‹‹99.9% አሰልጣኞች የባርሴሎናን አጨዋወት ለመቅዳት እየጣሩ ነው›› ሉዊስ ሴዛር ሜኖቲ

በ1978 አርጀንቲናን በአሰልጣኝነት ለዓለም ዋንጫ እየመሩ የሻምፒዮንነቱን ዘውድ እንድትደፋ አድርገዋል፡፡ ከ1983-1984 ደግሞ ባርሴሎናን አሰልጥነዋል፡፡ የሴዛር ሉዊስ ሜኖቲን አገልግሎት ያገኙ ክለቦች ብዛት ያላቸው ቢሆኑም በዋነኝነት ሪቨር ፕሌት፣ ቦካ ጁኒየርስና ሳንቶስ ጎላ ብለው ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ ሜኖቲ ከስፔኑ ኤል ፓይስ ጋዜጣ ጋር ተፈቃሪ ስለሆነው የጋርዲዮላ አጨዋወት፣ አርጀንቲናዊያን በሜሲ ዙሪያ ስላላቸው ጥላቻ እና በዘመናው እግርኳስ ሞውሪንሆ ስለፈጠሩት ተፅዕኖ ተወያይተዋል፡፡

ሉዊስ ሴዛር ሜኖቲ
‹‹99.9% አሰልጣኞች የባርሴሎናን አጨዋወት ለመቅዳት እየጣሩ ነው፡፡››

በ1938 በሮዛሪዮ-አርጀንቲና የተወሰዱት ‹‹ኤል ፍላኮ›› (ቀጫጫው) ከእግርኳስ ታላላቅ ተናጋሪ ፈላስፋዎች አንዱ ናቸው፡፡ በኤልፓይስ ጋዜጠኛ ጋር በተገናኙበት ወቅት ስለ ኮፓ አሜሪካ የብሔራዊ ቡድናቸው የወቅቱ የጨዋታ እቅድ ምን እንደሆነና የጋርዲዮላ ባርሴሎና እና የሞውሪንሆ ሪያል ማድሪድ ስለሚከተሉት የአጨዋወት ዘይቤ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ እና ሜኖቲ የተገናኙት ቡዌኖስ አይሬስ ውስጥ በሚገኘው ቢሯቸው ነበር፡፡ የዕለቱ አየር ቅዝቃዜ አጥንት ቢሰብርም በአሰልጣኙ ቢሮ የሚገኘው ምድጃ አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡ ስለዚህ ሜኖቲ እንግዶቻቸውን ይቅርታ መጠየቅ ነበረባቸው፡፡
‹‹ዛሬ ማለዳ ላይ ምድጃው ተሰበረብኝ፡፡ አዲስ መግዛት ይኖርብኛል፡፡ ቅዝቃዜውን መቋቋም አልቻልኩም›› በማለት ሰበባቸውን አከል አድርገዋል፡፡ ከመስተዋት በተሰራው ጠረጴዛ ላይ ልጆቻቸው እንደሆኑ የሚናገሩት ብዛት ያላቸው ፎቶግራፎች ተቀምጠዋል፡፡ በአንድ ወገን ደግሞ ብዙ መጽሐፍት ተከምረዋል፡፡ በቀኝ በኩል ዘና በሚያደርገው ወንበር ፊት ለፊት ንፁህ የሆነ የሲጋራ መተርኮሻ ተቀምጧል፡፡ ንጽህናው በከባድ የሲጋራ ሱሰኝነት ይታወቁ የነበሩት አርጀንቲናዊ ማጤስ ለማቆማቸው ማረጋገጫ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ሲጋራ ለማቆም አልተቸገሩም?
መልስ፡- ተቸግሬያለሁ፡፡ ማጤስ ያቆሙበት የመጀመሪያ ወር አስቸጋሪ እንደሚሆንና ከዚያ በኋላ ግን (እንደሚለመድ) ዶክተሮች ነግረውኝ ነበር፡፡ ግን በእያንዳንዱ ወር ሱሱ እየበረታ እንዳጨስ ተገፋፍቼ ነበር፡፡ ዶክተሮች (የሰዎችን) ህይወት ለማራዘምና በደስተኛነት ለመምራትም እንደሚሰሩ ይናገራሉ፡፡ አይደለም፡፡ እንዲያውም ስራቸው ህይወታችንን መራራ ማድረግ ነው ባይ ነኝ፡፡ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ደግሞ ይበላሉ፡፡ አሁን ጊዜው ተሻሽሎ ለቀዶ ጥገና አነስተኛ ማሽን ይጠቀማሉ፡፡ ልክ የህፃን ልጅ መጫወቻ ትመስላለች፡፡ ቀዶ ጥገናው በዚያችው መሳሪያ ይከናወናል፡፡ በቀስታ የሚደረገው የቀድሞው ኦፕሬሽን አሁን የለም፡፡ በቀዶ ጥገናው ክፍል ውስጥ ደም እንኳን አታይም፡፡ (ሜኖቲ በቅርቡ የሣንባ ካንሰር ቀዶ ህክምና አድርገው ነበር)
ጥያቄ፡- ከቀዶ ጥገናው በኋላስ…?
መልስ፡- ህክምናው ቀላል ነበር፡፡ ለሶስት ቀናት ያህል በሆስፒታል ቆየሁ፡፡ ከቀላልነቱ የተነሳ ነገሩ የተወገደልኝ እንኳን አልመሰለኝም ነበር፡፡ ሐኪሙ ስለህክምና ያወራልኛል፡፡ ‹‹ይህ የእናንተ ኃላፊነት ነው፡፡ እኔ ስለ እግርኳስ እንጂ ስለ ሣንባ አላውቅም›› በማለት ነገርኩት፡፡ ከዚያም ሲጋራ እንዳላጤስ መከረኝ፡፡ ካመቆምኩ ጤናማ የሆነ ህይወት እንደምመራ አስታወቀኝ፡፡ የተለመደ (ጤናማ) ህይወት ምን ማለት ነው? እኔ ጤናማ የምለው ህይወት እርሱ እንደሚለው አይነት አይደለም፡፡ ለሱሰኛ ግለሰብ ሲጋራ ድንቅ ወዳጅ ነው፡፡ የልብ ጓደኛዬ የተለየኝ ያህል ይሰማኛል፡፡ እንደ ሞተና ተመልሶ እንደማይመጣ…፡፡ በተለይ ብቻዬን ስሆንና ብዙ በምፅፍበት ጊዜ ትምባሆ ይበልጥ ይናፍቀኛል፡፡ የሲጋራ ጤስ በፊቴ ላይ ሲንቦለቦል እርካታ ይሰማኛል፡፡ የጢሱን ሽውታ በሬስቶራንቶች በር ላይ እፈልገዋለሁ፡፡ ትናንት በአንድ ቡና ቤት (ምን ገጠመኝ መሰለህ…) አንድ ሰው ‹‹ቆይ ወጣ ብዬ አጭሼ ልመለስ›› ሲለኝ፤ ‹‹ኖ ይልቅስ በቻልከው መጠን ቀርበኸኝ አጭስ›› አልኩት…፡፡
ጥያቄ፡- እግር ኳስንም እንዲሁ ትተውታል?
መልስ፡- ከባለቤቱ እጅ ላይ የተሰረቀውን እግር ኳስ ለማዳን የሚደረገው ትግል አጋር ስትሆን ምላሽ ታገኛለህ፡፡ ሁራካን የአርጀንቲናን እግርኳስ እንደታደገው ሁሉ ስፔንም ታጽናናኛለች፡፡ ይህ ደግሞ ለስፖርቱ ያለኝን ፍቅር መልሶልኛል፡፡ እነርሱ እንደ ህፃናት ነፃ ሆነው ሲጫወቱ መመልከት ትንሽ ምቾት ይሰጠኛል፡፡ እኔን እንዲያታልለኝ የምፈቅድለት ብቸኛው ነገር እግርኳስ ነው፡፡ እግር ኳስ ሶስት ነገር ነው፡፡ ጊዜ፣ ቦታ እና ማጭበርበር፡፡ ነገር ግን አሁን ጊዜ የለም፣ ቦታዎችም አይገኙም፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኋላ ፉትቦል እኔን ሊያጭበረብረኝ አይችልም፡፡ እግር ኳስ ብለው የሚጠሩት ጨዋታ እግር ኳስ ሳይሆን ሲቀር አዝናለሁ፡፡ 99.9 በመቶ የአሰልጣኞች ህይወት የባርሴሎናን አጨዋወት ለመቅዳት የሚጥር ነው፡፡ ሁሉም ጋርዲዮላን ለመሆን ይመኛል፡፡ ብዙዎቹ ግን እንዴት መሆን እንደሚችሉ አያውቁትም፡፡
ጥያቄ፡- ይህን የሚሉት ታላላቅ ተጨዋቾችን ይዘው ነው…
መልስ፡- አይደለም፡፡ የፈተናን መልስ የሚገዛ ደደብ ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ እንዲህ አይነት አይደለሁም፡፡ (ጋርዲዮላ) ትላልቅ ተጨዋቾች ስላሉት ብቻ በሜዳ ጠርዝ ላይ ቆሞ ዝም ብሎ አሁንም አሁንም ተቀባብሎ እያለ የሚጮህ ሰው አይደለም፡፡ የጋርዲዮላ ስትራቴጂ ከዚህም በላይ ውስብስብ ነው፡፡ ይህ የስልጠና፣ የግልፅ አስተሳሰብና ተጨዋቾችን የደጋፊዎቻቸውን ፍላጎት ተረድተው እንዲጫወቱ የማድረግ ፍላጎትን የማስረፅ ውጤት ነው፡፡ ጋርዲዮላ ተጨዋቾቹን ከእነርሱም በላይ ጠቃሚ መሆኑን አስገንዝቧቸዋል፡፡ ግን ጋርዲዮላ የሚናገረው ተቃራኒውን ነው፡፡ ራሱ ምርጥ ስለመሆኑ እንኳን አያምንም፡፡ ከጋርዲዮላ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ፔኬ፣ ፔድሮ እና ቡስኬት ምን እንደነበሩ እናስብ፡፡ ከኢንዬሽታ ጋር በቋሚነት ስለመሰለፍ እንኳን አያስቡም ነበር፡፡ አሁን ግን እንከን አልባ ሆነዋል፡፡ እውነታው እዚህ ጋር ዕድል ሳይሆን ችሎታ ብቻ መኖሩን ነው፡፡
ጥያቄ፡- በየትኛው መንገድ?
መልስ፡- (ፍራንክ) በራይካርድ የተጠረገውን መንገድ አግኝተውታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተሰናበቱ አሰልጣኞች ምስቅልቅል ፈጥረው ይሄዳሉ፡፡ ራይካርድ በዚህ በኩል ቁም ነገር ትቶ አልፏል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ክለቡ ጽኑ እምነት አለው፡፡ ሁልጊዜም እንደምናገረው ታላቅ ዳይሬክተር በታላላቅ ሙዚቀኞች ታላቅ የሆነ ኦርኬስትራ ማቋቋም ይችላል፡፡ ተራ ሙዚቀኞችንም በማቀናጀት ጥሩ ሙዚቃን ይፈጥራል፡፡
ጥያቄ፡- ተጨዋቾቹስ?
መልስ፡- ጋርዲዮላ የአሁኑን ጋርዲዮላ ለመሆን የቻለው ከተጨዋቾቹ የተነሳ ነው የሚባለው ቅጥፈት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኤቶ፣ ሆንሪ እና ኢብራሂሞቪች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ቪያን አግኝቷል፡፡ በግራ መስመር ተከላካይነት አራት ወይም አምስት ተጨዋቾች ተጫውተው ታይተዋል፡፡ ማሼራኖን በመሀል ተከላካይነት ተጠቅሞበታል፡፡ የጋርዲዮላ ሰዎች ጠንካራ ሠራተኞች በመሆናቸው እንድደነቅ ያደርጉኛል፡፡ በሌላው አባባል ግን አልስማማም፡፡
ጥያቄ፡- በሌላው ማለት?
መልስ፡- የባርሴሎናን አጨዋወት ዘዬ የጀመረው ክራይፍ ነው የሚባለውን ነዋ፡፡ እንደ ጋርዲዮላ ባርሴሎና ለመጫወት የሞከረው የመጀመሪያው ሰው ሴዛር ሜኖቲ ነው፡፡ ይህን ማድረጌ ደግሞ ገድሎኛል፡፡ በበዛ የኳስ ቅብብል ስለተጫወትን በተቃውሞ ይጮሁብን ነበር፡፡ ከእኛ በፊት ሌላ ሰው ስለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ልክ እንደዛሬው ሜሲ ማራዶናን በ9 ቁጥር ሚና አጫውተው ነበር፡፡ ካራስኮ እና ማርኮስ በቅይጥ ሚና እንዲሁም ሹስተር አሁን ዣቪ በሚጫወትበት ቦታ ይሰለፍ ነበር፡፡ በእንዲህ አይነት መልኩ መጫወት የለብንም ይሉን ነበር፡፡ ሁልጊዜ ሹስተር ኳስን ለአሌክሳንኮ ሲያሻግርለት ተቃውሞ ይሰማ ነበር፡፡ 3-0 መምራት ስንጀምር ግን ‹‹ኦሌ ኦሌ›› በማለት ይዘምራሉ፡፡ ነገሩ በእኛ ላይ ጫና ነበረው፡፡ እኔ ቡድኑን ከለቀቅኩ በኋላ ሚጉዌሊ ከእኔ በኋላ የሚሾመው አሰልጣኝ በማርኪንግ የሚጫወት ከሆነ እንደማይዘልቅ ይናገር ነበር፡፡ ምክንያቱም አጥቂን ማርክ በማድረግ መሰላቸቱ ስለማይቀር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አጥቂዎች ከእነጭራሹ አይኖሩም፡፡ 9 ቁጥርን ማርክ ላድርግ ካልክ ከቶውኑ መጫወት አትችልም፡፡
ጥያቄ፡- ባርሴሎናን ለምን ለቀቁ?
መልስ፡- እናቴ ይህችን ዓለም በሞት ተለየች፡፡ በአርጀንቲናም ዴሞክራሲ በመስፈኑ ወደ አገሬ መመለስ እንደሚኖርብኝ አሰብኩ፡፡ (ከወቅቱ የባርሴሎና ፕሬዝዳንት) ከኑኜዝ ጋር ምሳ እየተመገብን ሳለ ባዶ ቼክ ከፊት ለፊቱ በማስቀመጥ እንድቆይ እችል ዘንድ የሚያስፈልገኝ የትኛው ተጫዋች እንደሆነ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ምንም ነገር አልፍልግም አልኩት፡፡ እፈልግ የነበረው ያሉትን ትልልቆቹን ተጨዋቾች እንዲያሰናብትልኝና ድንቅ ክህሎት ያላቸውን ታዳጊዎች እንዲታወቁ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ኮፓ ዴል ሬይን ካሸነፍን በኋላ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ይህ ዋንጫ ምንም ማለት አልነበረም፡፡ አሁን ሪያል ማድሪድ አገኘሁት ብሎ ልክ የኢንተርኮንቲኔንታል ዋንጫን እንዳሸነፈ ይኮፈሳል፡፡
ጥያቄ፡- ስለ አሰልጣኝ ጠቃሚነት እየተነጋገርን ነበር…
መልስ፡- አዎን ትክክል ነው፡፡ የአሰልጣኝን ዋጋ በተመለከተ ጥልቅ የሆነ መሰረታዊ ትንተና ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ (አሰልጣኝ) እንደ ፕሮፌሰር ነው፡፡ አስተማሪዎች በተማሪዎች ላይ 99 በመቶ፣ መጥፎ ከሆኑም እንደዚያው፡፡ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ በምክንያቶች ላይ የሚደገፍ ነው፡፡ ለሶስት ዓመታት ያህል ከሶስት አስተማሪዎች የተነሳ ህይወቴ መራራ ሆኖብኝ በመቆየቱ የሂሳብ ትምህርትን ጠልቻለሁ፡፡ እወደው የነበረው የኬሚስትሪ አስተማሪዬን ነው፡፡ አስተማሪው በመጀመሪያው ቀን ወደ ክፍላችን ገብቶ ሲጋራውን እያቦነነ በጥቁር ሰሌዳው ላይ ከጥግ እስከ ጥግ ፎርሙላዎችን ከለቀለቀ በኋላ ‹‹ይህንን እስከ ማክሰኞ ዕለት ልታውቁት በተገባችሁ ነበር፡፡ ሆኖም የማይቻል ነው፡፡ ሕይወት እንደ ኬሚስትሪ መሆኗን እወቁ፡፡ ልትተረጉሟት ይገባል›› ያለንን አልረሳውም፡፡
ጥያቄ፡- በእኔ እምነት ፕሮፌሰሩ በቂ የሆነ ክብር አልተሰጠውም?
መልስ፡- ስለ ስፔን የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ እዚህ ግን ከባህል አፈንግጦ መኖር 50 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ በጣም ያስጨንቃል፡፡ ችግሩ አሁን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ከፍ ያሉትን ክፍሎች ህይወትንም እስከ ማበላሸት ደርሷል፡፡ በቀን ለስምንት ሰዓታት በመስራት ሲማረሩና ራሳቸውን ሲያጠፉ የነበሩ ሰዎች አሁን ለ14 ሰዓታት እየሰሩ ነው፡፡ የኑሮን ጫና ለመቋቋም ሲሉ ነው፡፡ አያማርሩም፡፡ መጥፎዎቹ ሰዎች በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ ቀን የሌላውን ዜጋ ንብረት ይዘርፋሉ፡፡ ነገር ሁሉ የራሳቸው ይመስላቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ እግርኳስንም የእነርሱ አድርገውታል፡፡ መንግስት መንገድ ሲሰራ ልክ ከራሳቸው ኪስ እንደሰሩ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ሙዚቃችንን ሰርቀውናል፡፡ መናፈሻዎቻችንንና አደባባዮቻችንም ዘርፈውናል፡፡ ይህን እያደረጉ ዜጎች ተሰላችተው በየአደባባዩ በድንኳን ሲኖሩ ተገርመው ያያሉ፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹ዘራፊዎቹ›› ይህንን መረዳት የሚችሉ ይመስልዎታል?
መልስ፡- በእርግጥ ይረዱታል፡፡ ይህ የማይረባ ነገር ነው፡፡ ተጠራጣሪ መሆን አልሻም፡፡ ነገር ግን ብሩህ ተስፈኛ አይደለሁም፡፡ ያለምንም ተጨማሪ ማብራሪያ ጥብቅ ማርክሲስት ነን፡፡ በ70 ዓመታት የምድር ላይ ቆይታዬ ካፒታሊዝም በእግርኳስ ላይ ሳይቀር በዙሪያዬ የፈጠረውን ምስቅልቅል ተመልክቻለሁ፡፡ ይህ በመሆኑ ይህች ሀገር ምንም ስሜት አይሰጣትም፡፡ የጎጆ ኢንዱስትሪን ለማጥናት ከባርሴሎና ለመጣው ጓደኛዬ ምን እንዳልኩት ታውቃለህ?
ጥያቄ፡- በፍፁም አላውቅም
መልስ፡- አርጀንቲና የጂኦፖለቲካን አብዮት ባለመራመዷ በማንም አታምንም፡፡ በ3 ሺህ ኪሎ ሜትር ውስጥ 600 ሺህ ሰዎች በአንድነት እንኖራለን፡፡ በጎረቤታችን ማታንባስ 500 ሺህ ሊያኖር በሚገባ ቦታ 4 ሚሊዮን ሆነው ተቀምጠዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሄርናንዴዝና ኦዚል የዘንድሮው ሲዝን በአውሮፓ ምርጥ ግዢዎች ተባሉ
Share