ለዘንድሮው በዓል ክብረ በዓል በመላ ሀገሪቱ ከግማሽ ቢልዮን (500 ሚልዮን) ብር በላይ ወጪ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም።ህዝቡ የመሰረታዊ ፍጆታዎችን የመግዛት አቅሙ ተዳክሟል።ቀድሞ እናት ልጇን እንጀራ በሽሮ ብቻ ማብላቷ ያሳስባት ነበር።ዛሬ ይህ ዘመን በተለይ በከተሞች አካባቢ በቁጥርም ከፍተኛ በሆነው ሕዝብ ዘንድ ችግሩ ከፍቶ ዳቦ ገዝቶ ማብላት ከባድ ሸክም ሆኗል።አብዛኛው ሕዝብ ስለ ዳቦ ብቻ አይደለም ጭንቀቱ።የሚጠጣ ውሃም ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚናፍቀው እና ለማግኘት የሚታትርበት አንዱ ተግባሩ ሆኗል የውሃ ነገር።ውሃ ፍለጋ ጀርካል ይዘው የሚንከራተቱ ሕፃናት እና እናቶችን ማየት የተለመደ ነው።በአዲስ አበባ ብቻ አደለም ሐረር፣ድሬዳዋ፣ሐዋሳ እና በርካታ ከተሞች የውሃ እጥረት ላይ ናቸው።
ይህ ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍጆታ አንፃር ብቻ የምናየው ኢህአዲግ/ወያኔ 23 ዓመት ሙሉ ሊያስተካክለው ያልቻለውን ጉዳይ ጠቀስኩ እንጂ ባለፉት 23 ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ በፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ዘርፍ ሁሉ ወደ አደገኛ መንገድ እያመራች ነው።እርግጥ ነው ከስርዓቱ በመጠቀማቸው የሀገራቸውን ችግር እና የሌላውን እሪታ ላለመስማት የወሰኑ ወገኖች የሚሉት በተቃራኒው ነው።እውነታው ግን ከእነርሱ አስተሳሰብ ብዙ የራቀ ነው።
ፖለቲካው
– ፖለቲካው በጥቂት በጎሳ የሚያምኑ ኢትዮጵያዊነትን በሚያጥላሉ እና የጎሳ ግጭትን ለመለኮስ እስከ 20 ሚልዮን ብር አውጥተው የእጅ እና የጡት ሃውልት በሚሰሩ ጉድ አመራር ስር ነው፣
– ፖለቲካው ለኢህአዲግ/ወያኔ ማጎብደድ እና መልመጥመጥን ብቻ እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ እና በዙርያው ተስፋ ቢስ ግን ለገንዘብ እና ለጥቅም ባደገደጉ አድር ባዮች ተከቧል፣
– ፖለቲካው ዲሞክራሲ ላይ እየተሳለቁ እና እያፌዙ በሚናገሩ የተቀመጡበትን የህዝብ ትከሻ በዘነጉ ባለግዜዎች ተተራምሷል፣
– ፖለቲካው በአንድ ወቅት በጠበንጃ ስልጣን በያዙ ኃይሎች ስር ወድቆ ለዘላለም ገዢዎች እኛ ነን ብለው እራሳቸውን በሾሙ ሹመኞች ተይዟል።
ምጣኔ ሃብቱ –
– ምጣኔ ሃብቱ አቅጣጫውን የማያውቅ በፖለቲካው እና በጎሳቸው ስም በተሰበሰቡ ግለሰቦች ፍላጎት እንጂ በሀገር ራዕይ እና እድገት መሰረት አይመራም፣
– ምጣኔ ሃብቱ ከ70 በመቶ በላይ በስርዓቱ ስር በተደራጁ ኩባንያዎች የሚሽከረከር እና ሀብት ለማጋበስ ባሰፈሰፉ የውጭ ጥቅመኞቹ እየታገዘ በአስፈሪ እና አደገኛ ኃይሎች እየተሽከረከረ ነው።
– ምጣኔ ሃብቱ ሙስና የገንዘብ ብቸኛ ምንጫቸው የሁኑ ግለሰቦች ኢንቨስተር ተብለው የሚጠሩበት ነው፣
– ምጣኔ ሃብቱ ብሔራዊ ባንክ የተጭበረበረ ወርቅ ከመግዛት አንስቶ እስከ ግምሩክ ኃላፊ ድረስ በሀብት የሚ ምነሸነሹበት ተቋማት ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከምንገምተው በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነች
ኢህአዲግ ኢትዮጵያን የዛሬ 23 ዓመት ከነበረችበት ከፍ አደረኩ እያለ ቢናገርም ዕውነታው ኢትዮጵያ ከምንገምተው በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነች።ከምጣኔ ሃብቱ እና ከፖለቲካው የተገለለው ሕዝብ ምሬቱ ገፍቶ የሚወስደው ጫፍ ለማወቅ ይከብዳል።የእዚህ ዓይነቱ ምሬት የኃይል እርምጃም ስለማይቀርለት ከትናንቱ ይልቅ መጪው አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል።
የዘንድሮው ግንቦት 20 እንደባለፈው ሁሉ ካለፈው ይልቅ መጪውን አስፈሪ አድርጎታል።ሃያ ሶስት ዓመት ደቡብ ኮርያ እና ብራዚል የድሃ ህዝባቸውን ቁጥር ቀንሰው ሀብት በፍትሃዊነት እንዲከፋፈል ያደረጉበት እረጅም የተባለ ብዙ ታምር የሚሰራባቸው ዓመታት ናቸው።በኢትዮጵያ ደግሞ 23 ዓመታት ሀብት የተወሰኑ ቡድኖች ውስጥ የተሰበሰበበት፣ ከአስር ሺዎች ወደ መቶ ሺህ ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑባቸው ዓመታት ናቸው።ህንፃ እና መንገድ መስራት ሕዝብ ማስተዳደር አደለም።የአረና አባል አቶ አሰግደ እንዳሉት ”መንገድ መስራት አስደናቂ ነገር አደለም።ጣልያን በአምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ቆይታው ከስድስት ሺ ኪ ሜትር በላይ መንገድ ሰርቷል።ይህንን ማድረጉ ፋሽሽታዊ ስራው ይቀጥል አያስብልም።
የሆነው ሆኖ ኢህአዲግ ከ70 ዓመት በፊት በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን በተገነባ ስታዲዮም ውስጥ ሆኖ ግንቦት ሃያን እያከበረ ኢትዮጵያ አድጋለች ይላል።ከየቀበሌው እና ትምህርት ቤቶች በልፈፋ አዲስ አበባ ስታድዮም ውስጥ ለተሰበሰበው ሕዝብ አቶ ኃይለማርያም ሲናገሩ ”በምግብ እራሳችንን ችለናል” ሲሉ ተደምጠዋል።”የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” እና ይችን ንግግር በመጪው የእህል መሰብሰብያ ወቅት ላይ እንደማይደግሙት እራሳቸውም ያውቁታል።እንዳፋቸው ቢሆንልን ጥሩ ነበር።እውነታውን እርሳቸው የቤተ መንግስት እንጀራ ከሚበሉት ይልቅ የሚያውቀው ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።
ለዘንድሮው በዓል ክብረ በዓል በመላ ሀገሪቱ ከግማሽ ቢልዮን (500 ሚልዮን) ብር በላይ ወጪ እንደሆነ እየተነገረ ነው።የግማሽ ቢልዮን ብር ብክነትን አስቡ እና በውሃ ጥም የሚንከራተቱ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎችን አስቡ።ስንቱ በእዚህ ገንዘብ ንፁህ ውሃ ባገኘበት ነበር። ስንት ገበሬ ከባህላዊ የበሬ አስተራረስ ወደተሻሻለ የትራክተር ማረሻ በተሻገረበት ነበር።ከሃያ ሶስት ዓመታት በኃላም በበሬ እያረስን ነው።ቀ 3 አመታት በኃላም ኢህአዲግ/ወያኔ ከ70 ዓመት በፊት በተሰራ ስታድዮም ውስጥ ሆኖ አደጋችሁ እያሉ መፎከር የጤና ይሆን?
ጉዳያችን
ግንቦት 20/2006 ዓም/ ሜይ 28/2014
Source: gudayachn