አስፈላጊው ለውጥ ፣ መጭው ምርጫና የተቃዋሚዎች “መሳተፍ” ጉዳይ

በናትናኤል ካብትይመር (ኦስሎ ኖርዌይ)

(ናትናኤል ካፕትይመር)የሰው ልጅ ግላዊና ማህበራዊ ህይወቱን ለማሻሻል እንዲሁም የለት ተለት ህይወቱን የተሻለ ለማድረግ በአካባቢው ወይም በሚኖርበት ሃገር ያለውን አካባቢያዊና መንግስታዊ ስርዓት ጤናማ መሆኑ ግድ ነው። የማህበረሰቡም የለት ተለት ህይወት ከግዜ ወደ ግዜ አስቸጋሪ እየሆነ ሲሄድ የዛ ማህበረሰብ መንግስት ወይም አገዛዝ መቀየሩ አንደኛው መፍትሄ ነው። እንደሁለተኛ አማራጭ መፍትሄ የሚወሰደው ደግሞ የነበረውን አገዛዝ ለአነስተኛና ከፍተኛ ለውጦች ካለው ምቹነት አንፃር ተመዝኖ አስፈላጊ የሚባሉ የፖሊሲና የመንግስታዊ አወቃቀር ለውጦችን መተግበር ሲሆን ይህም በሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ጥሩ ሊባል የሚችል ለውጥ ሲያስገኝ ተስተውሏል።

ነገር ግን ወደ ሃገራችን መንግስት ስንመጣ ከበድ ያሉ የማስተካከያ መፍትሄዎችን ቀርቶ እጅግ አነስተኛ የሚባሉ የማህበረሰብ የመብት ጥያቄዎችን እንኳን በሃይል በመጨፍለቅ ሃገራዊና ማህበረሰባዊ ችግሮችን ይበልጡን እያወሳሰበ ይገኛል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ የአለማችን ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ ዝንባሌው ከታችኛ ረድፍ ላይ ያሉትን ሃገራት የወደፊት እጣ ፈንታ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ እንድምታ እየተስተዋለበት ነው። ባለፉት ግዜያት በመጨረሻው ረድፍ ላይ ያሉ ሃገራት “ከድህነት ወለል በታች ያሉ ሃገራት” ተብለውም ቢሆን እንደሃገር ይመደቡ ነበር። ነገር ግን ከግዜ ወደ ግዜ ይህ እየተቀየረ እየሄደ ይገኛል። “ከድህነት ወለል በታች ያሉ ሃገራት” ከሚባሉት ውስጥ የተወሰኑ ሃገራት (Failed States) የሚባለው ምድብ ውስጥ እየገቡ ነው። ይህ ማለት በቀላል ማጠቃለያ በሚመጡት ግዜያት እንደ ከዚህ ቀደሙ ደሃ ሃገር ሆኖ መኖር ወደ የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ገብቷል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከመቼውም ግዜ በላይ የለውጥን አፋጣኝ አስፈላጊነት የሚያመላክት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ልማታዊው ጓደኛዬ - ከዋስይሁን ተስፋዬ

ከዚህ ቀደም በአለማችን ታሪክ ለውጥ በተለያዩ መንገዶች ሲካሄድ አስተውለናል ፡ ለአብነት ለመጥቀስም ያህል የነበሩትን ስርዓቶች ጭርሱን በማጥፋት ሌላ ስርዓት መገንባት አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ በነበረው ስርዓት ላይ ግጭቶችንና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶችን አቻችሎ ህዝብ በምርጫ መሪዎቹን የሚመርጥበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። በወያኔ ኢህአዴግ ስርዓት ህዝባችን በትዕግስትና በጨዋነት የለውጥን አስፈላጊነት አምኖ ፣ የምርጫን ምንነት ተረድቶ ፣ ይሆኑኛል ያላቸውን መሪዎቹን በተስፋ ሲመርጥ በምርጫ 97 አይተናል። ነገር ግን አሁንም ባባሰ መልኩ የህዝብ መብትና ፍላጎት ታፍኖ ህዝብና ሃገር በጉልበተኞች አምባገነናዊ ጭቆና ስር እየማቀቁ ይገኛሉ።

የወያኔ መንግስት ምርጫውን ብቻውን ሊያረገው አይፈልግም የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለይስሙላና ለውጭ ታዛቢዎች ማታለያ እንደሚጠቀመው የሚጠበቅ የተለመደ አካሄዱ ነው። የወያኔ መንግስት ለሃገር እድገትና ለህዝብ መብት መከበር ለሚጥሩ አማራጭ ሃይሎች ህዝብ የሰጣቸውንና የሚገባቸውን የህዝብ ውክልና መቀመጫ በጉልበት እንደነጠቃቸውም የከዚህ ቀደም ተሞክሮን ማስታወስ በቂ ነው። ታዲያ በዚህ መሰል የይስሙላ ምርጫ መሳተፍ ፋይዳው ምንድነው።

መጭው ምርጫን መሳተፍ ማለት ለወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በረሀብ ፣ በጥማት ፣ በእርዛትና በዲሞክራሲ እጦት አሰቃይ ብሎ ፍቃድ እንደመስጠት ነው፡፡ ምርጫ እኮ የህዝብን ፍላጎት መጠየቂያ ነፃ የሆነ የዲሞክራሲ መንገድ ነው እንጂ የመርሀግበር ማሟያ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ካለፉት ምርጫዎች የተወሰኑ ኩነቶች ማንሳት ይቻላል።

ምርጫ 97፡ በተነጻጻሪ የተሻለ ዲሞክራሲ የታየበት ነው ሲባል ይደመጣል ፡ በእርግጥ ወያኔ ለዲሞክራሲ እና ነፃ ምርጫ ዝግጁ ስለነበር ነው ወይስ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሄድኩ ብሎ ደጅ የሚጠናቸውን ምዕራብያዊያንን ልብ ለማለስለስ? ለዚህ ጥያቄ አዘል እይታ እንደ ዋና ማሳያ ሊሆነን የሚችለው ከምርጫው በኋላ ወያኔ የተከተለው የጭካኔ ግድያ ነው፡፡ ስለዚህም ወያኔ ምርጫን መሰረት አድርጎ ለሚመጣ ማንኛውም የስልጣን ሽግግር ያልተዘጋጀና ተቃዋሚዎችም ህዝቡ በሰጣቸው ድምጽ ሳይሆን ወያኔ ተምኖ በሰጣቸው ወንበር ፓርላማ ተቀምጠው ምንም ፋይዳ የሌለው የተቃውሞ እና የድምጸ ተዓቅቦ እጅ የማስቆጠር ስራ ብቻ እንዲሰሩ ስለሚፈልግ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወደነገ ለመድረስ፣ ዛሬን ማለፍ ግዴታ ነው። ዛሬ! አማራ በሕዝብ አመፅ የተደገፈ የትጥቅ ትግል ከማድረግ ውጭ አማራጭ የለውም።

ምርጫ 2002፡ ወያኔ ከምርጫ 97 ትምህርት በመውሰድ ከምርጫ በኋላ የሚመጣን ስልጣን የማጣት ስጋት ለማስወገድ በከፍተኛ ሁኔታ የተዘጋጀበት ነው፡፡ ይህ ምርጫ ወያኔ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያልተዘጋጀ መሆኑ በተጨባጭ የታየበት እና ምርጫ 97 ካጋለጠበት ትክክለኛው ፀረ-ደሞክራሲያዊነት ባህሪው በባሰ መልኩ ምርጫውን ከጅምሩ በቁጥጥር ስር በማዋል ጭቆና እና የመብት ረገጣ እለታዊ የኑሮ አካል በሆነባት ኢትዮጵያ በምርጫ ታሪክ ያልታየ የምርጫ ውጤት ሲመዘገብ አይተናል፡፡

መጭው ምርጫ 2007፡ ምርጫ 2002 በአጠቃላይ ሲታይ ለወያኔው ጨቋኝ መንግስት ከጠበቀው በላይ ቢሆንም ውጤቱ ፀረ-ዲሞክራሲያዊነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳየበት መሆኑ ለመጭው ምርጫ 2007 እንዳንድ ማስተካከያ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ለመገመት ያህልም በመጭው ምርጫ ወያኔ የተወሰኑ ወንበሮችን “ታማኝ” ለሚላቸው ተቃዋሚዎች ለመስጠት የሚያስብ ይመስለኛል፡፡ በዚህ መሰረተ የስልጣን እድሜውን እያራዘመ እና የውሸት ፕሮፓጋንዳውን እየነዛ በኢትዮጵያውያን ላይ ገደብ አልባ ገዥነቱን የሚያውጅ መሆኑ ማንም ሊገነዘበው የሚችል ሀቅ ነው፡፡

ተቃዋሚዎች ለመጭው ምርጫ መዘጋጀት ያለባቸው እንደቀድሞው “ተሳትፎ ለመሸነፍ” ከሆነ የወያኔ የጭቆና አጋፋሪ ከመሆን የዘለለ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈይዱለት አንዳች ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የህዝቡን ሮሮ፣ ችግር፣ የመብት ረገጣ እና ጭቆና ማዳመጥ እና ታግሎ ህዝብን በማታገል መፍትሄ የማምጣት ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ስለዚህም መጭውን ምርጫ አለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን ምርጫው እንደቀደሙት ምርጫዎች የህዝብ መብትን ማፈኛ እንዳይሆን መታገል አለባቸው፡፡ ከወያኔ በስተቀር ለማንኛውም የኢትዮጵያን ህዝብ እወክላለው ለሚል ተቃዋሚ ፓርቲ የጋራ አጀንዳ መሆን ያለበት በህዝብ እየተቀለደ የሚደረግ የይስሙላ ምርጫ እንዳይካሄድ ማድረግ ነው፡፡ ሥለዚህም መጭው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎችና ለህዝብ የቆሙ ሀቀኛ ጋዜጠኞች ሳይፈቱ ፣ ለወያኔ በግልጽ የሚያዳሉና አሳሪ የሆኑትን “የምርጫ ህጎች” ሳይሻሻሉ እንዲሁም ሌሎች መሻሻል ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ አለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን የምርጫው ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ ምርጫው እንዳይካሔድ ህዝቡን በነቂስ በመቀስቀስ የታሰበውን የይስሙላ ምርጫ ማስቆም አለባቸው፡፡ አዎ ይህ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሚቀለድበት እንዲሆን ማናችንም መፍቀድ የለብንም፡፡ ይህ ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች ከሚካሄድ ይልቅ ምርጫው ቀርቶ ለአለም የኢትዮጵያዊያንን ችግርና የጨቋኙን የወያኔን ትክክለኛ ማንነት ማሳወቅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛ የስልጣን ባለቤትነቱን ወያኔ ባዘጋጀው የይስሙላ ምርጫ ሳይሆን ነፃ የሆነ በሁሉም ተወዳዳሪዎች ይሁንታ ያገኘ አካል በሚያካሂደው እውነተኛ ምርጫ እንዲሆን ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ነጻ ምርጫ ለማካሄድ ጭርሱንም ፍላጎት ስለሌለው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ ደርሰው ለፌዴራሊዝም ጠበቃ ነን ሲሉ ለእኔ የሚመስለኝ ኢትዮጵያውያን ላይ ማሾፍ ነው” - ዶክተር ዓለሙ ስሜ በጠ/ሚ ጽ/ቤት ሚኒስትር

ውድቀት ለአምባገነኖች !!

1 Comment

  1. Common! Be creative. Boycotting only made dictators stronger. So boycotting did not work for the people in the past and will not work now. Learn from past mistake. Do not repeat failed thinking and expect different result. It is only insane people keep repeating the same idea and expect a different result.

Comments are closed.

Share