የተወዳጁ በቆሎ የጤና ጠቀሜታዎች

ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ

በያዝነው የክረምት ወራት በሀገራችን ተመራጭ ከሆኑ ምግቦች ውስጥ በቆሎ ግንባር ቀደሙ ነው-ዋጋው ባይወደድ በአሜሪካውያን ዘንድ com የሚሰኘውና በቀደምት አሜሪካ ነዋሪዎችና በተቀረውም አለም maize ተብሎ የሚጠራው በቆሎ ሳይንሳዊ ስሙ maize ከሚለው  ስሙ ይመነጫል፡፡ በቆሎ በተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ቀለማት ይታወቃል፡፡ ለአሜሪካን ቢጫ ቀለም ሲኖረው በአፍረካውያን ዘንድ ደግሞ ነጭ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም አለው፡፡ በሌሎች ሀገራት ፒንክ፣ ጥቁር ወይን ጠጅና ሰማያዊ ቀለሞችን ይዟል፡፡ አሜሪካ በአለም ላይ ቁጥር አንድ በቆሎ አምራች ነች፡፡ በአንድ ወቅት በሃገራችን በኩንታል 15 ብር ሲሸጥ የነበረው የጤና ጠቀሜታዎቹ ከብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስላል፡፡

በፕሮቲን የበለፀገ ነው

አንድ ኩባያ በቆሎ 4.7 ግራም ፕሮቲን ወይም ለእለታዊ ፍጆታችን ከሚያስፈልገን ውስጥ 9 ከመቶውን ይሰጠናል፡፡ የምግብ መዋሀድን ያፈጥናል፡፡ በቆሎ የምግብ መዋሀድን የሚያከላጥፍ ፋይበር ይዟል፡፡ ፋይበሩ የሆድ ድርቀትንና ኪንታሮትን ይከላከላል፡፡

በሚኒራሎች የታጨቀ ነው

ማግኒዚየም፣ አይረን፣ ኮፐርና ለጤናማ  አትንቶች የሚያስፈልገው ፎስፈረስ በከፍተኛ መጠን በቆሎ ውስጥ የገኛሉ፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች እድሜአችን ሲገፋ አጥንቶችን በቀላሉ እንዳይጎዱ ከማደረጋቸው በላይ ኩላሊቶቻችን ስራቸውን በአገባቡ እንዲወጡ ይረዳሉ፡፡

የቆዳ ጤናና በቆሎ

በቆሎ በአንቲ ኦክሲዳንቶች የበለፀገ ነው፡፡ እነዚህ አንቲ ኦክሲዳንቶች የቆዳን ውበት ረዘም ላለ ጊዜ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋሉ፡፡ በቆሎን በመብላት ብቻ ሳይሆን ሊኖሊክ አሲድን የያዘውን የበቆሎ ዘይት (corn oil) መጠቀም ይቻላል፡፡ የበቆሎ ስታርች በቆዳ ላይ የሚታዩ ሽፍታዎችንና ቁስለቶችን ለማለስለስ ይጠቅማል፡፡

የደም ማነስን ይከላከላል

የአይረን (ብረት) እጥረት የቀይ ደም ሴል መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ይህን ለመከላከል የሚረዱት ቫይታሚን ቢ እና ፎሊክ አሲድ በጥሩ መጠን በቆሎ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: 10 የእንቅልፍ ፀሮችና መፍትሄያቸው

የኮሌስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡ ኮሌስትሮል በጉበት የሚመረት ሲሆን ሁለት አይነት ነው፡፡ ጠቃሚ እና ጎጂ፡፡ ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች የምናዘወትር ከሆነ የጎጂ ኮሌስትሮል መጠን ይጨምራል፡፡ ይህ ኮሌስትሮል ልብን በማዳከም የደም ስር በሽታዎች እንዲከሰቱ ያደርጋል፡፡ በበቆሎ ውስጥ የሚገኙት ቫይታሚን ሲ፣ ካርቶናይድስ እና ባዮፍላቮኖይድስ የጎጂውን ኮሌስትሮል መጠን በመቆጣጠር የደም ዝውውር እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡

ለነፍሰጡሮች ጠቃሚ ነው

ለነፍሰጡሮች አስፈላጊ ከሆኑ ንጥረ ነገሮች ውስጥ ዋነኛው የሆነው ፎሊክ አሲድ በቆሎ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ይገኛል፡፡ የደም ግፊት ካለብሽ ወይም እጆችሽና እግሮችሽ ያበጡ ከሆነ ሐኪምሽን ማማከር ይኖርብሻል፡፡ የፎሊክ አሲድ እጥረት በህፃኑ ክብደት ላይ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ በቆሎ ለነፍሰጡሯና በሆዷ ላለው ልጅ ይጠቅማል፡፡ ህፃኑ ዝቅተኛ ክብደት እንዳይኖረው ከማድረጉም በላይ ሌሎች ችግሮችም እንዳይፈጠሩበት ይረዳል፡፡ ነፍሰጡሮች በቆሎ የሚያዘወትሩ ከሆነ በውስጡ ታጭቀው የሚገኙት ቫይታሚኖች፣ ሚንራሎችና ፋይበር በተለያዩ ህመሞች የመጠቃት እድልን ከመቀነሳቸውም በላይ ለተሟላ ጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይሰጣል፡፡

በካሎሪ የበለፀገ ነው

ጉልበትና አቅም የሚጠይቁ ስራዎችን የሚሰሩ ሰዎች ከበቆሎ የተሰሩ ምግቦችን ቢያዘወትሩ አስፈላጊውን ጉልበት ማግኘት ይችላሉ፡፡ በ100 ግራም በቆሎ ውስጥ 342 ካሎሪ የሚገኝ ሲሆን ከእህል ዘሮች ከፍተኛው ነው፡፡

ካንሰርን ይከላከላል

በኮርኔል ዩኒቨርስቲ የተደረጉ ጥናቶች በበቆሎ ውስጥ የሚገኙት አንቲኦክሲዳንቶች ካንሰር አምጪ የሆኑትን ፍሪ ራዲካልሶችን ይዋጋሉ ብለዋል፡፡ በቆሎን ከሌሎቹ ምግቦች የሚለየው ተጠብሶ ወይም ተቀቅሎ ከሚበላው ይልቅ በስሎ የሚዘጋጀው የአንቲኦክሲዳንቱ መጠን ጨምሮ መገኘቱ ነው፡፡ በበቆሎ ውስጥ የሚገኘው (ferulic acid) ወደ ጡትና ጉበት ካንሰር የሚመሩ እብጠቶችን ይከላከላል፡፡ ወይንጠጅ ቀለም ባለው በቆሎ ውስጥ የሚገኙ anthocyanins ካንሰር አምጪ ፍሪ ራዲላሎችን እያሳደዱ እንደሚያጠፉ በጥናቱ ላይ ተገልጧል፡፡ የልብን ጤንነት ይጠብቃል እንደ ተመራማሪዎች የጥናት ውጤት ከሆነ የበቆሎ ዘይት ኮሌስትሮልን የመቀነስ ብቃቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ጥቅሙ የተለያዩ የልብ ደም ስር በሽታዎች እንዳይከሰቱ ያደርጋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አነጋጋሪው የኮሮና በሽታ መድሀኒትና እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች ግድፈት - ሰርፀ ደስታ

ሌሎች ጠቀሜታዎች

በበርካታ ሃገራት በቆሎን ጠቀሜታ በተመለከተ ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ በቆሎ ከሌሎች ጥራጥሬዎች ጋር ተቀላቅሎ ለምግብነት ሲቀርብ ሚሰጠው ጥቅም ከፍ እንደሚል በርካታ ጥናቶች አስምረውበታል፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የጥናታቸው ዳራ የተመሰረተው በበቆሎ ውስጥ የሚገኙ ዚንክ፣ ካልሲየም እና አይረን ላይ ሲሆን ፕሮቲኑንም ችላ አላሉትም፡፡

በተለይ በቆሎን በገንፎ መልክ መመገብ ተክሉ የያዘውን ጠቃሚ ንጥረ ነገር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ያስገኛል ብለዋል፡፡

በቆሎና ኤችአይቪ

በተክሉ ዙርያ ከተደረጉ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች አንዱ በቆሎ ፀረ-ኤችአይቪ ባህርይ ሳይኖረው አይቀርም ብሏል፡፡ በቆሎን በየእለቱ መመገብ ከኤችአይቪ ጋር ስላለው ግንኙነት በአግባቡ ለመረዳት ግን ቀጣይ ጥናቶች ያስፈልጉታል ተብሏል፡፡

Share