የአቦይ ስብሐት ነጋ ‹‹ይሰቀሉ፣ ሞት ይገባቸዋል!›› የሚል የበቀል መንፈስ ከወዴየት ነው!?

በፍቅር ለይኩን

አቦይ ስብሐት ባለፈው ሳምንት ‹‹ከላይፍ›› ወርኻዊ መጽሔት ጋር ያደረጉትን ሰላም ሰላም የማይሸት፣ ፍቅርን የተራቆተ፣ የይቅር ባይነት መንፈስ ፈፅሞ የተለየው፣ በቀልንና ጥላቻን የሚሰብክና ‹‹ዕርቅ ለመፈጸም በማለት ሰዎችን ሲልኩ የነበሩ ቄሶች ስቅላት፣ ሞት ይገባቸዋል!›› የሚል የሞት ፍርድ አዋጅን የሚያስተጋባ የሚመስል ቃለ-መጠይቃቸውን እያዘንኩም፣ እያፈረኩም ለማንበብ ተገድጄያለሁ፡፡

ማፈሬና ማዘኔም እኔ እጅግ በጥቂቱም ቢሆን የማውቃቸው አቦይ ስብሐት እንደ ፖለቲከኛና ከፍተኛ የመንግሥት ሰው ሳይሆን እንደማንኛችንም ኢትዮጵያውያን በጎረቤት፣ በወዳጅ ዘመድ፣ በጓደኛ መካከል… በደስታውም በሐዘኑም የሚገኙ፣ ማህበራዊ ግዴታቸውን የሚወጡ፣ መልካም የሆነ ማህበራዊ ግንኙነት እንዳላቸው በጥቂቱ ስለማውቅ ነው፡፡

እናም የእኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛና የኢህአዴግ ታጋይ ሰው ሊያውም በሃይማኖት አባቶች መካከል እንዲህ ያለ የበቀል፣ የይሰቀሉ የሞት ፍርድ ያስተላልፋሉ ብዬ በፍፁም አልጠብቅም፡፡ እንደ አገራችን ባሕልና ወግ ቢሆንማ እንደ አቦይ ስብሐት ካሉት የዕድሜ ባለጠጋ ሰዎች የሚጠበቀው የእርቅ፣ የሰላም፣ የፍቅር… መልእክት ነበር፡፡ ግና አዛውንቱ አቶ ስብሐት ዛሬም እንኳን በሃይማኖት ሰዎችም ላይ እንኳን ሳይቀር የሞትንና የበቀልን ፍርድ ሲያስተላልፉ ትንሽ እንኳን ቅር አላላቸውም፡፡

እኚህ አንጋፋ የሕዋሓት ታጋይና መሪ የነበሩ ፖለቲከኛ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በአደባባይ በሚያደርጓቸው ንግግሮቻቸውና በሚሰጧቸው ቃለ መጠይቆች በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ ስማቸው እየተነሳ ነው፡፡

በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋምና አባቶች ዙሪያ እየተናገሩትና እየሰጡት ያለው ትንታኔ፣ አስተያየትና ቃለ መጠይቆች፣ አንዳንዴም ዘለፋ ድንበሩን ያለፈ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፣ የመሪዎቿን ክብርና ልእልና እየተዳፈረ ያለ እንደሆነ ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡

እንደ አንዳንድ ታዛቢዎች ደግሞ የአዛውንቱ ‹‹የቄሳርን ከእግዚአብሔር›› ጋር የቀላቀለ አካሄድ ፈፅሞ ሌላ መሰሪ የሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለውና እንደውም ሕወሓት/ኢህአዴግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያለው አቋም ሌላኛው ግልባጭ ነው በማለት ይገልፁታል፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለገባችበት ቀውስ፡- ጎሰኝነቱ፣ ጎጠኝነቱ፣ መለያየቱ፣ ሙስናው፣ የሞራል ውድቀቱና ዝቅጠቱ… ወዘተ ራሷ ቤተ ክርስቲያኒቱና የሚመሯት አባቶች/መሪዎቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመንፈሳዊነት ሕይወት መሰደድና መራቆት ባሻገር፤ ይኸው በተለያዩ ጊዜያት መንግሥታት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሲያራምዱት የነበረውና እያራመዱት ያለው ፖለቲካዊ አቋም ተጽእኖ ውጤት እንደሆነ ነው የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ ያጠኑ ምሁራን በጥናቶቻቸው የሚገልፁት፡፡

ባለፉት ረጅም ዘመናትም ሆነ አሁን በእኛ ዘመን በቤተ ክህነቱና በቤተ መንግሥቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል›› ተብሎ በተባለበት በደርግ ዘመነ መንግሥት እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱና ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚመሩት አባቶች ላይ ደርጉ ያሳረፈውን ብርቱ ክንድና የቤተ ክርስቲየኒቱን ፓትርያሪክ እስከ ማጋዝና በግፍ መግደል ድረስ የተጓዘበትን እርምጃ ማስታወስ በቂ ነው፡፡

ለሕዝቦች ነፃነት፣ እኩልነትና መብት፣ እንዲሁም ለማንነታቸው፣ ለሃይማኖታቸው፣ ለባህላቸው፣ ለቋንቋቸው፣ ለታሪካቸው፣ ለቅርሳቸው… መከበር በሚሊዮኖች በሚሆኑ ጭቁን ሕዝቦች መስዋዕትነት እውን አድርጌያለሁ የሚለው ኢህአዴግም ‹‹ከሃይማኖት ነፃነት እስከ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡›› የሚለውን አዋጅ በግልፅ በሆነ መንገድ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ያተካተተ ቢሆንም፤ መንግሥትና ቤተ ክህነቱ ግን አሁንም ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የማይተላለፉባቸውንና የማይጨካከኑባቸውን በርካታ አጋጣሚዎችን ደጋግመን አይተናል፣ ታዝበናልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  * በሀገሬ በኢትዮጵያ ግን ከቶም ተስፋ አልቆርጥም !!! - መስፍን ማሞ ተሰማ

መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማቶች ተለያይተዋል ቢባልም አንዱ አንዱን የሚስብበትና ወይም የሚሳሳቡበትን አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያት አስተውለናል፣ አሁንም እያስተዋልን ነው፡፡ በአንድ ወቅትም አቶ ስብሐት ይህንኑ ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ መካከል ስላለው መሳሳብና በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችን የመንፈስ ነፃነትና አርነት በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ከላይ ያነሳውን አሳብ የሚያጠናክርልን ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አቶ ስብሐት እንዲህ ነበር ያሉት፡-

‹‹… ጳጳሳቱ አይረቡም፣ ከመንግሥት ጥገኝነት ለመውጣት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ፣ ሁላቸውም በመንግሥት ሳምባ ለመተንፈስ የሚሹ የመንፈሳዊነት ለዛና መዓዛ የሌላቸው ናቸው…›› በማለት መረርና ጠንከር ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ በወቅቱም ይህ እሳቤያቸውና ዘለፋ የሚመስለው አስተያየታቸው ከሃይማኖቱ አባቶችም ሆነ ከምእምናኑ ዘንድ ድጋፍንም ትችትም አስከትሎባቸው እንደ ነበር እናስታውሳለን፡፡

አቶ ስብሐት ለድጋፉም ሆነ ለትችቱ ብዙ ልብም ሆነም ጆሮ የሰጡ አይመስሉም፡፡ እናም እኚህ ሰው የሰላ ትችታቸውንና እርግማናቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱና ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚመሯት አባቶች ላይ አሁንም እያወረዱት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ከላይፍ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅም ከመቼውም ጊዜ በላይ በሆነ ድፍረትን ከቂም በቀል የቀላቀለ በሚመስል ሁኔታ በአደባባይ እንዲህ ብለውናል፡-

‹‹በአሜሪካን ካሉ አባቶች ጋር የእርቅን መልእክት የላኩ ቄሶች መሰቀል ይገባቸዋል፣ ሞት ይገባቸዋል!›› ሲሉ አስቀድሞ ገና ከጠዋቱ በእሳቸው ሕሊና ውስጥ ምሕረት የለሽ የስቅላት/የሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መካከል እርቅንና ሰላምን እናወርዳለን በማለት የሚደክሙ ካህናትን የስቅላት የሞት ፍርዳቸው የጸና ይሆን ዘንድ፣ በቃ ይሰቀሉ! የሚል የሞት ፍርድ አዋጃቸውን ‹‹ያልሰማህ ስማ፣ የሰማህ ላልሰማ አሰማ!›› በሚል አኳኃን በድፍረት ያለምንም ማወላወል ለአደባባይ አብቅተውታል፡፡

ይህ ‹‹ይሰቀሉ፣ ሞት ይገባቸዋል!›› የሚል የአቦይ ስብሐት ምሕረት የለሽ ቂምንና በቀልን የተሞላ ፍርድ ምንጩ ከወዴየት ይሆን…!? አቶ ስብሐት በእርቅ መልእክተኞቹ ላይ ያስተላለፉትን የሞት ፍርድ አንድ ታሪክን አስታወሰኝ፡፡ በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ወንጌላዊው፣ ሐኪሙና ታሪክ ጸሐፊው ሉቃስ አንድ ከአቦይ ስብሐት ‹‹በቃ ይሙቱ፣ የእሳት ራት ይሁኑ!›› ፍርድ ጋር በሚቀራረብ መልኩ አንድ ታሪክን ያስነብበናል፡፡

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ በኢየሩሳሌም ዙሪያና በሰማርያ ለስብከት ላካቸው፡፡ ለዚህ ቅዱስ ተልዕኮ የተላኩት ደቀ መዛሙርት በሄዱበት ስፍራ ሁሉ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በመስበክ፣ ታላላቅ ድንቅና ተዓምራትን አድርገው ተልዕኮአቸውን በድል ፈፅመው በብዙ ሐሴትና ደስታ ወደላካቸው ወደ ጌታቸውና መምህራቸው ተመለሱ፡፡

ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ በመዋዕለ ስብከታቸው ወቅት በሰማርያ ሰዎች ላይ ክፉኛ ቂም ቋጥረውባቸው ነበር፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የሰማርያ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰብክላቸው ያለውን ‹‹የእውነት ቃልና የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ!›› ለሚለው ጥሪ ጆሮም ልብም ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩምና ነው፡፡ እናም፡-

‹‹ጌታ ሆይ እሳት ከሰማይ ወርዳ ይብላቸው ትል ዘንድ ትፈቅድልናለህን!?›› ብለው የሰማርያን ሰዎች ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ዘመን እሳት ከሰማይ ወርዳ ዶግ አመድ ያደርጋቸው ዘንድ ኢየሱስን ፈቃዱን ጠይቀውት ነበር፡፡

ጌታም መልሶ፡- ‹‹ምን ዓይነት መንፈስ እንደሆነላችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም፡፡›› ሲል በተግሣፅ ቃል መለሰላቸው፡፡

አቶ ስብሐት ደጋግመው እንደነገሩን እኛም እንደሰማናቸው፣ እንዳመንናቸው አላልኩም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ መሆናቸውን በጥቂቱም ቢሆን እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ አቦይ እምነቱን ከፖለቲካው፣ ፖለቲካውን ከእምነቱ ጋር እያቀላቀሉ የትኛውን ለእግዚአብሔር የትኛውን ለቄሳር እንደወሰኑ ባለየ መልኩ አቋማቸውን ማራመዱን ቀጥለውበታል፡፡ እናም አቶ ስብሐት ብዙዎችን ግራ እስኪያጋባ ድረስ በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እያራመዱት ያለው አቋማቸው ከአስገራሚነት አልፎ ልክ እንደዛሬው ደግሞ አስደንጋጭና ሰቅጣጭ እየሆነ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  [የሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ ጉዳይ] - አንድነት ይመጣል፡ እውነቱም ይገለጣል (ከዲ/ኤፍሬም ስለሺ)

በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል እርቀ ሰላም ይውረድ፣ ፍቅርና አንድነት በመካከላችን ይስፈን በማለት እንደ ኖህ ርግብ የሰላም ምልክት የሆነውን ዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ለእርቅና ለሰላም የሚደክሙትን ሰዎች ‹‹ሞት ይገባቸዋል፣ ይሰቀሉ በቃ!›› የሚል በቀልን የተሞላ ፍርድን ከአዛውንቱ ከአቦይ ስብሐት አንጠብቅም፡፡

ጥርስን በጥርስ፣ ዓይንን በዓይን እንጂ ምን ሲደረግ ፍቅር፣ እርቀ ሰላምና አንድነት ተብሎ ነገር በውጭ ካሉት አባቶች ጋር ሊታሰብ ይችላል ብሎ መናገር ከአንድ ኦርቶዶክሳዊ አዛውንት የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ይህ በቀልንና ፍርድን የተሞላ የአቶ ስብሐት አነጋገር በምንም መንገድ በፍፁም የኦርቶዶክሳዊነትም ሆነ የሰብአዊነት መነሻና መሠረት ሊኖረው አይችልም፡፡

አቶ ስብሐት ነጋ ስለ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና አስተምህሮ ምን ያህል የጠለቀ እውቀት እንዳላቸው ባላውቅም ቢያንስ በተወለዱበት፣ ባደጉበትና በኖሩበት አካባቢ ሌላው ቀርቶ ደም በተቃቡ ባላንጣዎች መካከል እንኳን ሳይቀር እርቅና ሰላም ይሰፍን ዘንድ የሚያደርጉ መካሪ ሽማግሌዎችን ሳያዩ እንደማይቀሩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለዚህም ደግሞ ቤተ የእምነት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች ምን ያህል ከፍተኛ የሆነ ሚና እንዳላቸው አቦይ ስብሐት ይስቱታል ብዬ አላስብም፡፡

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ ክብርና ፋይዳ እንዲሁም ትልቅ አገራዊና ባህላዊ እሴት ያለውን የእርቀ ሰላምን መንገድ በእሾህ አጥሮ፣ ለሰላም የሚተጉትንና እርቅን የሚሰብኩ ሰዎችን ሊያውም የሃይማኖት አባቶችን እንዲህ ባለ ድፍረት ‹‹ይሰቀሉ፣ ሞት ለእነርሱና ለግበረ-አበሮቻቸው ይሁን፣ ሰላም፣ ሰላም፣ እርቅ፣ እርቅ እያሉ የሚጮኹም መንገዳቸውም ዳጥና ጨለማ ይሁን፣ እነርሱ በእኛ ዘንድ ስም አጠራራቸው ይጥፋ ወንጀለኞች ናቸውና!›› ብሎ መናገርና መፍረድ በጎ ሕሊና ካለው፣ ሰብአዊነት ከሚሰማውና ሃይማኖት አለኝ ከሚል ሰው በጭራሽ የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ስለሆነም አቶ ስብሐት እባክዎት ምንም እንኳን በዕድሜዎት እኔን ሊወልዱኝ የሚችሉ አባቴ ቢሆኑም እንዲህ ዓይነቱን ከኦርቶዶክሳዊ እምነትና አስተምህሮም ሆነ ከሰብአዊነት መንገድ የወጣውን ፍርድዎን እየሰማሁ ዝም ለማለት ሕሊናዬ አልፈቀደልኝም እናም ይህችን አጠር ያለች ጦማር ላደርሰዎ ወደድሁ፡፡

ወደድንም ጠላንም፣ ተቀበልነውም አልተቀበልነው የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ሰላምንና እርቅን ገፍታ የመለያየትን መንገድ የምትመርጥ ቤተ ክርስቲያን ስም ብቻ ካልሆነ በቀር ሕይወት/ሕልውና ሊኖራት አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የቆመችበት መሠረቱ የመስቀሉ ፍቅር ነው፡፡ በዚህ የመስቀል ፍቅር ላይ ደግሞ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም፣ እርቅ፣ አርነት፣ ነፃነት፣ እውነት… ታውጇል፡፡

ስለዚህም በዚህ ፍቅር ውስጥ ያሉና የሚኖሩ፣ ይህን ታላቅ እውነት የሚያውቁ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን በቃላቸውም ሆነ በተግባራቸው ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም መሟገታቸውን መቼም ቢሆን አያቆሙም፡፡ ይህን የአባቶቻችንን ለቤተ ክርስቲያን ፍፁም አንድነትና ሰላም በልባቸው የሚነደውን ቅናታቸውን የኤልዛቤል ዛቻ አያስቆመውም፣ የክፉው ልጆች ስብከት አያሸንፈውም፣ በቅዱስ መቅደሱ የተንሰራፋ  የምናምንቴዎች የዔሊ ልጆች ዓመፃና ርኩሰትም ይህን የቅናት እሳት፣ ይህን በጎነትና ቅንነት በጭራሽ ሊያጠፋው አይቻለውም!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአሜሪካና ምዕራባውያን ጫናና መፈንቅለ መንግሥት በግርማዊነታቸው መንግሥት ላይ!! - መስፍን ማሞ ተሰማ

እናም ይህ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ፍፁም ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እዛም እዚህ ከፍ ብለው የሚሰሙ የአባቶችና የወንድሞች የእርቅና የሰላም ጥሪ ዋጋቸው ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ሞት ወይም ስቅላት ሊሆን አይችልም!! 

እናም አቶ ስብሐት እነዚህ ሰላምን፣ አንድነትንና እርቅን የሚሰብኩ ሰዎች የሚገባቸው ወይም ዋጋቸው እርስዎ እንደሚሉት ወይም እንደተመኙላቸው ‹‹ስቅላት ወይም ሞት!›› አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መካከል እርቀ ሰላምና አንድነት ይሆን ዘንድ የሚተጉትን ሁሉ ታላቁ መጽሐፍ የሞት ልጆች አይላቸውም፡፡ ነገር ግን፡-

‹‹የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና፡፡›› ሲል ትልቅ ክብርንና ስፍራን ይሰጣቸዋል፡፡ እነዚህ ትላንትም ሆነ ዛሬ ሰላምን፣ እርቅንና አንድነትን የሚሰብኩ ሰዎች መጽሐፍ፡- ‹‹እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እንዴት ያማሩ ናቸው፡፡›› ሲልም ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል፡፡ እናም አቦይ እባክዎት ቆም ብለው ያስቡ፡፡

በመጨረሻም መቼም እርስዎን ያህል አንጋፋ ፖለቲከኛ በዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ ትልቅ ስም፣ ዝና ክብር ያላቸውን እንደ ማንዴላ፣ ጋንዲ፣ ሉተር…ወዘተ ያሉ በሕዝቦቻቸውና በአገራትም ጭምር ሳይቀር ሰላምንና እርቅን የሰበኩ እነዚህ ሰዎች የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ አያውቁም ብዬ ለማሰብ አልደፍርም፡፡

እናም አቦይ እስቲ አንድ ጥያቄን ልጠይቅዎት፡- ለመሆኑ ለ27 ዓመታት በስደት፣ በግዞትና ሕሊና ሊሸከመው ከሚችል በላይ በሆነ መከራ ውስጥ ያለፉት ማንዴላ፣ እርሳቸውንና ሕዝባቸውን ለአስከፊ ጭቆና፣ መከራ፣ ስደትና ሞት የዳረገውን ዘረኛውን የአፓርታይድን ሥርዓት አቀንቃኞችን በሙሉ ልብ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሰላም ሲሉ ይቅርታ ማድረጋቸውና ሌሎችም ይቅር እንዲባባሉ መስበካቸው ስህተተኛ ነበሩ ማለት ነው!?

ለመሆኑ አቦይ ይህን ምሕረትና ይቅርታ በቂም በቀል ላይ፣ ደግነት በክፋት ላይ፣ ሕይወት በሞት ላይ፣ ቅንነት በተንኮል ላይ፣ ቅንነትና በጎነት በዓመፃ ላይ…  ድል ነስቶ የወጣበትን የማንዴላን የመንፈስ ልእልና እና ታላቅ ጀግንነት ዓለም በምን መንፈስ ነበር የተቀበለው!?

ክፋትን በደግነት፣ ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ ለማሸነፍ ቆርጠው የተነሱትን ማንዴላን ደቡብ አፍሪካውያኑ ወገኖቻቸውም ሆኑ የተቀረው የዓለም ሕዝብ ‹‹ሞት ይፈረድባቸው! መሰቀል ይገባቸዋል! ብሎአቸው ነበር እንዴ አቶ ስብሐት!?

አቦይ የህንድ ነፃነት አባት የሆኑትና በሕዝባቸው ዘንድ ‹‹ታላቁ ነፍስ›› ተብለው የሚሞካሹት አርበኛውና ታጋዩ ጋንዲስ በጥይት ለመታቸው ሰው በመጨረሻ ትንፋሻቸው ሆነው እባካችሁ አትግደሉት እኔ ይቅር ብዬዋለሁ፡፡ ሲሉ ተሳስተው ነበር ማለት ነው!?

የቀድሞው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ጆን ፖል የግድያ ሙከራ ያደረገባቸውን ሰው በእስር ቤት ድረስ ተገኝተው ሲጠይቁትና ይቅርታቸውን ሲለግሱትስ ለእርስዎም ሆነ ለእኛ እንዲሁም ለተቀረው ዓለም ምን ዓይነት መልእክት ነው እያስተላለፉ የነበረው!?

ስለሆነም ለአገራችንም ሆነ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን የሚስፈልገው ቂም በቀልን እየቆሰቆሰ የእልቂትን እሳት የሚያነድ፣ መለያየትን የሚሰብክ፣ እረቀ-ሰላምን የሚገፋ፣ በአባቶችና በወንድማማቾች መካከል ጠብንና መለያየትን የሚዘራ ሳይሆን፣ አንድነትንና እርቅን የሚሰብክ የሰላም ሐዋርያ ነው በእጅጉና በብዙ የሚያስፈልገን፡፡

አቶ ስብሐት አይሞኙ በእንዲህ ዓይነቶቹ የሰላም ሐዋርያት፣ እርቅን ሰባኪዎች፣ የእውነትና የፍትሕ ጠበቃዎች ላይ ሞት ኃይልም ስልጣንም የለውም! ለምን ቢባል መጽሐፍ ‹‹እርቅን የሚሰብኩ፣ የሚያስታርቁ እነርሱ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ!›› ይለናልና፡፡

ሰላም! ሻሎም! 

5 Comments

  1. የሰው ልጅ በምላሱ በአንደበቱ እንደሚፈረድበት እናውቃለን ከታሪክ፣ ምናልባት እኒህ ሰው የራሳቸው መጨረሻ እንዲህ እንደሚሆን ታይቶአቸው ይሆን?

  2. I fully support the idea of Sbaht, as these people are criminals against the interest of the people of Ethiopia, they should be punished as bad ccitizens of the country, like Meshin W.(professor). They are working to establish the rule of Menlik, who was the most criminal, anti-unity, destablizing man, the national cancer of the Empire. Now Mesfin is working day and night to bring this slavery, criminal system to the land of Ethiopia, as son of Menlik. These church people in name of religion, is also their mission is the same of the two faces. You never expect any good thing from such personalities, except destruction, war, disintegration, mesry and all sorts of enemity. Their leader is professor Mesfin W. who has been a national cancer since his birth. Still he is polishing our land with his dirty literature. I am sorry for those who are arround him to have a share from his dirty and criminal hand.

    • Now, opposition at Diaspora with their leader Professor Mesfin are looking at the grave of Menlik for their overall submission, to be extinct from the land of people.
      No loop holes for these dirty people, every body is working at all corners to evade them all in all with their dirty attitude. let alone to step foreward, even they are not able to play their fabricated drama at the screen of Esat. Now they are run out of every thing, including crying. Berhanu, your dream has turned into ashes. What is the age of berhanu, I think he is the elder of Meles, any way, he was planning to stay for two terms of EPRDF, but I don´t think so.

      • you talking about the opposit your eprdf is hated by 85 million people of ETHIOPIAN your time is in numbers.you don’t have money to buy votes now everything is dried up.the only thing you got left is your dirty mouth.

  3. This old devil does not deserve to be called “Aboy”! This cruel tyrant! His place is hell since his hands are full of blood; he only knows cruelty beyond imagination. I wonder if he would be able to utter some words of regret and repentance when it comes to the last breath in his death bed!

Comments are closed.

Share