ዛሬ የዘ-ሐበሻ ድረገጽና ጋዜጣ ስልክ ሲጨናነቅ ነበር የዋለው። “በጃኪ ጎሲ ላይ የመኪና አደጋ ደረሰበት ተብሎ በየፌስቡክና ትዊተር የሚወራው ወሬ ትክክል ነው ወይ? ይህንን አረጋግጡልን” የሚሉ ጥያቄዎች ደርሰውናል። በስልክ ለደወሉልን ሁሉ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የተሰራጩት ዜናዎች ውሸት መሆናቸውን ነገርናል።
ዘ-ሐበሻ ባደረገችው ማጣራት እንዲህ ያለው ተራ አሉባልታ ሲሰራጭ ጃኪ ጎሲ ከዓለም አቀፉ ተወዳጅ ድምጻዊ ኤከን ጋር በመገናኘት በቀጣይ አብረው ስለሚሰሯቸው ሥራዎች እያወሩ ነበር። በኤከን ስቱዲዮ በመገኘትም ጃኪ ከዓለም አቀፉ ድምጻዊና ከኢትዮጵያዊት ሚስቱ ጋር ተጫውቷል።
በሚኒሶታ የፊታችን ቅዳሜ የሙዚቃ ኮንሰርቱን የሚያቀርበው ጃኪ የተወራበት ወሬ ውሸት ሲሆን ድምጻዊው ነገ የሚኒያፖሊስ ኤርፖርት ሲገባ ዘ-ሐበሻ በቪድዮ በመቅረጽ ድምጻዊው የሚለውን ለማሰማት ትሞክራለች።
በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ የታተመውን የሚከተለውን ዘገባ ያንብቡ።
ጥቂት በሚኒሶታ የሙዚቃ ሥራዎቹን ስለሚያቀርበው ጃኪ
ከሊሊ ሞገስ
“ሰላበይ” የሙዚቃ ኮንሰርት በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ስቴቶች እየተደረገ አሁን ሚኒሶታ ደርሷል። የፊታችን ሜይ 31 ወጣቱ ድምጻዊ ጃኪ ከአንጋፋው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ጋር በመሆን ወደ ሚኒሶታ ይመጣል። ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ይኸው ኮንሰርት በሚኒሶታ መደረጉን በማስመልከት የጋዜጣችን አንባቢዎች ስለድምጻዊው ያላቸው ግንዛቤ ያድግ ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት ከሰጣቸውና በአዲስ አበባ ለዘ-ሐበሻ ወኪል ከዚህ ቀደም ከሰጠው ቃለምልልሶች አውጣተን የሚከተለውን ዘገባ ስለጃኪ ጎሲ አቀናብረንላችኋል።
ወደ ሙዚቃ ሕይወቱ እንዴት ገባ?
“በ13 ዓመቴ በህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት እሰራ ነበር፡፡ በቲያትር ቤቱ ውስጥ አማርኛ መዝፈን ጀመርኩ፤ መነሻዬ ያ ነው፡፡ ከዚያ ለሥራ ወደ ጀርመን አገር ሄድኩ፡፡ በሬጌ ባንድ ውስጥ የሬጌ ሙዚቃ እጫዎት ነበር፡፡ ኳየርም ነበርኩ። ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው ወደ አማርኛ ሙዚቃ የተመለስኩት፡፡ ራሴን ካገኘሁ በኋላ ማለት ነው፡፡ ሬጌ ሙዚቃ ዘፍኜ የሚሰጠኝ አስተያየት (ፊድባክ) አሁን እንደሚሰጠኝ አስተያየት አያኮራኝም ነበር። ዛሬ ‹‹ሰላ በይ›› ብዬ ዘፍኜ ከህዝብ የማገኘው ፍቅርና አድናቆት ኩራትና ደስታ ያጎናፅፈኛል፡፡ ራሴን እንደ ባህላዊ ዘፋኝ አድርጌ ብቻ አይደለም የምቆጥረው። በዘመናዊ ሙዚቃ በኩል ትውልዱ ባህሉን እንዲወድ የማድረግ አስተዋፅዖ ለማበርከትም እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ትውልዱ ዘመናዊነትን የሚከተል በመሆኑ ዘመናዊውን ቢሰማ ደስ ይለዋል፣ ሁለቱን በመቀላቀል ባህሉንም በዘዴና በጥበብ የበለጠ እንዲወደው ይሆናል፡፡ ወጣቱ ዘመናዊ ሆኗል፡፡ ቴክኖሎጂ ሲቀየር ሁሉም ሰው እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ ወደ ኋላ ሄዶ የድሮውን ነገር ከሚያይ፣ የድሮው ዛሬ ላይ መጥቶለት ሲያይ የመቀበል ሁኔታው ይጨምራል፡፡ በድምፃዊነት ስሰራ ቲያትር ቤቱ ብቻ የሚያቀርበውን ነበር የምሰራው፡፡ በብዛት “እቴ ሜቴ”፣ “እንዲች እንዲች” የመሳሰሉ የልጆች ዘፈኖችን ነበር የምሰራው፡፡ የፍቅር ከሆነ ደግሞ ስለ እናት ነው፡፡ ለፍቅረኛ ወይም ስለ ፍቅር አልዘፍንም ነበር፡፡ ዕድሜያችን ያንን ለመዝፈን ስለማይፈቅድ፣ የሚመጡትም ወላጆች ከህፃናት ጋር ስለሆነ፣ እነሱን የሚያስተምር ሙዚቃ ነው የምንሰራው፡፡ በዛን ጊዜ በቲያትር ቤቱ ከጎናችን ሆነው ሲያግዙን የነበሩት እነ ሙሉ ገበየሁ፣ ዛሬ እዚህ ለመድረሴ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገውልኛል፡፡ “
እንዴት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ወጣ?
“በ13 ዓመቴ ነው ለስራ የወጣሁት፡፡ መጀመርያ ከተለያዩ ታዋቂ አርቲስቶች ጋር ቲያትር ልናሳይ ወደ ፈረንሳይ ሄድን፡፡ ስራውን ከጨረስን በኋላ አክስት ስለነበረችኝ ወደ ኢትዮጵያ አልተመለስኩም፡፡ ሌሎች ሁለት ጓደኞቼም አልተመለሱም፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ኑሮዬ ውጪ ሆነ ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማዬ እስኪወጣ ድረስ ውጪ ነበር የምኖረው፡፡ ወደ 13 ዓመት ገደማ ውጭ ኖሪያለሁ ማለት ነው።
እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ነው የተማርኩት። ትምህርት ላይ ከልጅነቴ ጀምሮ ሰነፍ ነበርኩ። ሙዚቃ ብቻ ነበር የሚታየኝ፤ሌላ ምንም ነገር አይታየኝም፡፡ ውጪም ሳለሁ ሙሉ በሙሉ ፍላጎቴ ሙዚቃ ላይ ነበር፡፡ የሙዚቃ ስሜቴ ስለበለጠ፣ እንደምንም ገፍቼ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ብቻ ነው የተማርኩት፡፡”
ለምንድን ነው ጃኪ ጎሲ የተባለው?
“ስሜ ጎሳዬ ቀለሙ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ለራሱ መለያ ስም ይሰጣል፡፡ የአርት ስሜ ነው ጃኪ ጎሲ፡፡ በርግጥ ድምፃዊነት የእግዚአብሄር ተሰጥዖ ያስፈልገዋል፡፡ ያንን ጨምረሽ ት/ቤት ስትገቢ፣ ቴክኒካል ነገር ትማሪያለሽ፡፡ ለብዙ ነገር ይረዳል። ተሰጥዖ ብቻውን ምንም አይሰራም፤ተጨማሪ በትምህርት የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ትንፋሽ አያያዝና ዜማ አያያዝ ላይ ትምህርቱ ይረዳል፡፡ ከሁሉም ግን ተፈጥሮ ይቀድማል፡፡
“ወደ አምስት ዘፈኖች አሉኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ያልመጡና ያልተለቀቁ፡፡ እዚህ ይታወቃል ብዬ የማስበው ሶስት ወይንም አራት ዘፈን ሊሆን ይችላል፡፡ ጭራሽ፣ የእኔ አካል፣ ደሞ አፌ፣ ሰላ በይ፣ ባንዲራው የታለ—-እነዚህ ዘፈኖች በደንብ ነው የሚሰሙት—ተጨማሪ የመድረክ ስራዎችንም ይዤ እሄዳለሁ፡፡ የምወዳቸውን የታላላቅ አርቲስቶች ዘፈኖች ጨምሬ ነው የማቀርበው፡፡”
ስለአለባበሱ
እሱ በጣም ብዙ ሰዎችን ይገርማቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዘፈኑን ብቻ የሚያውቁት፣ እኔን በመልክ የማያውቁኝ ሰዎች አሉ፡፡ እና ሰዎች እንደነገሩኝ በፌስቡክ ላይ እኔን ሲፈልጉኝ የሚመጣላቸው የፕሮፋይሌ ፎቶ የሆነ ፍንዳታ የሆነ ልጅና ዘመናዊ አለባበስ ያለው ነው። በዚህ ጊዜ የተሳሳቱ ይመስላቸውና ድጋሚ የሚፈልጉኝ ጊዜ አከ። ምክንያቱም ከዚህ ዓይነት ፍንዳታ ልጅ ያንን ያባህል ሙዚቃ ድምጽ ይወጣል ብለው አይገምቱም። ደጋግመው ይሞክሩኝና ያው ፎቶ ደጋግሞ ሲመጣላቸው ያምናሉ። ሞደርን አገር በመኖሬ በአለባበስና በአንዳንድ ነገሮች የምትወራረሰው ይኖራል። ያንን ወደራሴ ስታይል አምጥቼ በስደርያ በከረባት አድርጌያለሁ። ያ የኔ ውጫዊ ገጽታ ነው። ውስጤ ግን ባህላዊ ነው። የኢትዮጵያዊነትን አዘፋፈንኔን አለቀቅኩምል። በእንግሊዘኛ ሬጌ ወየንም አር አኤንድ ቢ መዝፈን እችላለሁ። ግን በዚህ አለባበስ ሬጌ ብዘፍን ተቀባይነት ላይኖረኝ ይችላል። አለባበሴና ባህላዊ መዚቃዬ አብሮ ላይሄድ ይችላል። እኔም አብሮ አለመሄዱን እፈልገዋለሁ። ግዴታ ደበሎ ለብሼ ባህላዊ ሙዚቃ መጫወት የለብኝም። እኔ ደገሞ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተወለድኩም። አዲስ አበባ ተወለጄ እዚሁ ያደግኩ ነኝ። በመሆኑም የገጠሩን ልብስ ብለብሰውም እኔ አይደለሁም። እኔን የሚገልጸው የከተሜው አለባበስ ነው። በተጨማሪም ትንሽ ለየት ለማለት ስል ነው ይህን የምለብሰው።
ይህ አለባበሴ ይቀጥላል። አዎ! ይሄም ብቻ ሳይሆን የእኔ የሆነ ዳንስም መፍጠር እፈልጋለሁ። ‹‹ጭራሽ›› ቪዲዮ ክሊፔ ላይ እንዳየኸውው አይነት ዳንስ መስራትና ያ ዳንስ የጃኪ ዳንስ ተብሎ ቢደነስና የጃኪ ስታይል ተብሎ ቢለበስ እመኛለሁ፡፡ የእኔ ቢሆን የምለው የባህላዊና ዘመናዊ ቅልቅል ስታይሌን ነው፡፡ በዳንስም ባህላዊውንና ዘመናዊውን አጣምሬ እየሰራሁ ሲሆን ወደፊትም በዚሁ የምቀጥል ይመስለኛል።
በአውሮፓ መደበኛ ሥራው ምንድን ነው?
“ሥራዬ ሬጌ ባንድ ውስጥ ነበር፤ አሁን ትቼዋለሁ፡፡ ‹‹ጭራሽ›› የሚለውን ዘፈኔን እስከሰራ ድረስ ከነሱ ጋር ነበርኩ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ብዙ ታዋቂ የሬጌ ዘፋኞች አሉ..ያ የእኔ ባህል አይደለም፤ የነሱ ባህል ነው፡፡ ብታወቅበትም ሪፕረዘንት አላደርግበትም፤እኔነቴን ስለማይገልፀው ይሆናል። ኢትዮጵያዊነቱን ይዤ የራሳችንን ባህል ትንሽ አሳድጌው ወጣቱ ትውልድም ሆነ ትላልቁ ሰው እንዲወደው ማድረግ ለእኔ አንድ ሃላፊነት ነው፡፡ ናይት ክለብ ላልልሽው አልሰራም፡፡
በባህላዊ ዘፈን ላይ ዘመናዊ ዳንስ ነው የምደንሰው፡፡ ባህሉን ለማበላሸት ወይም ለመበረዝ አይደለም ዓላማዬ፡፡ ቢቱ ትክክለኛ ነው፤ አልቀየርነውም፡፡ ማሲንቆ አለው፡፡ ዜማ አወጣጤ የኢትዮጵያ ቀለም አለው፡፡ የቀየርነው ስታይሌንና አደናነሴን ነው፡፡ ያን ያደረግሁት ደግሞ ትውልዱን በዘመናዊ እንቅስቃሴ ለመሳብና ዘፈኑ ውስጣቸው ገብቶ እንዲወዱት፣እንዲኮሩበት ነው። ነጮች እንዲያዩትም ብዬ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባህላዊ ሙዚቃ እየጠፋ ነው፡፡ ትላልቅ ክለቦች ብትሄጂ ..ባህላዊ ሙዚቃ መክፈት ሃጢያት ነው የሚመስላቸው፡፡ ከውጪ መጥቼ አንዳንድ ጊዜ ትላልቅ ክለብ ስሄድ፣ የውጪ ዘፈን ብቻ ነው የሚደመጠው፡፡ አገሬ ላይ ሳይሆን እዛው ያለሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ እና ውስጤ ዘመናዊነትም ባህላዊነትም አለ፡፡ ያንን አቀናጅቼ ውጤት ለማምጣት ነው የሞከርኩት፡፡ ያንንም አምጥቼዋለሁ፡፡
እስክስታ የት ለመደ?
እስክስታ የለመድኩት ከ“ሶራዎች” ነው፡፡ ለ“ሰላ በይ” የሙዚቃ ክሊፕ ለመስራት ገጠር ሄደን ነው የ“ሶራ”ን ባንድ ያየሁት፡፡ በጣም ተደነቅሁኝ። “ሶራ”ን ይዘው ሲመጡ ለእኔ አዲስ ነገር ነበር — ከተለመደው ውጪ ስለሆነ፡፡ ደስ የሚል የእስክስታ አብዮት (ሪቮሉሽን) ነው የፈጠሩት፡፡ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የትም ብትሄጂ ደግሞ የእነሱ ተፅዕኖ አለበት። በሁሉም ቦታ እንደዚህ ዓይነት ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ .“ሶራ” ባይቀጥልም ሌላ ሪቮሉሽን ያስፈልጋል፡፡
“ሰላ በይ” ማለት ነፈታ በይ፣ አንቺ ፈታ ካልሽ ፍቅርም ይፍታታል። ሰላ ካልሽ በመካከላችን ፍቅርና ሰላም ይወርዳል—ነገር አለማክረር ማለት ነው፡፡
የሚያደንቀው አርቲስት?
በሰሜን አሜሪካ ከዝነኛው ቴዎድሮስ ታደሰ ጋር ሥራዎቹን እያቀረበ የሚገኘው ጃኪ ከዚህ ቀደም ከፍቅረአዲስ ነቅ ጥበብ እንዲሁም ከሄለን በርሄ ጋር ዱባይና አቡዳቢ ላይ ሰርቷል፤ ከጂጂ ጋር ጀርመንና ሆላንድ ዘፍኗል። ሌላስ?
“ ብዙ ታዋቂ ሳልሆን ደግሞ ከአስቴር አወቀ ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ሁሉም አበረታተውኛል፡፡ አስቴር አወቀ ‹‹ልጅ ነህ በርታ፤ጥሩ ነው ያለኸው›› ብላኛለች። ጂጂ እንደውም ከማደንቃት ነገር— ያኔ እኔ ሃሳቤ ሁሉ በሬጌ ውስጥ ስለነበር—አንድ አማርኛ ሬጌ ዘፍኜላት “በጣም አሪፍ ነው” ብላ እንደውም ማሲንቆ ክተትበት አለችኝ፡፡ ሬጌ ዘፈኑ ላይ እኮ ነው። በጣም አልረሳትም፡፡ ማሲንቆ እዚህ አገር ርካሽ ተደርጎ ነው የሚቆጥረው፤ሰው ዋጋውን በደንብ አላወቀውም። ውጪ አገር ግን አነጋጋሪ ነው፡፡ ማሲንቆ ስሰማ ሊወረኝ ይችላል፡፡ ባህል ሙዚቃ ውስጥ ማሲንቆ ነው ትልቅ ሚና የሚጫወተው፡፡ ማሲንቆ መጫወት ብችል ደስ ይለኛል፡፡ ኪቦርድ እሞክራለሁ፣ ቦክስ ጊተር እየተማርኩ ነው፡፡
ንቅሳቱ ትርጉም አለው?
አዎ፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ጀርመን የተነቀስኩት፡፡ እጄ ላይ በህይወት የሌሉትን የእናትና አባቴን ስም ነው የተነቀስኩት፡፡ አንገቴ ላይ ደግሞ የሙዚቃ ኖታ ነው፡፡ ሙዚቃ ህይወቴ የሚለውን ለመጠቆም፡፡ በዚች ምድር ላይ የምወዳቸውን ሶስት ነገሮች ነው የተነቀስኩት፡፡
ፍቅረኛ አለው?
“የለኝም፡፡ ለጊዜው ፍቅረኛዬ ሙዚቃ ናት” ይለናል።
ቅዳሜ ሜይ 31 ቀን 2014 የጃኪ የሙዚቃ ኮንሰርት በሚኒሶታ የሚደረግበት አድራሻ፦
Mill City Nights
111 5th St N, Minneapolis, MN 55403