May 19, 2013
9 mins read

ስድስት:- ቃል ኪዳን፤ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ (ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

መስፍን ወልደ ማርያም
መጋቢት 2005

እንግዲህ ኢሳት በነገረኛነትም ሆነ በጠመንጃ-ያዥነት በኩል ከሎሌነት ጠባይ ጋር የተያያዘውን ኢትዮጵያውያን ያለንን አጉል ባህል ሁሉ እየነቀስን እየጣልን በዘመናዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ መሠረት ለመጣል ዋና መሣሪያ ሊሆነን ይችላል ብሎ ማመን መነሻ ይሆናል፤ ይህ እምነት ከሌለ የእምቧይ ካብ ነው፤ ይህ እምነት ራስን ማጽዳትንም ይጠይቃል።

ማክሸፍ እንደምንችልበት ከማመን እንጀምር፤ ስለዚህም ኢሳት ሊከሽፍ የሚችልበትን እያንዳንዱን መንገድ ማጥናትና በቅድሚያ ፈውሱን ማዘጋጀት የሚጠቅም ይመስለኛል፤ ይህንን ጉዳይ በትጋት ለመከታተል የኢሳትን አማራጭ የማይገኝለት የአገር ጥቅም በእውነትና በትክክል መገንዘብ ያሻል፤ ዘመን-አመጣሽ ነገር ብቻ አድርጎ መመልከቱ ለወረት ይዳርገዋል፤ ወረትን ማክሸፍ ቀላል ነው፤ ከከሸፈ በኋላ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በጣም ከባድ ሥራን ይጠይቃል፤ ስለዚህ ከወዲሁ ኢሳት ጠንካራ መሠረት ላይ እንዲተከል የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ዘለቄታ እንዲኖረው ማረጋገጫ ይሆናል።

የኢሳት መክሸፍ የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨልማል፤ አንፈራጥጠው ከላይ ቤት እታች ቤት እየቀላወጡ አካላቸውን፣ አእምሮአቸውንና መንፈሳቸውን የሚያባልጉ ሰዎችን ያበራክታል፤ የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የጸዳውን ከአደፈው፣ ሳይለዩ ለሚያወሩት ደካሞች ሜዳውን ያሰፋላቸዋል፤ የወያኔ/ኢሕአዴግን ፍርሃት ወደመርበድበድ ይለውጠዋል፤ የጦርነት ጥሩምባ ለሚነፉትም ሜዳውን እያሳየ  የቀረርቶ በር ይከፍትላቸዋል፤ ይህ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምንና ስምምነትን፣ እድገትንና ብልጽግናን፣ ኩራትንና ክብርን አያስገኝም።

ንስሐ ለመግባት ወኔ ለሌላቸው፣ በሠሩት ጥፋት አገርን ወይም ወገንን በመበደላቸው ዛሬም ለመኩራራት ለሚፈልጉት፣ አርበኛውንና ባንዳውን ባንድ ሚዛን አስቀምጠው ለሚተቹት፣ የኢትዮጵያውያንን ሰውነት አራክሰው ጊዜያዊ ጥቅማቸውን ለሚያከማቹ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በተንኮል እየመነዘሩ የሥልጣን መሰላል ለሚያበጁ ሁሉ ፊት-ለፊት ቆሞ ለሚጋፈጣቸው ኢሳት መድረክ ይሆናል፤ የኢሳት ዋና ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው፤ ይህንን ተግባር ለመፈጸም ኢሳት የኢትዮጵያ፤ ኢሳት የኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲሆን መንገዱን እንጥረግ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በባለቤትነት የሚመራውና የሚያካሂደው እናድርገው፤ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢሳት ላይ ያለው መብት ነው ከተባለ፣ ግዴታውንም አብሮ መቀበል ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ ግዴታውን በቃል ኪዳን መቋጨት ከቻለ ኢሳት ከቀፈፋና ለመክሸፍ ይድናል።

የእኔ ምኞት ኢሳት በኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳን ተገንብቶ በሕገ ኀልዮት እየተመራ አዲስ ዓላማ፣ አዲስ የአሠራር ዘዴ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ጉድለቶችን ሁሉ አውቆ በጥንቃቄ እየነቀሰ አዲስ የመተማመንና የመተባበር ባህል ይፈጥራል የሚል ነው፤ (እኔ ቃል ኪዳን የምለው ሁለት ቁም-ነገሮችን የያዘ ነው፤ በአንድ በኩል እውነትን አለመፍራት (ወይም በጥሩ መልኩ ለእውነት መቆም፣) በሌላ በኩል ለአንድ የጋራ ዓላማ የራስን ግዴታ ሳያስተጓጕሉ ለመወጣት በቆራጥነት መቆም፤ ስንት ልጆች አሉህ ተብሎ ሲጠየቅ ሁለት ወይም ሦስት እያለ አጥር ላይ ተንጠልጥሎ የሚመልስ ለቃል ኪዳን አይበቃም፤) ከሩቅ እንደማየው ጥቂት ሰዎች ኢሳትን በቃል ኪዳን ተይዘው ሲጥሩ አብዛኛው ደግሞ በአጋጣሚ እንደተመቸውና እንደፈለገ የተቻለውን የሚያደርግ ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን የሌለው ነው፤ ከተሳሳትሁ ደስ ይለኛል፤ አስተያየቴ ትክክል ከሆነ ኢሳት አይዘልቅም፤ መክሸፍ ዕጣ-ፋንታው ይሆናል።

ዓላማውን ሳይመታ እንዳይከሽፍ ኢሳት በቃል ኪዳን መታሰር አለበት፤ እንዴት? ቢባል፣ አንድ ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ለኢሳት በአማካይ በወር አሥር ዶላር ለመስጠት ቃል ኪዳን ቢገቡና የየዓመቱን ግዴታቸውን በአንዴ ቢወጡ፣ በወር አሥር ሚልዮን ዶላር (በዓመት አንድ መቶ ሃያ ሚልዮን ዶላር) ኢሳትን  ኢትዮጵያዊነትን የሚያስከብር የሰላምና የፍቅር፣ የብልጽግናና የተስፋ መድረክ ሊያደርገው ይችል ነበር፤ አብዛኛዎቹ ችሎታው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለኢሳት የሚገቡት ቃል ኪዳን ለጥሬ ሥጋና ለመጠጥ የገቡትን ቃል ኪዳን ካላሸነፈ ታማኝ በየነን በያገሩ እየላከ በሚያደርገው ዓመታዊ ቀፈፋ ኢሳት ይገነባል ብዬ ለማመን ያሰቸግረኛል፤ በኢሰመጉ አይቼዋለሁ።

ቀፈፋ ወይም ልመና አንዱና ዋናው የባህል ሕመም ነው፤ እያንዳንዳችን ከዚህ ሕመም ለመዳን በራሳችን ላይ መዝመት የሚያስፈልገን ይመስለኛል፤ በተለይ በአገር ጉዳይ፣ በወገን ጉዳይ ማን ነው ለማኝ? ተለማኙስ ማን ነው? ስለአገሩና ስለወገኑ ችግር የማያውቅ አለ? ለማወቅ የማይፈልግ ይኖራል እንጂ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ችግር ገሀድ ነው፤ በአስከፊ መልኩ ለመረዳት የሚፈልግ በመረረ ቋንቋ የተጻፈውን የዶር. በድሉ ዋቅጅራን ሀገሬ ገበናሽ (ክፍል አንድ፣  ክፍል ሁለትና ክፍል ሦስትን)  ያንብብ።  አንብቦ ካላለቀሰ፣ አልቅሶ ‹‹ምን ላድርግ!›› የሚል ቁርጠኛነት ያላደረበት በዓመት አንድ ጊዜ በታማኝ ቀፈፋ አገሩንና ወገኑን መርዳት አይችልም፤ እምነቱ ካለ፣ ስሜቱ ካለ በገንዘብ የሚደረግ ማናቸውም እርዳታ የመጨረሻው፣ መናኛው ነው፤ መናኛ የሚያደርገው የገንዘቡ መብዛት ወይም ማነስ አይደለም፤ ለአገርና ለወገን ከዚያ በጣም የበለጠ የሚከፈል ዋጋ በመኖሩ ነው፤ አያቶቻችንና ቅምአያቶቻችን የከፈሉት ዋጋ በገንዘብ አይመነዘርም፤ እነሱ በሕይወታቸው ያስገኙልንንና እኛ በገንዘብ የሸጥነውን ኩራትና ክብር በገንዘብ ብቻ አናስመልሰውም፤ ቃል ኪዳን እንግባ!

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop