በቅርቡ “ልቤን” የሚል አልበሟን በማውጣት ተወዳጅነቷን ዳግም ያረጋገጠችው ድምጻዊት ነፃነት መለሰ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ የዘ-ሐበሻ አንባቢዎችም ይካፈሉት ዘንድ አስተናግደነዋል።
ወደ ዋናው ጥያቄ ከመግባቴ በፊት ስለ ልብሽ ልጠይቅሽ እፈልጋለሁ፡፡ ልብሽ እንዴት ነው?
(ረጅም ሣቅ)…ልቤ ድም ድም እያለ ነው፤ በአግባቡ ይመታል፡፡
በቅርቡ ያወጣሽው አልበም “ልቤን” ስለሚል ልቧን ምን አገኘው ብዬ ነው?
“ልቤን” የዘፈንኩት ዜማና ግጥም ተሰጥቶኝ ነው፡፡ የኔ ልብ ድጋሚ ሊወሰድ አይችልም፤ ምክንያቱም አንዴ የወሰደ ወስዶታል፡፡ ሌሎቹን ልባቸው የተወሰደባቸውን ይወክላል ማለት ነው፡፡
አንቺ በጣም የታወቅሽበት ዘፈን የመጀመሪያው “ፏፏ ይላል ዶጁ” ዘፈንሽ ይመስለኛል፡፡ እውነት ነው እሱ ነው? በዛን ጊዜ ስለ ዶጁ መኪና፣ ስለ አረንቻታ መጠጥና ስለ ቸርችል ጐዳና በግጥሞችሽ ውስጥ ዘፍነሻል፡፡ ዶጁ መኪናን ደርሰሽበታል? አረንቻታ መጠጥ ምን አይነት ነበር? ቸርችል ጐዳና አንቺ ከምታውቂው ምን ያህል ተለውጧል? ምክንያቱም ያኔ ታዋቂ ጐዳና ነበርና?
ዶጅ እንግዲህ የመኪና ብራንድ ነው፡፡ አሁንም አለ፤ በጣም ፋንሲ (ቄንጠኛ) የሆነ መኪና ነው፡፡ ያኔ በእናቶቻችን ጊዜ የነበረ ስለሆነ ያኔ የማውቀው ነገር የለም፣ ዘፈኑ ሲሰጠኝ ዘፈንኩት፣ መኪናውን አላየሁትም አላገኘሁትም፡፡ ክሊፑን ስሰራ ግን ካፕቴይን አለማየሁ ይሁኑ ካፕቴይን ከበደ ስማቸውን በትክክል አላስታውስም፤ የሳቸው መኪና ነበር ይህ መኪና ዶጅ ነው ግን የመጀመሪያው ሳይሆን ተሻሽሎ የመጣ ቆንጆ መኪና ነበር፤ እሱን አይቻለሁ፣ የድሮውን አልደረስኩበትም፡፡
አረንቻታን አላውቀውም፤ በኛ ጊዜ የነበረውና አረንቻታ ተብሎ የሚሸጠው በቢራ ጠርሙስ አይነት ሆኖ እንደ አረንቻታ ይሸጣል እንጂ ራሱ አረንቻታ አይደለም ያው እሱንም አላውቀውም፤ ግን ይሄኛውም አረንቻታም ለስላሳ መጠጥ ነው፡፡ ቸርችል ጐዳና ያኔ ከነበረው ብዙ አልተለወጠም፡፡ ድሮ የነበረው አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ይህን ጐዳና ብዙ ለውጥ አላይበትም፡፡ እኔም በዘፈኑ ብቻ ሳይሆን ካቴድራል ስማር የማውቀው ይሄንኑ ቸርችልን ነው እና ብዙ ልዩነት የለውም፡፡
“የታል ልጁ የታል” የሚለው ክሊፕሽ ላይ ሰውነትሽ ደንደን ያለ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ “ባይ ባይ”ን ስትሰሪ በጣም ሸንቃጣ ሆንሽ፡፡ ይሄ ደግሞ የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ነበር፡፡ እንደውም አንድ ሰሞን ባይ ባይ ያለችው ሰውነቷን ነው እንዴ ሲባል ነበር፡፡
ትንሽ ደጋግሜዋለሁ፡፡ ይህንንም ቢሆንም ልንገርሽ ባይ ባይ ያለችው ሰውነቷን ነወይ የሚለው ሊሆን ይችላል፤ ያስኬዳልም፡፡ ሰውነቴን ልቀንስ የፈለግሁት በህመም የተነሳ ነው፡፡ ሰውነቴ ከባድ ስለነበረ ለቁመቴ አይመጥንም፤ “ፕሮፖርሽናል” አልሆነም፣ እግሬ ሰውነቴን መሸከም ስለማይችል ዶክተሮች ያለሽ አማራጭ መክሳት እንጂ ሌላ የምንሰጥሽ አማራጭ የለም ስላሉኝ በዛ ምክንያት ነው የከሣሁት፡፡
ከአኗኗር ዘይቤ መቀየር ጋር በተያያዘ በአገራችንም ብዙ ሰዎች ከልክ በላይ እየወፈሩ ነው፤ በተለይ ሴቶች በአሁን ሰዓት ውፍረት እየፈሩ ነው፡፡ መቀነስ ይፈልጉና መቀነስ ምኞት ይሆንባቸዋል፡፡ እንዴት መቀነስ እንዳለባቸው ምክር ልትለግሻቸው ትችያለሽ?
ዋናው የህክምና ባለሞያን ማማከር ነው፡፡ ዝም ብሎ መክሳትም የራሱ ችግር አለው፡፡ ምክንያቱም ሰውነት ከካሣ በኋላ በሚፈለገው መጠን በምግብ ካልተደገፈ ጥሩ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የስነ – ምግብ ባለሙያዎችን በማማከርና በእነርሱ በመታገዝ ነው መሆን ያለበት፤ ከዚያ በኋላ ይህን ተግባራዊ ማድረግ ያንቺ ድርሻ ነው፡፡ በቀጣይ መሆን ያለበት ሌላው ዋና ነገር ለዚህ ነገር አዕምሮን ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ መክሳት አለብኝ ስትይ አዕምሮሽ ዝግጁ ካልሆነና ጀምሮ ለመተው ከሆነ ይሄ አካሄድ የትም አያደርስም፡፡ እንደውም ከሁሉም የሚቀድመው ሰውነቴን እቀንሳለሁ ብለሽ ለአዕምሮሽ መንገርና መዘጋጀት፣ ከዚያም ሌሎቹን ሂደቶች መከተል ነው፤ ዋናው ከዛ በኋላ እስከ መጨረሻው ክትትሉ መሄድ አለበት፡፡ አሁን ከስቻለሁ ብለሽ ብታቆሚ ተመልሶ ይመጣል፡፡ የምንበላውንና የምንጠጣውን ነገር በአግባቡ ለሰውነት በሚስማማ ሁኔታና መጠን ማድረግ አለብሽ፡፡
ወደ አዲሱ ሥራሽ ከመምጣቴ በፊት አንድ ነገር ልጨምር፡፡ ቀደም ሲል መንፈሳዊ መዝሙር ሠርተሽ ነበር፡፡
በዚህ ወቅት በቃ ነፃነት ወደ ዘፈን አትመለስም የሚል አስተያየት ሲሰጥ ነበር፡፡ አንቺ አሁን “ልቤን” ብለሽ ወደዘፈን መጥተሻል፡፡ ከመዝሙር ወደ ዘፈን መምጣት ምን አይነት ስሜት አለው?
መዝሙርና ዘፈን ለእኔ አይለያዩም፤ አንድ ናቸው ዋናው ልዩነታቸው የምንጠቀምባቸው ቃላት ናቸው እግዚአብሔር ለእኛ ድምፃችንን መክሊት አድርጐ እስከሰጠን ድረስ እግዚአብሔርን ልናመሰግንበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ አታፍቅሪ አትባይም አግብተሽ በአንድ ተወስነሽ ኑሪ ነው ትዕዛዙ፡፡
ስለዚህ የምትሰሪያቸው ነገሮች ትምህርታዊ እስከሆኑ ድረስ ከሃይማኖት ጋር የሚያጋጭ ነገር የለም፡፡ እኔም ብሆን እድገቴ በቤተ – ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠንና ቤተ – ክርስቲያንን መርዳት ስላለብኝ የማገለግለው እግዚአብሔር በሰጠኝ ድምጽ በመሆኑ በተሰጠኝ ፀጋ እግዚአብሔርን እና ቤተ – ክርስቲያንን አገለግላለሁ፡፡ በዚህ መሠረት ሁለቱም ለእኔ ልዩነት የላቸውም፡፡
ባለፈው ገና በኢቴቪ አንቺና ኩኩ ሰብስቤ ስለወርቃማ የጓደኝነት ጊዜያችሁ እያነሳችሁ ተመልካቹን ስታዝናኑ ነበር፡፡ ስለ ጓደኝነታችሁ እስቲ ንገሪኝ…ይህን የምልሽ የአሁን ዘመን ጓደኝነት የአንድ ሰሞን ብቻ ነው ስለሚባል ነው፡፡
በእኔ እምነት ጓደኝነት እንደአያያዝሽ ነው፡፡ እኔ የምፈልጋቸው እሷም የማትፈልጋቸው ነገሮች ካሉ እነዛን አቻችለን መኖር ነው፡፡ በአጠቃላይ ተቻችለሽ መኖር ከቻልሽ ብዙ የጓደኝነት ዕድሜ ታስቆጥሪያለሽ፡፡ አሁን እኔ ከኩኩ በተጨማሪ ብዙ ጓደኞች አሉኝ፤ እሷም ብዙ ጓደኞች አሏት፡፡ እነዚህን ጓደኞችሽን ጓደኝነታቸውን ጠብቀሽ ለመቆየት መቻቻል እና አንዳንድ ነገሮች ሲኖሩ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲኖሩ ጓደኝነት ይጠነክራል እድሜውም ይረዝማል፡፡ የእኔና የኩኩም ጓደኝነት በዚህ መርህ የተቃኘ እንጂ ሌላ ምስጢር የለውም፡፡
በዛው ፕሮግራም ላይ አንዳችሁ የአንዳችሁን ዘፈን ስታንጐራጉሩ ነበር፡፡ ከኩኩ ዘፈኖች የትኞቹን ታደንቂያለሽ?
እንዳልሽው በፕሮግራሙ ላይ የሷን ዘፍኛለሁ፤ ዘፈን ስጀምርም ድምፄን የገራሁት በእሷ ዘፈን ነው፡፡ ዘፈኖቿን ሁሉ እወዳቸዋለሁ፡፡
“ልቤን” በተሰኘው አልበምሽ ላይ አብይ አርካ የተባለ ወጣት አቀናባሪ ነው የመረጥሽው፡፡ በፊት በፊት ለሙዚቃ ቅንብር አንጋፋዎቹ ይመረጡ ነበር፡፡ አሁን ወጣቶቹ ትኩረት እየሳቡ ነው፡፡ አንጋፋዎቹ ጋር ወረፋ ከመጠበቅና ሥራን ከማጓተት ተብሎ ነው ወይስ ወጣቶቹን ለማበረታታት?
የኔ ምላሽ ሁለቱንም ያነሳሻቸውን ሃሳቦች የሚያስታምም ነው፡፡ ምን ማለቴ ነው በአብዛኛው ትልልቆቹ አቀናባሪዎች ብዙ ሥራ ስላላቸው የሚሰጡሽ ጊዜ በጣም ትንሽ ነው፡፡ እንደምታውቂው አሁን ያለነው ዘፋኞቹ ደግሞ እንደበፊቱ ውስን አይደለንም፤ በጣም በዝተናል፡፡ እነዛን ሁሉ አንጋፋዎቹ ማስተናገድ አይችሉም፡፡ ከታችም ያሉትን ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ በስራ እስከተግባባችሁ ጥሩ እስከመጣልሽ ድረስ እና ደስ የሚል ቅንብር ከሠራ ምንም ችግር የለውም፡፡ ወጣቱን የሚደግፍ ቤዝ ተጫዋች ትንሽ አንጋፋ የሆነ አብረሽ ታሠሪያለሽ፡፡ ይሄ ከሆነ ከወጣቶቹ ጋር የማንሰራበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስራም ከሚጓተት ወጣቶችም መስራት ስለለባቸው በዚህ መልኩ ነው አብይን የመረጥኩት፡፡
በካሴት ሽፋንሽ ላይ ላቅ ያለ ምስጋና ካቀረብሽላቸው ውስጥ አቀናባሪሽ አብይ አንዱ ነው “እደግ ተመንደግ” ብለሽዋል፡፡ በስራው ያን ያህል አስደስቶሻል ማለት ነው?
አዎ ደስተኛ ነኝ፡፡ ይሄ ልጅ በጣም ልጅ ነው፣ በዛ ላይ እኛ አርቲስቶች ስንሰራ ብዙ አይነት ፀባይ አለን፡፡ ሙዚቃ ሲሰራ በርካታ ውጣ ውረዶች አሉት፡፡ ያንን ሁሉ በትዕግስት ችሎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ሌላ ጊዜም እንዲህ አይነት ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አስቦና ታግሶ ሲሰራ ደስ ይልሻል፡፡ ስለዚህ ማመስገንና እውቅና መስጠት አለብሽ፡፡ በዚህን ጊዜ ለሌላ ጥሩ ስራ ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡ ለዚህ ነው ወጣቱን ያመሰገንኩት፡፡
ለዚህኛው ጥያቄዬ “ልጅ ከልጅ አይበልጥም” የሚል የተለመደ መልስ አልጠብቅም፡፡
(ሣ…ቅ…)
ጥያቄውን ልስማው?
አንዳንድ አስተያየቶችን ስሰማ “ልቤን”፣ “አትደውልልኝ”፣ “ከረሜላዬ” እና “እሩቅ” በጣም እየተደመጡ ነው፡፡ አንቺ ከዚህ አልበም በጣም የወደድሽው የትኛውን ዘፈን ነው?
(ረጅም ሣቅ) ይሄንን ነገር አንቺ ካልፈለግሽው ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ አባባሉ ግን አሁንም ትክክል ነው ልደግምልሽ እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድን ስራ ስትሰሪ ጠልተሽው የምትሠሪው ሥራ የለም፡፡ ሁሉንም መርጠሽና ወደሽ ነው የምትሠሪው፡፡ ልታበላልጭ አትችይም፡፡ አድማጭ አንዱን ዘፈን አሁን ካለበት፣ ካለፈውና በቀጣይ ካሰበው ነገር ጋር አገናኝቶ ሊወደው ይችላል፡፡ እኔ ግን እንደዘፋኝ ዘፈኖቼን አላበላልጥም፡፡ አንዱ ልነግረሽ የምፈልገው “ይላል ዶጁ”ን ብትይኝ የታወቅኩበት ዘፈን በመሆኑ በጣም እወደዋለሁ፡፡ በተረፈ ሌሎቹን ፈልጌ የሠራኋቸው በመሆናቸው ሁሉንም እወዳቸዋለሁ፡፡
በአዲሱ አልበምሽ ውስጥ “አትጠይቀኝ፣ አትደውልልኝ” የሚል ዘፈን አለ፡፡ ይሄ ዘፈን መቻቻልን አያበረታታም የሚሉ አሉ፡፡ አንቺ እንዴት አየሽው?
“አትደውልልኝ” አሉታዊ መንፈስ የለውም አትጠይቀኝ አትደውልልኝ የሚለው ሃሳቡ “አንተን ካየሁ ያገረሽብኛል” ነው፡፡ ግን ስታየው ድምፁን ስትሰማ ወደቀድሞው ስለምትመለስ፣ ካለህበት ልውደድህ፤ እኔም ኑሮዬን ልኑር፤ አትደውልልኝ አታስታውሰኝ ትላለች፡፡ ሳልፈልግ ስለሄድክብኝ አሁን ሳልፈልግ አትምጣ ነው፡፡
ወባና ፍቅር ካገረሸ ይገድላል ይባላል፡፡ እንዳትሞት ፈርታ ይሆን?
(ሣ…ቅ…) ይመስለኛል፡፡ እንደዛ አይነት ፍራቻ ሳይኖራት አይቀርም፤ ጥላቻው ግን የላትም፡፡ ነገር ግን ተመልሳ ከገባችበት የባሰ እንዳትጐዳ ብላ ነው፡፡
“ከረሜላዬ”ን ለማን ነው የዘፈንሽው? ሌላው ከረሜላዬ ትንሽ ወዝወዝ የሚያደርግና ዳንስ የሚፈልግ ነው፡፡ ለክሊፑ ዳንስ ተለማመድሽ ወይስ ቀድሞም ትችያለሽ? ወጣቶችም በፊቸሪንግ አጅበውሻል፡፡ እነማን ናቸው?
ለነገሩ ፊቸሪንግ ቶኪቻው (ዮሐንስ በቀለ) ነው የሠራው፡፡ ክሊፑ ሲሰራ ከእኔ ይልቅ የቶኪቻውን ዳንስ የበለጠ የምትመለከቱ ይመስኛል፡፡ እኔ ልሞክር እፈልጋለሁ ግን እስካሁን አልቻልኩበትም፡፡ ዘፈኑን የዘፈንኩት ለባለቤቴ ለሱራፌል በዛብህ ነው፡፡ ሌላውም እንግዲህ ከረሜላዬ ለሚለው ሊጋብዘውና ሊዘፍነው ይችላል፡፡
ባለቤትሽ አቶ ሱራፌል በአልበምሽ ላይ በግጥምና ዜማ ተሳትፏል፡፡ የሙዚቃ ባለሙያ ነው እንዴ? በስራሽስ ምን ያህል ያግዝሻል?
ባለቤቴ ከሙዚቃ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ የራሱን ቢዝነስ የሚመራ ነው፡፡ ነገር ግን ለእኔ ስራ በተለይ ለዚህ አልበም በጣም ነው የደከመው፡፡ ለዚህ ሥራ ባለቤቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከእኔ በላይ ማለት ነው፡፡ ገብቶ መዝፈን ነው የቀረው እንጂ እስከመጨረሻው ሲታገል ነበር፡፡ ዜማ ሲያስመጣ፤ ወዲህ ሲል ወዲያ ሲታገል ብዙ ረድቶኛል፡፡ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ሥራዬ እዚህ ደረጃ የደረሰው በእርሱ ብርታት ነው፡፡
ከዚህ በፊት “ፍርቱና” በተሰኘው ዜማሽ ላይ ናቲ አያሌው (ናቲማን) በፊቸሪንግ አብሮሽ ተሳትፏል፡፡ አሁን ደግሞ በ”ከረሜላዬ” ቶኪቻው ሰርቷል፡፡
የቀድሞ ዘፋኞች ከወጣት ድምፃዊያን ጋር ሲሰሩ ብዙ አይታዩም፡፡ የቀደመውን ዘፈን ከዘመኑ ጋር አቀላቅሎ መስራት አልተለመደም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያንቺ አስተያየት ምንድነው?
እንደሚታወቀው እኔ ከድሮ ጀምሮ ስሰራ የነበርኩት ዘመናዊ ሙዚቃዎችን ላይ ነው፡፡ እናም ድሮ ሙዚቃ በደንብ በማይታወቅበት ጊዜ የሙዚቃ አቅርቦቱ ውስን ነው፡፡ አሁን ግን ሙዚቃው በጣም ሰፊ ሆኗል፡፡ በእኛ ጊዜ ስትዘፍኚ አድማጭ ድምጽን የማድነቅና የግጥሙ መልዕክት ላይ የበለጠ የማተኮር ነገር ነበረው፡፡ አሁን ያሉት ዘመናዊ ዘፈኖች እያደጉ በመምጣታቸው፣ የእኛም አገር አድማጭ በደንብ ሞቅ ያሉና ፈጠን ያለ እንቅስቃሴ ያላቸውን የውጭ ዘፋኖች መከታተልና የዘፋኞቹ የህይወት ታሪክ ሳይቀር፤ ምን እንደበሉና እንደጠጡ የሚያውቅበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ብዙ ወጣት የሚያዳምጠው ዘመናዊ ዘፈን በመሆኑ ራሴን ከዘመኑ ጋር በማስማማት ወጣቱም፣ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉትም ሆነ የድሮዎቹን ባማከለ መልኩ ለመስራት ሞክሬያለሁ፡፡ ይሄ የበለጠ ጠቃሚ ነው፤ ሁሉንም ታሳቢ ማድረግ፡፡
አሁን ከካናዳ ጠቅልለሽ አንደኛሽን ነው የመጣሽው ወይስ ለአልበም ሥራሽ ብቻ ነው?
ጠቅልዬ አልመጣሁም ግን ለመምጣት በሂደት ላይ ነኝ፡፡ ጠቅልሎ ለመምጣት ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ በቀላሉ መጥተሽ ለመኖር አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ አስፈላጊ ነገሮችን በማመቻቸት ላይ ነኝ፡፡ ምን ልስራ፣ ልጄን የት ላስተምር የሚሉ ነገሮች ከወዲሁ እያስተካከልኩ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በሚቀጥለው ዓመት የሚሣካ ይመስለኛል፡፡
አንድ ልጅ ብቻ ነው ያለሽ፡፡ ሌላ ልጅ መድገም አልፈለግሽም ነበር?
ልክ ነው አንድ የ10 ዓመት ልጅ ነው ያለኝ – ኢዮስያስ ሱራፎል ይባላል፡፡ እንደምታውቂው የእኛ ሥራ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፤ እንደፈለግሽ ልጅሽን ጥለሽ የምትንቀሳቀሽበት አይደለም፡፡ አገሩ ሠራተኛ እንደልብሽ የምታገኝበት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ እና የዛ አገር ኑሮ በፍፁም አንድ አይደለም፡፡ እና ልጅሽን አሳልፈሽ ለሌላ ሰው ጐረቤት ጠብቁልኝ ምናምን የሚባል ነገር የለም፡፡ የግድ ራስሽ መንከባከብና መጠበቅ አለብሽ፡፡ ስለዚህ አንዱን በደንብ ጠብቆና ተንከባክቦ ማሳደግ ይሻላል ከሚል ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ይባርከው፤ እሱኑ ሺህ ያድርገው እላለሁ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲካ ኤቨንትስና ኮሙኒዩኬሽን የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን እያነቃቃ ነው ይባላል፡፡ አንቺም አብረሽው እየሰራሽ ነው፡፡ እንዴት ነው ከአዲካ ጋር ያለሽ ስምምነት?
ያው ስምምነታችን የገዢና የሻጭ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አዲካ የኛ ስራ በቀዘቀዘበትና በሞተበት ሰዓት ተነሳሽነትን ወስዶ ለሙዚቃው ትንሣኤ በመሆኑ ሊወደስ ይገባዋል፡፡ ሙዚቀኞች በተስፋ መቁረጥ ውስጥም ሆነው ሙዚቃ ሠርተው ሲጠብቁ እየገዛና እያበረታታ ያለ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡
የእኛ ስራ ደክመሽ የትም የመጣል ያህል ነው፡፡
የኮፒ መብት ጉዳይ ያልተረጋገጠበት አገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ አዲካዎች መጥተው ይህን ነገር እንዋጋለን ብለው በድፍረት በመጋፈጣቸውና ለአርቲስቶች ብርታት በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ትልቅ ኃላፊነት ነው የወሰዱት፡፡
አዲካዎች አልበም ከገዙ በኋላ ከዘፋኙ ጋር ትልልቅ ኮንሰርቶችን የመስራት ልምድ አላቸው፡፡ ከአንቺ ጋር ኮንሰርት እንደሚኖራቸው እንጠብቅ?
አዎ ትልቅ ኮንሰርት እንደሚኖረን ተነጋግረናል፡፡ ያው የናፈቅሁትን የኢትዮጵያ ህዝብ በዛ ኮንሰርት ፊትለፊት አገኘዋለሁ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡
ያው እንግዲህ ኮንሰርቱ ላይ ዳንስ አልችልም ብሎ ነገር የለም መዘጋጀት አለብሸ…
(ሣ…ቅ) አዎ ግን ብዙ ጊዜ መድረክ ላይ ዳንስ ከዘፋኝ ብቻ የሚጠበቅ አይደለም፤ መድረክ ላይ የሚያጅቡኝ ዳንሰኞች ይኖራሉ፡፡ የዳንሱ ጉዳይ ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ ለእኔም ጥሩ ነው፤ ለእነሱም የስራ ዕድል መፍጠር ይፈጥራልና መልካም ነው፡፡ እኔም እንግዲህ አቅም በፈቀደ ነቅነቅ ለማለት እዘጋጃለሁ (ሣ…ቅ)
“ልቤን” ሠባተኛ አልበምሽ ነው ልበል?
ከሌሎች ጋር በኮሌክሽን ከሠራኋቸው ጋር ልቤን ስምንተኛ አልበሜ ነው፡፡ ለነገሩ በዛን ጊዜ በኮሌክሽን ሲሰራ አንድ ታዋቂ ዘፈንሽ ነው አልበም የምትይው እንጂ እንደአሁኑ ሙሉ ካሴት ለብቻሸ አይደለም፡፡ እና በዛ ነው ስምንተኛ የምልሽ፡፡
ካናዳ ብዙ ስለቆየሽ ስለ አዲስ አበባ ጥቂት ጥያቄዎችን ልጠይቅሽ?
እኔ እኮ እዚሁ ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ለምን ብትይ… በየስድስት ወሩ፣ በየአመቱ እመጣለሁኝ፡፡
ጥሩ እንግዲያውስ ወደ ጥያቄው አሁን ያለነው አዲስ አድማስ ቢሮ ነው ከዚህ ተነስተን ሸጐሌ የሚባለው ሠፈር እንሂድ ታክሲ ከየት እንያዝ?
ጉድ ፈላ! ሸጐሌ የት ነበር? (በጣም ማሰብ ጀመረች) ሸጐሌ ስሙን አውቀዋለሁ እውነት ለመናገር የት ጋ ታክሲ እንደሚያዝ፣ አቅጣጫውም የት እንደሆነ አላውቅም፡፡ (ሣ…ቅ)
ከቶታል ፒያሳ – ከፒያሣ አስኮ መድሃኒያለም ሄደሽ፣ ከዚያ ነው ሸጐሌ መንደር ሰባት የሚባል ታክሲ የምትይዢው፡፡
በፊት ብዙ ከተማ ውስጥ አትዞሪም ነበር ማለት ነው?
አዎ የመዞር “ተሰጥኦ” የለኝም፡፡ ብዙ ጊዜ ቤቴ መሆን ነው የሚያስደስተኝ፡፡
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ጉዳይ፣ ሹምሽሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚዲያ ትከታተያለሽ ብዬ አስባለሁ?
በሚገባ! እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ሁሉንም እከታተላለሁ፡፡
ስለዚህ አዲሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልትነግሪኝ ትችያለሽ ማለት ነው?
ኦ…አቶ ሃይለማሪያም ናቸዋ!
እሣቸው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ እኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ነው ያልኩት…
ኦ…ስማቸው ማን ነበር? ዶክተር…እንትን የነበረው አይደለ? የጤና ጥበቃው የነበሩት እንደሆነ አውቃለሁ ዶክተር…ስማቸው ዘነጋሁት…እ…ዶክተር ቴዎድሮስ ናቸው… አለፋሽኝ፡፡
ካናዳ ምን ነበር የምትሠሪው? የምሽት ክበቦች አሉ ወይስ እንዴት ነበር?
በፊት አሜሪካ እያለሁ የምሽት ክበብ እሠራ ነበር፡፡ ካናዳ ከሄድኩ በኋላ ግን በሙዚቃ ደረጃ ሠርቼ አላውቅም፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አሜሪካ እየተጋበዝኩ ሾው ሠርቼ እመለሳለሁ፡፡ ካናዳ ግን ቅድም እንደነገርኩሽ የባለቤቴ ቢዝነስ አለ፤ እሱን ነው የማግዘው፡፡
ከሙዚቃው ብዙ ርቀሽ ስትመለሽ በድምጽሽ ላይ የተፈጠረ ችግር የለም ምክንያቱም አሁን የነፃነት ድምጽ ትንሽ ጐርነን ብሏል የሚሉ አድማጮች አሉ፡፡
እውነት ለመናገር በድምፄ ላይ የተፈጠረ ችግር የለም ምክንያቱም እዛ ሁሌ ቤተክርስቲያን ስለማገለግልና ተሰጥኦ ስለምቀበልና ስለምጮህ ያው ፕራክቲስ እያደረግኩ ነው ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ድምጽ ሁሌም ካልሠራሽበት ክራክ እያደረገ ይመጣል፤ የታወቀ ነው፡፡ የምታንጐራጉሪና የምትዘፍኚ ከሆነ ድምጽሽ እንደተጠበቀ ይቆያል ማለት ነው፡፡ እንዳልኩሽ ቤተክርስቲያን ተሰጥኦ ስቀበል በጣም እጮሀለሁ፡፡ እዛ ማሪያም ቤተክርስቲያን አለች፤ በኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ የተሠራች እዛ አገለግላለሁ፤ ድምፄ በዚህ ምክንያት አላረፈም፡፡ የድምፄ ነገር ትንሽ ወፈር ብሏል ግን የተጋነነ አይደለም፡፡
አዲሱ አልበምሽ እንዴት ነው… ተቀባይነት አግኝቷል ትያለሽ?
ለነገሩ አንዳንዶቹ ትንሽ ድምጽሽ ተቀይሯል ይላሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ጥሩ ጥሩ አስተያየቶችን ተቀብያለሁ፡፡ በስራዬ ደስተኛ መሆናቸውን ይነግሩኛል፡፡
አንድ አስቤው ያልጠየቅኩሽ ነገር አለ፡፡ ስለ “ባይ ባይ” ዘፈንሽ ብዙዎች በጣም አንጀት የሚበላ ዘፈን ነው ይላሉ፡፡ የሃሳቡ መነሻ ምንድን ነው?
የዘፈኑ ግጥምና ዜማ ደራሲ አብርሃም ወልዴ ነው፡፡
መነሻችን ከሊባኖስ ወደ ኢትዮጵያ ሲበር ሜዲትራንያን ባህር ላይ ለተከሰከሰው የኢትዮጵያ አውሮፕላንና ላለቁት ወገኖቻችን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሊፕ ለመስራት ፈልገን ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስንሄድ በፍፁም ሊተባበሩን አልቻሉም፡፡ አየር መንገድ ውስጥ አውሮፕላኖቹ አካባቢ የምንቀረፀው ነገር ነበር፡፡ ብዙ የድሮ አውሮፕላኖች አሉ፤ የሚበሩትንም አካተን መቅረጽ ፈልገን ነበር፡፡ በጣም ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ተቸገርን፡፡
በዚህ ምክንያት “ባይ ባይ” ራሱ ለሞት ብቻ መሆን ስለሌለበት ሁሉንም እናካተው ብለን በቃ “ቻው” ለማለት ይሁን ብለን መንፈሱን ወደዚህ ቀየርነው ማለት ነው፡፡ ሰው ከአገር ሲወጣ፣ አብሮ ውሎ ሲለያይ ቻው ቻው ብሎ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ በሞትም ይሁን በጉዞ የሚለያይ ሰው ቻው ብሎ መሄዱን ይወክላል፡፡ የሆነ ሆኖ አየር መንገዱ ባይፈቅድም የሞቱት ወገኖች በዘፈኑ ተካተዋል፡፡
ያልተነሳ ነገር ካለ… ወይም ማከል የምትፈልጊው እድሉን ልስጥሽ፡፡
ሁሉም ነገር ተዳስሷል፡፡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡