ጥያቄ፡- ድንግልናዬን ያስረከብኩት ከሁለት ወራት በፊት በጣም ለምወደው ፍቅረኛዬ ነው፡፡ እንደጠበቅኩት ግን በወሲብ መደሰት አልቻልኩም፡፡ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ይሄን ደብዳቤ እስከፃፍኩላችሁ ዕለት ድረስ በፈፀምነው ወሲብ እሱ መደሰቱን ይግለፅልኝ እንጂ እኔ ግን ሥቃይና ሕመም ነው የተረፈኝ፡፡ ጓደኛዬን ከዚህ በኋላ ግንኙነት መፈፀም ይቅርብን ብለው ሌላ ነገር ተጠራጥሮ ፍቅራችን እንዳይቋረጥ ፈራሁ፡፡ እባካችሁ ምን መፍትሄ ትጠቁሙኛላችሁ?
ቅ.አ
ምላሽ፡- በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት የሚሰማ ሕመም እንዳልሽውም ለመግለፅ የሚከብድ ቢሆንም አንዳንዴ የማቃጠል ወይም ጨምድዶ የመያዝ ስሜትም ሊፈጥር ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ሕመሙ በብልት አካባቢ የሚሰማ ቢሆንም አንዳንዴ ወደ ውስጥ ጠልቆም ይሰማል፡፡
ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም በደምሳሳው በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
የመጀመሪያው በመራቢያ አካላት አካባቢ የአቀማመጥም ሆነ ውስጣዊ ችግር ሲኖር የሚከሰት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመራቢያ አካላት አካባቢ የባክቴሪያም ሆነ የፈንገስ ኢንፌክሽን ተፈጥሮ ከሆነ የሕመም ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ኢንፌክሽኖች ብዙ የወሲብ ጓደኛ ባላቸው ላይ የሚከሰት ቢሆንም አንዳንዴ ግን በታቀቡ ወይም በተወሰኑትም ላይ ሊከሰት ይችላልና መጠርጠሩ አይከፋም፡፡ ከግንኙነት ውጪ የማቃጠል ስሜት ካለ ወይንም ፈሳሽ ከማሕፀን (ከተለመደው የተለየ ዓይነት) የሚወጣ ከሆነ ችግሩ የመራቢያ አካላት ኢንፌክሽን ነውና እሱን በማረም ከችግርሽ መላቀቅ ትችያለሽ፡፡
እንደገለፅሽው አንቺ ለመጀመሪያ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የጀመርሽው ከሁለት ወራት በፊት ነው፡፡ ታዲያ አንዳንዴ በመጀመሪያው ግንኙነት ወቅት ሴትን ድንግል (virgin) የሚያስብላት ስስ ቆዳ መሰል ሽፋን ሙሉ ለሙሉ ይወገድና የቀረው ቦታ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በግንኙነት ወቅት ሕመም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚህ ላይ ይህ ስስ ቆዳ መሰል ሽፋን አንዳንዴ ጠባሳ ሊፈጠርበትም ይችላል፡፡ ከነዚህም በተጨማሪም ውስጣዊ የመራቢያ አካሎች እንደ ማሕፀንና እንቁላል አምራች አካል (Ovary) በአቀማመጣቸው መዛነፍ ይሁን የወሲብ ጓደኛሽ ብልት መጠን በመተለቁ ምክንያት በግንኙነት ወቅት የሚነኩ ወይም የሚገፉ ከሆነም ሕመም ሊከሰት ይችላል፡፡ በግንኙነት ወቅት ሴቷ ከላይ በመሆን ይህን ችግር መፍታት ትችላለች፡፡ በዚህ የወሲብ ዓይነት (position) የወሲብ ጓደኛዋ ብልት እምን ድረስ ዘልቆ መግባት እንዳለበት በቀላሉ መቆጣጠር ትችላለች ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ምድብ ምክንያት ደግሞ ከላይ እንዳየናቸው በመራቢያ አካላት ላይ ምንም አይነት ችግር ሳይኖር በግንኙነት ወቅት የሚከሰት ሕመም ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ አይነተኛ ምክንያት የሴቷ ብልት በሥርዓቱ ሳይዘጋጅ (በፈሳሽ ሳይለዝብ) ግንኙነት ሲፈፀም ነው፡፡ ከግንኙነቱ በፊት የፍቅር ጨዋታ (foreplay) በመፈፀምና በበቂ ሁኔታ በመተሻሸት የሴቷ ብልት በቂ ፈሳሽ እንዲያመነጭ ማድረግ ይቻላል፡፡S