ፖለቲካ ቆሻሻ አይደለም!
በርካቶች በተለምዶ “ፖለቲካ ቆሻሻ ነዉ” ሲሉ ይሰማል። በአንድ መልኩ እዉነት አላቸዉ። በተበላሸ ፖለቲካ ምክንያት በርካታ ሀገራት ለመከራና ለችጋር ተጋልጧል። ለፖለቲካ በሚሸረቡ ሴራዎች ምክንያት ሚሊዬን ንፁኃን ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲጎሳቆሉ ይታያል። ማህበራዊ መስተገብሮችና ዘማናትን የተሻገሩ እሴቶችም ፈርሰዉ ጥላቻና ነዉር እየተስፋፋ ይገኛል። አሳዛኝ ክህደቶች፥ ከባባድ ውሸቶችና ዘግናኝ ግድያዎችም በፖለቲካ ሽፋን ተፈፅሟል። ትላልቅ ሀገራት በፖለቲካ ብልሽት ተዳክሟል። ከኢትዮጵያ አኳያ ደግሞ ፖለቲካ ከውሸታምነት፣ ከሌብነት፣ ከአድርባይነት፣ ከሴረኝነትና ከግፈኝነት ጋር ተዛምዷል። ፖለቲከኛ ሲባል ሙስና፣ ቅጥፈት፣ አሰመሳይነት፣ ግለኝነት፣ ክህደትና ገዳይነት በዓይነ-ሂሊና ይከሰታል። ለህዝብና ለሀገር ጥቅም በእዉነት አስቦ የሚሰራ ዜጋ “ፖለቲካ ያልገባዉ ሞኝ” እስከ መባል ደርሷል። በተለይ ደግሞ የወቅቱ ሁኔታችን እጅግ ይሰቀጥጣል። ከዚህ አኳያ ሲመዘን “ፖለቲካ ቆሻሻ ነዉ” ማለት ትክክል ይመስላል።
ይሁንና ፖለቲካ- እንደማንኛዉም ሞያ ሊቆሽሽ ቢችልም- በተፈጥሮዉ ግን ቆሻሻ አይደለም። ይልቁንም የቆሸሸዉን ስርዓት ያነፃል። በትክክለኛ ትርጉሙ የተለያዩ ፍላጎቶችን በማስታረቅ ለጋራ ዓላማዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችል ጥበብ ይባላል። ችግሮች የሚቀረፉበትና አቅሞች የሚጎለብቱበትን ስርዓት ለመዘርጋትና ለመተግበር ያስችላል። ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ሠላምና ተድላ የሚሠፍኑበትን ሁነኛ መንገድ ይቀይሳል። የደከሙትን አጠንክሮ ለስኬት ያበቃል። የወደቁትን አንስቶ የደሀዩትን ያበለፅጋል። ስብራቶችን እየጠገነ ህመሞችን ያክማል። እዉነትን በማዉጣት እርቀ-ሠላም ያወርዳል። በአግባቡ የህግ የበላይነትን በማስፈን ለዜጎች ደህንነት፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ሠላም ዋስትና ይሰጣል። ይህ ሁሉ ግን እንዳሁ በተፈጥሮ አይከሰትም። የፖለቲካዉ በቅንነት፣ በብቃትና በብለሀት መመራትንና የቁም ነገረኛ ዜጎች ተሳትፎን ይጠይቃል። ፖለቲካ በሀገር ኪሳራ በሚነግዱ ቁማርተኞች ሳይሆን በሀገር ወዳድና ብቁ ፖለቲከኞች ሊያዝ ይገባል።
ለአንድ ህዝብ ፖለቲካ ፍፁም ወሳኝ ሞያ ነዉ። በትክክል ሲከወን ተዓምር ሊባል የሚችል አዎንታዊ ለዉጥ ያመጣል። ከዚህ አኳያ ተጨባጭ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። የዛሬ 250 ዓመት ገደማ የኢንግሊዝ ኮሎኒ የነበረችዉ አሜሪካ ላለፉት ሰባ ዓመታት ገደማ የዓለም ልዕለ ኃያል ነች። ከስልሳ ዓመት በፊት በድህነት አዙሪት ተይዛ የነበረችዉ ቻይና ዛሬ በዓለም ኢኮኖሚ ሁለተኛዉን ሆናለች። ከሶቪዬት መፍረስ በኋላ እጅግ ደግማ የነበረችዉ ራሽያ በ30 ዓመታት ውስጥ የማትበገር ኃያል ሆናለች። ከ31 ዓመታት በፊት የአፓርታይድ ሰለባ የነበረችዉ ደቡብ አፍሪካ ዛሬ በአፍሪካ የተሻለዉን ኢኮኖሚና ዴሞክረሲ ገንብታለች። በአስተዳደርና በፀጥታ ቀውስ ታንቃ የነበረችዉ ቡርኪናፋሶም በሶስት ዓመታት ውስጥ ባሳየችዉ አስገራሚ ለውጥ በአፍሪካ ብቸኛዋ ከእዳ ነፃ ሀገር ሆናለች። ጀፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኢንዲያ፣ ሩዋንዳና የመሳሰሉት ሀገራትም በአጭር ግዜ ተዓምር የሚመስል እድገት አሳይቷል። ሁሉም የሆነዉ ግን በተዓምር አይደለም። የሀገራቱ ፖለቲካ በብቁ፣ በነቁና በትክክለኛ ፖለቲከኞች በመመራቱ የመጣ ውጤት ነዉ! ፖለቲካ ሲሰምር ያነፃል፥ ያነቃል፥ ያስተባብራል፥ ያሰራል፥ ያሳድጋል፥ ያስከብራል! አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሰበዓዊ በሽታዎችነ ይፈውሳል።
በአንፃሩ ግን ፖለቲካ በግለኞችና ቁማርተኞች ሲያዝ ቆሽሾ በሽታ ይሆናል። በሽታዉም ሁሉን የህይወት ዘርፍ በማናጋት ዙሪያ መለስ ቀዉስን ያስከትላል። ፍትህን፣ ነፃነትን፣ ሠላምን፣ አንድነትንና እድገትን በማጥፋት ስርዓት አልበኝነትን፣ ጭቆናንና ድህነትን ያነግሳል። በዚህ መልኩ ፖለቲካ በሽታ የሆነባቸዉ ብዙ ሀገራት አሉ። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የዓለም ስልጣኔ ቁንጮ የነበረችዉ ሶሪያ ዛሬ ፈራርሳ አሸዋ መስላለች። የነቻይና ጎረቤት የሆነችዉ ማይናማርም በኦርስ በርስ ጦርነት ትታመሳለች። በአፍሪካ ትልቋ ሀገር የነበረችዉ ሱዳን ለሁለት መከፈሏ ሳያንስ ሁለቱም ክፋዮቿ በጦርነትና በድህነት ቀውስ ተይዟል። የዓለም ውድ ማዕድናት ማዕከል የሆነችዉ ኮንጎ ኪንሻሳም ለዘመናት በግጭትና በድህነት አዙሪት ውስጥ ትገኛለች። የሶማሊያ፣ የእራቅ፣ የሊቢያ፣ የሄይቲና የመሳሰሉት ሀገራት ሁኔታም በዚሁ መንገድ ይታያል። ይህ አሳፋሪ ዉድቀት ግን በአንዳች እርግማን የተፈጠረ አይደለም። የሀገራቱ ፖለቲካ በአቅምና ሞራል አልባ ትናንሸ ሰዎች እጅ መግባቱ የወለደዉ ብልሽት ያመጣዉ ውጤት ነዉ። ፖለቲካ ሲበላሽ ያቆሽሻል፥ ያደነቁራል፥ይከፋፍላል፣ ያጣላል፣ ያሰንፋል፣ ያደሀያል፥ ያዋርዳል! ለሰላምና ደህንነት፥ ለኢኮኖሚ እድገት፥ ለማህበራዊ ልማት፥ ለሰበዓዊ መብት ጥበቃና ለመልካም አስተዳደር አደገኛ ካንሰር ይሆናል!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከማንም በላይ የተበላሸ ፖለቲካ ሰለባ ሆናለች። ብልሽቱ አድዋ ላይ ለጥቁሮች የነፃነትና የክብር ችቦ የለኮሰዉን ታላቅ ህዝብ ዛሬ ከፋፍሎ እያባላዉና አደህይቶ ለሰደት እየዳረገዉ አንገቱን አስደፍቶታል። ዉሃ ሲጠይቁት ወተት ያቀብል የነበረዉ ቸር ህዝብ በልቶ ማደርና ወጥቶ መግባት ብርቅ እንዲሆንበት አድርጎታል። እዚህ ያደረሰን የፖለቲካ መቆሸሽ- የሩቁን እንተዉና-አፄ ኃይለስላሴ አርበኞችን ክደዉ ባንደዎችን ከሾሙበት ግዜ ይጀምራል። በወቅቱ “እናት ሀገር ኢትዮጵያ ሞኝ ነሸ ተላላ፥ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” መባሉ ይታወሳል። ሲሻሩ ላይቆጩ ሲሾሙ መዝረፍም እንደግኝት ተቆጥሯል። የ1966-ቱ አብዮትም ምርጥ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን በልቶ “ፖለቲካንና ኮሬንቲን በሩቁ” አሰኝቷል። ፖለቲካ በዋናነት ግፍንና ውሸትን ለማይፈሩ ሞራል አልባ ግለሰቦች የተመደበ “ቆሻሻ” ስራ ተብሏል። በኢህአዴግ “ምሁር አድርባይ ነዉ” በሚል በአብዘኛዉ ፖለቲካ ላልገባዉ ወንበር ተሰጥቷል። የሹመት መስፈርት የፓርቲ ታማኝነት እንጂ እዉቀትና ብቃት አለመሆኑም በግላጭ ተነግሯል። ዛሬ ላይ የነበረዉ ብልሽት መታረም ሲገባዉ ፖለቲካችን የመጨረሻ ቆሽሿል። ፖለቲካ ሴረኝነትና ቁማርተኘነት መሆኑን በግልፅ የሚናገሩ ግለሰቦች ስልጣን ለመያዝ በቅቷል። በዚህም ምክንያት የዜጋችችን ህይወት ከአበባ ቅጠልና ከ200 ብር በታች ሆኗል። ለአፍሪካ ኩራት ምልክት የነበረዉ ህዝብ ለራሱም መሆን አቅቶታል። አንዳንዱም በትግል ስም ያልተገባ ትርክት ፈብሪኮ የሌለ ልዩነት እየፈጠረና ትናንሽ ስንጥቃቶችን እያሰፋ ቁማርተኞቹን በነፃ ሲያገለግል ይታያል። በታሪካችን ከገጠሙን አደጋዎች ይህ ትልቁ ይመስላል። በፀጥታዉ፣ በኢኮኖሚዉ፣ በማህበራዊዉና በደፕሎማሲዉ ረገድ ዙሪያ መለስ ቀውስ ውስጥ ከቶናል። ከክብደቱ አኳያ አደጋዉ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ ፍትህን፣ እኩልነትንና ሀብት-ንብረትን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ሊያሳጣን ይችላል። በተቻለ ፍጥነት መቀልበሱ ለሁሉም የህልውና ጉዳይ ይሆናል። ይህ ደግሞ እዉነተኛ፣ ብቁና ሀገር ወዳድ ዜጎች ተባብረዉ በፖለቲካዉ መሳተፍን ይጠይቃል። በፈረንጆቹ “ነፃ ምሳ የለም” ይባላል። ጉዳዩ ለፖለቲካችንም በትክክል ይሰራል። ሠላማችንን፣ ነፃነታችንንና ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸዉ ከወደድን በፖለቲካ መሳተፍ ይኖርብናል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ!
በፖለቲካ “አያገባኝም” አይባልም። ፖለቲካ- በተለይም የተበላሸዉ- አንተ ባትፈልገዉም ፈልጎ ያገኝሃል። አርሶ አደር ከሆንክ በማዳበሪያና በግብር አስታኮ ይመጣብሃል። ከይዞታህ ሊያፈናቀልህ ወይም ማሳህን የጦር ሜዳ ሊያደርግብህም ይችላል። ነጋዴ ብትሆን አገልግሎት ሊከለክልህ ወይም ለሌብነት ሊያጋልጥህ ይችላል። በፀጥታ ችግር ግበዓትና ገበያ አሳጥቶ ያከስርህ ወይም በስፖንሰር ስም ያዳክምህ ይሆናል። የትኛዉም ዓይነት ሠረተኛ ከሆንክ በዋጋ ግሽበት ደሞዝህን ነጥቆህ ኑሮን መራራ ያደርግብሃል። ወላጆችህን መርዳት እያለብህ የበነሱ ተረጂ ያደርግህም ይሆናል። ተማሪ ብትሆን ተስፋና ስራ አሳጥቶ በስደት መንገድ ላይ የአዉሬ ሲሳይ ያደርገሃል። ለዓመታት የቤተሰብ እጅ ያሳይህም ይሆናል! የልጆች አሳዳጊ ከሆንክ በብልግና፣ በሀሺሽና በሺሻ ይበከሉብሃል። የስርዓት አልበኝኘት ሠለባም ያደርግብሃል።
ስማኝማ! ሾፌር ወይም መንገደኛ ከሆንክ ለግድያ፣ ለእገታና ለዘረፋ ያጋልጠሃል። በትራፊክ በኩል አበባና ዘምባባን ይዞ ሊመጣብህም ይችላል። ወጣት ከሆንክ በግድ ወታደር አድርጎህ ባልተገባ ጦርነት ይማግደሃል። የሞትህ መርዶ እንዳይነገርም ያደርግ ይሆናል። ገንዘብ ቢኖርህ አንድ የምንዛራ ውሳኔ የመግዛት አቅሙን ከእጥፍ በላይ ያዳክምብሃል። በመንገድ ላይ ቤት ቢኖርህ በኮሪደር ስም አፍርሶ ካሳ ሊከለክልህ ይችላል። መደበኛ ዜጋ ብትሆን የሚሊሻ ልብስና ስንቅ ሊጠይቅህ በርህን ያንኳኳል። ነፃነትህንና ሠላምህን ከመንጠቁ ባሻገር እንደሶሪየውያን ሀገር አሳጥቶህ በየቦታዉ ሊበትንህም ይችላል። የወረዳና የዞን አመራር ወይም የቀበሌ ሚሊሻ ከሆንክ አንድ መጥፎ አጋጣሚ ህይወትህን ወሰዶ ልጆችህን የጎዳና ተዳዳሪ ሊያደርግ ይችላል። ዳያስፖራ ወይም ከፍተኛ አመራር ብትሆን እንቅልፍ አልባ የሂሊና ቁስለኛ ወይም ግድ-የለሽ የሁኔታ እስረኛ ያደርግሃል። ከተበላሸ ፖለቲካ ማንም የትም ሊያመልጥ አይችልም ማለት ነዉ!
ስለዚህም “ፖለቲካ ቆሻሻ ነዉ” ብለህ አትራቀዉ። ሊቆሽሽ ብችልም ሁነኞች ከያዙት ፖለቲካ መድኃኒት እንጂ በሽታ አይደለምና ከእንቅልፍህ ነቅተህ ተሳተፍ! ከተባበርክ አቅምህ የማይበገር መሆኑን እወቅ! በፖለቲካ ቁማርተኞች የከፍፍል ሴራ አትዉደቅ! ፈፅሞ በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በጎሳና በአከባቢ ተለያይተህ አትጨቃጨቅ! ጥቅምህ በህብረትህ ውስጥ መሆኑን ተገንዝበህ ልዩነትህን በማክበር አንድነትህን አጥብቅ! ያልተገባዉን ሁሉ አትስራ! ህጋዊዉንና የሚገባዉን በማድረግ መብትህን ለማስከበር ግን አትፍራ! ሠላም፥ ነፃነት፥ የተሻለ ህይወት፣ እኩልነትና ፍትህ ይገበሃል! ስኬቱ ተባብሮ መስራትን ብቻ ይጠይቃል! ዓለም የዘላለም ላትሆን አድርባይ አትሁን! በማንኛዉም ሁኔታ ውስጥ ለክብርህ ዋጋ ስጥ!
እንኳን ለስቅለትና ለትንሳኤ በዓል ዋዜማ አደረሰን!