ባለቤቷ በመላው አከላቷ ላይ አሲድ ደፍቶባት የተሰወረውና በስቃይ ላይ የከረመችው ትግ እግስት መኮንን ከዚህ ዓለም መለየቷን የዘ-ሀበሻ ጋዜጣ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ዘገበ::
ትዕግስት አሲድ ከተፈዳባት በፊት በየካቲት 12 ሆስፒታል በህክምና ስተረዳ የቆየች ቢሆንም ትናንት ሃሙስ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው::
ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ዘ-ሀበሻ ጋዜጣ አሲዱ ሰውነቷ ከተፋባት በኋላ ስለነበረው ታሪክ የጻፈውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
ከእግሯ እስከ ራሷ ድረስ በፋሻ ተጠቅልላ ከተኛች ሦስት ሳምንት የሆናት ትዕግስት መኮንን፡ አልፎ አልፎ የልጆቿን ስም እያነሳች ከማቃዠት በስተቀር ሰዉ ማናገር አትችልም፡፡ ልጆቿ ግን እናታቸዉ ምን ዓይነት ስቃይ ዉስጥ እንደሆነችና ምን እንደደረሰባት አይዉቁም፡፡ የሚነግራቸዉም አላገኙም፡፡ እናታቸዉ ከቤት የለችም፡፡ አባታቸዉም እንደወጣ ቀርቷል፡፡ ሁለት ልጆችን ከወለደች በኋላ ባለቤቷ የሞተባት የ32 ዓመቷ ትዕግስት መኮንን ባለቤቷ የተወላትን ቤት በማከራየት ነበር የምትኖረዉ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት እንደገና ትዳር ከመሰረተች በኋላ ሦስተኛ ልጅ ብትወልድም፡ ትዳራቸዉ የሰከነ እንዳልነበረ ቤተሰቦቿ ይናገራሉ፡፡ ቤታቸዉ በጭቅጭቅ የተረበሸ እንደነበረና ባለቤቷ በተደጋጋሚ አጠፋሻለሁ እያለ ይዝትባት እንደነበረ የሚገልጹት የትዕግስት ቤተሰቦች፡ ሰላማዊ ህይወት ለማግኘት በተደጋጋሚ በሽማግሌዎች ሞክራለች ብለዋል፡፡ በየግዜዉ የሽማግሌዎች ጥረት ሳይሳካ ሲቀር በፍቺ ለመለያየት ደጋግማ ሞክራለች ይላሉ ቤተሰቦቿ፡፡ ዛሬ ተጠርጣሪዉ ባለቤቷ ጭንቅላቷ ላይ ካደረሰባት የዱላ ድብደባ በተጨማሪ ከእግሯ እስከ ጭንቅላቷ ድረስ በደፋባት አሲድ ሰዉነቷ ተቃጥሎና ቆሳስሎ የተኛችዉን ትዕግስት እየተመለከተ፡ እህቴ በተደጋጋሚ ለአከባቢዉ ፖሊስ አመልክታ ነበር ብለዋል ታናሽ ወንደሟ ዮሐንስ፡፡
‹‹ባለቤቷ እስከነ ልጆችሽ እጨርስሻለሁ እያለ ይዝትባት ነበር›› ሲል የተናገረዉ ዮሐንስ፤ ከእግሯ አስከ ጭንቅላቷ ድረስ በፋሻ የተጠቀለለችዉን እህቱን በቁጭት እያየ፤ ‹‹ዛቻዉን እየፈራን ከአጠገቧ ላለመለየት እንሞክር ነበር፡ በዚያች ቀን ግን አጠገቧ አልነበርንም›› ብሏል፡፡ ያቺ ዕለት እሁድ ሚያዚያ 29 ቀን ነች፡፡ ከሰዓት በኋላ ትዕግስት ከምትኖርበት ኮተቤ አከባቢ ወደ ለገሃር አከባቢ ወደ እህቷ ቤት የሄደችዉ የታመመ ሰዉ ልትጠይቅ ነዉ፡፡
በዚህ ጊዜም ነዉ የ10 ዓመት ልጇ ስልክ የደወለላት ‹‹ ደዉልና ጥራት›› ተብሎ፡፡ በቁጣና በንዴት ያዘዘዉ፣ በሹፍርና የሚተዳደረዉ ባለቤቷ ነዉ፡፡ ልጅ ግን እንደታዘዘዉ አላደረገም፡፡ ቤት ዉስጥ የባልና ሚስት ጭቅጭቅ ሁልጊዜ ስለሚያስጠላዉ ሁኔታዉም ስላስፈራዉ፡ እናቱጋ ደዉሎ እንዳትመጣ ነግሯታል፡፡ ‹‹እሷ ግን አላስቻላትም ምክኒያቱም ብዙ ጊዜ ‹‹ ልጆችሽን አጠፋቸዋለሁ›› እያለ ይዝትባት ስለነበር ተነስታ ወደ ኮተቤ ሄደች›› ይላሉ ቤተሰቦቿ፡፤ ከታክሲ ወርዳ ወደ መኖሪያ ቤቷ በማምራት በርጋ ስትደርስ ነዉ የገጠማት፡፡ ጭንቅላቷ ላይ በተደጋጋሚ ተደብድባ ወደቀች፡፡ ከዚያም ሰዉነቷ ላይ በተረጨ አሲድ አካሏ ተቃጠለ፡፡ ወጣቷ ያለችበት ሁኔታ በጣም አሰቃቂ መሆኑን የሚገልጹት ሲስተር ታደለች ህክምናዋን ግን እየተከታተሏት እንደሆነ ነዉ የሚገልጹት፡፡ የደረሰባት የአሲድ ቃጠሎ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ሰዉነቷ በቀላሉ ለኢንፌክሺን የተጋለጠ ነዉ፡፡ እንደቃጠሎዉ ስፋት ስቃይዋም ከፍተኛ ስለሆነ የስቃይ ማስታገሻና ማደንዘዣ በተከታታይ ይሰጣታል፡፡ ነገር ግን ሰዉን ማናገር የማትችለዉ በማደንዘዣ ምክኒያት ብቻ አይደለም፡፡ ከማደንዘዣ ስትነቃም በትክክል ማዉራት እንደማትችል ዮሐንስን ጠቅሶ አልፎ አልፎ ግን የልጆቿን ስም እያነሳች ትቃዣለች እንዴት ድብደባና ቃጠሎ እንደተፈጸመባት ታወራለች ብሏል፡፡ በባለቤቷ የሚደርስባት ዛቻና ሁኔታ ስለሚያስጨንቀን ‹‹ አንድ ነገር ቢያደርጋትስ›› እያልን ከአጠገቧ ላለመለየት እንሞክር ነበር የሚለዉ ዮሐንስ ‹‹ ባለቤቷ ይህን ሁሉ ድብደባና ቃጠሎ ከፈጸመባት በኋላ ራሱ ደዉሎ ነዉ የነገረኝ›› ይላል እሰካሁን በፖሊስ እንዳልተያዘ በመጥቀስ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡