May 19, 2013
12 mins read

የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ርዕሠ አንቀጽ፡ የሙስናን ዛፍ ለማድረቅ ቅርንጫፉን ብቻ መቁረጥ በቂ አይሆንም

ፈረንጆች ታይታኒክ የተባለችውን ግዙፍ መርከብ የገለበጠውን ዓይነት ከባሕር በታች የተደበቀ ግግር በረዶ ‘ለአንዳንድ የማይታዩ ነገር ግን ግዙፍ የሆኑ’ ችግሮች ተምሳሌት አድርገው ይጠቀሙበታል።ከባሕሩ ውስጥ ብቅ ብሎ የሚታየው የበረዶ ጫፍ ሲያዩት ትንሽ ስለሚመስል ብዙዎችን ያሳስታል-ከሥሩ ያለውን ተራራ የሚያህል ግዙፍ የበረዶ ግግር ለመገመት አያስችልምና።ለዚህም ነው አንዳንድ ተገልጦ ያልታየ ነገር ግን በትንሹ ብቅ ያለ ችግርን “this is only the tip of the iceberg” (ይህ የግግር በረዶው ጫፍ ብቻ ነው) በማለት የሚገልጹት-ከሥሩ ቢታይ ሥር የሰደደና ሰፊ ነው ለማለት።
ሰሞኑን ከተራ ደላሎችና ትራንዚተሮች አንሥቶ እስከ ቱጃር ባለሀብቶችና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ድረስ የተዳረሰው የሙስና ቅሌት የብዙው ዜጋ የመወያያ ርእስ ሆኖ ሰንብቷል።ይህ የሰሞኑ ክስተት ብቻውን ግን የመጨረሻ ውጤት አይደለም።ይልቅስ ከባሕር በታች ገዝፎ እንደተደበቀው የግግሩ በረዶ ጫፍ ጥቂቱ ማሳያ ነው እንጂ።
መንግሥት ለረጅም ዘመን ሙስናን የመዋጋት ቁርጠኝነትም ቢያሳይም በዚያው ልክ ግን ችግሩ በአገራችን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አልደረሰም ሲል ኖሯል። አንዳንድ መረጃዎች ብቅ ሲሉም ችግሩ እንደሚወራው አይደለም፣ የተጋነነ ነው ሲል ተደምጧል። ይህን ሲል ቢቆይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሙስናን አፈጻጸም ረቂቅነትን እያባከነ ያለውን የሕዝብና የሀገር ንብረት ሲያስተውል ግን አሳሳቢነቱን አምኖ ለመቀበል ተገድዷል፡:
በአገራችን እየተስፋፋ የመጣውን ሙስና በተመለከተ ከመንግሥት አስቀድሞ የነቃው ሕዝቡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሙሰኞችን በተመለከተ ሕዝቡ “በማስረጃ ካልሆነ” እየተባለ ሐሳቡን የሚገልጽበት መድረክ ባያገኝም እርስ በርሱ መወያየቱ ግን አልቀረም፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት ወደላይ እየተተኮሰ የመጣውን የአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት አኗኗር በመመልከትም ሆነ ያካበቱትን ንብረት በመታዘብ ከጥርጣሬ ያለፈ ግንዛቤ ይዞ ነበር፡፡ ቢያንስ እነዚህ ሰዎች ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብና ሀብት ማካበታቸውን መጠርጠር ችሏልና።
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እስከ አሁን ድረስ በሙስና ባሕር ውስጥ ሲዋኙ የቆዩትን ትንንሾቹን ዓሣዎች እንጂ ዓሣ ነባሪዎቹን ለመያዝ ድፍረቱም፣ ፍላጎቱም አቅሙም የለውም እየተባለ ሲታማ ቆይቷል፡፡ በተለያዩ መድረኮችም ተጠይቋል። ለምሳሌም ኮሚሽኑ ባለፈው ማክሰኞ የሰሞኑን ሙስና በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ይኸው ጥያቄ ለኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን ተነሥቶላቸው ነበር። “እኛ ከግለሰቦች ጋር ሳይሆን ከወንጀሉ ጋር ነው ጉዳያችን። ሙስና ከፈጸመ ማንንም አንተውም። ሁሉንም ጥፋተኞች ለሕግ እናቀርባለን” ብለዋል።
ያም ሆኖ ‘የመንግሥትን ሌቦች’ በተፈለገው ሁኔታ ወደፍርድ አደባባይ ቶሎ ቶሎ ብቅ ሲሉ አይተናቸው አናውቅም። አንዳንድ ጊዜ ስለመንግሥት ሌቦች በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ መሰግሰግና አለአግባብ መበልፀግ አልፎ አልፎ በራሱ በመንግሥት ከሚነገረው ውጪ እነዚህ ‘ሌባ’ የተባሉት ሰዎች የት እንዳሉና የተነከሩበት የሙስና ባሕር ስፋትና ጥልቀትስ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአብዛኛው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሹሞች የሚፈፀሙትን የሙስና ድርጊቶች ተከታትሎ በማጋለጥና አጥፊዎች በማስቀጣት ረገድ የማይናቅ ሥራ ቢሠራም ትልልቆቹን ዓሣዎች ግን በተደጋጋሚ ጊዜ ሳይደፍራቸው ቆይቶ ነበር፡፡
አሁን ፀረ ሙስና ኮሚሽን የጀመረው ሙሰኞችን ወደሕግ የማቅረብ አካሄድ ይበልጥ ይግፋበት የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ ለዚህ የኮሚሽኑ እርምጃም ከመቀመጫችን ተነሥተን ተገቢውን ክብርና አድናቆት እንሰጣለን፡፡ ሙስናን መዋጋት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ሓላፊነት መሆኑን በመረዳት ለኮሚሽኑ ሥራ መቃናት የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ በስም ያልተገለጹ ዜጎችም በአድናቆት እናጨበጭባለን። ይህን በምንናገርበት አንደበታችንም እግረ መንገዳችንን እርማት የሚያሻውን የኮሚሽኑን አካሔድ ለመጠቆም እንሞክራለን፡፡
አንደኛ ነገር ኮሚሽኑ በአንድ መንግሥት መሥሪያ ቤትና በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በተመረጡ ተቋሞች ላይ ጊዜ ወስዶ ተመሳሳይ መረጃ የመሰብሰብ ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ውጤቱን በአንድ ላይ ይፋ ቢያደርግ የተሻለ ይሆን ነበር እንላለን፡፡ አሁን እንዳደረገው በአንድ ቦታ ላይ ማተኮሩ ለሌሎች የማንቂያ ደወል ሊሆናቸው ይችላል፡፡ በዚህም መረጃዎችን ለመደበቅ፣ ምስክሮች ሊሆኑ የሚችሉትን የዶክመንትና የሰው ማስረጃዎችን ደብዛ ለማጥፋት እንዲሁም በሙስና የሰበሰቡትን ሀብትና ንብረት በተለያዩ ዘዴዎች ለማሸሽ ጊዜ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
አሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት እልባት እስኪያገኝ ድረስ የሕዝቡም የኮሚሽኑም ትኩረት በእነሱ ላይ ይውልና ያልተጋለጡ ባለሥልጣናት ከሚታዩበት የግግር በረዶው ጫፍ ተነሥተው ወደ ጥልቁ ባሕር ለመግባትና ለመሰወር አመቺ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይችላል፡፡ ሁለት ዓመት ፈጀ የተባለው ክትትል እነዚህን 24 ሰዎች ብቻ ለመያዝ ከሆነ በርግጠኝነት ዘግይቷል። ክስ ከተመሰረተበት የሙስና ጉዳይ ተነካኪነት አንጻር ሲታይ ሌሎችም ባሕሩ የደበቃቸው ብዙዎች መኖራቸው አይቀርም።
ያም ሆኖ አሁን የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ የግግሩ በረዶ ጫፍ በባሕሩ ተሸፍኖ ሳይጠፋ በፊት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በሌላ አባባል የአንድ ሰሞን የሚዲያ ግርግር ከመሆን አልፎ ተከታታይ መሆን ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ ኮሚሽኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባ ውጤት ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ብሎ ቃል ከገባ ረዘም ያለ ጊዜ ቢሆንም ይህ እስከ አሁን ባለመፈፀሙ የትኛው የመንግሥት ባለሥልጣን ምን ያህል ሀብት እንዳለው በሕዝቡ ዘንድ ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡ ይህ የ30ሺህ ሰዎችን ሀብት መዝግቤያለሁ የሚለው የኮሚሽኑ ድክመት ነው። የባለሥልጣናት ሀብት በጊዜ ቢታወቅ ኖሮ ከሚታወቀው አቅማቸው በላይ ሲያካብቱ ሕዝብ አይቶ ዝም አይልም ነበር።
ሌላው ኮሚሽኑ የግሉን ዘርፍ ‘አያገባኝም’ ብሎ መተዉ አግባብ አይደለም እንላለን። እስከ አሁን ድረስ በሙስና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተከሰሱት የግል ባለሀብቶች ናቸው። ከየት እንዳመጡት ሳይታወቅ ድንገት ጣሪያ ላይ የሚወጡት የግል ባለሀብቶች ጀርባ ካልተጠና ወደፊትም ባለሥልጣናትን ማባለጋቸው፣ ሙስናውም ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም።
የሆነው ሆኖ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እስካሁን የሠራው ሥራ የሚያስመሰግነው ነው። የራሱን አቃቤ ሕግ በሙስና ከመክሰስ አንሥቶ ‘የመንግሥት ሌቦችን’ ጥሩ እያየ ነው። አሁንም የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሀብት በፍጥነት ለሕዝቡ ያሳውቅ፡፡ ካሁን በኋላም ጥረቱን በማጠናከር ከሕዝቡም ከሚዲያው ጋር ይበልጥ በመተባበር በሙስና ላይ የተጀመረውንና ጠብ…ጠብ የሚለውን ካፊያ ዘመቻ ወደ ጎርፍ ይለውጥ! ከግግር በረዶው ጫፍ ላይ የሚታዩትንም ሆነ ከባሕሩ ሥር የተደበቁትን ተጠርጣሪዎች ለማጋለጥና ለፍርድ ለማቅረብ ይበልጥ በተቀናጀ ሁኔታ ይነሳ! የሙስናውን ዛፍ ከቅርንጫፉ ብቻ ሳይሆን ከሥሩ ይቁረጥ!!

2 Comments

  1. I am happy that some of the corrupted are in jail but one thing is for sure those TPLF who crippled the countries economy and stole billions of dollar are still the one with absolute power in Ethiopia.They are thousands of them who became millioners over night.They hate Ethiopia and they fought with Shabia to make Ethiopia land locked and to liberate Tigray from Ethiopia and still are working on there case to create greater Tigray.They have not only stolen the countries wealth but they have taken a part of Wello,Afar and Gondar. They are the one who suppose to be in jail.Sebhat Nega,Seyum Mesfin,Abay tsehay,Arkebe,Samora.Tsadkan And The mother of corruption Azeb Mesfin and many more TPLFist who at least stolen 20 billion dollars.God will help us and pretty soon Ethiopia will be free from Ethnofasists.Long live Ethiopia and Humanity before ethnicity.Death for TPLF:

  2. who are after all these people who called themselves ” anti corruption commission and commissioners? are they really committed to fight back corruption .How can a corrupted expose the corrupted ? can the writer of this article can prove with evidence wherein the commission had seriously exposed a single person found convicted in real corruption ? we know number of people handpicked by woyane and thrown to jail on account of their political views,beliefs and ethnicity by branding them as corrupted.Now the woyane is blowing its trumpet as if committed to stamp out corruption when the big fishes and the big military brass are the ones playing the grand corruption game in the very face of the so called anti corruption commission which itself an instrument in conduit billion and billion of dollars to woyane hard cores like Melese ,abay tsehaye ,Seyoum Mesfen Azeb Mesfen (the mother of corruption)and many others have not been accounted for the last 22 years. Following the formation of the commission, the rate of corruption has surged dram atically since the commission granted permission to many of big sharks to freely loot and plunder .So what the big deal here for some people i see fully engaged in an exercise of extol of the woyane commission . It is a suicidal to woyane to let the commission unchecked when trying to dismantle the corruption institution set to trap those hodams and bandas born to serve as mental slave to woyane and its likes.Please dont misleaad us .”Anti -corruption commission is the political right hand of the woyane mafiosos.Nothing expected from the commission .

Comments are closed.

serawit fikre
Previous Story

የ’ልማታዊው አርቲስት’ ሠራዊት ፍቅሬ የኢቲቪ ፕሮግራም ታገደ

freedome
Next Story

በአካል ቅኝ ሳንገዛ፣ ለምን የኅሊና ቅኝ ተገዥዎች ሆን? – ከተክሌ የሻው

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop