June 26, 2011
11 mins read

የእግር ኳስ አጥቂ አበበ ቢቂላ

(ከገነነ መኩሪያ ሊብሮ) ጊዜው በ1957 ዓ.ም ነው በጦር ሐይሎች የስፖርት ውድድር ከተሳተፉት ውስጥ አንዱ ክብርዘበኛ ነው፡፡ የጦር ሐይሎች የስፖርት ውድድር ወታደሩ ለክፍሉ ያለውን ፍቅር የሚገልፅበጽ ነበር፡፡ ክብር ዘበኛና ጦር ሠራዊት ለዋንጫ ደረሱ ግጥሚያው የገና ጨዋታ በጦር ሀይሎች ውድድር ውስጥ ይሄ አልተካተተም ነበር፡፡ በዚህ ጨዋታ ክብር ዘበኛና ጦርሰራዊት ሲገናኙ ብዙ ሰው ጨዋታውን ሊያይ መጣ፣ የክብርዘበኛ የገና ቡድን አንበል አበበ ቢቂላ ነው፡፡

አበበ ዱላውን ይዞ ቡድኑን እየመራ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ ብዙዎቹም የእሱን ችሎታ ሊያዩለት ነው፡፡ ክብር ዘበኛና ጦር ሠራዊት አይጥና ድመት ናቸው፣ በመንግሥቱ ነዋይ ግርግር በተፈጠረው ሁኔታ ሁለቱም ሆድና ጀርባ ሆነዋል፣ ያ ስሜት በየቦታው ይከሰታል በእግር ኳሱ ሁለቱ ባደረጉት ጨዋታ በተነሳ ረብሻ መድፍ እስከመተኮስ ተደርሷል ( ይሄንን ታሪክ ሌላ ጊዜ አጫውታችዃለሁ) የሁለቱ ፀብ እዚህ ድረስ ነው፡፡
በገናው ጨዋታ ክብርዘበኛ ጥሩ ያጠቃል፣ አበበ ከፊት ነው የተሰለፈው እሱ ባስቆጠራት ጎል ክብርዘበኛ እየመራ ነው፣ ሌሎች ተጨማሪ ጎሎችን የአበበ ጓደኞች አስቆጠሩና 3 ለ 1 መምራት ጀመሩ፣ አንድ ኳስ አበበ ይዞ ሄደ ከውጭ ድንጋይ ተወረወረ አበበ ተመታ ወደቀ፣ ጨዋታውም ቆመ፣ ከውጭ ረብሻ ተነሳ እንደገና ፀቡ ቆመና ጨወታው ተጀመረ፣ አንድ የክብር ዘበኛ ተጨዋች ኳሷን እመታለሁ ብሎ በዱላ የተጋጣሚውን እግር መታ ሁለት የጦር ሠራዊት ቦክሰኞች ሜዳ ገቡና ተጨዋቹን ደበደቡት፣ እንደገና እነዚህም በገላጋይ እንዲወጡ ተደረገ፣ ጦረሠራዊት 2 አገባና 3 ለ 3 ሆኑ፣ አበበ አንድ ኳስ አስቆጠረና 4 ለ 3 አደረጋቸው ሌላ ኳስ እየገፋ ሲሄድ እግሩን ተጠልፎ ወደ የጦር ሠራዊት ደጋፊዎች ‹‹እግሩን በለው›› እያሉ ሲጮሁ ነበር፡፡ አበበ እንደወደቀ በዱላ ልጁን ይመታዋል፣ በዚህም ፀብ ተነሳ ማሞ ወልዴ እንዲህ ይላል ‹‹ የዚያን ቀን አበበ እንዳይጫወት ተነግሮት ነበር ፣ በነጋታው በጦር ሐይሎች ውድድር የሩጫ ውድድር ነበር፣ እሱ ግን እምቢ አለ ቡድኑ ወስጥም ጎበዝ ተጨዋች እሱ ነው፣ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች እግሩን በለው ይሉ ነበር ለእሱ ክፋት አስበው አይደለም በሩጫ ውድድር እንዳይሳተፍና ክብር ዘበኛ ውጤት እንዳያገኝ ነው፣ በሁለታችን ክፍል መሐል ደግሞ መቃቃርም ነበር፡፡
አበበ ከወደቀበት ተነስቶ ልጁን ባይመታው ኖሮ ፀቡ አይከርም ነበር፡፡ በዚያን ቀን ብዙ ድብድብ ተነሳ ሰውም ተጎዳ እኔም ባልጫወትም ተመታሁ፡፡ የክፍላችን የስፖርት መኮንን ሻምበል ተከስተ አባይ መሣሪያ ይዘው እየተኮሱ አበበን ከልለው ይዘውት ሄዱ የኛ ቡድን አሸናፊ በመሆኑ በሌላ ቀን ዋንጫው ተሰጠን ከአንድ አመት በፊት በማራቶን ሩጫ 20 ኪ.ሜ ከሄድን በኃላ ጠርሠራዊቶች አበበን ጠልፈው ጣሉት ከወደቀበት ተነሳና የጠለፈው ሄዶ መትቶ ጣለው በመኪና ይከተሉ የነበሩት ገላግለው እንደገና አበበ ጥሩ ውጤት አመጣ በጦር ሐይሎች ውድድር ጦርሠራዊትና ክብር ዘበኛ የትም ቦታ ይጣላል፣ በሐገር ውድድር ሲሆን ግን ሁለቱም ይፈቀራሉ›› ይላል፡፡
እስማኤል አበበን ቀደመው
የሜክሲኮ ኦሎምፒክ የተካሄደው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960 ነው፣ አበበ ቢቂላ ለ3ተኛ ጊዜ ወርቅ ያመጣበታል ተብሎ የተጠበቀበት ነው፣ ከሜክሲኮ ጋር ተመሳይ የአየር ፀባይ አለው በሚል ወንጂ ለዝግጅት ተመረጠ ፡፡ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኑም በማጣሪያው ስለወደቀ ውድድሩ ላይ ባይሳተፍም በጃንሆይ ወጪ ይሂድ ተባለና ለዝግጅት ከአትሌቲክስ ቡድን ጋር አብሮ ተቀመጠ፡፡
እስማኤል ገሪሌ የብሔራዊ ቡድኑ የክንፍ አጥቂ ነው፣ ከአበበ ጋር ሁሌም ይቀላለዳሉ፡፡
– እስማኤል፡- ሩጫ እንወዳደር ?
– አበበ፡- ከእኔ ጋር?
– እስማኤል፡- አዎን
– አበበ፡- ሩጫ ትችላለህ?
– እስማኤል፡- አዎን
– አበበ፡- በስንት እንወዳደር?
– እስማኤል፡- መቶ ሜትር
ሁለቱም ገበታ ላይ በተገናኙ ጊዜ አብረው ስለሚቀመጡ ያወራሉ፣ ይፎካከራሉ፡፡ ይሄን ሁሉም ሰሙት፣ ሩጫው ይደረግ ተባለ ቀን ተቆረጠ ሌሎች ገንዘብ አስያዙ የወሬው ፉክክር ተጋጋለ፣ እስማኤል እንዲህ ይላል ‹‹ ካሸነፍከኝ ቶኪዮ ላይ ያገኘሁትን ሜዳሊያዬን እሰጥሀለሁ አለኝ የቀልድ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ ግን 100 ሜትር ተወዳደርን ሩጫው ተካሄደና እኔ አሸንፍኩ አንዳንድ ሰዎች ‹‹ አበበ የአለም ሻምፒዮና ነው አንተ አበበን ከቀደምከው ለምን በኦሎምፒክ አትሮጥም›› አሉኝ፡፡ ሰዎች ያልገባቸው አበበ እና እኔ በማራቶን ሳይሆን 1500 ሜትር እንኳን ብንሮጥ አልችለውም›› በማለት ይናገራል፡፡ ስለ ኳስ ችሎታውም ሲናገር ‹‹ አበበ ኳስ የሚችልም አይመስለኝም ነበር ብሔራዊ ቡድኑ ወንጂ ልምምድ ሲያደርግ ከእኛ ጋር ይጫወት ነበር በአጥቂ ቦታ ነው የሚሰለፈው አስረዝሞ ነው የሚገፋው ኳስ ጎበዝ ነው፣ እሱ እንደነገረኝ ከሆነ ብዙ ስፖርቶችን እንደሚጫወት ነው›› ይላል፡፡
አበበ እና ጋቢው
አበበ በሮም ኦሎምፒክ በማሸነፉና የኢትዮጵያ ስም በማስጠራቱ ትልቅ ኩራት ሆነ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት ተጀምረ፡፡ አበበ በተለያየ ጊዜ ሩጫ ሲያካሄድ እያቋረጠ ይወጣ ጀመር፡፡ ችግር ሲገጥመው ለይድነቃቸው ያማክራል፣ የቡድኑ ሐኪም ዶክተር ፍሬደሪክና ይድነቃቸው በአበበ ጉዳይ ተወያዩና አስመረመሩት ትርፍ አንጀት አለበት፣ እንዲህ ሆኖ መሮጥ አይችልም አሉ፣ ኦፕራሲዮን መሆን አለበት፣ ሁለቱም ወሰኑ ለአበበም ነገሩት፣ ‹‹ እናንተ እንዳላችሁ›› አለ፡፡ ሆስፒታል አስተኙት ኦፕራሲዮን ተደረገ፡፤ጉዳዩ ሌላ ቦታ ተሰማ ጭቅጭቅ ተፈጠረ፡፡ ‹ይድነቃቸውና ፍሬደሪክ አበበን አስቀደዱት›› ተባለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ወርቅ እንዳታመጣ በማሰብ ነው ተብሎ ተወገዙ፣ አበበ ግን ‹‹ከማንም በላይ እነሱ ለእኔና ለውጤቱ አስበው ነው›› አለ፡፡ አበበ ገና ኦፖራሲዮኑ ሙሉ በሙሉ ሳይደርቅ ወደ ቶኪዮ ሄደ አበበ በሽተኛ ነውና ጋቢ ለብሶ መሄድ ነበረበት የጃፓን ሐኪሞቸም ህመሙንና ስፌቱን አዩ እንዲህ ሆነህ መንቀሳቀስ አትችለም አሉት፣ አበበ ግን ልዩ ፍጡር ነበር ሮም በባዶ እግሩ ሮጧላ፡፡ ቶኪዮ ላይ ደግሞ ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም ማራቶንን ሮጠ የጃፓን ጋዜጦች አበበ በሽተኛ መሆኑን ነው የሚያውቁት በመሮጡ ተገረሙ፣ በማሸነፉም ተደነቁ እውነትም ልዩ ፍጡር ነው አሉ፡፡ ለብሶት የሄደው ጋቢ አሁንም ድረስ እዚያው ጃፓን ይገኛል፣ ሰዎች ጋቢውን ይጎበኙታል ገንዘብ ከፍለው ይለብሱና ፎቶ ይነሳሉ አበበ ሮጦ እንዳሸነፈ ወደ ይድነቃቸው ሄደና ‹‹ ወሬኞችን ጭጭ አደረግናቸው›› አለ፡፡ ሮም ላይ ሲያሸንፍ ደግሞ ወደ ይድነቃቸው ጠጋ ብሎ ‹‹ አንጀቶን አላራስኩትም ?›› አላቸው ያን ጊዜ ምንም ለማያመጡ ለምን ሄዱ ተብሎ ከቤተ መንግሥት ወቀሳ ነበር፣ አበበም የመጀመሪያውን ወርቅ በማምጣቱ ይድነቃቸው ተደሰቱ አበበ የሮጠው መስከረም 1 ቀን ነው ይድነቃቸው የተወለዱት ደግሞ መስከረም 1 ቀን ነው፡፡ ይድነቃቸው ሻምፓኝ ይዘው መጡ፡፡ ‹‹ ለኔም ለአንተም›› አሉት መስከረም 1 ለሁለቱም ልዩ ቀን ነበር፡፡
Go toTop