ያለ ወቅቱ በደረሰ ዝናብ እየራሰች ያለችው አዲስ አበባ ዛሬም ከመለስ መንፈስ ተፅእኖ ነፃ አልወጣችም፤ ጣራና ግድግዳዎቿ እንዲህ በምስሉ እና በድርጅቱ አርማ መዥጎርጎሯን ያስተዋለ አንድ ቀልደኛ የባህር ማዶ ወዳጄ ‹‹እኔ ከሀገሬ ከወጣሁ በኋላ የኢህአዴግ ዋና ከተማ ሆነች እንዴ?›› ብሎ ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡ በእርግጥ ይህችን ቀልድ ስንፍቃት የምናገኘው ቁም ነገር፡- ከተማዋ በመለስ ውርስ ድንዛዜ ላይ መሆኗ፣ አስተዳደሯም ያለ ቅድመ-ዝግጅት ‹‹አፍርሼ ካልሰራሁሽ›› በሚሉ ካድሬዎች ጫጫታና ሩጫ ልቧን እያጠፋት እንደሆነ፣ አንድ ፓርቲ ተመራጭ፣ አስመራጭ፣ ታዛቢ መሆኑን እና የመሳሰሉትን ነው፡፡ የአቶ መለስ ሞትም ወቅቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ስርዓቱን እያንገጫገጨው ነው፡፡ በግሌ በመለስ ህልፈት ያለማዘን በሥነ-ምግባር የመዝቀጥ ጉዳይ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቴ ሰውየው ክፉ አምባገነን ከመሆኑም በላይ በዙፋኑ ሙጭጭ እንዳለ ህይወቱ በማለፉ ነው፤ ታዲያ ይህንን ሰው እንዴት አድርገን ነበር ከስልጣን ማውረድ የምንችለው? መቼም አቅመቢሶች ከመሆንም አልፈን በተራራና ሸንተረር ሳይቀር የተከፋፈልን ለመሆናችን ከራሳችን በላይ መስካሪ የሚያሻን አይመስለኝም፡፡ እዚህች ጋ ከሩሲያዊው ሌኒን ህልፈት ጋር የተያያዘ አንድ ነገር ትዝ ስላለኝ ልንገራችሁ፡-
እንደሚታወቀው ሌኒን የሩሲያ አብዮትን የመራ ሁነኛ ኮሚዩኒስት ቢሆንም፣ ምሁራዊ ሰውነቱ ከሌሎች አብዮተኞች በእጅጉ ይገዝፍ እንደነበረ ጠላቶቹም ሳይቀር የመሰከሩለት ጉዳይ ነው፡፡ እናም ህልፈቱ ሲሰማ፣ ሩሲያን በአይነ ቁራኛ ይከታተሉ የነበሩ ምዕራባውያን ድንጋጤ አደረባቸው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት የአንዱ መሪም ድንጋጤውን እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር አሉ፡-. ‹‹ሌኒን ሆይ፣ ባትወለድ መልካም ነበር፤ ከተወለድክ ደግሞ ትንሽ ብትቆይ ይሻል ነበር፤ ምክንያቱም ለማን ትተኽን እንደሄድክ እኔ አውቃለሁና!›› በእርግጥም ሌኒንን የተካው ባለ ብረት መዳፉ ጆሴፍ ስታሊን መሆኑን ስናስተውል የሰውየው ቁጭት ይገባናል፤ ግና ከአስር ወር በኋላም
ሊገባን ያልቻለው የእኛው መለስ ለማን ትቶን እንደሄደ ነው፡፡ ከስታሊንም ለባሱት? ወይስ… የሆነ ሆኖ መለስን ተክተው ከጀርባ የሚዘውሩትን አንጋፋ ታጋዮች ለጊዜው ባሉበት አቆይተን፣ ገብስ ገብሱን እንነጋገር ካልን የኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ወቅቱን የጠበቀ አይደለም የሚለው አያከራክረንም፡፡ የሶስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመትም እንዲሁ፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ነው አገዛዙን ወቅቱን ባልጠበቀ አጀንዳ እንዲወጠር ያደረገው፡፡
ያለወቅታቸው ‹‹ተከሰቱ›› ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉ አጀንዳዎች መካከል ‹‹የመለስ ፋውንዴሽን ምስረታ›› አንዱ ነው፡፡ በእርግጥ መለስ ባይሞት ኖሮ፤ ከሞተም በኋላ ስርዓተ ቀብሩ ትኩረት ባይስብ ኖሮ፤ ከተቀበረ በኋላም ‹‹ሌጋሲው ይቀጥላል›› ባይባል ኖሮ፤ ከሌጋሲው ውስጥም ‹‹ራዕዩ ፈለቀ›› ባይባል ኖሮ… ‹‹ፋውንዴሽን›› ጂኒ ቋልቋል… ባልተከታተለብን ነበር እያልን መቆጨታችን አይቀሬ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከመለስ ህልፈት በኋላ ‹‹የመለስ ራዕይ›› እያለ መጮኹ አናዳጅ ብቻ ሳይሆን ‹‹እመራዋለሁ›› ለሚለው ህዝብም ያለውን ንቀት የሚያሳይ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳም ነው ‹‹መለስ ኖሮ፣ ራዕዩ በሞተ›› የሚያስብለው (አሁን የፋውንዴሽኑ ምስረታ ዕለት የተከሰቱ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዮች በአዲስ መስመር ጨርፎ ወደማየቱ እንለፍ) ፋውንዴሽኑ ደረጃውን የጠበቀ መናፈሻ፣ ቤተ መፅሀፍት (የመለስ ስራዎች በአማርኛ ተተርጉመው ይቀመጡበታልም) እና የተለያዩ መዝናኛዎችን ጨምሮ አስክሬኑ የሚያርፍበት ልዩ ስፍራ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በግልባጩ ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ አዲስ አበባ ነው ከማለት ባለፈ በትክክል የት አካባቢ እንደሆነ ተለይቶ አልተገለፀም፡፡ ሆኖም ለግንባታው ተብሎ በግዴታ በርከት ያሉ መኖሪያ ቤቶች ከይዞታቸው እንደሚነሱ ተነግሯል፡፡ በግሌ ይህ አግባብ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምንም እንኳ በ‹‹ስመ-ልማት›› እየተደረገ ያለውን ማፈናቀል ጠቀሜታው የሀገር ነው ብለን ልንወስደው ብንችልም፤ ይህ ግን… (አጀንዳዬ የፋውንዴሽኑን ጥቅም ወይም ጉጂ ጎን መተንተን ሳይሆን፣ በምስረታው እለት የታዩ ጥቂት ተመንዛሪ ክስተቶችን መተንተን ነው ብያለሁና ወደዚያው አልፋለሁ)
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝከዚህ ቀደም የህወሓት አመራር አባላት የመለስ ህልፈትን ተከትሎ በሁለት ጎራ ተቧድነው ‹‹ቀዝቃዛ ጦርነት›› ውስጥ መግባታቸውን ያመላክታሉ ያልኳቸውን ፍንጮች ጠቅሼ መነጋገራችን አይዘነጋም፡፡ (‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት፡- ከአመታት በፊት ዓለም በአሜሪካን እና
ሶቭየት ህብረት ፊት አውራሪነት በርዕዮተ-ዓለም ተከፍሎ ሲፋለም ነበር፤ ያለታንክና መድፍ፤ ያለ ተዋጊ ወታደርና ያለ አዛዥ ጄነራል፤ ፍልሚያው ሟችም ሆነ ቁስለኛ፣ አሊያም ምርኮኛ አልነበረውም፤ የርዕዮተ-ዓለምን ልዩነት በበላይነት ለመወጣት ነበርና፡፡ አንደኛው ከሌላኛው ጎራ ከቻለ ሀገርን፣ ካልቻለም ስልጣን ላይ ያለ ግለሰብን ለማስኮብለል ይቀምራል፣ ያሴራል፣ ይሰልላል…፤ ይህንን ሁኔታ ነው የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› (Cold War) ያሉት) ዛሬ ደግሞ የህወሓት የአመራር አባላት በእንዲህ አይነት ጦርነት መጠመዳቸውን ጆሮአችን እስኪግል እየሰማን ነው፤ ልዩነቱ የህወሓት ችግር ርዕዮተ-ዓለምን መሰረት ያደረገ አለመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ህወሓት እንኳን ዛሬ፣ በትልቁ የተሰነጠቀ ጊዜም (በ1993 ዓ.ም.) ርዕዮተ-ዓለም አላጨቃጨቀውም፡፡ የስዬ አብርሃ ወደ አንድነት መግባትም ሆነ፣ የእነ ገብሩ አስራት በ‹‹ሶሻል ዴሞክራሲ›› አስተሳሰብ የሚመራውን አረናን መመስረት የልዩነቱ ምክንያት አልነበረም፡፡ እነገብሩ አረናን ለመመስረት ሲንቀሳቀሱ፣ በክፍፍሉ ወቅት ‹‹የቡድን አባታቸው›› እንደነበር የሚነገርለት ተወልደ ወ/ማርያም የአዲሱ ፓርቲ መስራች እንዲሆን ሲጠየቅ ‹‹ርዕዮተ-ዓለማችሁ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ ከሆነ ብቻ ነው የምቀላቀለው›› አለ መባሉ መከራከሪያችንን ያጠነክረዋል፡፡
እናም የህወሓት ሰዎች (ከእነ አረጋዊና ግደይ ዘርአፅዮን ዘመን ጀምሮ) ስልጣን እንጂ፣ የፖለቲካ አመለካከት የፀብ መንስኤ ሆኗቸው አያውቅም፡፡ የዘንድሮውም ‹‹ቀዝቃዛ ጦርነት›› ቡድተኝነትና የስልጣን ፍላጎት የፈጠረው ቅራኔ ነው፤ አሊያም ከጆርጅ ኦርዌል ‹‹እንሰሳት ሁሉ እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንሰሳት ግን ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው›› መንፈስ የተናጠቀ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም የፋውንዴሽኑ ምስረታ የእነአዜብን ቡድን የሚያጠናክር ፖለቲካዊ አንድምታ አለው፡፡ በእነአባይ ፀሀዬ ቡድን ውስጥ ከተሰባሰቡት አብዛኛው ለመለስ ያደሩት ፈርተው እንጂ አምነውበት ወይም ወደውት አይደለም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከእነርሱ ቡድን አንድም
የአመራር አባል የፋውንዴሽኑ ቦርድ አባል ሆኖ ያልተመረጠው፡፡
የሁለቱ ቡድኖች አሰላለፍ በ‹‹አባይ-ደብረፅዮ››ን እና በ‹‹አዜብ-አባይ ወልዱ›› አስተባባሪነት መሆኑን ሰምተናል (በነገራችን ላይ ከ1983-1993 ዓ.ም ኢህአዴግ ‹‹ሁሉም የግንባሩ አባል ፓርቲዎች እኩል ናቸው፤ ህወሓት ግን ከሁሉም ይበልጣል›› የሚል ያልተፃፈ ህግ ነበረው፡፡ በ93ቱ ክፍፍል አብዛኛው የህወሓት አመራር ከተባረረ በኋላ ደግሞ ያ ህግ ‹‹ሁሉም የኢህአዴግ የአመራር አባላት እኩል ናቸው፤ መለስ ግን ከሁሉም ይበልጣል›› ወደሚል ተቀይሮ ነበር፡፡ አሁን መለስ አልፏል፤ እናም አፍጦ የመጣው ጥያቄ ‹‹ከሁሉም የሚበልጠው ማን ነው?›› የሚለው ነው ብል ማጋነን አይሆንም)
የሆነ ሆኖ በ‹‹የመለስ ፋውንዴሽን ምስረታ›› ወቅት የታዩ ሁነቶች ሁለት ነገር ይፋ አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያው በእነአዜብ ጎራ እነማን እንደተሰለፉ የሚያሳይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የጦር አዛዦችም ፍልሚያውን መቀላቀላቸውን ማመላከቱ ነው፡፡ የእነአዲሱ ለገሰ-ብአዴን ገና ከመነሻው ከእነአዜብ ጎን መሰለፉ ይታወቃል፡፡ በፋውንዴሽኑ ምስረታ ወቅትም ይኸው ነው የታየው፡፡ ‹‹የጠቅላይ ሚንስትር መለስ የሌጋሲ ኮሚቴ›› ሰብሳቢ የነበረው አዲሱ ለገሰ፣ የስብሰባውን አካሄድ እየተከታተለ የተጣመመውን ሲያቃና፣ ማጣመም የፈለገውን ደግሞ ሲገፋ ተስተውሏል፡፡ ለምሳሌ የብአዴኑ ካሳ ተ/ብርሃን የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባል ሆኖ መመረጡን ተቃውሞ በእርሱ ምትክ ሌላ ሰው እንዲመረጥ ሲጠይቅ፣ አዲሱ ስራው ጊዜን የማይሻማና ቦርዱን የሚመለከት ነገር ሲኖር ብቻ ውሳኔ መስጠት እንደሆነ ጠቅሶ ካሳ መቀጠል እንዳለበት ሲናገር፣ የመድረክ መሪው በፍጥነት ሃሳቡን ቤቱ እጅ በማውጣት እንዲደግፍ ቀስቅሶ የሰውየውን ተቃውሞ ውድቅ አድርጓል፡፡ በግልባጩ የኦህዴዱ ሙክታር ከድር ሲመረጥ፣ የብአዴኑ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑን መግለፁን ተከትሎ፣ ሙክታር ‹‹ድርጅቶቹ ራሳቸው ለምን አይጠቁሙም?›› ገና ከማለቱ፣ እነአዲሱ ተሽቀዳድመው ‹‹ከአንተ ነው መጀመር ያለበት›› የሚል ግፊት በማድረግ የተመረጠውን ሙክታር ከድርን በ‹‹ድርጅታዊ አሰራር›› ከጨዋታ ውጪ አድርገው፣ አስቴር ማሞን አስገብተዋል፡፡ ሶፍያን አህመድ፣ ቴዎድሮስ አድሀኖም፣ ቴዎድሮስ ሀጎስም የቦርዱ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በመጨረሻም አዜብ የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ሆና ስትመረጥ፣ ምክትሏ ደግሞ የብአዴኑ ካሳ ተ/ብርሃን እንዲሆን ተደርጓል (ሁሉም በእነአዜብ ቡድን ስር ናቸው) የሁለቱም ቡድን አባላት ‹‹ቃየል››ን እንጂ ‹‹አቤል››ን መሆን አይፈልጉም፡፡ እናም የከፋ ነገር ከመጣ ‹‹ቃየላዊ›› እርምጃዎችን እስከመውሰድ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታም ሊሳካ የሚችለው የታጠቀውን ኃይል ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ ለተንቀሳቀሰ ኃይል ነው፡፡ እናም ከእርስ በእርስ ግጭቱ በበላይነት ለመውጣት እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ (እያሴሩ) ነው (እስከአሁን ባለው ሁኔታ ብአዴን ሙሉ ድጋፍ እያደረገለት ያለው የእነአባይ ወልዱ ቡድን ‹‹የተሻለ›› ሊባል የሚችል የበላይነት አሳይቷል)፡፡ በዚህን ጊዜም ከድንገቴ አደጋ ራስን መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ የግል ጥበቃቸውን አጠናክረዋል፡፡ ለምሳሌ በረከት ስምዖን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠባቂዎቹን ከሁለት ወደ ስድስት አሳድጓል፤ ሁለት ተጨማሪ መኪናዎችም ከፊትና ኋላ ሆነው እንዲያጅቡት አሰማርቷል፡፡ ባለፈው ወር በተካሄደው የግንባሩ ዘጠነኛ ጉባኤ አዜብ መስፍን ‹‹መለስ በስልጣን ላይ እያለ ደሞዙ ስለማይበቃን ብዙውን ጊዜ ከወር እስከ ወር ቀለብ ሳያልቅብን ለመድረስ እንቸገር ነበር›› የሚል አንድምታ ያለው ንግግር አድርጋ ካለቃቀሰች በኋላ ‹‹በደሞዝ (በፔሮል) የሚኖረው ባለስልጣን መለስ ብቻ ነው›› ስትል ማድመጣችን ይታወሳል፡፡ በእርግጥ አዜብ ልታስተላልፍ የፈለገችውን መልዕክት አንጓ ከ‹‹ሰሙ›› ለይተን ስናወጣው ‹‹ቅልጥ ባለ ዘረፋ ላይ የተሰማራችሁ ባለስልጣናት በልዩነታችን ላይ ካልተግባባን ላጋልጣችሁእንደምችል እንድታውቁት›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የበረከት ‹‹ቴሌቪዥን ጣቢያ››ም ይህንን ሃሳብ በተለየ ሁኔታ ያስተላለፈው ትርጉሙ ሳይገባው ቀርቶ አይመስለኝም፡፡ እነዚህን ኩነቶችም ስንጨምቃቸው ‹‹ህወሓት የውስጥ ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየባሰ ሄዶበታል›› የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሱናል (የአዜብን መልዕክት ባደመጥን ማግስት አራት ኪሎ አካባቢ ከአንድ የአረና አመራር አባል ጋር ድንገት ተገናኝተን ይህንን ሁኔታ አንስተን ስናወራ እንዲህ አለኝ፡- ‹‹እነርሱ ቀልደኞች ናቸው፤ በ1993 ዓ.ም የክፍፍሉ ወቅት መለስ ለቤተመንግስቱ የተመደበው ሁለት ሚሊዮን ባጀት የት እንደሚገባ ሲጠየቅ ‹ይሄ ግቢ እኮ ከምንሊክ ዘመን ጀምሮ ጮማ የለመደ ነው› ብሎ አድበስብሶ አልፎት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በተቀረ አዜብ ‹በመለስ ደመወዝ ብቻ ስለምተዳደር ሽሮና በርበሬ እያለቀብኝ እቸገራለሁ› ማለቷ ከእርሷ ጋር የአቋም ልዩነት ላላቸው የህወሓት አመራር በጎንዮሽ የማስፈራሪያ መልዕክት ከማስተላለፍ የዘለለ ቁም-ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡››)
ሌላኛው በዕለቱ የታየው ዓብይ ጉዳይ መከላከያን የሚመለከተው ነው፡፡ የተመረጡት ሰዎች ውክልናቸው ተቋምን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሰረትም መከላከያን ወክለው የቀረቡት ጄነራል ሳሞራ የኑስና ጄነራል ሰዓረ መኮንን ናቸው፤ ሳሞራ ሙሉ ጀኔራል ነው፣ ሰዓረ ደግሞ ሌፍቴናንት፡፡ ስለዚህም መከላከያን ወክሎ የቦርድ አባል መሆን ያለበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለ አራት ኮከብ ጄነራል የሆነው ሳሞራ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፤ በዚህም ማንም አልተቃወመም-ከጄነራል ሰዓረ በቀር፡፡ ለምን? ሁለቱ ጄነራሎች በግል ስለማይግባቡ? በጥቅም ተጋጭተው? ሰዓረ ‹‹ሳሞራ አይመጥንም›› ብሎ አስቦ? እውነት ጉዳዩ የሁለቱ ብቻ ነው? ወይስ የሰዓረ ተቃውሞ መነሻ ምንድር ነው? …ይህንን ተቃውሞ የግለሰብ አድርገን እንዳንወስደው የሚያስገድዱ ገፊ ምክንያቶች የምላቸውን መጥቀስ እችላለሁ፡- ሁለቱም ተመሳሳይ ተቋም ወክለው መቅረባቸው አንዱ ነው፤ ሁለቱም ወታደሮች መሆናቸው ሌላኛው ነው (የወታደር ዲሲፕሊን በተለይም የኢህአዴግ ወታደራዊ አደረጃጀት ከታች ወደላይ ተቃውሞን እንደማያበረታታ ማንም አይጠፋውም) ሆኖም ‹‹የሳሞራን የቦርድ አባል መሆን በምን አያችሁት?›› ሲል የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል፡፡ በተጨማሪም ሰዓረ ያ ሁሉ ህዝብ በተሰበሰበበት አዳራሽ የሳሞራን ስም ሲያነሳ በሰራዊቱ ደንብ መሰረት በማዕረግ ስሙ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው በዕለቱ የተከሰተው ነገር ሁለቱ ጄነራሎች እያራመዱት ያለውን ልዩነት የሚያሳይ ነው የሚለውን መከራከሪያ የሚያጠናክረው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚከታተል የሠራዊቱን ወሳኝ ጄነራሎች ከጎኑ ማሰለፍ የቻለ ማንኛውም ቡድን ዳዊት የማይኖርበት ጎልያድ ሊሆን እንደሚችል አይጠፋውም፡፡ እናም ይህ ኩነት አንደኛ ዓመቱን ሊደፍን እየተቃረበ ላለው የሁለቱ ቡድኖች ፍጥጫ የመቋጫው ቀናት እየቀረበ እንደሆነ የሚያመላክት ይመስለኛል (በነገራችን ላይ በመከላከያ ውስጥ ከሳሞራ ቀጥሎ ባለ የስልጣን ወንበር ላይ የምናገኘው በተመሳሳይ ማዕረግ የሚገኙ ሶስት አቻ ጄነራሎችን ነው፡፡ ሁለቱ ጄነራል አበባው ታደሰ እና ጄነራል ሰዓረ መኮንን ናቸው፡፡ እነዚህ ጄነራሎች አንም ቀን ተስማምተው ሰርተው አያውቁም፡፡ ስልጣናቸውና ኃላፊነታቸው ተመሳሳይ ቢሆንም አበባው የሚመራው ቢሮ በተሰሚነት ጎላ ያለ ነው፡፡ …ሳሞራ በግልፅ ‹‹በዚህ ቀን›› ብሎ ባይናገርም ከኤታማዦር ሹምነቱ የመልቀቅ እቅድ አለው፡፡ በአሁኑ አሰላለፍም ከእነአዜብ ጎን ይመደባል፡፡ አበባውና ሰዓረ ደግሞ የእርሱን ቦታ ይፈልጉታል፡፡ አበባው የሳሞራ የቅርብ ሰው ነው፡፡ ከሰዓረ ጋር ያለው ግጭትም ከሳሞራ ጋር ካለው ግንኙነት ጋር ይያያዛል)
የሆነ ሆኖ ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት››ን በሚመለከት ተጨማሪ ነጥብ ልጥቀስ፡፡ ከቀኑ ስብሰባ በኋላ በሸራተን ሆቴል ለፋውንዴሽኑ ገቢ ማሰባሰቢያ አንድ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ የክልል አስተዳደሮች ‹‹አቅማችን ይመጥናል›› ያሉትን ያህል የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከሁሉም ቀድሞ አንድ ሚሊዮን ብር ያዋጣው እነአዲሱ ለገሰ እንደግል ንብረታቸው የሚቆጥሩት ‹‹ጥረት ኢንዶውመንት›› ሲሆን፣ የአላሙዲ ‹‹ሚድሮክ ኢትዮጵያ››ም ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገብቷል፡፡ ትኩረቴን የሳበው ግን ይህ አይደለም፤ ገቢና ወጪው ከህዝብ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ኦዲተርም አይን የተሰወረ ነው
የሚባለው እጅግ ባለፀጋው የህወሓቱ ‹‹ኤፈርት›› በዕለቱ ሰባራ ሳንቲም ለማዋጣት ቃል አለመግባቱ እንጂ፡፡ ለምን? ኤፈርት በእነአዜብ ስር ከመሆኑ አኳያ ለትችት ያጋልጠናል በሚል? ወይስ ገና ያልተደረሰበት እንቆቅልሽ ይኖር ይሆን? ጥያቄው ይህ ነው፡፡ የዚህን መልስ ጨምሮ ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች ሲፍታቱ ልዩነቱን እና አሰላላፉን ያጎሉታል ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደመውጫ
በሀገራችን ላይ ‹‹ለውጥ አመጣለሁ›› የሚለው የተቀውሞ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ ‹‹ይህን ዓመት አያልፍም!›› በሚል ሟርት ሲጠመድ፣ ድርጅቱ ግን ሃያ ሁለተኛ ዓመቱን ሻማ ለኩሶ ሊያከብር ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ዘንድሮም የመለስን ሞት ወይም የግንባሩን መከፋፈል ብቻ ስናመነዥክ የቋመጥንለት ለውጥ የውሃ ሽታ ሆኖ ነገሩ ሁሉ ‹‹የሞትንም እኛ፤ ያለንም…›› እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ እናም በላያችን ላይ እያመፀ ያለውን ፍርሃት ማረቅ ያስፈልጋል፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነት ያስፈልገናል፤ ከኢህአዴግ በኃላም ሊኖር ስለሚገባው ለውጥ መነጋገር ያስፈልጋል፤ ስርዓቱ ሀገር የሚጠቅም አለመሆኑን በበቂ ሁኔታ ገብቶናልና፣ የርዕዮተ-ዓለም ወይም የፖሊሲ ድክመቱን በምክንያትና አመክንዮ (ሎጂክ) እየተነተንን ብቻ ተጨማሪ ጊዜ ማባከኑ ፋይዳ የለውም፡፡ ፋይዳ ያለው በሰላማዊ መንገድ አደባባይ ወጥቶ የስርዓት ለውጥ ማድረግ ነው፤ ትንተናዎችም ይህ አይነቱን እንቅስቃሴ ወደ መሬት ማውረድ የሚቻልበት እና ከኢህአዴግ በኋላስ? የሚለው ላይ ሲያተኩሩ ነው፡፡