት ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ ቀለም ቀመሱ ትውልድ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም፣ አዲስ ሃይማኖት በመቀበል፣የስም አጠራሩን ለውጭ አገር ሰዎች በቀላሉ አይገባም በሚሉና በመሳሰሉ ምክንያቶች በቤተሰብ የተሰጣቸውን ስም ሆነ እነርሱ ለወለዷቸው ልጆች ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ስሞች ሲሰጡ መታየቱ እግዳ ነገር አይደለም፡፡ ሊያ፣ሚኩ፣ሚሚ፣ሣራ፣ማይክ፣አቤነዘር፣ሌላም ሌላም ሕዝቡ የሚያውቃቸው ከኢትዮጵያዊነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኑነት የሌላቸው ስሞች እንሰማልን፤እናውቃለን፡፡ ይህ የራስን ዕንቁ ወርውሮ የሌሎችን ነሃስ መሰብሰብ ከመሆኑም በላይ፣ ራስን ለኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነትን ወዶ ማሰለፍ ነው፡፡ ሌሎቹን ሁሉ ለትዝብት ትተን ሣራ የሚለውን ስም እንደኛ(እንደ ኢትዮጵያዊ) ሆነን እንሰብ፡፡

ማንም መጽሐፍ ቅዱስን የሚከታተል ሰው ሣራ የሚለው ስም እንግዳ ነገር አይሆንበትም፡፡ “የአባታችን” የአብርሃም ባለቤት መሆኑዋን ይረዳል፡፡ ይህ ስም በእበራይስጥ ቋንቋ ትርጉሙ “እናት” እንደማለት ይመስለኛል፡፡ የእብራይስጥን ቋንቋና ባህል ለሚያውቅ ሰውና በዚያ ባህል ለኖረ ስሙ ወርቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ባህልና ቋንቋ ባለቤት ለሆነ ሰው ደግሞ ይህ ስም እንኳን የልጅ መጠሪያ ሊያደርጉት ሊናገሩት የሚከብድ ትርጉም ያለው ነው፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ! “ሣራ ነጋ” ብሎ ስም የሚያወጣ ሰው ለልጁ መጠሪያ ሳይሆን መሰደቢያ ነው የሰጣት፡፡ የቋንቋው ሥርዓትና የሕዝቡ ባሕል ከሚፈቅዱት ውጭ የተሰጡ ስሞች የኅሊና ቅኝ ተገዥነት ስሜት የፈጠራቸው ስሞች መሆናቸውን መጠራጠር አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያዊው በተለይም ዐማራው ማንነቱን ፈቅዶና ወዶ እያወለቀ እየጣለ የሌሎችን ማንነት እያጠለቀ መሆኑ ጉልሁ ማመላከቻ ለልጆቹ የሚያወጣላቸው ስሞች ናቸው፡፡

በአማርኛ ቋንቋ ሥርዓት ውስጥ በተጸውዖ ስም ላይ እየተደረቡ የሚገቡ ለሁለቱም ፆታዎች የሚያገለግሉ ድርብ ስሞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ድርብ ስሞች የማዕረግ፣የአክብሮትና የተዘምዶ ስሞች ይባላሉ፡፡ የማዕረግ ስሞች በቤተ እምነቶች ወይም በቤተ መንግሥት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ምሳሌ፡- ቤተእምነት፣ እጨጌ፣ጳጳስ፣ቆጶስ፣መላዕ-ከፀሐይ፣ግራ ጌታ፣ ሸህ፤ወዘተ፣፣ ቤተ መንግሥት፣አጼ፣እቴጌ፣ንጉሥ፣ራስ፣ቢትወደድ፣ደጃዝማች፣ፊታውራሪ፣ቀኛዝማች፣ግራዝማች፣ብላታ፤ እነዚህ ስሞች ግለሰቦች ለአገራቸው ባበረከቱት ተግባር፣ባሳዩት አርዓያነት ያለው ሥራ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካለት ተመርምሮ የሚሰጡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስሞቹ የክብር መጠሪያዎች በመሆናቸው ሌሎች የዚያ ስም ባለቤት ለመሆን የተሻለ ተግባር እንዲፈጽሙ አነቃቂ እንደነበሩ ግልጽ ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ የሚሰጡት የማዕረግ ስሞች በአብዛኛው አገርን ከጠላት በመከላከል ሂደት ውስጥ በተጫወቱት ሚናና በሰላም ጊዜም በአስተዳደር፣ በልማትና መሰል ተግባሮች አርኣያነት ያለው ተግባር ለተወጡ ግለሰቦች ነው፡፡ የቤተ እምነቶቹ ስሞች የሚሰጡት በሃይማኖቱ መንፈሳዊ ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ በዚያ ተግባር ላይ ያበረከቱት አስተዋጽዖ ተመዝኖ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ዛሬ በምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ የቤተ እምነቶቹ ስሞች በአገልግሎት ላይ ሲገኙ፣ ከመንግሥት በኩል የሚሰጡት ስሞች እንደ አድኃሪና ኋላ ቀር ነገር ተቆጥረው ተወግዘው የተወረወሩ ሆነዋል፡፡ ማዕረግተኞቹም በማረጋቸው ያፈሩ ይመስላል፣ ሊጠሩበት አይሹም፡፡ ለምሳሌ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ከዚህ ስማቸው ይልቅ “ታጋይ” የሚለው እንደሚመቻቸው ሲናገሩ የተደመጠበት ጊዜ አለ፡፡ “ታጋይ” መንገሻን ለዚህ ያበቃቸው የማዕረግ ስሙን ያገኙት በግል ባስመዘገቡት የመልካም አርኣያነት ተግባር ሳይሆን፣ከንጉሡ ጋር በመጋባታቸውና ከአጼ ዮሐንስም እወለዳለሁ ስለሚሉ፣በነዚህ ሁለት ምክንያቶች ያገኙት በመሆኑ ለስሙ ክብደት ከመስጠት ይልቅ አሳፍሯቸዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ግራዘመም አመለካከት አቀንቃኝ የሆነው ትውልድ ማዕረጎቹን የተረዳበት አቅጣጫ ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ባፈነገጠ መልኩ መሆኑ መዕረጎቹ የገዥና የተገዥ፣የአዛዥና የታዣዥ፣ የሀብታምና የድሀ ግንኙነት መገላጫዎች አድርጎ በመመልከቱ ትውልዱ ስሞቹን በጭፍን አወገዛቸው፡፡ ማዕረግተኞቹም አብዛኛዎቹ በአብዮቱ በግራ ቀኙ ኃይሎች ተመቱ፡፡ የቀሩትም እንደ ራስ መንገሻ ያሉት ዘመኑን ለመምሰል ሌላ ዘመነኛ ስም መረጡ፡፡ ትውልዱ ኅሊናው በቅኝ ተገዥነት ስሜት ሳያወቀው ባይገዛ ኖሮ፣ስሞቹ በልዩ ልዩ መስኮች አርኣያነት ያለው ተግባር ላከናወኑ ሰዎች መጠሪያ እንዲሆን ይፈቅድ ነበር፡፡ይህም ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ እንጂ ማፍዘዝ አይሆንም ነበር፡፡ እንግሊዞች ንጉሣዊ አመራርን አሻሻሉት፣ሕዝቡ በሚፈልገው ደረጃ አሳደጉት እንጂ፣ፈጽሞ አላወደሙትም፡፡ በዚህም የተነሳ “ሰር” የሚለውን የማዕረግ ስም ዛሬም በልዩ ልዩ መስኮች ለሰው ልጅ ጠቃሚ ሥራዎችን ለሠሩ ሰዎች መጠሪያና መከበሪያ እንዲሆን እያደረጉት ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን የራስን ማጥፋት፣የራስ ያልሆነን መካብና ማድመቅ በመሆኑ ሥራችን፣ እነዚህን አገራችን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስትገለገልባቸው የነበሩ የማዕረግ ስሞች እንዲጠፉ ፈርደንባቸዋል፡፡ ይህም ውጭ አምላኪነት ነው፡፡ ውጭ አምላኪነት ደግሞ ፈቅዶና ወዶ ቅኝ ተገዥነትን መለማመድ ነው፡፡

የተዘምዶ ስሞች የምንላቸው ልጆች ለወላጆቻቸው፣ታናናሾች ለታላላቅ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የሚሰጡዋቸው እንዲሁም በዕድሜ ታናሽ የሆኑ ሰዎች ታላላቆቻቸውን የሚጠሩባቸው ስሞች ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ልጆች ወላጆቻቸውን አባባ፣አባበይ፣ እማማ፣ እማመይ፣ታላላቆቻቸውን አይወይ፣ክንዴ፣ጋሻዬ፣መከታዬ፣ወንድም-ዓለም፣እዋዋ፣ወንድም-ጥላ፣ወንድም-ጋሼ፣ እታበባ፣እታለም፣እትሸት፣እንጎቻዬ፣እባባ እገሌ፣ጋሼ እገሌ ፣አይዋ እገሌ፣እማማ እገሊት፣እታታ እገሊት ወዘተ እያሉ መጥራት የቋንቋው ሥርዓትም ሆነ የሕዝቡ መልካም ባህል ነበር፡፡ በሌላም በኩል ወንዶች ለአቅመ አዳም፣ሴቶች ለአቅመ ሔዋን ከደረሱ በኋላ የሚጠሩበት የማዕረግ ስም አላቸው፡፡ ወንዶች “አቶ” ሲባሉ ሴቶች “ወይዘሮ” ላገባች፣ “ወይዘሪት” ላላገባች እያሉ መጠራት እንዳለባቸው ባህሉና ሥርዓቱ ያዛል፡፡

እነዚህ ስሞች ከማዕረግ መገለጫቸው በተጨማሪ በጠሪውና በተጠሪው በካከል እጅግ የቀረበ የሥጋ ዝምድና ያላቸው መሆኑን ከማመልከቱም በላይ፣ ባለማዕረግ ስሙ ታላቅ፣ በማዕረግ ስም ጠሪው ታናሽ መሆናቸውን ላድማጭ ግልጽ በሆነ መንገድ ያስረዳሉ፡፡ ከዝምድና መገለጫ ውጭ ያሉት የአክብሮት ስሞች በአክብሮት ስም ጠሪው በዕድሜ ታናሽ፣ ተጠሪው ታላቅ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ እንዴት ያለ የኢትዮጵያዊነት ልዩና ውብ መታወቂያ ነበር፡፡ ዳሩ ምንያደርጋል/ እነዚህ እንኳን ውጪ ተወልደው ባደጉ፣ በአገር ቤት በተወለዱትና ባደጉት ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በተወለደው ትውልድ ያላዳች አስገዳች ውጫዊ ኃይል በራስ ፍጹም ፈቃድ ስሞቹን ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ተድርጓል፡፡ አባትና እናትን እንደ ጓደኛ በስማቸው መጥራት እንደስልጣኔ ተቆጥሯል፡፡ አለያም እንደምዕራባዊኑ “ዳድ” ፣”ማም” ማለት የተዘወተረ ሆኗል፡፡ የኅሊና ቅኝ ተገዥነት ማለት ሌላ ምንም ሳይሆን፣የራስን ጥሩ ነገር ትቶ የሌሎችን ባህል፤እምነትና ማንነትን መላበስ ነው፡፡ ወላጆቹን በባህላችን የአክብሮት ስሞች የማይጠራ፣ታላላቅ ወንድሞቹንና እህቶቹን በኢትዮጵያዊ የአክብሮት ስም የማይጠራ ከማንነቱ የተፋታ ነው፡፡ ተጠሪዎችም በባህላችን የሚመጥናቸውን የማዕረግ ስም ነጥለው የሚጠሩዋቸውን ልጆቻቸውንም ሆነ ወንድም እህቶቻቸውን አዎንታዊ መልስ ከሰጡ የመጀመሪያዎቹ ባህል ጣሾችና ሥርዓት አፍራሾች መሆናቸውን ሊረዱት ይገባል፡፡ ለሁሉም ቀለም ቀመሱ ትውልድ ከኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ባህልና ማንነት ራሱን እያፋታ የመጣ መሆኑ ባህላችን የሚገኝበት ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ የኅሊናዊ ቅኝ ተገዝነት መገለጫ ነው፡፡

3. ቋንቋ፡- ቋንቋ መግባቢያ፣ሀሳብ መግለጫና መለዋወጫ የሆነ የድምፅ ሥርዓት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የተለያዩ ሕዝቦች የተለያዩ የድምፅ ሥርዓት የሚከተሉ ቋንቋዎች አሏቸው፡፡ ቋንቋ አዳጊም ጠፊም ነው፡፡ ቋንቋ የሚጠፋው በሥራ ላይ የሚያውለው ማኅበረሰብ በልዩ ልዩ ምክንያቶች አልገለገልበት ሲል ነው፡፡ ቋንቋ ዳባሪ የሚሆነውም የቋንቋው ባለቤት የሆነው ሕዝብ የኢኮኖሚ ደረጃ ማደግና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የሚፈመሠርተው ግንኙነት ሲሠፋ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በዓለማችን ላይ የጠፉ ቋንቋዎች የመኖራቸውን ያህል፣የዳበሩም እንዳሉም እንረዳለን፡፡ ዳበሩ ከምንላቸው ቋንቋዎች ውስጥ እንግሊዝኛ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ ነው፡፡ ጠፉ ከሚባሉት ውስጥ ላቲን አንዱ ነው፡፡በአገራችን ከጠፉ ቋንቋዎች ውስጥ ጋፋትኛ የመጀመሪያው ነው ፡፡ አንፃራዊ በሆነ መልኩ አድጓል ወይም ዳብሯል ከሚባሉት ውስጥ አማርኛ አንዱ ነው፡፡

አማርኛ ቋንቋ አድጓል ስንል በሚጠበቅበት ደረጃ እያደገነው ወይም አድጓል ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ቋንቋው በጽሑፍ ሥራ ላይ ከዋለ ከ320 ዓ.ም ጀምሮ ካስቆጠረው ዘመን አንፃር ሲመዘን ወደ ኋላ እንጂ፣ወደ ፊት ሄደ የሚባል አይደለም፡፡ ይኸም ሆኖ፣ትውልዱ በተጠናወተው ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት ስሜት ሳቢያ፣ አባቶቻችን ባቆዩልን መልኩ እንኳ ለልጆቻችን ለማስረከብ ከማንችልበት ደረጃ ላይ ነን፡፡ ቋንቋ ባህል በመሆኑ የሚከተላቸው የራሱ የሆኑ መንገዶችና ሥርዓቶች አሉት፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ቋንቋ ሰዎች ሰላምታ ሲለዋወጡ የሚከተሉት ሥርዓት አለ፡፡ ሰላምት ሰጪው ጤና ይስጥልኝ እንዴት አደራችሁ? ዋላች? አመሻችሁ ፣ሲል፣ ሰላምታ ተቀባዩ ወይም መላሹ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ ፣ደህና ነን ሲል መመለስ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይህ በዛሬው ትውልድ እንደነውር የሚቆጠር ሆኖ፣የሰላምታው ዘይቤ የምዕራባውያኑን መንገድ ተከትሏል፡፡ እዴት አደርክ? አደራችሁ ሲባል መልሱ ደህና ወይም መልሶ እንዴት አደርክ የሚል ነው ፡፡ ይህ የራስን ውብ ነገር መጣል ነው፡፡ በንግግር ወቅት በአማርኛ ጀምሮ በአማርኛ መጨረስ የሚታሰብ አልሆነም፡፡ በመሀሉ እንግሊዝኛ፣ፈረንሣይኛ፣ዐረብኛ፣ ወዘተ ጣልቃ ማግባት የዐዋቂነት ምልክት እንደሆነ መቆጠር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በሌላም በኩል የአማርኛ እናት ግዕዝ መሆኑ እየታወቀ ግዕዝን እንድንማር ባለመደረጉ፣እኛም ራሳችን ለማስተማርና ለመማር ባለመትጋታችን ዘመኑ ለሚፈጥራቸው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠሪያ የሚሆኑ ቃሎች ከአማርኛ ስናጣ፣አማርኛን መውቀስና የውጭ ቋንቋዎችን ማግነን የራስን ካለማወቅ የተፈጠረን ችግር፣የቋንቋው ችግር አድርጎ ማቅረብ የራስን ከመናቅ የመነጨ ውጭ አደርነት ስሜት የፈጠረው መሆኑን መጠራጠር አይቻልም፡፡

ትውልዱ ግራ ዘመም ርዕዮት በመከተሉ ሳቢያ፣የተለያዩ ግንኙነቶች መገለጫ የሆኑ ስያሜዎቸን “ ገዥ መደቦች ወይም ብሔረሰቦች” እንዳዎጡዋቸው በመቁጠር ከንግግር ዘይቤ ውጭ እንዲሆኑ ሆኗል፡፡ ምሳሌ “አዝማሪ”፤ ይህ ቃል ትርጉሙ አዘመረ አመሰገነ የሚል ሲሆን፣ትርጉሙን በሚገባ ካለማወቅ የሙያ ማንቋሸሻ እንደሆነ ተቆጥሮ “ አርቲስት” በሚል የውጭ ቃል እንዲተካ ተደርጓ፡፡በምዕራቡ አገር ጢሰኛ፣ገባር የሚሉት ቃሎች ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቤቶችን ፣መሬቶችን የሚከራዩ ሰዎች የሚጠሩበት የተከራይና አከራይ ግንኙነት መገለጫዎች በመሆን በሥራ ላይ ውለው እናያለን፡፡ እነዚህ ቃሎች በኢትዮጵያችን የጭቆና መገለጫዎች እንደሆኑ ተቆጥረው ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰል ሌሎችም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ቋንቋው እንዳያድግ ፍላጎት ባላቸው ክፍሎች ስልታዊ በሆነ መንገድ የአማርኛ ቋንቋ እንዲጠፋ የሚሠራው የቤት ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ ዛሬ ወያኔ በዘረጋው የትምህርት ፖሊሲ በተዘጋጁ የማስተማሪያ መጽሐፍቶች ፊደሎች ካለቦታቸው ከመግባታቸው በላይ ፣ቃሎቹን በሚገባ የሚገልጹ የግዕዝና የአመርኛ ቃሎች እያሉ ሆን ተብሎ እንግሊዝኛ ወይም ትግርኛ ቃሎች ከአማርኛ ጋር እንዲዳቀሉ ተደርጓል፡፡

አባቶቻችን ስድስት ሀ፣ሃ፣ ሐ፣ሓ ፣ኀ ፣ኃ፣ሁለት ሰ ፣ ሠ ፣ሁለት ጸ፣ ፀ ፣አራት አ፣ኣ፣ ዐ፣ዓ ፣ ፊደሎች ድምፅ የቀረጹት የተለያየ ድምፅና ትርጉም ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡ ለምሳሌ ሀብት፣ሃብት፣ ሐብት፣ሓብት፣ኀብት፣ኃብት ተብለው በተገቢው ድምፅ የተገለጠውን ምረጥ ብንባል ትክክለኛው መልስ በሀሌታው “ሀ” የተጻፈው ነው፡፡ የቀሩት በድምፅና በትርጉም የተለያዩ ናቸው፡፡ ሐመር፣ሐረግ ሕዝብ፣ የሚሉት ቃሎች በሌሎች የሀ ድምፅ እንዳላቸው በሚታወቁት ፊደሎች ቢጻፉ ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ሠራ፣ሥራ፣ንጉሥ፣ ንግሥት ወዘተ የሚሉ ቃሎች በሌላ ሰ ድምፅ ባላቸው በሚመስሉ ፊደሎች ብንጽፋቸው ስሕትት ነው፡፡ ኃይል፣ኃይሉ፣ኅብረት፣ማኅበር፣ ቤሎች የሀ ድምጽ ያላቸው ፊደሎች ቢጻፉ ስሕተት ነው፡፡ በአጠቃላይ ለፊደሎቻችን የሚወክላቸውን ድምፅ በሚገባ አለማወቅ በማይወክሉበት ቦታ ፊደሎችን እያስገባን የቋንቋውን ሥርዓትና አጠቃቀም ከማዛባት አልፎ እያጠፋነው መሆኑን ትውልዱ የተገነዘበ አይመስልም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሀ፣ ሃ ፣ሐ፣ ሓ፣ ኀ፣ ኃ፣ ኻ ፣ህ፣ ሕ፣ ኅ፣ ኽ ፣ ወ ፣ዎ፣ ዉ ፣ ው፣ ዪ ፣ይ ቸ፣ ቼ፣አ፣ ኣ ፣ ዐ፣ዓ፣ ሸ፣ ሼ ፣ ዠ ፣ዤ፣ጀ ፣ ጄ፣ጨ ፣ጬ ወዘተ የሚሉትን ድምፆች ልዩነት በሚገባ ባለማወቅ በማይወከወሉበት ቦታ እያስገባናቸው የቋንቋው ሥርዓት እንዲፋለስ እየተደረገ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህም ሂዶ ሂዶ መዳረሻው ራስን ለቅኝ ተገዥነት ማመቻቸት መሆኑ የተገለጠልን አይመስልም፡፡ የአማርኛን ቋንቋ ድምፆች በሚገባ ለማወቅ ባለመቻላችን፣ ልናውቅም ጥረት ባለማድረጋችን ፊደሎች እንደበዙና አንዳንዶቹም የተደጋገሙ ናቸው በማለት ምትክ የሌላቸውን ቅርሶቻችን እንዲጠፉ እያደረግን ነው፡፡ ቃሎች በሚመጥኑአቸው ድምፆች ፊደሎች አለመጻፍ የድምፅ ልዩነት ብቻ ሳይሆን፣የትርጉምም ለውጥ አላቸው፡፡ በሌላም በኩል ተገቢዎቹን ፊደሎች እንዲጠፉ ፈረድንባቸው ማለት ነው፡፡ ይህም የራስን መጣል፣የሌሎችን ማንጠልጠል ነው፡፡

በቋንቋ ረገድ የራሳችን እየጣልን የኛ ያልሆነን የማንጠልጠላችን ሁኔታ ጎልቶ የሚታየው በሕፃንነታቸው ከአገር የወጡና ውጭ የተወለዱ ልጆች የወላጆቻቸውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲያውቁ አለመደረጉ ነው፡፡ ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ከተሰዳጁ ኢትዮጵያዊም ውስጥ በርካታውን ቁጥር የያዘው የዐማራው ነገድ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ልጆቹን የማንነታቸው ቋሚ መገለጫ የሆነውን ቋንቋቸውን እዲያውቁ ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋ ባለማወቃቸው፣ወላጆችም ልጆቻቸው የሚያውቁትን የነርሱ ያልሆነ ቋንቋ ስለማያውቁ በቤት ውስጥ የመግባባት ችግር እንዳለ ጎልቶ መነገር ጀምሯል፡፡ ወላጆች ላሉበት አካባቢና ቋንቋ ባይተዋሮች በመሆናቸው የልጆቻቸውን ቤት ሥራ ተከታትሎ ለማሠራት ባለመቻላቸው ወላጅና ተወላጅ “ፈረንጅና አበሻ” ለመባባል በቅተዋል፡፡ ከዚህ የባሰ ውርደትና ሞት የት አለ?

ልጆቻችን የአገራቸውን ቋንቋ እንዲያውቁ አለመደረጉም ወጥተው እንዲቀሩ፣ከማንነታቸው እንዲፋቱ፣ከኅሊና ቅኝ ተገዥነት በባሰ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገው መሆኑ በውል የተጤነ አይመስልም፡፡ በዓለም ላይ እንደጨው ተዘርተው ከሁለት ሺህ ዘመን በላይ የኖሩት እስራኤላውያን ቋንቋቸውንና ሃይማኖታቸውን ፈጽሞ አላጠፉም፡፡ እንዳውም በስደት ዓለም አዳበሩት፡፡ ዐማራው ምን እንደነካው አይታወቅም ከእሱነቱ አልፎ፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ፣የጥቁር ሕዝብ መመኪያ የሆነውን የአፍሪካ ብቸኛ የጽሁፍ ቋንቋ ባለቤት የሆነውን የዐማርኛ ቋንቋ እንደዘበት ተመልክቶ እዲጠፋ የፈረደበት ይመስላል፡፡ “ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ፣ ባለዕዳ አይቀበለውም” ነውና እኛ ለልጆቻችን ለማውረስ የተጠየፍነውን ቋንቋ ማን ሊወርስልን፣ሊያሳድግልንና ሊያዳብርልን እንሻለን? ለአማርኛ ከዐማራው ነገድ ሌላ ማን ባለቤት እንዲሆን ይጠበቃል? ቋንቋችን ለመጠበቅና ለማዳበር አለመትጋታችን የኅሊና ቅኝ ተገዥነታችን ያሳደረብን ተፅዕኖ መሆኑን መጠራጠር አይቻልም፡፡

4. አገር የመጥላት ስሜት እየጎለበተ መምጣት፡- ማንም ሰው አገሩን ይወዳል፡፡ ይህ አጠቃላይ አገላለጽ ነው፡፡ አገራቸውን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚጠሉ መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ካለባት የመልካም አስተዳደር ዕጦት በላይ፣ ታዳጊ አገር በመሆኗ ለዜጎቿ የዕለት ተዕለት ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በብዛትና በጥራት የምታቀርብ አይደለችም፡፡ የየብስ፣የባሕርና የአየር መጓጓዣ እንደፈለጉት አይገኝም፡፡ ቴሌቪዥን፣ማቀዝቀዣ( ፍሪጂ)፣አውቶሞቢል፣ የቤት ውስጥ መጸዳጃ፣ ሶፋ፣ ወንበር ጠረጴዛ፣ የአካል ንጽሕና መጠበቂያ ሙቅና ቀዝቃዛ ውኃ በቤት ውስጥ መኖር ለሰው ልጆች እንደመሠረታዊ አስፈላጊ ነገሮች የሚታዩ ሳይሆን፣ የሀብት መገለጫ፣ያላቸው ሰዎች ብቻ ሆነው የሚታዩ በመሆኑ ለአብዛኛው ሰው እንደቅንጦት የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ “ተድራ ብትመለስ የውኃው መንገድ ጠፋት” ዓይነት የሆነባቸው ሰዎች አውሮፓና አሜሪካ ደርሰው ወይም ኑረው ሲመለሱ በውጭ ያዩትን የመገናኛና የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በፈለጉት መጠን አለማግኘት አገራቸውን ጠልተው እንዲመለሱ ይሆናሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ወደ ገጠር ጎራ ካሉ አቧራው፣ቁንጫው፣ትኋኑና የመንገዱ ውጣውረድ በሚፈጥርባቸው የተለየ ስሜት የተነሳ ዳግም ወደ አገራቸው ላለመመለስ ምለው የሚመጡ አያሌዎች እንደሆኑ በየአጋጣሚው የምንሰማው ሐቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ሁለመናቸው ለውጭው ኑሮ የተገዛ መሆኑን ያሳይል፡፡ ሁኔታውን ለመለወጥ ከእኔ ምን ይጠበቃል ብሎ የተሻለ ነገር ለመሥራት፣ቴከኖሎጂ ለማሸጋገር በመትጋት፣ የራስን ድርሻ ተወጥቶ አገርን ሌሎች ከደረሱበት ደረጃ ለማድረስ የሚቻለውን ሁሉ በግልና በተናጠል ከመሥራት ይልቅ፣ የራስን ጠልቶ አያሳየኝ ብሎ ምሎ መመለስ ምን ይባላል/ይህን አቋምና አመለካከት የኅሊና ቅኝ ተገዥነት ካልሆነ ሌላ ምን ልንለው እንችላለን፡፡

5. ስደት ናፋቂነት፡- “ሞት በእንቅልፍ ይለመዳል” እነዲሉ ሆኖብን፣ኢትዮጵያውያን በመሣሪያ ኃይል የፖለቲካ ሥልጣን በጨበጡ ቡድኖች በተከታታይ በተፈጸመብንና በሚፈጸምብን የአፈናና ረገጣ አገዛዞች ስደትን የሞት ያህል እየተለማመድነው መጥተና ፡፡ በግልጽ እነደሚታወቀው፣ አንድ ሰው ከተወለደበትና ካደገበት አካባቢ የሚሰደደው ለሕይዎቱ ቀጣይነት አስጊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው፡፡ እነዚህ የሕይዎት አስጊ ሁኔታዎች ከፖለቲካ አቋም፣ከሃይማኖት፣ከነገድና ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ መንገድ ልዩነቶች ሲፈጠሩና አለመግባባት ላይ ሲደረስ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድርቅ፣በአንበጣ ወረራ፣ በመሬት መንሸራተትና በጦርነት ምክንያቶች በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ፣ የሰሜኑ ወደ ደቡብ፣የደቡቡ ወደ ሰሜን፣የምሥራቁ ወደ ምዕራብ፣የምዕራቡ ወደ ምሥራቅ በመፍለስ እንደኖረና ይህም ለአንድነቱ መሠረት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የአገር ውስጥ ፍልሰት የባህል፣የቋንቋና የሃይማኖት መወራረስን በመፍጠር ሕዝቡ የአካባቢያዊ ልዩነቶችን ግድግዳ በመሰባበር፣ኢትዮጵያዊ የሆነ የወል ማንነትን እንዲገነባ እንዳደረገው ግልጽ ነው፡፡ በግልጽ ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣የአገር ቤቱ ፍልሰት፣የጠነከረ ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ፣ ሃይማኖት፣ባህልና ቋንቋ ያላቸው በሄዱበት አካባቢ ነዋሪ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይዘነጋም፡፡ ተፅዕኖው ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ ስለነበር የነገዶች ልዩ መታወቂያ የሆነው ቋንቋቸው ተጠብቆ እንዲዘልቅ ሆኗል፡፡

እስከቅርብ ዘመን ድረስ አገርን ጥሎ ወደ ባዕድ አገር መሰደድ ለኢትዮጵያዊያን የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ትውልዱ የስደትን ሕይዎት እየተለማመደው የመጣው ከአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ትግል ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ የስደትንም ሕይዎት ለትውልዱ ያስተማሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከነቤተሰባቸው መሣፍንቱንና መኳንንት የሚባሉትን ይዘው አውሮፓ መግባትና መኖር ጋር ተያያዞ ነው፡፡ “እንደንጉሡ አጎንብሱ” ወይም “ግዝ እንደንጉሡ አውድማ እንደ አግማሱ” ይሉ ሆኖ፣ ከዚንያ ዘመን ጀምሮ ትውልዱ ስደትን የሕይዎት ማቆያ አማራጭ መንገድ አድርጎ ወሰደው፡፡ በማከታተልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ 1948 የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ባጸደቀበት ወቅት አንድ ሰው ወይም ቡድን በዘሩ፣በሃይማኖቱ እና በሚያራምደው የፖለቲካ አቋም የተነሳ፣መሳደድ፣መታሰርና መገደል የሚደርስበት መሆኑ ከታወቀና ይህም ከተረጋገጠ ወደ ሁለተኛ አገር ሂዶ የመኖር መብት እንዳለው ያወጣው ሕግ የስደተኝነትን መንፈስ በሕዝቦች ላይ እንዳሳደረ እንገነዘባለን፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ከንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻዎቹ ሁለት ዐሥረተ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን “የመደብና የብሔር ጭቆና” ተፈጽሞብናል፣ለዲሞክራሲ ቆመናል የሚሉ ወገኖች በአገዛዙ ሊፈጸምብን ይችላል የሚሉትን እስራትና እንግልት በመፍራት መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡
በዘመነ አብዮት ትውልዱ በየፊናው ተደራጅቶ ባካሄደው የፖለቲካ ሥልጣን ሽሚያ በርካታ ዜጎች ለሞትና ለእስራት መዳረጋቸው ይታወቃል፡፡ አገዛዙ በሥልጣን ተቃዋሚዎቹና በተገንጣይ ቡድኖች ላይ በወሰደው መራር ርምጃ አያሌ ሰዎች ስደትን እንዲመርጡ እንዳደረጋቸው ግልጽ ነው፡፡ ስደቱ በተከታዩም ብሔርተኛው አገዛዝ በከፋ መልኩ ቀጠለ፡፡ በዘመን ደርግና በዘመነ ወያኔ የሕዝቡ ስደት መሠረት ያደረገው በሚከተለው ፖለቲካዊ አቋም፣ሃይማኖት፣ዘር ወዘተ ከሚመነጭ ግድያና አስራት ፍራቻ ብቻ አይደለም፡፡ የተሻለ ሕይዎት ለመኖር ከመነጨ ፍላጎትም ስደትን የመረጠው ወገን ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ የዚህ ፍላጎት ምንጩም የአገሪቱ ሰላም አስተማማኝ አለመሆን፣ የሥራ ዋስትን አለማግኘት፣የግል ሀብት ተገቢ የሆነ ሕጋዊ ጥበቃ አለማግኘት፣ሥራ በችሎታ ሳይሆን፣ በፖለቲካ ሽርክናና በዘር ላይ መመሥረት ወዘተ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ፣ ፖለቲካዊ ሁኔታውን መነሻ በማድረግ በልዩ ልዩ መንገዶች ሕዝቡ መሰደድን ሥራዬ ብሎ ተያያዘው፡፡ ለዚህም ዋናው ተጠቃሽ ምክንያት ቀድመው የተሰደዱ ሰዎች የግልና የቤተሰብ ሕይዎት በአገር ቤት ከሚኖሩ ጥሩ ነዋሪ ከሚባሉ ሰዎች የተሻለ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በሁለተኛና በሦስተኛ አገር ጥገኝነት ለመጠየቅም ባገር ቤት ያለው የዘር ፖለቲካና በሕዝቡ ላይ የሚፈጸሙ ኢ-ሰባዊ ድርጊቶች ተባብሰው መቀጠል ከፖለቲካ ጋር ምንም ዓነት ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ለሚያቀርቡት “የመብታችን ተገፈፍን ጥያቄ” ተቀባይነት እንዲኖረው አስገደደ፡፡ ስለሆነም በዓለም አቀፍ ሕጉ መሠረት ወደ ፈለገው አገር መግባት ያቃተው ተሰዳጅ ወገን፣ከኢትዮጵያ ኬንያ፣ ከኬንያ ታንዛኒያ፣ከታንዛኒያ ሞዛምቢክ፣ ከሞዛምቢክ ደቡብ አፍሪካ፣ከደቡብ አፍሪካ ብራዚል፣ ከብረዚል ሜክሲኮ፣ከሜክሲኮ ዩ፣ኤስ.ኤ እያለ አያሌ ፈተናዎችንና ውጣውረዶችን አልፈው የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ቀላል አለመሆኑ በጉልህ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ውጣ ውረድ በሞላበት አስቸጋሪ የስደት ጉዞ በአራዊቶች ተበልተው፣በወባ ተነድፈው፣በልዩ ልዩ በሽታዎች ተይዘው ምኞታቸው ሳይሳካ ለሕልፈተ ሕይዎት የሚዳረጉት ቁጥር የት እየለሌ እንደሆነ በጉዞ ቀንቷቸው ከተመኙት አገር የደረሱ ሰዎች የሚናገሩት ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ከግብፅና ከሶማሊያ ተነስተው ወደ እስራኤልና የመን፣ ከሊቢያ ወደ ጣሊያንና ግሪክ ለመግባት የሚጥሩ፣ ኢትዮጵያኖች በባሕር ላይ በሚያደርጉት ጉዞ ፣ ጉዞው ሕጋዊ ካለመሆኑ የተነሳ ከሚደርስባቸው የመጓጓዣ ጫና፣ እንግልትና መሳቀቅ በላይ የሚጓጓዡበት ጀልባ እየሰጠመና እየተገለበጠ የዓሣ ቀለብ የሚሆኑት አያሌዎች እንደሆኑ፣ የዓለም ብዡኃን መገናኛ መሣሪያዎች ዘወትር ለሕዝብ ጆሮ የሚያደርሱት ዜና ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ነኝ ባዩ ሕፃናትና ወጣት ሴቶችን ለባርነት የሚሸጥ ድርጅት አቋቁሞ ሕዝቡን ለባርነት፣ለኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት አመቻችቶታል፡፡ ወደ ዐረቡ ዓለም በአገራቸው ሠርተው የመኖር ዕድሉን አጥተው በግልና በመንግሥት የሚሄዱት ሴቶች እህቶቻችን ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ እነዚህ እህቶቻችን በዐረቡ ዓለም የሚገቡት ስማቸውን ለውጠው፣ሃይማኖታቸውን በልባቸው ይዘው፣በአፋቸው ግን ቀይረው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህስ በላይ የኅሊና ቅኝ ተገዥነት በምን ይገለጣል?
እኛ ኢትዮጵያውያን ለኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት እጃችን የሰጠን መሆኑ ማሳያው፣በሚደርሰብን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖች ባስከተለብን ሁለንተናዊ ጫና ብቻ የተሰደድን አለመሆኑን ስንገነዘብ ነው፡፡ እነዚህ ጫናዎች የደረሱባቸው ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነትን ወደው ወይም ፈቅደው ሳይሆን፣ ተገደው፣ ከቁጥጥራቸው ውጭ በሆነ ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን ስለሚገነዘቡ፣ቅኝ ተገዥነቱ በኅሊናቸው ውስጥ ቦታ አይኖረውም፡፡ በመሆኑም የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ ዕሴቶቻቸውን የኔ ብለው ይጠብቋቸዋል፤ይንከባከቧቸውል፤ያስተዋውቋቸዋልም፡፡ በሌሎች ምክንያቶች ማለትም በኢኮኖሚ ጥቅሞችና ለተሻለ ሕይዎት ሲሉ የተሰደዱ ግን ፣ቀድመው ውጪ ያዩ በመሆኑ የነርሱነት መገለጫ የሆኑ ዕሴቶቻቸውን ፈጥነው ከኅሊናቸው መፋቅ ብቻ ሳይሆን፣ በጥላቻና በንቀት ስለሚመለከቷቸው ያፍሩባቸዋል፤ አይገለገሉባቸውም፤እንዲታወቁም አይፈልጉም፡፡ ከሁሉም በላይ ወላጆች በፈለጉ ጊዜ ከፈለጉት አገር ለመውጣትና ለመግባት እንዲያም ሲል ለመኖር የሚፈልጉ ሰዎች፣ በአገራቸው ምንም ዓይነት የመኖር ችግር ሳይገጥማቸው ሚስቶቻቸው ሊወልዱ ጥቂት ሳምንታት ሲቀራቸው፣ አሜሪካ፣ካናዳ፣ጀርመን ወይም ሌላ አገር ሂደው እንዲወልዱና ሕፃናቱ የዚያ አገር ዜግነት እንዲኖራቸው የማድረጉ ተግባር በስፋት የሚታይ ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ኅሊናዊ ቅኝ ተገዥነት መጠኑን ያለፈ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ስሜትና እምነት ባንዳዊ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የተሻለ ገቢ ካላቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ልጆቻቸው የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ያላቸው አይደሉም፡፡ ይህም ሕዝቡ ትናንት በዘመነ ቅኝ አገዛዝ ወቅት በአካል ቅኝ ያልተገዛው ኢትዮጵያዊ በሚከተሉት ሁለት ተያያዥና ተደጋጋፊ ምክንያቶች ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት እንደተዳረገ እናያለን፡፡
አንድ ሕዝብ ትውልድ አገሩን ትቶ ወደማያውቀው አገር የሚሰደደው ሁለት ተያያዥና ተደጋጋፊ የሆኑ ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ነው፡፡ የመጀመሪያው በአገሩ በሰላም ሠርቶ የመኖር ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ማኅበራዊና ባህላዊ መብተና ነፃነቶቹን ሲገፈፍና ሲነጠቅ፣ በሕይዎት ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ ሲጣበብበት ነው፡፡ ሁለተኛው ከአገሩ ወጥቶ ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ መኖሩ አስተማማኝ ሲሆን ናቸው፡፡ እነዚህም ከውስጥ አስወጪ ገፊ ኃይል እና ከውጪ ተቀባይ ሳቢ ኃይል መኖር ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሕዝቡን በነበረ መልኩ እንዲኖር የፈቀደ አልሆነም፡፡ ትውልዱ በፖለቲካዊ ፍልስፍና፣በነገድ፣ በሃይማኖት፣በሥልጣን አያያዝ ተከፋፍሎ አገሪቱን የብጥብጥ ምድር አደረጋት፡፡ ሥልጣን የያዙ ቡድኖች ተቀናቃኛችን ነው ያሉትን ግለሰብና ቡድን ያላንዳች ርኅራኄ ገደሉ፣አሰሩ፣አሰቃዩ፤ የፖለቲካ ትርምሱ ማኅበራዊ ሰላምን በእጅጉ በማመሱ፣በሰላም ወጥቶ ለመግባት፣ሠርቶ ለማምረት፣ወልዶ ለመሳም፣አሳድጎ ለመዳር አላስቻለም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በስፋትና በተከታታይ መታየት ሕዝቡን አማራጭ የመኖሪያ አካባቢን እንዲያማትር ግድ አለው፡፡ ባደረገው የአማራጪ መኖሪያ ፍለጋም ለማስተማር ቀይ ሳንቲም ሳያወጡ በተማረ የሰው ጉልበት ያልተማረ ሰው ሊሠራቸው የሚችሉ ሥራዎችን በጥራት፣በቅልጥፍናና ሥጋት በሚፈጥረው ጥንቃቄ ኃላፊነቱን የሚወጣ ፣ያወቀ፣ግን በርካሽ የጉልበት ዋጋ ጥራት ያለው ሥራ የሚሠራ የሰው ኃይል የሚፈልጉ አገሮች ቁጥር መበራከት፤(አሜሪካ፣ካናዳ፣አውትራሊያ፣ጀርመን፣ኖርዌ፣ስውዲን) የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነትን ለማጥፋት የረጅም ጊዜ ዕቅድ የነበራቸው አገሮች የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ትውልዱን ከኢትዮጵያዊነት ስሜትና እምነት ለማፋታት ባለቸው የቆየ ዓላማ መሠረት፣ ስደት ፈላጊዎችን በገፍ የመቀበል ፍላጎት አሳዩ፡፡ ይህም የሕይዎት ማቆያ ፣የተሻለ ኑሮ መምራት አማራጪ ይፈልግ ለነበረው ሰው እንደመልካም አጋጣሚ ቆጥሮ የተቸገረውም ያልተቸገረውም ለስደት ተሰለፈ፡፡ ፣ስደትንም አማራጭ የሌለው ተመራጭ አድርጎ እንዲይዘው አደረገው፡፡ በነዚህ የውስጥና የውጪ ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት ኢትዮጵያዊው የተሻለ ኑሮና ሰላም የነበራቸው ሁሉ ቋሚ ንብረቶቻቸውን በአልባሌ ዋጋ እየሸጡ ተሰደዱ፡፡ ምዕራባውያኑ በተለይም ዩ.ኤስ.ኤ በራሱ ፍላጎት የሚሰደደው ሕዝብ የሚፈልገውን ያህል የተማረ የሰው ኃይል ሊያስገኝላት ባለመቻሉ፣ዲ.ቪ የሚል ፕሮግራም በመዘርጋት አያሌ የሦስተኛው ዓለም ሕዝቦችን የተማረ የሰው ኃይል መሳቡ ይታወቃል፡፡ በዚህ ፕሮግራም የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህም ወዶና ፈቅዶ ራስን ለኅሊና ቅኝ ተገዥነት ማዋል አለመሆኑን በምን መልክ ማሳመን ይቻላል?
በዚያም አልን በዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን በአካል ቅኝ ሳንገዛ፣የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች መሆናችንን ልናስተባብልበት የምንችልበት ማስረጃ የለም፡፡ የሚያዋጣው የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች አልሆንም ብሎ በመሸምጠጥ ሳይሆን፣ለዚህ የዳረጉንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ዐውቀን ከነዚያ ሁኔታዎች ልንወጣ የምንችልባቸውን መንገዶች ማመቻቸት ነው፡፡ እንደ ነገድ ሳይሆን፣እንደ አገር በአንድነት ማሰብና በአንድነት መቆም ስንችል ነው፡፡ የተጫነንን ከማንነት የመፋታት አባዜ ከላያችን ላይ አራግፈን ጥለን አኩሪው ማንነታችን ስንላበስ ነው፡፡ ታሪካችን ፣ባህላችን፣ቋንቋችን፣ በአጠቃላይ እኛነታችን ዐውቀን ለማንነታችን ዳብሮ መቀጥል ስንቆም፣ለዚህም ተገቢ የሆነውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ስንሆን ብቻ ነው፡፡

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop