ከድምጻችን ይሠማ
የኮሚቴዎቻችን የፍርድ ሂደት ለአስር ቀናት ተቋረጠ
አቃቤ ሕግ ምስክሮች አለቁበት
‹‹ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ ምን ይሰራል? ውሳኔ እንደሆነ ከባለስልጣናት ወርዶ በኢቲቪ በኩል ተወስኖብናል፡›› ኡስታዝ አቡበከር
በዝግ እየታየ የሚካሄደው የመሪዎቻችን እና የሌሎች ወንድሞቻችን የፍርድ ሂደት ለአስር ቀናት ያህል እንዲቋረጥ መደረጉ ተሰማ፡፡ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ በሀሰት እንዲመሰክሩለት ያሰለጠናቸውን ‹‹197›› ሀሰተኛ ምስክሮች ለ10 ተከታታይ ቀናት ለማድመጥ ከዚህ ቀደም ውሳኔ ሰጥቶ መደመጥ የጀመሩ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን እስከአሁን ከ16 ቀናት በላይ በተካሄደ ችሎት ማዳመጥ የተቻለው 33 ምስክሮችን ብቻ ነው፡፡ አቃቤ ሕግ ያዘጋጃቸው ብዙዎቹ ምስክሮች በሀሰት ለመመስከር ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው እና ጥቂት የማይባሉትም ሸሽተው በመጥፋታቸው አቃቤ ሕግ አሁን ምሰክሮች እንዳለቁበት ተሰምቷል፡፡ ፍ/ቤቱ ይሄንን የአቃቤ ሕግ ችግር ለመፍታትና አቃቤ ሕግ ሌሎች ምስክሮችን እስኪያዘጋጅና እስከያሰለጥን ድረስ ‹‹በዳኞች ስራ መደራረብ›› ምክንያት የሚል ሰበብ በመጥቀስ ችሎቱ ለአስር ቀናት እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በቀዳሚው ጊዜ በፍ/ቤት ተወስኖ የነበረው በአስር ተከታታይ የስራ ቀናት ምስክሮችን አስመስክሮ ለመጨረስ ነበር፡፡ አቃቤ ሕግ ተጨማሪ ምስክሮችን ከስር ስር ለማሰባሰብ እንዲረዳው ከዳኞች ጋር በመጣመር እና የምስክርነት ስርአቱን በማዘግየት በአማካይ በቀን ሲያስመሰከክር የቆየው ሁለት ምስክሮችን ብቻ ነበር፡፡ አሁን ባለው የፍርድ ስርአት መሪዎቻችን ፍትሃዊ ውሳኔ ሊያገኙ እንደማይችሉ የሚጠቁሙ መሰል አሻጥሮች ተደጋግመው እየታዩ ሲሆን በችሎት ሰአትም ውስጥ በአቃቤ ህግና ዳኞች መሀል ይህ ነው ሊባል የሚችል ልዩነት ሁሉ እየጠፋ ነው ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሚቴው ሰብሳቢና በማእከላዊ ከፍተኛ ድብዳባ ካስተናገዱ ወንድሞች አንዱ የሆነው ኡስታዝ አቡበከር በቃሊቲ ከዞን አራት ወደ ዞን አንድ መቀየሩ የታወቀ ሲሆን አዲሱ የተቀየረበት ዞንም ፍጹም ለጤናው እንዳልተስማማው መረዳት ተችሏል፡፡ ዞን አንድ በቃሊቲ ከፍተኛ የእስረኛ ቁጥር ያለባቸውና የንጽህናና መሰረተ ልማት ይዞታቸው አስከፊ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዞኖች በዋነኝነት የሚጠቀስ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞም አቡበከር ያለበት የሳይንስ ህመም አገርሽቶበት ችግር ውስጥ እንዳለ ተሰምቷል፡፡ በዞኑ ያለው መጥፎ ጠረን እስረኞችን አስከፊ የጤና ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ፤ የአቡበከር ህመም በገጽታው ላይ እብጠት እንደፈጠረና ሁኔታው አሳሳቢም እንደሆነ ታውቋል፡፡ ኡስታዝ አቡበከር ከዞን አንድ አንጻር የተሻለ ከሚባለው ዞን አራት ወደ ዞን አንድ እንዲዘዋወር የተደረገበት ምክንያት አሁንም በውል ያልታወቀ ሲሆን ምንአልባትም ግን ባለፈው ሳምንት ችሎት ውስጥ በተናገረው ንግግር ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
ኮቴዎቻችን ባለፈው ሳምንት በነበረው ችሎት የ‹‹ጂሐዳዊ ሐረካት›› መታየትን ተከትሎ ለፍ/ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ብዙዎቹ የህሊና እስረኞችም በፍ/ቤቱ አሰራር ላይ ቅራኔ እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ ፊልሙ በወቅቱ በኢቴቪ እንዳይተላለፍ ከታገደ በኋላ መንግስት በራሱ ሕጉን በመጣስ ፊልሙን ያስተላለፈው ሲሆን ፍ/ቤቱም ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ ሳያደርግ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከሩና ውሳኔው ያለበት ሁኔታ አለመታወቁ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ ኡስታዝ አቡበከርም በቀዳሚነት ኮሚቴዎቹ የተሰባሰቡት እና የጠየቁት የእምነት ነፃት መሆኑን፤ ይህንን ህገ-መንግስታዊ መብት መጠየቅ እንደወንጀል ተቆጥሮ መከሰሳቸው አግባብ እንዳልሆነ በማንሳት፤‹‹የፍርድ ቤቱ ስራ አልገባንም፤ ለምን ትእዛዙ መድረስ አለመድረሱን ለማረጋገጥ እንኳን አልፈለገም፤ በግልጽ ህዝብ ሁሉ እንዳወቀው ትእዛዙ የኢቲቪ መዝገብ ቤት ደርሶ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ነው መልሶ ወጪ የሆነው፤ በማእከላዊ እስርቤት የሰቆቃ ተግባር የፈፀሙብን ሰዎች (ፍርድ ቤቱ ውስጥ ይገኝ ወደነበረው የማእከላዊ ገራፊ ኮማንደር ከተማ እየጠቆመ) የሰሩት ወንጀል ምንም ሳይሰማቸው አሁንም በፍርድ ቤት እኛን ወንጀለኛ ለማስባል ከህግ ውጪ ምስክሮችን እያስፈራሩ የሀሰት ምስክርነት ሲያስመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ነፃ ሆኖ ይታዘባል ብለን ዝም ብለናል፡፡ አሁን ግን በህዝብ ፊት ኢቴቪ ወንጀለኛ መሆናችንን አውጇል፤ ከአሁን በኋላ ከፍርድ ቤቱ የምንጠብቀው ነገር ምንድን ነው? ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ ምን ይሰራል? ውሳኔ እንደሆነ ከባለስልጣናት ወርዶ በኢቲቪ በኩል ተወስኖብናል፡›› ብሎ ንግግር ያደረገ ሲሆን፤ አህመዲን ጀበልም በበኩሉ ‹‹የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ኢቴቪ የደረሰው 11፡00 ሰአት ላይ ነው፤ ከዚህ ሰአት በኋላ የትኛውም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት አዲስ ጉዳይ ተቀብሎ አጣርቶ እግድ ሊሰጥ አይችልም፤ ትእዛዙ ይግባኝ ተብሎበታል ቢባል እንኳን ይግባኙ ሊሆን የሚችለው ጠዋት ላይ ነው፤ ኢቲቪ የፍርድ ቤቱን የእግድ ትእዛዝ በምሽት ጥሶ ዶክመንተሪውን ማቅረቡ እንዴት አያስጠይቀውም?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡