
አሚኮ በዜና ዘገባው በአማራ ክልል ወልቃይት ሁመራ አካባቢ ስለተከናወነ አንድ የልማት ይሁን የጥፋት ድርጊት ሽፋን ሰጥቶ አሠራጬ አሉ – ሰሞኑን፡፡ ለካንስ ስለ ስያሜዎች አጠራር እንደዱሮው ሕወሓትን አላስፈቀደ ኖሯል፡፡ ከዚያማልህ ጄኔራል ታደሠ ወረደ አበደልሃ! “እንዴት ምዕራብ ትግራይን የአምሃራይ ክልል ክፍሊ አድርጋቹ ትዘግብኣላቹ፤ ህገ መንግሥቲ መጣሽ አይደለም ወይ…” ብሎ ታዴ ቅሪተ-ሕወሓት ዕ. ብ. ድ አለላችኋ፡፡
በኢትዮጵያ የዘመናችን ድፍርስና amorphous ፖለቲካ እንደወያኔና እንደኦህዲድ ሥነ ተፈጥሯዊ ብልሽት የሚገርመኝም ሆነ የሚያሣዝነኝ የለም፡፡ የኦህዲድ ይቆየኝ፡፡
ሕወሓት ራያንና ወልቃይትን በጉልበት ወደትግራይ አካለለና ሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ ያሻውን ሁሉ አደረገ፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ እንደመስበሩ ከስድስት ሚሊዮን የትግራይ ሕዝብ የወጡ ውሉዳነ አጋንንት የሕወሓት ‘ኤሊቶች’ ሕዝቡን በፕሮፓጋንዳ ድማሚት አደንቁረው የርሱ ያልሆነን የርሱ እንደሆነ አምኖ እንዲቀበልና በዝርፊያው እንዲተባበራቸው ካደረጉ በኋላ የመሬት ግዛትን ጨምሮ ሌላ ሀብት ንብረትንና ገንዘብን ከሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ለ27 ዓመታት በተለይ ሙልጭ አድርገው በመውሰድ የትግራይ ምድር እስኪሰምጥ ድረስ- የወቅቱን አባባል ለመጠቀም ነው – ትግራይን ወርቅ በወርቅ አደረጓት፡፡ መጨረሻውን መናገር ግን ለቀባሪ ማርዳት ነውና ብዙም አንናገርም – ይቅር፡፡ የግፍ ሥራ ውጤቱ ሌላ ግፍ ነውና ትግራይም ተጋሩም በዚያ የዝርፊያና የጥጋብ ዘመን ዕኩይ ተግባሮቻቸው እንዳልተጠቀሙ ግነን አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡ የዘሩትን አጨዱና ትግራይ አሁን የዚያን ሁሉ ግፍና በደል ዕዳ፣ የኢትዮጵያን ልቅሦና የኢትዮጵያውያን የተከማቸ የደም ዕንባ የፈጠረውን የበደልና ግፍ ውቅያኖስ ውዝፍ ዕዳ እየከፈሉ ነው፡፡ በቀላሉ ከፍለው የሚጨርሱም አይመስሉም፡፡ ዳር ዳርታቸው የሚጠቁመው ደግሞ እነዚህ ሰዎች ጸጸት የሚባል ያልፈጠረባቸውና በበደል ላይ በደል ለመጨመር እየተጉ መሆናቸውን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወልቃይቴዎችን በወልቃይት ተራሮች ጫፍ እየወሰዱ “የትግራይን ነፃ መንግሥት ስንመሠርት አጥንታችሁን ፈጭተን የአፈር ማዳበሪያ እናደርገዋለን” እያሉ ንጹሓንን በመግደል ገደል የከተቱት ዘግናኝ ግፍ ገና ብዙ አሣር ያወርድባቸዋል፡፡
ወንድሜ ጥጋብህን ተቆጣጠር፡፡ በልክ ያዘው፡፡ ጥጋብ ዕብሪትን ይወልዳል፡፡ ዕብሪት ትዕቢትንና ትምክህትን ይወልዳል፡፡ ትዕቢተኛና ትምክህተኛ ደሞ ፈጣሪንም ሣይቀር ይረሣና እንዲያውም ራሱን እንደፈጣሪ ይቆጥርና ከፀሐይ በታች የማይፈጽመው ግፍና ሰቆቃ የለም፡፡ የኔ አይደሉም ብሎ የሚፈርጃቸውን ወገኖች ከእንስሳትም በታች በመቁጠር እንዴት እንደሚጫወትባቸው በወያኔም ሆነ ከነሱ ከፍቶ በመጣው ኦሮሙማ እየታዘብን ስለሆነ እነዚህን መሠል ጉግማንጉግ ፍጡራን በደምብ እናውቃቸዋለን፡፡
ታደሠ ወረደ ስለወልቃይት ከሚጮህ ሌላውን የትግራይ መሬት ያልማ፤ ስነንተትና ስንት ጦመም ያደረ ባዶ መሬት አለ፡፡ የትግራይ ችግር ጭንቅላት እንጂ መሬት አይደለም፡፡ በጦርነት የተጎዱና በርሀብ አለንጋ የሚገረፉ ዜጎች የሚቋቋሙበትን ብልኃት ያፈላልግ፡፡ ይሄን ምዕራብ ትግራይና ሰሜን ትግራይ የሚል ቀልድም ከማሣቀቅ ባለፈ አያስቅምና ያቁም፡፡ ነገሩ ቀድሞ የመቀመጫየን እንደሚባለው ነው፡፡ አጉል እልህ ጥሩ አይደለም፡፡ በመሠረቱ ራያም ሆነ ወልቃይት እንኳንስ ሀገራዊ ባለቤቱ ትግራዋይ ይቅርና ፈረንጁም ሆነ አፍሪካዊ ጥቁሩ ሄዶ ሊኖርባቸው ሀብትም ሊያፈራባቸው ይችላል፡፡ በምን ኃጢኣታችን እነዚህ ወያኔዎች ተልከውብን በቁራጭ መሬት የይገባኛል ጥያቄ እንደሚያጨራርሱን አልገባኝም፡፡ ነገሩ ሁሉ ሲታይ “ከወረቱ ስንቁ” እንዲሉ ነው፡፡ በነዚህ ግዛቶች ሰበብ የሚያልቀው ሕዝብና ግዛቶቹን በስም መዝግቦ በመያዝ ሊገኝ የሚችለው ምናባዊ ጥቅም ሲነፃፀር ነገረ ሥራችን ሁሉ ጅልነት ነው፡፡ በተለይ ትግራይ አሁን ከምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስለወልቃይት እንዲህ ማቃሰት “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም”ን የሚዘክር ነው፡፡ የወልቃይት ሕዝብ፣ የራያ ሕዝብ “ተውኝ ልኑርበት” እያለ፣ የየትኛው ግዛት አካል መሆን እንደሚፈልግም ከአንደበት ባለፈ በጠበንጃ አፈሙዝ እየገለጸ በግድ የኔ ነህ ማለት የጤና አይደለምና እነፕሪቶሪያ – ማናቸው እቴ – እነሕወሓት ወደሸንኮራ ዮሐንስ ወይም ለብቃየሱስ ጸበሎች መጥተው ለሰባት ሰባቶች ያህል ቢጠበሉ የተሣፈረባቸው በሚሊዮን የሚቆጠር የአጋንንት መንጋ ሊለቃቸው ይችል ይሆናል – በበኩሌ ባይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅማ፡፡
አለመለከፍ ነው ወገኖቼ፡፡ በቅሚያና ዝርፊያ የተለከፈ ሰው ከዚህ ደዌ በቀላሉ አይፈወስም፡፡ መጥፎ ሱስ ነው፡፡ እንጂ እነታደሠ ማድረግ የነበረባቸው ወደኅሊናቸው በመመለስ በዕብደታቸው ሰሞን ባጠፉት ጥፋት ተጸጽተው “አገራችን ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂ ናት፡፡ ዱሮም ቢሆን ከራስ ዱሜራ እስከራስ ካሳር ትግሬም ሆነ አማራ፣ ኦሮሞም ሆነ ጉራጌ … በነፃነት ተዘዋውሮ የሚሠራባት ኢትዮጵያ ናት የነበረችን፡፡ አሁንም በቁርስራሽ መሬት ከምንጣላ የቀድሞው ይሻለናልና እስካሁን ላጠፋነውና በዚያም ሳቢያ ለተበዳደልነው ይቅር ተባብለን ወደቀድሞ ፍቅራችንና ሀገራዊ አንድነታችን እንመለስ፡፡” ማለት ነበረባቸው – ሽበታቸው የእንጨትና የድንጋይ ሣይሆን የእውነተኛ የሰው ልጅ ዕድሜ መገለጫ ቢሆን ኖሮ ፡፡ ጥፋትን በጥፋት ማጀብ ይቅር፡፡ በ50 እና በ60 ሚሊዮን የሚገመተው አማራ የተደገመበት የአፍዝ አደንግዝ የዘመናት ድግምታዊ አዙሪት መሻሪያው የተገኘ እንደሆነ ደግሞ … ለነገሩ ምን አገባኝ፡፡
እኔ ግን ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋየም ትልቅ ነው፡፡ ከነዚህ እዚያና እዚህ ሆነው ከሚያባሉን ድኩማን ማይም ፖለቲከኞች የሚገላግሉን የሁሉም ነገድ ኅብር የሆኑ ወጣቶች በእግዚአብሔር ረድኤት ታግዘው ከገባንበት የዘረኝነት ክርፋትና የአስተሳሰብ ድህነት ነፃ ያወጡናል፡፡ ከእንጨት ሽበቶች የጦርነት ነጋሪት ጉሰማም ያላቅቁናል፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠረውንና ወጣቶቻችን ከምርት ሥራ ይልቅ ወደእርስ በርስ ፍጂት የሚማግደውን የጦር መሣሪያም ወደማረሻና ወገል የሚለውጡ የአዲስ ትውልድ ፍሬዎችን በቅርቡ እናገኛለን፡፡ የሰው ሥጋና ደም ካልተቋደሰ የሌት ዕንቅልፍና የኅሊና ሰላም የማያገኘውን አቢይ አህመድንም እንገላገላለን፡፡ ያ ዓይነት ዘመን ሲብት ይታየኛል፡፡