ከ10 በላይ ኢትዮጵያዊያን በየመን ጦርነት ሞትና ያሳደረው ስሜት…!!!

June 11, 2011

በሰው ሀገር ያውም አረብ ሀገር በስደት መኖር ራሱን የቻለ ሰቆቃ አለው:: ያን ስቆቃ መግፋት አንሶ ያለንባት የመን የጦርነት ቃጣና ሆና..ያልፍልኛል..እሰራለሁ ተብሎ ተወጥቶ የትም ድፍት ብሎ መቅረት ሰቅጣጭ..ዘግናኝ ውስጥን የሚያቆስል ሆኗል:: ከ10 በላይ ኢትዮጵያዊያን ያጣንበት የየመን-ሰነዓ ጦርነት ውስጣችን የጸነሰውን ጣባሳ ማን ይረዳናል?ያሳደረውን ፍርሀት ማን ያውቅልናል? ያላረገዝነው የማንወልደው ጭንቀታችን ፍርሃታችንን ከእኛ በስተቀር ያወቀው የለም:: የመን ያለችበትን ሁኔታስ ያወቀ ወገንስ በዝምታ ሲያየን…የመገናኛ ብዙሀን ጩኸታችንን ውጠው ሲቀሩ የሚሰማን የሞራል ድቀት የመገፋት የመረሳትን ስሜት ያስተዋለ ይኖር ይሆን? ይከፋል…እጅግ ይከፋል:: በእልቂት መሀል ሊያወጣን የሞከረ..ያሰበ..ያለንበትን ችግር ያስተላለፈ ሚዲያ አለመኖሩ..አይዟችሁ ያለ አለመኖሩ…የሞቱትን ወገኖች መቅበር አለመቻሉ የሚያስከትለውን የሞራል ድቀት ከግምት ያስገባ ይኖር ይሆን?
በአረቡ አለም ላይ የተቀጣጠለው የለውጥ ንቅናቄ ከዳር ዳር አጥለቅልቆ ከቀናት አልፎ ወራቶችን አስቆጥሯል:: በተለይ የመን መብራት ማግኘት ሳይቻል ቀርቶ በጨለማ 24 ቀናትን አስቆጥረናል:: ሌላው ቀርቶ በተኩስ የቆሰለ ቤት ንብረቱን ያጣ.. ሞቶ የትም የቀረው ቁጠር ቀላል አይደለም:: ባለስልጣኖች…ተቀዋሚዎች…ሼሆች..ቤት ሰራተኞች ሀበሻዎች ናቸው:: የባለስልጣኖች ቤት ሲደበደብ..የተቃዋሚዎች ቤት ሲደበደብ…የሼሆች ቤት ሲደበደብ ስንቶቸ ወገኖቻችን ሞቱ? ስንቶቸ ሀበሾች ቆሰሉ? ስንቶች ኢትዮጵያዊያን ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ? የተፈናቀሉት ስደተኞች የUNHCR ሰራተኞች በጥይት መቷቸው:: የሚያሳዝነው አሳባ የሚባለው ቦታ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ስደተኞች ከመጠለያችን ተፈናቀልን መወደቂያ የለንም ያሉትን ከመኖሪያቸው ሰለተፈናቀሉ UNHCR እንዲረዳቸው ሲጠይቁ IDF ወደ ተባል ቢሮ ተላኩ:: UNHCR ስር ያለው የዚህ ድርጅት ስራተኞች ሁለት ስደተኞቸን ያቆስላሉ:: ቢሮው የወሰደው እርምጃ የለም::
የኑሮ ግሽበቱ..የጥይት ጩኸቱ..የነዋሪው ዛቻው ያላሳቀቀው ኢትዮጵያዊ የለም:: ክላሽንኮቭ የሌለው የለም:: ሼኮቹም ቢሆን ከተራ ጦር መሳሪያ ጀምሮ ታንክ..አየር መቃወሚያ ድረስ የታጠቀ እስከ 40ሺህ ስራዊት ያላቸው ሼሆች አሉ:: የፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች መሳሪያ አላቸው::ታጥቀውም ይታያል:: በሰቀቀን ተወቶ በሰቀቀን ይገባል:: በሰቀቀን ተሰርቶ በሰቀቀን ይበላል:: በተለይ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ምንም አመቺ ነገር የለም:: UNHCR የሚሰጠን ግምት..ቦታም ከወያኔ የተለየ አይደለም:: ሲከፋፍሉን..የኦሮሞ ኮሙኒቲ..የኦጋዴን ኮሙኒቲ.. የኤርትራ ኮሙኒቲ..እያሉ ከፋፍለውናል:: አማራም ሆነ ትግሬ ግን ኮሙኒቲ እንዲያቆም አልተፈለገም:: አልተፈቀደም:: አይፈቀድምም:: ይህ ከዚህ ቢሮ የሚጠበቅ ባይሆንም አለን የሚባል ሰራተኛ ይህን ሚና እንደሚጫወት በማወቄ በጋራ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ማህበር የሚል ሁሉን ያካተተ ኮሙኒቲ ማቆም እንዳለብኝ ለራሴ የቤት ስራ ሰጥሁ:: መከፋፈሉን ለማጥፋት ትግሌ አድካሚ ቢሆንም ሁሉም የሆዱን በሆዱ አድርጎ በጋራ መታገል እንዳለብን አሳምኜ ህብረቱ ተመሰረተ:: ትግሉ ቀጠለ:: በፊት..በፊት ከፍለውን በተናጠል ችግራችንን ስንናገር ባጀት የለንም:: አርፋችሁ ተቀመጡ..የመሳሰሉት ምላሽ ጠንከር ካለ መታወቂያህን እንዳንነጥቅህ የሚል ዛቻ ጋር ይሰነዝራሉ:: ጦርነቱ ለህይወታችን ያሰጋል ስንልም ዝም በሉ ነው መልሱ…
አሁን የመን የጦርነት ቀጠና ከሆነች ከረመች::በርካታ ማለት የሚያስችል ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ ለሞት ተዳረገ:: መጀመሪያም ቢሆን አለን እንዳንል የለንም… የለንም እንዳንል አለን የሚያስብል አይነት ኑሮ ነበር ያለነው:: ጦርነት ለመግጠም የነበረው ዛቻ ሁሉን ኢትዮጵያዊ ፍርሃት የጫረ ነበር:: ፍርሃቱ ከፍርሃትነት አልፎ በእለተ ዕሁድ ባሩድ ማፈንዳቱ ገላን በእርሳስ መነዳደሉ ቀጠለ:: ረቡዕ ዕለት ሞባይል ስልኬ አንቃጨለ::የማውቀው ቁጥር አይደለም::
አነሳሁት::
መልዕክቱ 4 ኢትዮጵያዊያን ተገደሉ ነበር:: ሊሰማኝ የሚችለውን ስሜት
ማን ይረዳኛል? የውስጤን እንባ ማን ያየዋል?…የነገሩኝም ቢሆን ጩኸታቸውን የሚሰማ አካል በማጣት የሚያረጉት ስለጠፋቸው ነው:: በቀጥታ..ሆስፒታል ለመሄድ ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ አልያዝኩም:: ስልኩን ዝጉት ካልኩ በሁዋላ ደውዮ ሬሳውን አንሳ ተብዮ ነበር ያለውን ጀማል የሚባል ሰው አናገርኩ እና ዜናውን ሌላው ወገኔ ቢሰማው ብዮ ጽፌ በየዌብ ሳይቱ ላኩት:: ግን ማንም የእነዚህ ኢትዮጵያዊያን ሞት ምንም አልመሰለውም?….ዜና አድርገው ያሰፈሩት ጥቂቶች ናቸው::
ያሳዝናል::
በማግስቱ ጠዋት ኩዌት ሆስፒታል ሶስት ሆነን ሄድን:: በምሰባብራት አረብኛ ከማናገር አብረውኝ ያሉትም ይረዱኛል ብዮ ነበር:: <<መምኑዕ ተስዊር>> የሚለውን ቃል አስቀድመው አስገቡን:: ፎቶ ክልክል ነው ማለታቸው ነው:: ሶስቱ ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ሴት ናት:: ጠቆር ያለው ልጅ ጀርባው ላይ ሲሆን የተመታው አንደኛው ራሱ ላይ ነው:: የሴቷን ሬሳ አላሳይም አሉን:: ከሶስቱ ወንዶች ሁለቱ የኦሮሞ ተወላጆች የመኒያ ኤርላይንስ ጋር መኪና ሲያጥቡ ብዙ ሰው የሚያውቃቸው ናቸው:: እዛ ጋር መኪና የሚያጥቡ ሌሎች ሲማሊያዊያንም ሞተዋል:: ሆስፒታል ያሉትና ያየኋቸው ግን ሶስት ሶማሊያዊያን ናቸው:: ከሆስፒታል ስንወጣ ራሴን እያዞረኝ ነው::

ጦርነቱ የተካሄደበት ቦታ አሳባ የሚባል የሰነዓ ከተማ አንዱ ክፍል ነው:: በሼህ ሳዲቅ አል-አህመር እና በመንግስት መካከል ነው::ያልወደመ ንግድ ቤት ያልወደመ የመንግስት መስሪያ ቤት..መኖሪያ ቤት የለም::ትዝ አለኝ………እዛው ሼኩ ቤት ውስጥ ወደ 15 የሚጠጉ የቤት ሰራተኞች አሉ:: አንድ ጓድኛ ያላት ልጅ ስለማውቅ ደወልኩና አረጋግጪ እስኪ አልኩዋት:: አትክልተኛም ሆን መላላክ የሚሰሩ ወንዶች እንዳሉም ሰምቻለሁ:: ስልክ የደወልኩላት ልጅ የምታውቃት ልጅ ጋር ደውላ ስድስቱን አውጥተው ኤርፖርት አካባቢ እንደወስዷቸው ሶስቱ ኮንትራት ያመጣቸው አምራን የሚባል ደላላ ጋር መመለሳቸውን ቀሪዎቹ ጊቢ ውስጥ ያለ አንደርግራውንድ ውስጥ መሆናቸውን ነገረችኝ ብላ አበሰረችኝ:: ተመስገን ውስጥ ያሉትንም እግዚአብሃር ይጠብቃቸው ከማለት ውጭ ምን ማለት እችላለሁ::
የሚቱትን ጉዳይ ለUNHCR አሳወቀን ሬሳው እንዲቀበር ኤምባሲም የሚገቡ እንዲነግሩ ነገርን:: ግን ዛሬ ድረስ አስታዋሽ ያጣው ሬሳ ፍሩጅ ውስጥ ነው:: መቅበር አቅቶን ቀረ:: ሞት አንድ ሁለት እያለ ማስቀረት ሲጀምር ዝም ብሎ ማየት አያዋጣም:: ተሰባስበን UNHCR አንድ መፍትሄ ይስጠን ብለን ጥያቄ አቀረብን:: UNHCRም በጠመንጃ አፈሙዝ ነው ወይ የሚያምነው? እስክንል አስደበደቡን …አሳሰሩን…4 ሰዎች በእስር ቤት ሆነው ትግላችንን ቀጠልን:: ውጤቱ ካምፕ ግቡ የሚል መፈክር ሆነ::
አልተቀበልንም::
በአል-ቃይዳ የሚረዳ እስልምና አክራሪ ቡድን ሲዋጋበት አለም እንደሚያውቀው የሁቱ ጦርነት የተከሄደበት የነበረ ቦታ ነው ካምፑ::..በዛ ላይ እነዚሁ ቡድኖች አይለው አንድ ከተማ በተቆጣጠሩበት ወቅት እዛ መሄድ ግደሉን ብሎ እጅ እንደመስጠት ይቆጠራል ብንልም ሰሚ ጠፍቶ የተወሰኑ ሶማሊያዊያን እና የኦሮሞ ኮሚኒቲ በሚባለው የተደለሉ ልጆች ሄዱ:: የሄዱት በሶስት አውቶቡስ ነው:: እንደፈራነው ተያዙ:: እዛ ሲደርሱ የUNHCR ባለስልጣኖቸን ጭምር ያዙዋቸው ከፍተኛ እልቂት ይፈጠራል ብለን ስናስብ ሁሉም መስሊሞች በመሆናቸው <<እዚህ ማስፈር አትችሉም>> ብለው በሰላም ለቅቋቸው::
ይህ የኦሮሞ ኮሙኒቲ የሚባለው የስደተኛ ወንድሞቻችንን መብት ለመርገጥ አለን በሚባል በUNHCR ሰራተኛ የተመሰረተ ሲሆን የኦሮሞን ልጅ መብት በሸጡበት ቢሮ ተሰቷቸው የተጎለቱ ደም መጣጮች ናቸው:: ወደ 2000 የሚጠጉት ግን ከእኛ ጋር ታግለው UNHCR በር ላይ ተኝተው መፍትሄ ይሰጥን ይላሉ::

በሌላ በኩል ከስደተኞች ቢሮ/UNHCR / እውቅና ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊም አሳዛኝ ነገር ነው ያለው:: ኤምባሲ አለልኝ እንዳይል እንደሌባ ኪስ..ኪስ የሚያይ ኤምባሲና ኮሙኒቲ ነው ያለው:: እምነት የሚጣልበት አይደለም:: ከዱርዮ የማይሻል አጭበርባሪ መንግስት የሰራው ሁሉ የመን ያለ ስደተኛ ላይ እና ቤተስቡ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ የዋዛ አይደለም:: በባህር ሲገቡ የተያዙትን እና በየመን ሀገር ወጭ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱትን በራሴ ወጭ ለዜጎቼ አስቤ መለስኳቸው አለ:: “አምራን” እና “ሀርዝ”የሚባል ካምፕ ውስጥ ቀይ መስቀል ያስቀመጣቸውን ስደተኞች አግባብቶ 125 ዶላር እየሰጠ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እኔ መለስኩዋቸው ብሎ ጡሩንባ የነፋ መንግስት ምን ሊያደርግላቸው? የትኬት ከፍላችሁ ነው የምንመልሰው..ያላቸው መመዝገቢያ ሁለት ሺህ ሪያል ቅርጥፍ አድርጎ ከበላ በሁዋላ ነው:: ከዜጋ ይልቅ ገንዘብ ያስቀደመ ኮሚኒቲ ነው ያለን ከዚህ ምንም አንጠብቅም ባዩ ብዙ ነው::

ታዲያ ህይወታችንን ማን ይታደገው? UNHCR ምንም ማድረግ አንችልም ብሎ ተስፋ አስቆርጦናል:: ኤምባሲም በሱ በኩል ያሉት ላይ ድብብቆሽ ይጫወታል:: ምንድን ነው እጣ ፋንታችን? ሞትን መጠበቅ? ወደ ሳዑዲ አረቢያም አይታሰብም::ኢትዮጵያዊ ስደተኞቸን ይዛ አሰቃይታ ወደ ሀገር መመለስ ነው ተግባርዋ::ወዴት እንሰደድ?
ወገን አለን ሀገር አለን ግን እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ መስራት የሚችሉ ወገኖቻችን በዝምታ እያዩን ነው:: ብዙ ስደተኞችን የሚረዱ አልፎ ተርፎ ከኢትዮጵያዊነት ዘሎ አህጉራዊ እና አለማቀፋዊ ስደተኞችን የሚያንቀሳቅሱ የሚረዱ የኢትዮጵያዊያን ተቋሞች አሉ:: በቺካጎ ኢትዮጵያ ኮሙኒቲ..ካናዳ ቅ/ማርያም አባ ፍቅረማርያምን..ጣሊያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባ ሙሴን..የሀረር ወርቅ ጋሻውን..ዶ/ር ጸሀዮን…. የመሳሰሉ በርካታ ወገኖችን የሚረዱ ሰዎች እያሉን በስው ሀገር ጦርነት ረግፈን ልንቀር ነው:: መርገፍም ጀምረናልም::

የመን ያለ ኢትዮጵያዊ ሰሞኑን አንድ የሚለው ነገር አለ::<<ሀገር እያለን እንደሌለ በሰው ሀገር መቅረታችን ነው>> ይህን የሚለው ከምንም ተነስቶ አይደለም :: ነዋሪው ዛቻው ስለበዛ ነው:: እኔ ደሞ ሰሞኑን የሚባለውን አባባል አጠናክሬ..ወገን እያለን ወገን እንደሌለው…ሀገር እያለን ሀገር እንደሌለው የትም ልንቀር ነው ሌላው እላለሁ:: በቀጣይስ ምን ሊደርስብን እንደሚችል መገመት የሚከብደው ወገን ማጣታችን ያሳዝናል:: የኢትዮጵያዊያን ዌብ ፔጆች የየመን ጉዳይ አይመለከተንም ሊሉ ይችላሉ:: የመን ያለ ኢትዮጵያዊ ችግርስ ችግራቸው አይደለም ችግራችሁ አይደለም? የ4 ኢትዮጵያዊያን መኖታቸውን አስመልክቼ የሰራሁትን ዜና ለሁላችሁም ባድልም ከጥቂቶች በቀር ዝምታን መርጣችኋል:: ለምን? ራሳችሁ መልሱት..

Previous Story

ባለቤቷ አሲድ የደፋባት ትዕግስት መኮንን አረፈች

Next Story

በአሲድ የተደፋባት ትግስት ቀብሯ ተፈጸመ

Go toTop