February 15, 2013
13 mins read

ታገል ሰይፉ፡ ኢሕአዴግ ካምፕ ውስጥ ያደገው አውሬ

“ራሱን መከላከል የማይችል አብዮት እርባና የለውም”
ሌዋታን…ኢ. ህ. አ. ዴ. ግ. ካምፕ ውስጥ ያደገው አውሬ

ከዳንኤል ገዛኽኝ አትላንታ

ከሰሞኑ ገጣሚ ታገል ሰይፉ ሃገር ቤት እየታተመ ከሚሰራጨው ቁም ነገር መጽሄት ጋር አንድ ቃለ ምልልስ አድርጎዋል። በቃለምልልሱ ውስጥም ታገል ብዙ አሳፋሪ አንገት የሚያስደፉ ነገሮችን መናገሩን አንብቤ ከልቤ አዝኛለሁ። በተመሳሳይ የታገል ምልልስ አንጀታቸውን ያሳረራቸው…ወሽመጣቸውን የቆረጣቸው ግለሰቦች ቁጣቸውን በታገል ላይ ይገልጻሉ። አሁንም በታገል ላይ ያላቸውን ቁጣ በርካታዎቹ እየገለጹ ነው። በመሰረቱ ይህ አሁን ስለሆነ እንጂ ቀደም ሲልም ታገል ሰይፉ በህይወቱ ገንዘብ የማግኛ መንገዶችን በመተለም ስራዎቹን የሚሰራ ገጣሚ ነው። እርግጥ ነው ሰው ለሚሰራው ስራ ዋጋ ቢያስፈልገውም ታገል ግን ለገንዘብ ተፈጥሮ ለገንዘብ ህሊናውን የሸቀጠ መሆኑን ለማሳየት የተጠቀምኩበት ነው። ለነገሩ በመሃል ገጣሚነቱን እርግፍ አድርጎ በመተው ወደ ወግ እና ኩመዳ እልም ብሎ ገብቶም ነበረ አልተሳካለትም እንጂ።
ለነገሩ ቁም ነገር መጽሄት ላይ ስለሰጠው ነገር ከማለቴ ይልቅ ታገልን የማውቀውን ያህል በጥቂቱ ልበል። ታገል ሰይፉ ገና የ ኤለመንተሪ ተማሪ እያለ ነበረ የመጀመሪያውን የግጥም መድብል መጽሃፉን የጻፈው። እናም ያ መጽሃፍ ግን የራሱ ሂደት እና ታሪክ ነበረው። ነገሩ እንዲህ ነው መጽሃፉን ከጻፈ በሁዋላ ቤተሰቦቹ የማሳተም አቅም ስላልነበራቸው በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ያየህ ይራድ ቅጣው በሆነ አጋጣሚ የታገልን አብዮታዊ ስሜት ቀመስ በመንግስት ጋዜጣ ላይ ወጥቶ በማየታቸው ታገልንም እንደዚያው በአጋጣሚ ሲያገኙት ምን ሊደረግለት እንደሚፈልግ ይጠይቁታል። ታገልም መጽሃፉን እንዲያሳትሙለት ይጠይቃል። እንዲያሳትሙለት ይጠይቃል።
በዚህ መሰረት ሚኒስትሩ ብጣሽ ወረቀት ላይ በመጻፍ የታገል መጽሃፍ እንዲታተምለት ለብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ይልካሉ። ወዲያው የታገል የመጀመሪያ መጽሃፍ ብርሃን እና ሰላም ለህትመት ይገባ እና ታትሞ ይጠናቀቃል። እናም ለታገል እባት እና ለታገል እንድ መል ዕክት ይደርሳል። መጽሃፋቸው ታትሞ በማለቁ ህትመቱን እንዲረከቡ ይገለጽላቸዋል። ታገል እና አባቱም በፍጥነት ከማተሚያ ቤቱ ሲገኙ የማተሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ገንዘቡን ለህትመት የሚከፈለውን ከፍለው መጽሃፋቸውን እንዲረከቡ ይነግሩዋቸዋል። ሁኔታው በመንግስት ደመወዝ ለሚተዳደረው የታገል ቤተሰብ ትልቅ ድንጋጤን ይፈጥራል። ነገሩ እየተካረረ ሄዶ ታገል እና አባቱ እስከመታሰር ፍርድ ቤትም እስከ መቅረብ ይደርሳሉ በሁዋላ አባቱ ከደመወዛቸው እየተቆረጠ እንዲከፍሉ ይወሰናል። ታገል እንግዲ በቀደመው ዘመን ነበረ ከአብዮቱ ጎን ተሰልፎ የበኩሉን አስተዋጾ ሲያደርግ የቆየው።
ይህ አለፈ እና ወያኔ ሲመጣ ታገል የአስተላለፍ ለውጥ ለማድረግ ቀፎውን አትንኩት የምትለውን መጽሃፉን አሳትሞ አድፍጦ ሲጠብቅ ቆየ። በሁዋላም ሃምሳ አለቃ ገብሩን ይዞ ኢትዮጲያ ሬድዮ ሰተት ብሎ ገባ። ትንሽ ተረጋግቶ ደግሞ ሌዋታን ሲል የቀረቀበውን እንቶ ፈንቶ ግን በ አቅሙ ወያኔን ሊሞግት እና ሊያብጠለጥል የሞከረበትን ልብ ወለዳዊ ትረካ ያለውን መጽሃፉን አሳተመ። ይህ መጽሃፍ ብዙም ሽያጭ ባያገኝም ግን በተለይ እንደ ንኡስ አርስት ኢህአዴግ ካምፕ ውስጥ ያደገው አውሬ የሚለው ወያኔን የሚገልጽ እና ማነነቱን የሚያሳይ ትረካ ነበረው። ይሁን እንጂ ታገል በአቁዋሙ አልጸናም። ለተወሰኑ አመታቶች ማህበራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሲጽፍ ቆይቶ በሁዋላም አስቂኝ እና ለየት ያሉ ጉዳዮችን የያዙ ተንቀሳቃሽ እና ቁዋሚ ምስሎችን ከድምጽ ጋር እያዋሃደ በሲዲ እያወጣ መሸጥ ጀመረ። ለጠቀ እና የአዲስ አበባ መስተዳደር የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲጀምር ታገል እነዚያን ምስል ከድምጽ ጋር እያወዳጀ የሚሰራቸውን ቪዲዮዎች ማቅረቡን ቀጠለ። በነዚህ ቪዲዮዎች ውስጥ ታዲያ ታገል አዘውትሮ ታዋቂ በተለይም ሃብት ያላቸውን ሰዎች እንደ አትሌቶች ያሉትን አወዳሽ እና አሞጋሽ ስራዎች ላይ ማተኮሩን አዘወተረ። ታዲያ እንዳውም ከሃይሌ ገብረ ስላሴ እና ከደራርቱ…ከጥሩነሽ እና ከሌሎቹም የገንዘብ ስጦታ ከጅሎ የሰራቸው ስራዎች እንዳሰበው ስኬታማ ሳያደርጉት እንዲያውም የሚከፈለኝ ክፍያ በቂ አይደለም በሚል የክፍያ እድገት ከአዲስ አበባ መስተዳደር ቲቪ ሃላፊዎች ጋር ሳይግባባ ቀርቶ ከስራው ተሰናበተ።
እንግዲህ ግጥም አሳትሞ በቂ ገቢ ማግኘት ለታገል አስቸጋሪ ሆነበት መቆየት ብቻም አይደለም የልጁ እናት ላይ የፈጸመው ያማያዳግም በደል ታገል ህይወት ላይ ጥላውን አጠላበት። ከዚህ በሁዋላ ነበረ እንግዲህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ በተዋቀረው የኢቲቪ መዝናኛ ፕሮግራም ውስጥ እግሩን ለማስገባት የ አቶ በረከት ስምኦንን ደጅ መጥናት የጀመረው። የሆነው ሆኖ ግን ታገል ያሰበው ሳይሆን ያላሰበው የነዋይ በረከት በበረከት ስምኦን በኩል የፈሰሰለት ወቅቱም መለስ ዜናዊ ላይመለስ በሞት ያሸለበበት ነበረ እና እነሆ የታገልን አፍቃሪ ነዋይነት ግልጽ አድርጎ ያሳየው ስሙን መጥራት የማልፈልገው አዲስ መጽሁፉ ላይ የመጽሃፉን መታሰቢያነት ለ መለስ ዜናዊ ልጆች እንዲሰጥ ሆኖዋል። እንዲያውም በዚህ ጉዳይ የቁም ነገር ዘጋቢ ባቀረበችለት ጥያቄ መሰረት ሲመልስ አባታቸው ጊዜውን ሙሉ ላሃገሩ በመስጠት ለልጆቹ ጊዜ ሳይሰጥ በሞት ለተለየው አባት ልጆች ለመለስ ልጆች የመጽሃፉን መታሰቢያነት መስጠቱን በኩራት ተናግሮዋል።
እንግዲህ ይህንን ማንም ያስበው መለስ ዜናዊ ለልጆቹ ፍቅር ሳይሰጥ ያለፈበት ለ እትዮጲያውያን የሰራው እኔ የማውቀው ዘጎችን እርስ በ እርስ እንዲፋጁ እና እንዲባሉ እንዲከፋፈሉ ከማድረግ በላይ በራሱ በመለስ ዜናዊ የቀጥታ ትዕዛዝ የተገደሉት የምርጫ 97 ሰለባዎችን የጨረሱበት ሁኔታ ነው መለስን ጊዜ አጥተው ለልጆቻቸው ፍቅር እንዲሰጡ ጊዜያቸውን ከ ልጆቻቸው ጋር እንዳያሳልፉ ያላደረጋቸው። ታገል እንግዲህ ከዚህ ሁኔታ ስር ነው ያደፈጠው። ይህ ብቻም አይደለም ታገል በፌስ ቡክም ዙሪያ መረን የለቀቀ አስተያየቱን ሰጥቶዋል የፌስ ቡክ ማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎችን አብጠልጥሎ ስድ ስድቦችን ተጠቅሞ ተሳድቦዋል። ከዚህ በላይ “ጌታዋን የተማመነች በግ ላትዋን ደጅ ታሳድራለች” የሚለውን የሚያስተርት ምን ይገኝ ይሆን ? አይ ታገል እንጭጩ! አይ ታገል መረኑ! ሌላም አለ ሃብታሞችን በመጽሃፉ የምስጋና ገጽ ውስጥ ማመስገኑን መግለጹን አስመልክቶ ቁም ነገር ላይ ሲጠየቅ “ደሃን የማመሰግንበት ምክንያት የለኝም” በማለት ለድሃው የመጽሃፉ አንባቢም ሆነ በዚያ የቲቪ ኩመካው የሚያደንቀውን ደሃ ህዝብ ማስታወስ አልፈለገም። ስለዚህ የተመሰገኑት የሃብታም ምልክቶች ደግሞ መለስ ዜናዊ እና በረከት ስምኦን ናቸው። እንግዲ ማንም ማስተዋል ይችላል ይህ ልጅ ምን ማለት እንደፈለገ ይበልጥ መገንዘብ የሚቻለው ፌስ ቡክን የመጸዳጃ ቤት ግድግዳ እንደሆነ ሁሉ በማመላከት ነው ታገል የተናገረው። እንግዲ ፌስ ቡክን የመሰለ የነጻነት ወንጌል የሚሰበክበትን ማህበራዊ ድረ-ገጽ አብዮተኛዎቹንም ጭምር አንቁዋሾ ገልጾዋቸዋል። እኔ ደግሞ ግብጽን ያየ…ቱኒዚያን የተመለከተ…የሊቢያን መጨረሻ ያስተዋለ ለታገል የሚሰጠው ምላሽ ምን እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ደግሞም የመናገር የመጻፍ የመሰብሰብ እና የመደራጀት ነጻነትን ከሚያፍኑ ሃብታሞች ብሎ ከገለጻቸው ሰዎች የተጠጋው ታገል መልዕክቱ ግልጽ ነው። በመጨረሻም የምለው በፌስ ቡክ ድምጻቸውን የሚያሰሙ የሚታገሉ አብዮተኛዎች ራሳቸውን መከላከል ካልቻሉ ሌኒን እንዳለው ራሱን መከላከል የማይችል አብዮት እርባና የለውም እና በአንድ ረብ የለሽ ግለሰብ የተሰደባችሁ አብዮተኛ ሳተናዎች ራሳችሁን ተከላከሉ እላለሁ። ከማን ካላችሁኝ ኢሃዴግ ካምፕ ውስጥ ተወልዶ ካደገው አውሬ ብያለሁ። አበቃሁ ሰላም።

Go toTop